the brocken hamaer

ብዙ ወዳጆቼ ስለምንድን ነው የቅማንትን ጉዳይ ዝም ያልከው እያሉ በየቀኑ መልዕክት ይልኩልኛል፡፡ ላም እሳት ወለደች እንዳትልሰው ፈጃት እንዳትተወው ቆጫት ይላሉ አበው ሲተርቱ፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ አንድ ጽንፍ ይዞ መሔዱን አማራጭ አድርጌ አላየሁትም፡፡ መሀል ሰፋሪ ለመሆንም አይደለም፡፡ ግና ዕውነታውን ይዘን ለሁሉም የሚበጀውን መከተል አስፈላጊ ነው ብዬ ስለማምን ነው፡፡ እነኚህ ወዳጆቼ እንደሚሉት ዝም ብዬም አላውቅም፡፡ ነገርን ከሥሩ ውኃንም ከጥሩ እንደሚሉ ከሥር መሠረቱ ጉዳዪን መዘርዘር አስፈላጊ ይመስለኛል፡፡
የቅማንትን ጉዳይ መከታተል የጀመርኩት በ2003/4 ዓም ጀምሮ ነበር፡፡ ይህም የተፈጠረበትን አጋጣሚ ከዚሁ ላይ መግለጹ አስፈላጊ ይመስለኛል፡፡ አይከል ከተማ እሜቴ አይከል የምትባል ዛፍ አለች፤ የሚገባላት ብጻት ብዛት ይኽ ነው አይባልም፡፡ ምርጥ ምርጡን ገብስማ ዶሮ ከጊወን ወንዝ ጋር እኩል ትወስዳለች፤ የምትቀባው ቂቤ መጠኑ ጎጃም በረንዳ ያለ ሲራራ የቂቤ ነጋዴ ጋር ቲማ ይሆናል፡፡

ሙሉቀን ተስፋው

የዚችን ስለቷ የሚሰምር ዛፍ ጉዳይ ለማየት ወደ ጭልጋ ሔድኩ፡፡ የቅማንት ጓደኞችም ዘመዶችም አሉኝ፤ በአንድ ዝናባማ የነሐሴ ዕለት ከቅማንት ዘመዶቼ ቤት ምሳ በላሁና አባ ወንበሩ መርሻን ለማግኘት እሳቸው ወዳሉበት የገጠር ቀበሌ ጉዞ ጀመርኩ፡፡ የአባ ወንበሩ የቅርብ ዘመድ የሆነች እህቴም አብራኝ መንገድ እየመራችኝ አብረን ሔድን፡፡ በቅማንት ማኅበረሰብ የበላይ ኃላፊ ወንበር ይባላል፡፡ ወንበር በእምነት እንደ ፓትሪያርክ ወይም ሊቀ ጳጳስ ሊሆን ይችላል፤ በአስተዳደር ደግሞ ንጉሥ ወይም ንጉሠ ነገሥት ሊሆን ይችላል፡፡ ስለዚህ ወንበር የእምነትና የአስተዳደር ሁሉ ኃላፊ ነው ማለት ነው፡፡ አንድ ወንበር በሕይወት እያለ ሌላ ወንበር አይሾምም፡፡ እኔ እስከማውቀው የመጨረሻው የቅማንት ወንበር አባ ወንበሩ መርሻ ናቸው፤ እሳቸው ካለፉ በኋላ ግን ሌላ የተሾመ አይመስለኝም፡፡

ለማንኛውም አባ ወንበሩ መርሻ ጋር የአንድ ሰዐት ቃለ መጠይቅ ካደረግኩ በኋላ ስመለስ አህያ የማይችለው ዝናብ መጥቶ ከተማ ከመግባታችን በፊት ወረደብን፡፡ እግረ መንገዴን በጭልጋና አካባቢው ያለውን ሁናቴ በዝርዝር በመያዝ ተመልስኩ፡፡ በጊዜው እጽፍበት የነበረው ኢትዮ ምህዳር ጋዜጣ ላይ የአካባቢውን ችግር ነቅሼ አሰፈርኩ፡፡ በተለይ በሚሊዮን የሚገመት ንብረት ዘርፈው ከአገር ወጥተው ስለሚደበቁት የአይከል አስተዳዳሪዎች ጉዳይ ብዙ አወያይቶ ነበር፡፡ ይህን የተመለከተ የቅማንት ማንነት ጉዳይ ኮሚቴ አባል የሆነ ሰው በኢሜል አገኘኝ፡፡

እኔ በሰበሰብኩት ዳታ መሠረት ቅማንትኛ የሚናገር ብሎም ቅማንትኛ የሚያምን ሕዝብ ባለማግኘቴ የማንነት ጥያቄው መነሳቱ ግራ አጋብቶኝ ነበር፡፡ በላይ አርማጭሆና በጭልጋ ወረዳዎች በተደረገ ዳሰሳ ጥናት አባ ወንበሩን ጨምሮ ወደ 1000 የሚጠጉ እድሜያቸው ከፍ ያሉ ሰዎች ቅማንትኛ ቋንቋውን ይችላሉ፤ ግን ለመግባቢያነት አይጠቀሙበትም፡፡ ቅማንትኛ የሚያምን ግን የአባ ወንበሩን ልጆች ጨምሮ የለም፡፡ ከአባ ወንበሩ ጋር በነበረኝ ቆይታ እሳቸውን የሚተካ ሰው አለመኖሩ እንዳሳሰባቸውም ለመረዳት ችያለሁ፡፡ ለዚህ ነበር ጥያቄው ሲቀርብ ግር ያለኝ፡፡ እኔም ለምን አቀረባችሁ ከማለት አብሮ ሆኖ ጉዳዩን የበለጠ መረዳት ይሻላል በሚል ከአስተባባሪ ኮሚቴዎች ጋር የቀረበ ግንኙነት መሠረትኩ፡፡

ባሕር ዳር ፋሲሎ ሁለተኛ ደረጃ የሚያስተምሩ አቶ ምስጋናው ፈንቅለው የተባሉ መምህርና ጎንደር ደግሞ አቶ አበራ ጋር በተደጋጋሚ በየአሉበት ቦታ እየሔድኩ ተነጋገርኩ፡፡ የክልሉ ምክር ቤት ጥያቄው ሲቀርብ የኮሚቴው ተወካዮች ለስብሰባ ሲጠሩ እኔም እንደ አንድ የኮሚቴው አባል ሆኜ እንድገባ ከተመቻቸልኝ በኋላ ‹‹አንተ የምትታወቀው በተቃዋሚነትህ ነውና ከሌላ አንጻር እንዳይታይብን ባትገባ ይሻላል›› የሚል ውሳኔ በመጨረሻው ቀን ደረሰኝ፡፡ ጉዳዩን ከእናንተ ጋር እሰማለሁ ብዬ ሳልገባ ቀረሁ፡፡ ከስብሰባ ሲወጡ ሁሉንም ያማከለ አንድ የጥናት ቡድን ተቋቁሞ ጉዳዩን እንዲያጠና እንደተወሰነ ነገሩኝ፡፡

በዚሁ መካከል ግን የራሴን ጥናት ማካሔድ ጀመርኩ፡፡ የቅርብ ጓደኞቼንና እንደ ቤተሰብም የማያቸውን ቅማንቶች በጉዳዩ ላይ ያላቸውን አስተያየት መሰብሰብ ጀመርኩ፡፡ ለዚሁ ሥራ ስል ትክል ድንጋይ ሁለት ጊዜ ጭልጋ ደግሞ ከሦስት ጊዜ በላይ ተመላልሻለሁ፡፡ ሁሉንም ሊያጠቃልል ስለሚችል የሚከተሉትን ሦስት እይታዎች ባካፍል አስፈላጊ ይመስለኛል፡፡

ናሙና አንድ፤ አይከል ከተማ ከቅማንቶች ቤት ምሳ ልበላ ገባሁ፡፡ የፆም ወቅት በመሆኑ እንደምፆም ስናገር ‹‹ኧረ እኛም እኮ ክርስቲያን ነን! ቅማንት እኮ አሁን የለም›› አለችኝ፡፡ ቅማንት ስትል ማኅበረሰቡን አይመስለኝም፣ ቅማንት እንደ እምነት አለመኖሩን እየነገረችኝ ነው፡፡ ይህችን በልቼ የጠገብኩ የማይመስላት እህቴን ስለ ቅማንት ማንነት ጉዳይ አነሳሁላት፡፡ ‹‹ባሌ ቅማንት አይደለም፤ የእኔ እናቴ ቅማንትኛን ትችላለች ግን እንደሷ ያሉ ትላልቅ መነኮሳት ካልሆኑ በስተቀር ቋንቋውን የሚችሉ ሰዎች ስለሌሉ አሁን ላይ የተለየ ቅማንት የተባለ ማንነት አለ ማለት ይከብደኛል፡፡ ደግሞም ያልተጋባና ያልተዛመደ ሰው የለም በምን ይለያል፡፡ እኔ ሳስበው እንዲያው እርስ በእርሳችን የሚያስተላልቁን ይመስለኛል›› አለችኝ፡፡ የአብርሃም ቤት ይሁን ብዬ በልቼ ወጣሁ፡፡

ናሙና ሁለት፤ በዩንቨርሲቲ የመጀመሪያ ዲግሪ በማኅበራዊ ሳይንስ ዘርፍ አለው፡፡ እሱን ስጠይቀው ‹‹ቅማንትና አማራ ብሎ መከፋፈል አሁን ምንም ጊዜው አይደለም፤ እስኪ በእኔና በአንተ መካከል ምን ልዩነት አለ? የምንናገረው ቋንቋ ተመሳሳይ፣ የምንሔድበት ቤተ ክርስቲያን አንድ ዓይነት፣ ቀለማችን ነው ደማችን ልዩነቱ? የቅማንት ቋንቋ መጠበቅ ነበረበት ግን በጣም ዘግይተናል፤ አሁንም የጎንደር ዩንቨርሲቲ እንደ ጋፋት ያለ ምንም ዱካ ከመቅረቱ በፊት ምርምር ማድረግ ይጠበቅበታል፣ በተረፈ ግን እኔም አንተም አማራ ነን›› ነበር ያለኝ፡፡

ናሙና ሦስት፤ ይኼኛው ደግሞ በአንድ ሙያ በጣም የተማረ ነው (ሙያውን ግለሰቡን ሳላስፈቅድ መግለጽ ስላልፈለግኩ ነው)፤ በዩንቨርሲቲ አስተማሪም ነው፡፡ ለጥያቄ መልስ መስጠት የጀመረው ‹‹ቢያንስ አማራ እየተባልኩ በሔድኩበት ሁሉ ከችግር ይታደገኛል›› በማለት ነበር፡፡ በእኔና በአንተ መካከል ምን ልዩነት አለ ስለው ‹‹እኔ ቅማንት ነኝ፣ አንተ ደግሞ አማራ ነህ›› በማለት መለሰ፡፡ ሊለየን የሚችለውን ባሕላዊና ተዛማጅ ጉዳዮች መዘርዘር አልፈለገም፡፡ በዚህ ጊዜ መቀሌ ዩንቨርሲቲ በእሱው ሙያ የምትማር (የምታስተምር) ልጅ ጋር ደውሎ ስለምናወራው ጉዳይ ጠየቃት፤ ‹‹ማንነታችን በመስዋትነት እንደምናስከብር እርግጠኛ ነኝ›› ስትል ላውድ ድምጹን አጥፍቶ የነበረውን ስልክ በጀሮው ማወራት ጀመረ፡፡

በተለያየ ጊዜ በጭልጋና በትክል ድንጋይ የሰበሰብኩት መረጃ ከዚህ የተለየ ስላልሆነ የሦስቱ ናሙናዎች ገላጭ ይመስለኛል፡፡ ወደ ቀደመው ጉዳይ ስመለስ በሌላ ጊዜ አቶ ምስጋናው ፈንቅለውን ደውዬ ባሕር ዳር ጊወርጊስ ፊት ለፊት ካለች ካፌ ተገናኝተን አወራን፡፡ በቅማንት ጉዳይ የበለጠ ማጥናት ስለምፈለግ ያቀረባችሁትን ማመልከቻ ብትሰጡኝ ስለው ከአንቀጽ 49 አንጻር የተጻፈች አንዲት መጽሐፍ ስላለች እሷን አንብባት አለኝ፡፡ የዚሁ ኮሚቴ አባል የሆነው ደረጀ (ደረጀ መጽሐፍት) መጽሓፏን ያከፋፍላት ስለነበር ከእርሱ ገዝቼ አነበብኳት፡፡ አንድ መቶ ገጽ አካባቢ ስለሆነች የገዛዋት እለት ነው ያነበብኳት፤ አንብቤ ስጨርስ ደነገጥኩ፡፡ መጽሐፏን የጻፈው በብእር ስሙ ‹‹ትንቢቱ ደረሰ›› ይባላል፡፡ በአጪሩ መጽሐፉ የብስራት አማረ ወይም የመምህር ገብረ ኪዳን የስድብ ጥራዞችን ነው የምትመስለው፡፡ ካነበብኩት በኋላ ከአቶ ምስጋናው ጋር እንደገና ተገናኘንና በመጽሐፉ ጉዳይ እንደገና አወራን፡፡ በኋላ እሳቸው በዚህ ዓይነት መሔድ ማንን ይጠቅማል? አልኳቸው፡፡ በዕውነቱ ያለተደባለቀ በቤተሰብ ያልተሳሰረ ሰው እንደሌለ የታወቀ ነው እንዴት ነው ቤተ ዘመድን ከቤተ ዘመድ፣ ወንድምን ከወንድም ጋር ለማፋጀት ቆርጦ መነሳቱ እንደርስዎ ላለ ሰው እንዴት ተዋጠልዎ? ለምንስ በዚህ መልኩ ሲኬድ ዝም ይላሉ አልኳቸው፡፡ እሳቸውም የራሳቸውን ቤተሰብ አንስተው በእናታቸው እነ አዲሱ ለገሠ ለትግሬ የሸጧቸው የጠለምት ተወላጅ መሆናቸውን ጨምረው ነገሩኝ፡፡

ከአቶ ምስጋናውና ከአቶ አበራ ጋር ሲያገናኘኝ የነበረው በኢሜል ብቻ መልእክት የምንለዋወጠው የኮሚቴው አባል (በኋላ ላይ የመጽሐፉም ደራሲ እርሱ እንደሆነ ተረድቻለሁ) የማንነት ጥያቄውን ሙሉ ዶክመንት በኢሜል ላከልኝ፡፡ ጥያቄው የጭልጋ፣ የመተማ፣ የቋራ፣ የላይ አርማጭሆ፣ የወገራ፣ የጎንደር ከተማን፣ የደንቢያና የጎንደር ዙሪያ ወረዳዎችን ያካትታል፡፡ ከትግራይ ጋር ለመግጠም የቀረው የበለሳ ወረዳ ብቻ ነው፡፡ ይህም ሌላው አስደንጋጭ ጉዳይ ነበር፡፡ በተለይ ያን በ‹‹ትንቢቱ ደረሰ›› የተጻፈ መጽሐፍ ጋር በማመሳሰል እጅጉን አሳሰበኝ፡፡

በ2006 የበጋ ወቅት ቅማንትን በተመለከተ ሰላማዊ ሰልፍ ይደረጋል የሚል ወሬ ከአዘጋጆች ደረሰኝ፡፡ ከአዲስ አበባ ወደ ጎንደር የግድ መጓዝ ነበረብኝ፡፡ አዘዞ አውሮፕላን ጣቢያ ቢጫ ታክሲ ይዤ ወደ ማርፍበት ሆቴል ስሔድ አንድ የነገሩን ክብደት የበለጠ ያስገነዘበኝ አጋጣሚ ተፈጠረ፡፡

አሁን ጊዜ ስለዘረዘመ እንዴት እንደተጀመረ አላስታውስም፤ ግን የቢጫ ታክሲው ሾፌር የራሱን አሳዛኝ ታሪክ ሲነግረኝ እጅግ አሳዛኝ ነበር፡፡ የግለሰቡ ታሪክ በአጪሩ ይህ ነው፡፡ በ2006 ዓም ከትክል ድንጋይ የባለቤቱ እናት የጥቅምት መድኃኒዓለም ፀበል ለማዘጋጀት እንድትረዳት እንድትመጣ ትጠይቃለች፡፡ ባልም የሦስት ልጆቹን እናት ወደ ትክል ድንጋይ በደስታ ይልካል፡፡ በኋላ ባለቤቱን የሸኘው ባል ከዛሬ ነገ ትመጣለች እያለ ቢጠብቅም የውኃ ሽታ ትሆንበታለች፡፡ ስልክ ሲደውል አያነሱም፡፡ አማቱ ጋም ሲደውል አያነሱም፡፡ በኋላ አይከል ከጎንደር ሩቅ ባለመሆኑ ይሔዳል፤ ከአማቶቹ ጋር ተጣልቶ የሚወዳት ሚስቱን ሳያገኝ ይመለሳል፡፡ ሽማግሌ ይልካል፤ ሽማግሌዎቹ ባለቤቱ አማራ አግብታ እንደማትኖር የአማቶቹ ፍላጎት መሆኑን ይገልጹለታል፡፡ ይህ ግለሰብ በተለይ ትንሹ ልጅ ሌሊት እየተነሳ ‹‹እማዬ›› እያለ ጡት ለመጥባት ሲፈልግ ሁሌ እያለቀሰበት ለማታለል ሲሞክር ለሰው የሚያስቀና የነበረው ትዳር እንደዋዛ ብትንትኑ የወጣበትን አጋጣሚ ልብ በሚሰብር ትርክት ከአዘዞ እስከ ፒያሳ ድረስ አወጋኝ፤ ምንም ልለው አልቻልኩም፡፡

በቀጣዩ ቀን ጎንደር እስታዲዮም የቅማንት ማንነት አስተባባሪዎች በጠሩት ሰልፍ ላይ ተገኘው፡፡ አቶ አበራን ካሜሎት ካፌ ቀጠርኩትና በዝርዝር ተወያየን፡፡ በቀጣዮቹ ቀናት በሰሜን ጎንደር ዞን ያሉ የፍርድ ቤት ፋይሎችን ኢንፎርማል በሆነ መልኩ መረጃ ለመሰብሰብ ሞከርኩ፡፡ አብዛኛዎቹ ፋይሎች የጋብቻ ፍችና የንብረት ክፍፍል ጋር የተያያዙ እንደሆኑ ለማወቅ ቻልኩ፡፡ ይህም የተጋረጠው አደጋ ምን ያክል እንደሆነ ተረዳሁበት፡፡ በኋላ የታዘብኩትንና ያየሁትን መፍትሔ የምለውን ሁሉ ጨምሬ በፋክት መጽሔት ላይ ጻፍኩት፡፡ ጉዳዪ በብስለት ካልተያዘ በስተቀር ያልተፈለገ ደም መፋሰስ ሊያስከትል እንደሚችል ግልጽ ሆኖልኝ ነበር፡፡

በ2008 ዓም በጎንደር በርካታ ጉዳዮች ተከናውነዋል፤ በዓመያ ያሉ ዐማሮቸ ንብረት ሲወድም ዓመያ ለማጣራት ሔድኩና ያን ጨርሼ ስመለስ ጎንደር ማረሚያ ቤት በነበረ ቃጠሎ ከ70 በላይ ሰዎች በእሳት ተቃጥለው ሲያልቁ ሒጄ ማጣራት ነበረብኝ፡፡ በዚያም ከመተማ እስከ ጎንደር ድረስ በዚሁ ቅማንት አማራ በሚል በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች የሞቱበትን ጉዳይ ማጣራት ነበረብኝ፡፡ አለፍ ሲልም ከሱዳን ድንበር ጋር ያለውን ሁናቴ እንዲሁ ማየት ሞራላዊ ግዴታዬ ነበር፡፡

በኋላ ባሰባሰብኩት መረጃ መሠረት ብዙ አሳዛኝ ነገሮችን ለማግኘት ቻልኩ፡፡ የቅማንት ማንነት አስተባባሪ የተባሉ ሰዎች መቀሌ ቢሮ ተከፍቶላቸው ስልጠና እንደተሰጣቸው ለማወቅ ቻልኩ (በእርግጥ መቀሌ ያለውን ቢሮ ለማወቅ መቀሌ ድረስ ብሔድም ላገኘው አልቻልኩም)፡፡ በጣም የሚያሳዝነው ደግሞ ከትግራይ ክልል በተላኩ የሆስፒታል አምቡላንሶች ሞርታርና ብሬን የመሣሰሉ መሣሪያዎች ተልከው ያለምንም ፍተሻ ጎንደር መግባታቸው ነው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ አንዲት ቡና የምታፈላ ሴት በጉንፏ አንድ ሚሊዮን ብር ይዛ መያዟ ሌላው ገራሚ ጉዳይ ሆነ፡፡ በዚህም ቤተሰብን ከመበታተን ጀምሮ እርስ በእርስ ለማጫረስ ከጀርባ ማን እንደነበረም የሚያሳይ ምስል ይመስለኛል፡፡

የሆነው ሆኖ አሁን ላይ ደርሰናል፡፡ አሁን ላይ ለቅማንት 42 ቀበሌዎች ተሰጠዋል፤ 12 ቀበሌዎች ላይ ሪፈረንደም ይደረጋል፡፡ አሁን ላይ ያሉትን ችግሮችና የግል አቋሜን በተመለከተ ወደፊት የምገልጽ ይሆናል፡፡

ያቀረብኩት ዝርዝር ሒደት ጠቅለል ያለ ምስል የሚሰጥ ይመስለኛል፤ ከስሜት በፀዳ መልኩ አስተያየታችሁን መስጠት ትችላላችሁ፡፡

– ሙሉቀን ተስፋው

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *