የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ በተከሳሾቹ ላይ 40 የተለያዩ ክሶችን አቅርቧል።

law

ክስ የመሰረተባቸውም፥ 1ኛ አቶ አብይ አበራ፣ 2ኛ አዲስ ቪው ጀኔራል ሰርቪስ ሃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር፣ 3ኛ ሚስተር ጀሮስላው ፋልኮስኪ የሚባሉ እና በፖላንድ የሚገኙ ግለሰብ፣ 4ኛ ቢፕሮማስ ቢፕሮን ትሬዲንግ ኤስ.ኤ የተባለ የፖላንድ ኩባንያ እንዲሁም 5ኛ አቶ ዮናታን ቦጋለ ናቸው።

ጠቅላይ አቃቢ ህግ ካቀረበው ክስ ውስጥ ግን አብዛኛውን ድርሻ የሚይዙት አንደኛ ተከሳሽ ሆነው የቀረቡት አቶ አብይ አበራ ናቸው።

አንደኛ ተከሳሽ አቶ አብይ አበራ ንብረቱ ከ10ኛ እስከ 15ኛ የተጠቀሱት ክሶች ላይ ምንም አይነት ፈቃድ ሳይኖራቸው ኢትዮጵያውያን ዜጎችን በህገ ወጥ መንገድ ለስራ በሚል ወደ ውጭ ሀገር በመላክ ገንዘብ አግኝተዋል የሚል ይገኝበታል።

ከ3ኛ እስከ 5ኛ ባለው ክስ ላይ ደግሞ በከፍተኛ ወለድ አራጣ በማበደር እና ንብረት ማፍራት፣ በ37ኛ ክስ ላይ የመንግስት ይዞታን በህገ ወጥ መንገድ በመያዝ በሚል እንዲሁም በ6ኛ እና በ16ኛ ክሶች ላይ በተመለከተው ፈቃድ ሳይኖረው የባንክ ስራ በመስራት በህገ ወጥ መንገድ ያገኘውን ገንዘብ መጠቀም የሚል ይገኝበታል።

ከ7ኛ እስከ 9ኛ እንዲሁም 38ኛ ክሶች ላይ በተገለፀውም ግለሰቦችን በማታለል የወሰዱትን ገንዘብ እና ንብረት መገልገላቸውን ይገልጻል።

በ17ኛ እና 37ኛ ክስ ደግሞ 1ኛ ተከሳሽ የመንግስት ግብርን በማጭበርበር ያገኙትን ገንዘብ በኢትዮጵያ ውስጥ ህጋዊ አስመስለው በራሳ፣ በባለቤታቸው፣ በቤተሰቦቻቸው እና በድርጅታቸው ስም ለመኖሪያ ቤት እና ለሆቴል ግንባታ በማዋል የተለያዩ ስፋት ያላቸውን የከተማ ቦታዎች እና የአክሲዮን ድርሻዎችን በመግዛት፤ በጥሬ ገንዘብ ባንክ ማስቀመጥ በሚል ተከሰዋል።

በክሱ በተጠቀሱት የወንጀል ተግባራት ያገኙትን ገንዘብ ወደ ውጭ ሀገራት በማሸሽ ጀርመን በሚገኝ ኮሜርስ ባንክ፣ በአሜሪካ እና በሌሎች የአውሮፓ ባንኮች ማስቀመጣቸውም በክሱ ተጠቅሷል።

በጀርመን ሀገር ከኮሜርዝ ዶክዜ የተባለ ትርፍ የሚያስገኝ አክሲዮን በመግዛትና ህጋዊ አስመስለው በመገልገልም ክስ ቀርቦባቸዋል።

በአጠቃላይ 1ኛ ተከሳሽ አቶ አብይ አበራ በፈፀሟቸው የወንጀል ተግባራት ያገኙትን ገንዘብ ወይም ንብረት ምንጩ እንዳይታወቅ በማድረግ እና በመደበቅ፥ ንብረቱን በመለወጥ እንዲሁም ወደ ውጭ ሀገር ማሸሽን ጨምሮ በተለያዩ መንገድ ያስተላለፉ በመሆኑ ህጋዊ አስመስለው በማቅረብ ወንጀል ክሱ ተመስርቶባቸዋል።

2ኛ ተከሳሽ አዲስ ቪው ጀኔራል ሰርቪስ ሃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር፥ 1ኛ ተከሳሽ ድርጅቱን ስራ አስኪያጅ ሆነው በሚመሩበት ጊዜ በአራጣ፣ በህገ ወጥ የሰዎች ዝውውር፣ በህገ ወጥ የባንክ ስራ እና ከላይ በተጠቀሱት የወንጀል ድርጊቶች የተገኘውን ገንዘብ ድርጅቱን በመሳሪያነት በመጠቀም በድርጅቱ ስም በሚገኘው አዲስ ቪው ሆቴል ግንባታና ለአገልግሎት እንዲውል በማድረጉ ነው ክሱ የቀረበበት።

3ኛ ተከሳሽ ሚስተር ጀሮስላው ፋልኮስኪ በ1ኛ ተከሳሽ አቶ አብይ አበራ በ33ኛ ክስ የቀረበውን ምንም አይነት የንግድ ስራ ፈቃድ ሳይኖረው ቢቢቲ በሚል የሚታወቀውን የውጭ ሀገር ድርጅት ወክሎኛል በማለት ከ2005 እስከ 2009 ዓ.ም የኢፌዴሪ መከላከያ ሚኒስቴር ባወጣው ጨረታ ተሳትፈዋል።

በጨረታውም ሚኒስቴሩ የጦር እና የመከላከያ መሳሪያዎች እንዲሁም መለዋወጫ ለመግዛት ባወጣው ዓለም አቀፍ ጨረታ ላይ፥ 1ኛ ተከሳሽ በአዲስ ቪው ጀኔራል ሰርቪስ በተመዘገበ የተዛማጅ እቃዎች አስመጪ የሚለውን ፈቃድ በመጠቀም የቀረቡ መሆኑ ተጠቅሷል።

ከዚህ ባለፈም ቢቢቲ የተሰኘውን ድርጅት በመወከል ጨረታ ላይ በመሳተፍ እና ድርጅቱ ሲያሸንፍ ያሸነፈበትን ገንዘብ 5 በመቶ ለመውሰድ ስምምነት መግባታቸውም በክሱ ተዘርዝሯል።

በዚህ መሰረት ድርጅቱ ባሸነፋቸው 9 ጨረታዎች ያገኘው የገንዘብ መጠን ከ58 ሚሊየን ብር በላይ ሲሆን፥ ከዚህ ውስጥ በመመሳጠር ከ3 ሚሊየን ብር በላይ በጀርመን ሀገር በመገኘት መውሰዳቸውና 3ኛ ተከሳሽም ለዚህ ተግባር በመተባበራቸው ነው ክስ የተመሰረተባቸው።

4ኛ ተከሳሽ ቢፕሮማስ ቢፕሮን ትሬዲንግ ኤስ.ኤ ደግሞ 1ኛ እና 3ኛ ተከሳሾች የጨረታ ሂደቱን ሲያጭበረብሩ ለተከሳሾቹ እንደ መሳሪያ ሆኖ አገልግሏል በሚል ነው ክስ የቀረበበት።

5ኛ ተከሳሽ አቶ ዮናታን ቦጋለ ለ1ኛ ተከሳሽ የማይገባውን ብልፅግና እንዲያገኝ ለማድረግ ሀምሌ 11 ቀን 2009 ዓ.ም በፌደራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ልዩ ቢሮ በመቅረብ፥ አቶ አብይ አበራ በባለቤትነት ተረክቦ ሲገለገልበት የነበረውን ቶዮታ ተሽከርካሪ የ1ኛ ተከሳሽ መሆኑን እያወቁ አይደለም በማለት የወንጀል ፍሬ የሆነውን ተሽከርካሪ አታለው የወሰዱ በመሆኑ በመንግስት አስተዳደር እና አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ላይ ከባድ የማታለል ወንጀል በመፈጸም ተከሰዋል።

የተከፈተው ክስም ሀሙስ ለተረኛ ችሎት የሚቀርብ ሲሆን፥ ተረኛ ችሎትም ተከሳሾች በቀረቡበት ክሱን ያነባል ተብሎ ይጠበቃል።

በሀይለኢየሱስ ስዩም fana

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *