“Our true nationality is mankind.”H.G.

የማውቀው ቅማንትነት በጥቂቱ

መቸም ስለቅማንት ጉዳይ ሲነገር ዝም የማይባሉ ብዙ ነገሮች ይኖራሉ፡፡ አንዱን እኔ እንዳየሁት ላስቀምጥ፡፡ አይኔ ላየው እና ጆሮየ ለሰማው፤ ለማውቀው ነገር ልመስክር፡፡ እኔ እያልኩ ልጻፍ፤ ሁኔታውን ልመሰክር የምችለው እኔ ብየ ስለሆነ፡፡

በአባቴ በኩል ጫጭቁና እወለዳለሁ፡፡ ጫጭቁና አማራና ቅማንት በአንድነት እና በፍቅር ይኖራል፡፡ አያቴ (እሚታየ) ባሻ ምህረቴ የቀኛዝማች አራጋው ለምለሙ ልጅ ናቸው፡፡ ቀኛዝማች አራጋው ለምለሙ የእነ ወይዘሮ ያጆነሽ አባትም ናቸው፡፡ በጫጭቁና፣ ጎንደርና ዙሪያዋ በባላባትነት ኖረዋል፡፡ ደፈጫ ኪዳነ ምህረትና ጎንደር ባታ እስካሁን ድረስ የእርሳቸው ትውልድ የሚሆኑ ዘመዶቸ አሉ፡፡ ቀኛዝማች አራጋው ለምለሙ በተወለዱ በ103 አመታቸው እስካረፉበት ጊዜ ድረስ የአማራና ቅማንት ጀግኖችን በመያዝ በአርበኝነት ጣልያንን ተዋግተዋል፡፡ ጣልያን ከወጣም በኋላ የዚሁ አካባቢ አስተዳዳሪ ሆነው በተድላ በደስታ ኖረዋል፡፡ የቀኛዝማች አራጋው አባት አቶ ለምለሙ ከደርቡሽ ጋር የተያያዘ ታሪክ አላቸው፡፡ ደርቡሽ ጎንደርን ባቃጠለ ጊዜ ቄሶች ሁሉ ገሚሶቹ ታርደው፣ ገሚሶቹ ሸሽተው ነበርና የጫጭቁና ማርያምን 30 ኪሎ የሚመዝን ስንክሳር የብራና መጽሀፍ እና ሁሉንም ንዋየ ቅድሳት ሰብስበው ደብቀው አትርፈዋል፡፡ የደበቁበትም ቦታ ውስጡ የተቦረቦረ የዋንዛ ዛፍ ዋሻ እንደሆነ አባቴ ነግሮኛል፡፡ አባቴ እንዲያውም “ቅድመ አያቴ ለምለሙ ባህታዊ ናቸው፤ ከደርቡሽ የቤተ ክርስቲያን እቃ ሁሉ ደብቀው፣ ክህነት ሳይኖራቸው ነገር ግን ታቦቱን ሳይቀር የደበቁበት ቦታ ውስጥ ማእጠንት እያጠኑ ክፉ ቀን ያሳለፉ ያልተማሩ ካህን ነበሩ ይለኛል፡፡” የጫጭቁና ማርያም ንዋየ ቅድሳት እና በተለይም 30 ኪሎ የሚሆነው የብራና መጽሀፍ እስከቅርብ ጊዜ ድረስ እንደነበረ አውቃለሁ፡፡

ባሻ ምህረቴ (እሚታየ) በአጼ ሀይለ ስላሴ መንግስት ወታደር ሆነው የአባታቸውን የቀኛዝማች አራጋውን ፈለግ ተከተሉ፡፡ ሻዕብያ ኤርትራን እስከተረከበት እለት ድረስም በኤርትራ ምድር ለ30 አመታት ያህል ሲዋጉ ኖረው፤ ተሸንፈው በተፈናቃይነት ጎንደር ተመለሱ፡፡ ከኤርትራ ተመልሰውም ጥቂት ጊዜ አዘዞ ቆይተው እዛው ጫጭቁና ይሻለኛል ብለው በወገናቸው አማራና ቅማንት መሀል ኖረው በ76 አመታቸው አርፈዋል፡፡

ባሻ ምህረቴ ታዲያ የንጉሱ ወታደር ከመሆናቸው ቀደም ብሎ ከቅማንት ወይዘሮ ሴቶች ልጆች ወልደዋል፡፡ የመጀመሪያዋ ልጅ ጸሀይ ትባላለች፡፡ ህጻን እያለሁ ነበር ያረፈችውና አላስታውሳትም፡፡ ግን በቤተሰቡ በጠቅላላ በቁንጅናዋና በለጋስነቷ ስሟ አሁንም ድረስ እንደታቦት በየእለቱ ሽህ ጊዜ የምትጠራ፣ መቸም የማትረሳ ሴት ናት፡፡ ሌሎቹ ከአማራው እሚታየ እና ከቅማንቷ ወይዘሮ የተገኙት ልጆች ግን አሁንም አሉ፤ ብዙ ልጆችን ወልደው ሰፊ ቤተሰብ ሆነዋል፡፡ ሁለቱ በተለይ እኔን ያሳደጉኝ ናቸው፡፡ ከዛም እንግዲህ የአክስቶቸ ልጆች አሉ፡፡ ከእነሱ ጋር ነው ያደግሁት፡፡ ጓደኞቸና ቤተሰቦቸ ሆነው፡፡ ጫጭቁና ብዙ ጊዜ እመላለስ ነበር፡፡ ኑሬበታለሁ ማለት እችላለሁ፡፡ አንድስ እንኳ ልዩነት አልነበረም፡፡ ሰውም ለስሙ አማራ/ቅማንት ይባባል እንጅ ልዩነት የለም፡፡ በሌላ ማህበረሰብ ውስጥ እንዳለው አይነት የመናናቅም ሆነ የበደል ታሪክ/ተረት የለም፡፡ የለም ስል በቃላት ብቻ የለም ብየ የምገልጸው አይደለም፡፡ የለም፣ አልነበረም፡፡ እንዴት እንዳልነበረ ለመጻፍ ብዙ ገጾች ያስፈልጉ ይሆናል፡፡ ግን አልነበረም በሚል ብቻ ዘግቸው ልለፍ፡፡

Related stories   ሻለቃ ሰከን ይበሉ እንጂ! – ባይሳ ዋቅ-ወያ

በእናቴ በኩል ጭልጋ እወለዳለሁ፡፡ የአያቶቸ መንደር አሰፋፈር በቤተ እስራኤላዊያን እና በቅማንቶች መካከል ነበር፡፡ በሰሜን ምእራብ ጫፍ ቅማንት፣ በደቡብ ምስራቅ ቤተ እስራኤሎች፤ በመሀል ደግሞ አማሮች ተብለው ይኖሩ ነበር፡፡ ሶስቱም በማህበራዊ ህይወት እና በኢኮኖሚዊ ህይወት በአንድነት በፍቅር ይኖሩ ነበር፡፡ በኋላ ቤተ እስራኤላዊያን ወደእስራኤል ሄዱ፤ ሁሉም ሄዱ፡፡ አማሮቹ ዘመዶቸ ያዘኑትን ማዘን እኔ ነኝ የማውቀው፡፡ ሴት አያቴ ከማዘኗ የተነሳ ቅማንት ራሱ ይሄዱብናል ብላ ትጨነቅ ነበር፡፡ አንድ ቀን “ቅማንቶች የት ነው ሚሄዱት?” ስላት “አመደ ጉባይ የሚባል የግብጥ አገር አለ፤ ኸዚያ ይኸዳሉ፤ ቀድሞም አመጣጣቸው ኸግብጥ አመደ ጉባይ ነበር” ለችኝ፡፡ “እኛስ?” ስላት “እኛማ ልጀ ወዴት እንኸዳለን ብለህ ነው? ኸዚሁ ብቻችን ቀረነ እንጅ” አለችኝ፡፡ አመደ ጉባይ ከሚባል አገር መምጣታቸውን አላውቅም፡፡ ግን በአካባቢው ህዝብ ከሌላ አገር (ከግብጽ) እንደመጡ ይታመናል፤ ይሄንም ብዙ የአካባቢው ሰው ያውቃል፡፡ አማራ/ቅማንት ከግብጽ ጋር ግንኙነት እንደነበረውና እንዳለው ግን የታሪክ መጽሀፍትን ምእራፎች የሞላ ጉዳይ ስለሆነ የማህበረሰቡን እምነት ቅቡል ያደርገዋል፡፡

በዚህ በጭልጋ ውስጥ አማራ/ቅማንት በሰላም፣ በአንድት በፍቅር ኖሯል፡፡ የጠብና የበደለኝነት ታሪክ አንድስ ቀን እንኳ ሲወራ ሰምቸ አላውቅም፡፡ በዚህ አካባቢ አምስተኛ ቅድመ አያቴ በጣልያን ሰይፍ ተገድሎብኛል፡፡ 5ኛ አያቴ ቄስ የኔነህ እና ስሙን የማላውቀው ዲያቆን ልጁ ዷዱ ማርያምን የሚያገለግሉ ነበሩ፡፡ ጣልያን አገር እያጠፋ ሲመጣ አባትና ልጁንም ገደላቸው፤ አባትና ወንድሟ የተገደሉባት ሴት አራተኛ አያቴ ተርፋ የእኔን አያት እና ሌሎችን ለመውለድ በቅታለች፤ አምላክ ረዥም እድሜ ሰጥቶ ስላኖራት ለእኔ ለአራተኛ የልጅ ልጇ ይሄንን ታሪክ ሁልጊዜም በቁጭት ታጫውተኝ ነበር፡፡ ታዲያ ይሄንን የጣልያን ድርጊት በመቃወም አማራ/ቅማንት ሳይባባሉ በአንድነት የአርበኛ ስራ እንደሰሩ፣ በነጋዴ ባህር እና በአዳኝ አገር ጫቆ ሸፍተው ብዙ እንደተዋጉ ይነገራል፡፡ ቤተ ክርስቲያኗን ግን ቀደም ብላ አንዲት ወይዘሮ ባላባት እንዳሰራች እና አምስተኛና 6ኛ ቅድመ አያቶቸ አገልጋዮች እንደነበሩ ቤተሰቦቸ አጫውተውኛል፡፡ እንዲያውም ሴትዮዋ ዷዱ ማርያምን እና ሙዘደባ ኪዳነ ምህረትን እየተመላለሰች ስታሰራ የሙዘ ደባ ወንዝ ወሰዳት አሉ፡፡ ከደንቀዝ ተቀጥሮ የመጣው አናጢ በፋሲል ግንብ አይነት እንደሰራትም ይነገራል፡፡ አሁንም የፋሲል ግንብ አይነት ግንቧ አለ፡፡

———
ጎንደር ፋሲለደስ የመሰናዶ ትምህርት ቤት ከአምስት ከፍተኛ ትምህርት ቤቶች ነበር አንድ ላይ ተሰባስበን የምንማረው፤ ከልማት በር፤ ትክል ድንጋይ፣ ሸዋ ሜዳ፣ ደብረ ብርሀን እና አዘዞ፡፡ በዛ ጊዜ አማራና ቅማንት የሚሉ ስሞች ለመጠራት እንኳ በቅተው አላየሁም፡፡ አማራ/ቅማንት/ትግሬ የሚል ክፍፍልም አልነበረም፡፡ አንዲት የክፍላችን ልጅ እንኳ ማርታ በርሄ ነበር ስሟ እና ከብዙ ጊዜ በኋላ አዲስ አበባ ተገናኝተን ስሟን ማርታ በርሄ ብየ በአማራ እንደምንጽፈው ስጽፍ ቆጣ ብላ “በርሄ ሳይሆን በርሀ ነው የሚባለው” አለችኝ፡፡ “ይሄማ በርሀ (ምድረ በዳ) ማለት ነው፤ በርሄ እንዴት በርሀ ይሆናል?” ስላት “ኖ ኖ በትግርኛ እና በአማርኛ ይለያያል” አለችኝ፡፡ “ስትናገሪው እኮ በርሄ ነበር ምትየው ፋሲለደስ እያለን” ስላት “አትሰማኝም ነበር እንጅ በርሀ ነበር ምልህ ድሮውንም” አለችኝ፡፡ እስከዚህች ሰአት ድረስ ትግሬ መሆኗን አላውቅም ነበር፡፡ ይሄን ያወቅሁት እንግዲህ አዲስ አበባ ማስተርስ ትምህርቴን ልጨረስ አካባቢ ነው፡፡

Related stories   ሕዝብን ማን ይሰራዋል?

እና ምን ለማለት ነው፡ በፋሲለደስ ትምህርት ቤት ውስጥ ንጹህ ተማሪዎች፤ ንጹህ ልቦች የነበሩን፤ አገራችን ኢትዮጵያን በልባችን ያተምን (በመምህሮቻችን እና በህዝባችን አገር ወዳድነት ባህርይ ምክንያት) ነበርን፡፡ አይደለም አማራ/ቅማንት ቀርቶ አማራ/ትግሬ የሚል ክፍፍል አልነበረንም፡፡ መቸም ጊዜ ሁሉን ያሳያልና ያ ሁሉ አለፈ፡፡ ጎንደር ዩኒቨርሲቲም ገባን፡፡ ጎንደር ዩኒቨርሲቲም የፋሲለደስ ተማሪዎች የነበርን ተገናኘን፡፡ አሁንም አማራ/ቅማንት የሚል ነገር አልነበረም፡፡ አማራ እና ትግሬ የሚለውን ግን ከትግሬ የመጡ ልጆ በደንብ አድርገው አስተማሩን፡፡ ከኦሮሞ የመጡትም እንደዛው አስተማሩን፡፡ አብዱል ፋታህ የተባለው የክፍላችን ልጅ እንኳ አማራና ሱማሌ የሚል ልዩነት አስተማረን፡፡ አንድ ቀን ማራኪ ግቢ ውስጥ ቆመን ፕሮፌሰራችንን ስንጠብቅ አብዱል ፋታህ “ከደርግ ህወሀት ይሻላል” አለን ድምጹን ዘለግ አድርጎ፤ ከሩቅ ሌላ ክብ ሰርተው ቆመው የነበሩ ተማሪዎች እንኳ ሰምተው ወደእኛ ዞር እስኪሉ ድረስ፡፡ “በምን?” ብየ ጠየቅሁት፡፡ “ይሄው አሁን ከደርግ አገር አማራ መጥተን እየተማርን” ብሎ መለሰልን፡፡ ያው እንግዲህ ሱማሌዎች ከእነሱ ውጭ የሆነውን (ኦሮሞውንም ሀረሪውንም) አማራ እንደሚሉት የታወቀ ነገር ሆኖ ግን በግቢው ፖለቲካ ውስጥ ህወሀቶች (ትግሬዎች) ሱማሌዎችን እየሰበሰቡ “ይሄው እኛ ነን እኮ ከአማራ ከደርግ አገር እንድትማሩ ያደረግን” ይሏቸው እንደነበር በኋላ አወቅን፡፡ እንግዲህ አማራ/ቅማንትን በተመለከተ በግቢ ውስጥ ከዚህ የተለየ ነገር አልነበረም፡፡

ዛሬ ግን እነዛ አማራ እና ቅማንት ሳንባባል የኖርን ልጆች በሁለት ጎራ ተከፍለን አገኘሁ፡፡ ከፋሲለደስ ጀምሮ እስከ ጎንደር ዩኒቨርሲቲ ድረስ በሰላምና በፍቅር በጓደኝነት የተማርን ልጆች በአሳዛኝ ሁኔታ በሁለት ጎራ ተሰልፈናል፡፡ ያሳዝናል፡፡ ያን ጊዜ አማራ ይሁኑ ቅማንት የማናውቃቸው ጓደኞቻችን ዛሬ በቅማንትነት ተሰልፈው አማራ እያሉ ትግሬ ከሚሰድበን የከረፋ ዘመቻ ሲያካሂዱ እናያለን፡፡ እነሱ የሚከሱት፣ የሚዘልፉት እና የሚዝቱበት አማራ እውን እነሱ እንደሚሉት ነውን? መልሱን ለፈጣሪ እና ለጊዜ እተወዋለሁ፡፡ ሰው እንዴት ያልነበረን ነገር ፈጥሮ ሲያበቃ ሊያምን ይችላል? ለነገሩ በምጣኔ ሀብታዊ አተረጓጎምስ የካርል ማርክስ “ኮሜዲቲ ፌቲሽዝም” ሰውን በኢንዱስትሪ የሰራውን ሀብት ማምለኩን መግለጹስ አይደል፡፡ ብቻ እንደቅማንት ጉዳይ ማንነት ከዜሮ ተፈጥሮ እስከለቅሶ፣ እርግማንና ማህበረሰባዊ ቀውስ እንደሚደርስ እና ራስ ላይ እንደሚያስዘምት የሚያረጋግጥ ሌላ ምንም ምሳሌ የለም፡፡

——–
ለመሆኑ ለምንድነው ይሄን ሁሉ የምዘረዝረው? በጫጭቁናና ጭልጋ ማስታወስ እስከምችለው ብቻ እንኳ እስከ ዘጠኝ ቅድመ አያቶቸ ኖረዋል፡፡ አማራ/ቅማንት የሚባል ነገር ሳይኖር በሰላምና በፍቅር ኖረዋል፡፡ አሁን ግን ጭልጋና ጫጭቁና በቅማንት አስተዳደር ስር ሊወድቅ ነው፡፡ ይሄ ማለት የራሴው የትውልድ አሻራ ሁሉ ሌላ ታሪክ ተፈጥሮለት፣ ሌላ ማንነት ተፈጥሮለት፣ ሌላ ቅርጽና ይዘት እየተበጀለት ነው ማለት ነው፡፡ የቅድመ አያቶቸ አጽመ ርስት ተነቀለ ማለት ነው፡፡ ያሳደጉኝ ወገኖቸ፤ አክስቶቸና ልጆቻቸው ለሁለት ተከፈሉ ማለት ነው፡፡ ወይም ቤተሰቤ በትግሬ ርካሽ እና ስግብግብ ፖለቲካ ተበታተነ ማለት ነው፡፡ አሁን እነዚህን ቤተሰቦቸን በቅማንትነት ወይስ በአማራነት ነው የማውቃቸው፤ የምቀርባቸው? እነሱስ በአማራነት ወይስ በቅማትነት ይኖራሉ? ከፋሲለደስ ጀምረን አብረን ተምረን ስናበቃ፤ ምንም ነገር ባልነበረበት ከመሬት ተነስተው የትግሬ አጀንዳ አስፈጻሚ በመሆን ተሰልፈው የገዛ ወገናቸውን ሲራገሙና ሲሳደቡ፤ ለሁለት ሲከፍሉ ሳይ እጅግ ተገረምኩ፡፡ ከዛም አልፈው በእነሱ ተላላኪነት ሰበብ ከግራና ቀኝ ብዙ ወገናችን ደሙ እንዲፈስ ምክንያት መሆናቸውን ሳይ እጅግ አዘንኩ፡፡ እውነት ለመናገር እነዚህ ጓደኞቸ ትግሬ በአማራ ላይ የከፈተውን የጥፋት ዘመቻ በወንድምነት ለመመከት ቀድመው መገኘት ነበረባቸው፡፡ አማራ ተብሎ ከተፈረጀው ጋር ቆመው ጥፋቱን ለመከላከል እኩል መድረሳቸውን ራሱ አልወደውም፤ ቀድመው መድረስ አለባቸው ብየ ነው የማምነው፡፡ ከአማራ በፊት እኔን ማለት ነበረባቸው፡፡ ያ ግን አልሆነም፡፡ ያሳዝናል፡፡

Related stories   ሕዝብን ማን ይሰራዋል?

እና የቅማንት ነገር ለእኔ በተለይ እጅግ ሲበዛ የግል፣ የቤተሰብ፣ የጓደኝነት ጉዳየ ነው፡፡ በቅማንት የመጣው ችግር እንደ አማራነቴ፣ ከሁለቱም ወገን ቤተሰብ እንዳለው ሰውነቴ፣ እንደ ትምህርት ቤት ጓደኞቸ፣ እና እንደታሪኬ ነው የሚነካካኝ፡፡ የቅማንት ችግር የመላው አማራ ችግር ከመሆን አልፎ፣ ለእኔም እንደ አንድ አማራ ድርሻየን የምወስድበት ችግር ከመሆን አልፎ የግሌና የብቻየ ሁሉ ይመስለኛል፡፡ ከቅድመ አያቶች ታሪክ፣ ከአሁን ዘመዶቸ ህልውና፣ ከጓደኞቸ አሰላለፍ፣ አማራ እንደ ህዝብ ከገባበት አስቸጋሪ ሁኔታ ጋር ሁሉ ይተሳሰራል፡፡ እናም የቅማንት ጉዳይ ለእኔ ከሁሉም የባሰ ከባድ ይመስለኛል፡፡ ለዛም ነው አንዳዴ ሳስበው የግሌ ችግር ብቻ እስኪመስለኝ ድረስ የምደርሰው፡፡

እንግዲህ ጓደኞቻችን ልብ ገዝተው ቢሆን ኖሮ መልካም ነበር፡፡ ያ ግን አልሆነም፡፡ የቅማንት ሁኔታ አማራ ላይ እንኳን ሰው ድንጋይ እንኳ አፍ ቢኖረው አማራ ለረዥም ጊዜ ሽምግልና በሚያደርግበት ጊዜ ሲቀመጥብኝ ነበርና ጨቋኝ ነውና ይጥፋልኝ ማለቱ እንደማይቀር ያስተምረናል፡፡ አማራ ላይ ያልተነሳ አላየንም፡፡ አማራ ላይ ያልተነሳ ምንም ነገር እስካላየን ድረስ አማራ ላይ የማይነሳ ምንም ነገር አይኖርም ለማለት አንቸገርም፡፡ ስለሆነም አማራ ከአማራነቱ ውጭ ሌላ መፍትሄ የለውም፡፡ አማራ በአማራነቱ መቆም ብቻ አይደለም፤ በርትቶ መታገል አለበት፡፡ ሞትን የጠራብንን አማራነታችንን የምስራች ነጋሪ ማድረግ አለብን፡፡ ያን የምናደርገው ቀጥ ያለ፣ ጠንካራ እና አስተዋይ እንዲሁም ስርአት ያለው አማራ ስንሆን ነው፡፡

—–
ከላይ የተዘረዘረው ታሪክ በቅማንትነት ለትግሬ ያደሩትን ልብ ያራራል ተብሎ አይታሰብም፡፡ ነገር ግን ለሪኮርድ ያህል ብቻ ነው፡፡ የአማራ ችግር የሚፈታው እንዲህ አይነት እውነተኛ ታሪኮችን በመደርደር አይደለም፡፡ በትክክል በአማራነት ጸንቶ በመታገል ብቻ ነው፡፡ መዋደድ፣ አብሮ መኖር እና ውለታ በመስራት ቢሆን ኖሮ ሳሙናና ብስኩት የጫንለት ኤርትራ እንኳ ባልከዳን ነበር፡፡ በየጊዜው ከሚመጣው እውነታ ጋር እርምጃችንን እያስተካክልን መሄድ ብቻ ነው ሚሻለን፡፡
ምስጋናው አንዱዓለም፡፡   Mesganaw Andualem

(ለዚህ ለቀረበው ሀተታ እውነተኝነት እዚሁ ፌስቡክ ላይ ከደርዘን በላይ ምስክሮች እንዳሉም መጠቆም እፈልጋለሁ፡፡)

Share and Enjoy !

Shares
0Shares
0