የመኪና አደጋ

ሥፍራው በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ሰባተኛ እየተባለ በሚጠራው አካባቢ ሲሆን ጊዜያቱ ደግሞ ከአራት ወራት በፊት ማለዳ ነበር፡፡ እኩሉ ወደየሥራው፣ ከፊሉ ደግሞ ወደየግል ጉዳዩ ይነጉዳል፡፡ የ90 ዓመት ዕድሜ ባለፀጋ የሆኑ አንዲት ባልቴት ግን ወደ ቤተ ክርስቲያን ለማስቀደስ ይጓዛሉ፡፡ ካሰቡበትም ሳይደርሱ በአንድ ተሽከርካሪ ተገጭተው ለጉዳት ተዳረጉ፡፡ አሽከርካሪውም ተጎጂዋን ባልቴት ከወደቁበት ቦታ አንስቶ ሆስፒታል የሚወስዳቸው በማስመሰል ተሽከርካሪው ውስጥ አስገባቸው፡፡

ሞተሩንም አስነስቶ ወደ ኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ነጎደ፡፡ በተለምዶ አሸዋ ሜዳ እየተባለ በሚጠራው አካባቢ ደርሶ በአንድ ሰዋራ ሥፍራ ተሽከርካሪውን አቆመና ባልቴትዋን አወጣቸው፡፡ አፈሩንም ማስ ማስ አደረገና ከእነ ሕይወታቸው ቀበራቸውና ነጎደ፡፡ እንደ አጋጣሚ ሆኖ እግሮቻቸውን አፈር አላለበሳቸውም ነበር፡፡

በዚህም የተነሳ እግሮቻቸው መወራጨት ጀመሩ፡፡ ይህንን የተመለከቱ የአካባቢው ሰዎች ለፖሊስ ጥቆማ ሰጥተው ባልቴቷ ከተጫናቸው አፈር ሊወጡ እንደቻሉ፣ ወደ ሆስፒታል ቢወሰዱ ወዲያውኑ ሕይወታቸው እንዳለፈ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የሕዝብ ግንኙነት የሬድዮ ዝግጅት ኃላፊ ኢንስፔክተር ማርቆስ ታደሰ ተናግረዋል፡፡

የአሥራ አምስት ቀናት ጨቅላቸውን ለማስከተብ ወደ ሕክምና ተቋም ያመሩ በነበሩ ቤተሰቦች ላይ የደረሰው የትራፊክ አደጋ ሌላው ዘግናኝ፣ ሰቅጣጭና አሳዛኝ ክስተት ነው፡፡ በግራ ወይም በተቃራኒ መንገድ ይጓዝ የነበረው ይኼው አሽከርካሪ በላያቸው ላይ እንዳለ ወጣባቸው፡፡ ከመካከላቸውም ጨቅላ ሕፃኑ ይህችን ዓለም ወዲያውኑ ተለያት፣ እናትና አባቱም በደረሰባቸው ጉዳት የተነሳ የአልጋ ቁራኛ ሆነው እንደቀሩ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የትራፊክ ቁጥጥር መምርያ ኃላፊ ኮማንደር ግርማ ተሰማ ገልጸዋል፡፡

ከሰዓት በኋላ ልትሞሸር ጠዋት ፀጉሯን ለመሠራት ወደ ውበት ሳሎን የሄደች አንዲት ወጣት በትራፊክ አደጋ ሳቢያ በወጣችበት መቅረት፣ አንድ አባት በአጥር ግቢው ውስጥ የቆመውን ተሽከርካሪ ዙሪያ ገባውን ሳያይ አስነስቶ በመንዳት መኪናው ሥር ተቀምጦ የነበረውን የአምስት ዓመት ልጁን ገጭቶ መግደሉ፣ ለዘመናት ጥረው ግረው ለመመረቅ አንድ ቀን ሲቀራቸው በትራፊክ አደጋ ያጣናቸው ወይም የበርካታ ተማሪዎች ሕይወት መቀጨት በከተማው አነጋጋሪ ጉዳይ ከሆኑ የትራፊክ አደጋዎች ይጠቀሳሉ፡፡

ጉዳቶቹ የትራፊክ ሕግና ደንብ ካለማክበር፣ ከአሽከርካሪዎች የሥነ ምግባር ጉድለትና ከቸልተኝነት የመነጩ መሆናቸውን ነው ኃላፊዎቹ የጠቆሙት፡፡ ይህ ችግር መቼ ነው የሚቆመው? የት ጋ ነው? ማንን ነው የሚመለከተው? አደጋ ነክ የሆኑ ዜናዎች መቼ ነው መስማት የምናቆመው? የሚሉት ጥቄዎች ለመመለስ ከጊዜ ወደ ጊዜ ውሉ እየጠፋ ነው፡፡

እንደ ዓለም ጤና ድርጅት ሪፖርት በመላው ዓለም በሚገኙ አገሮች በየዓመቱ 1.25 ሚሊዮን የሚጠጉ ሕዝቦች በትራፊክ አደጋ ለሞት፣ ወደ 50 ሚሊዮን ያህሉ ደግሞ ለአካል ጉዳተኝነት ይዳረጋሉ፡፡ 90 ከመቶ በላይ የሚሆነው ሞት የሚከሰተውም ዝቅተኛና መካከለኛ ገቢ ባላቸው አገሮች ውስጥ ሲሆን፣ በዚህ ዓይነት አደጋ የመጋለጡ ሁኔታ በአብዛኛው የሚታየው በአፍሪካ በተለይም በኢትዮጵያ ነው፡፡

የመንገድ ላይ የትራፊክ አደጋ በ2017 ዓ.ም. ገዳይ ከሚሆኑት ኤችአይቪና ቲቢ ቀጥሎ ሦስተኛው መከራ እንደሚሆን የዓለም ጤና ድርጅት አመልክቷል፡፡ በኢትዮጵያም ከጤና ችግሮች በዋነኝነት የሚጠቀስ ሲሆን፣ በተለይም በዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እንደሚያሳድር ዕሙን ነው፡፡

ይህን መሰሉ ችግር ቢያንስ ለመቀነስ የጋራ ርብርብና ጥረት ይጠይቃል፡፡ ጉዳዩ በይበልጥ የሚመለከተው መንግሥታዊ አካል አደጋውን ለመቀነስ እየሠራሁ ነው ቢልም፣ የአደጋውና የጉዳቱ መጠን እየጨመረ ከመምጣቱ በስተቀር ምንም ጠብ ያለ ነገር አላመጣም፡፡

አገር አቀፍ የሆነ የሕዝብ ንቅናቄ ተደርጓል፡፡ በተደጋጋሚ ውይቶች ተካሂደውበታል፡፡ በአደጋው መንስዔዎቸም በውል ተለይተዋል፡፡ ጅማ ዩኒቨርሲቲም ከሉሲ ኮንሰልቲንግ ኢንጂነርስ ጋር በመተባበር ‹‹ደኅንነቱ የተጠበቀ መንገድ ለዘላቂ ኢኮኖሚያዊ ልማት›› በሚል መሪ ቃል በመንገድ ደኅንነት ጉዳይ ያጠነጠነ ጉባኤ አካሄዷል፡፡

ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ለሁለት ቀናት ያህል በተካሄደው ጉባዔ በምሁራን የተዘጋጁና በመንገድ ደኅንነትና በትራፊክ አደጋ ዙሪያ ያተኮሩ ጥናታዊ ጽሑፎች ቀርበዋል፡፡ ከቀረቡትም ጽሑፎች ለመረዳት እንደተቻለው፣ አዲስ አበባ ውስጥ ከእግረኞች መካከል 75 ከመቶ ያህሉ ለትራፊክ አደጋ የሚጋለጡት መንገዶችን ሲያቋርጡ ነው፡፡

ከአደጋው ተጠቂዎች መካከል 95 ከመቶ የሚሆኑት ከ18 እስከ 50 የዕድሜ ክልል የሚገኙ አምራቾችና ለሥራ የደረሱ ዜጎች ናቸው፡፡ የትምህርት ደረጃቸውም ሲታይ 50 ከመቶ የሚሆኑት የከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ 40 ከመቶው የመጀመርያ ደረጃ ትምህርት ያላቸው ናቸው፡፡

የትራፊክ አደጋ መንስዔ ከሆኑት ምክንያቶች መካከል በዋንኛነት የአሽከርካሪዎች የብቃት ማነስና የትራፊክ ሕጎችንና ደንቦችን አለማክበር ናቸው፡፡ ለእነዚህም ችግሮች አሽከርካሪዎች 80.3 በመቶ የሆነ ድርሻ ሲኖራቸው፣ እግረኞች ደግሞ 14 በመቶ ያህሉን እንደሚጋሩት አመለክተዋል፡፡ በቀድሞውና በአዲሱ የመንጃ ፈቃድ መካከል ልዩነት መታየቱን፣ በዚህም መሠረት አብዛኛው የትራፊክ አደጋ የሚከሰተው አዲሱን መንጃ ፈቃድ በያዙ አሽከርካሪዎች እንደሆነ፣ የአሽከርካሪዎች ዕድሜ፣ ፆታ፣ የመንጃው ፈቃድ ዓይነት፣ የአልኮል መጎንጨትና ፍጥነት በመንገድ ላይ ለሚደርሰው አስከፊ አደጋ መንስዔዎች እንደሆኑ ተጠቁሟል፡፡

በአዲስ አበባ መንገዶች ባለሥልጣን የሬጉራላቶሪ አማካሪ መላኩ መንግሥቱ (ኢንጂነር) እንደገለጹት፣ ከመንገድ ደኅንነት አኳያ እስካሁን የተሠራው ነገር ቢኖር በተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ ስድስት አደባባዮች ፈርሰው ተሽከርካሪዎቹ በትራፊክ መብራት (ሲግናላይዜሽን) እና ፖሊስ እየተስተናገዱ እንዲተላለፉ መደረጉ ነው፡፡

ይህ ዓይነቱ አካሄድ ቀደም ሲል ለነበረው የትራፊክ መጨናነቅ ጊዜያዊ መፍትሔ መስጠቱን፣ ለዘለቄታው መፍትሔ ግን የላይ ወይም ታች መተላለፊያ ማስገንባት ግድ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ከዓለም ባንክ በዕርዳታ በተገኘ 8 ሚሊዮን ብር ደረጃውን የጠበቀ የውኃ ማስተላለፊያ ቱቦዎች ለማሠራት የሚያስችል ጥናት በመካሄድ ላይ ሲሆን፣ ይህም ያስፈለገበት ምክንያት ከከተማው ዕድገት ጋር የሚመጥንና አብሮ የሚሄድ የፍሳሽ ቱቦ በማስፈለጉ ነው፡፡

ያሉትም ነባር የፍሳሽ ቱቦዎች በየመንገዱ ግራና ቀኝ ተቀብረው እንጂ ከየት የሚመጣን ውኃ ወዴት አቅጣጫ እንደሚያፋስሱ አይታወቅም፡፡ በአጠቃላይ አነጋገር የፍሳሽ ሥርዓቱን ተከትለው ያልተሠሩ ኋላ ቀርና የተዘበራረቁ ናቸው፡፡

የመንገዶች ባለሥልጣን በየዓመቱ ከሚጠይቀው አሥር ቢሊዮን የመንገድ ግንባታ በጀት እስካሁን ድረስ ከአምስት ቢሊዮን ብር በላይ የተፈቀደለት ጊዜ እንደሌለ ኢንጂነር መላኩ ተናግረው፣ ያም ሆኖ 54 ስኩዌር ኪሎ ሜትር ስፋት ባላት አዲስ አበባ ውስጥ እስካሁን ያከናወነው የመንገድ ግንባታ ሽፋን 22 ከመቶ መድረሱን ገልጸዋል፡፡

ሆኖም በመንገዶች የደንብ ጥሰት የፈጸማል፣ የችርቻሮ ንግድ ይካሄዳል፣ ያላግባብ የተተከሉ ዛፎችና የደረቅ ቆሻሻ ማጠራቀሚያዎችም እንቅፋቶች ናቸው፡፡

እነዚህን ተግዳሮቶችና የመንገድ ላይ ችግሮች እግረኛው ለመሸሽ ሲል ወደ አስፋልት ዳር እንደሚወጣ በዚህም ለትራፊክ አደጋ እንደሚጋለጥ አማካሪው ተናግረዋል፡፡

የኮንስትራክሽን ሚኒስትሯ አይሻ መሐመድ (ኢንጂነር)፣ ‹‹የመንገድ ደኅንነት ለአገር ልማት ገጽታ፣ ግንባታና ለዜጎች ደኅንነት መሠረታዊ ጉዳይ ነው፡፡ ከዚህ በተቃራኒ ከዓለም አገሮች በተሽከርካሪ ቁጥር ዝቅተኛ ወይም የመጨረሻው ተርታ ላይ አገራችን በትራፊክ አደጋ የሚቀጠፈው የሰው ልጅ ሕይወት፣ የአካል ጉዳትና ከፍተኛ ንብረት ውድመት ቀዳሚውን ሥፍራ ይዛ ትገኛለች ተብሎ ይታሰባል፤›› ብለዋል፡፡

ፎቶና ዜና ሪፖርተር አማርኛ 

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *