ቆይ ግን ለመሆኑ እኛ ከተቀረው ዓለም በምን ተለይተን ነው የፀሐይ ግርዶሽ የማናየው? እኮ ምን ያንሰናል? አሻግረን በመነፅር የምናየው ፤ በቪዲዮ ቀርፀን ለታሪክ የምናስቀምጠው የፀሐይ ግርዶሽ ብናጣ ‘የፀሐይ መንግሥት ግርዶሽ’ እንኳን እንጣ? በምን አንሰን ነው?
ፀሐይ?
ፀሐዩ መንግስት ከአንድ ግለሰብ ጋር እንዲህ ግብ ግብ ሲገጥም ደሞ አሜሪካና ቢንላደን ትውስ ይሉኛል፡፡ እሱስ መንታ ህንፃ ዶግ አመድ አድርጎ ነው ይኸኛው “መንታ ወድጄ” እንጂ መንታ አንድጄ አላለ፡፡ ምን በወጣው ነው የሚያሳቅቁት? እኩዮቻቸው እዛ ተሰብስበው የሰሜን ኮሪያን የሃይድሮጅን ቦንብ ሙከራ ያወግዛሉ እነዚህኞቹ ተሰብስበው የአልበም ምርቃት ሙከራ ያወግዛሉ፤ያግዳሉ…ወይ እኩያ ማጣት! ይቅር አውሮፓ ጎረቤታቸውን እንኳ አያዩም?
ጎረቤት?
“Gebreselassie bitten Tergat again”
እንዳለው የሲድኒ ኦሎምፒክ ዘጋቢ…
“Kenya bitten Ethiopia Again” አልኩኝ እኔ፡፡
ልክ ነኝ፡፡ ከሩጫው ሜዳ በስተቀር በየግንባሩ ተከታታይ ሽንፈቶችን እንዳስተናገድን አለን…ባለፈው ጊዜ ልጇ የአሜሪካን ፕሬዘዳንት ሲሆን ይኼ ልጅ የጎረቤት ልጅ ነው አትመቅኙት … ይሁንለት … ይሳካለት … ይለፍለት… ለኛም ይተርፍ ይሆናል ብለን ዝም አልን፡፡ እሱቴ! ደሞ በቀደም ለት… “ፌስታል የሚባል ቁስ እንዳትጠቀሙ ፤ ለአካባቢ ጥበቃ ጠንቅ ነውና ይዞ የተገኘ ከባድ ቅጣት አለበት” ብለው ሲያውጁ ከፌስታል የተገነባች የምትመስል ከተማችንን ታቅፈን ዝም አልን፡፡ በደል ደርሶብን ‘አቤት’ ባይ ፍርድ ቤት አጥተን … ባሉትም እምነታችን ተሸርሽሮ እጅና እግራችንን አጣጥፈን በተቀመጥንበት ጭራሽ የነሱ ፍርድቤት ምርጫ ሰረዘ ሲሉን …
“Kenya bitten Ethiopia Again” ከማለት ውጪ ምን ልበል? ብቻ በድጋሚው ምርጫ ኦዲንጋ አሸነፉ ብለውኝ የበለጠ እንዳይገርመኝ፡፡ እነሱ እንደሆነ “ጎረቤት ምን ይላል?” ይሉት ይሉኝታ አልፈጠረባቸውም፡፡
(ኬንያ ኬኛ ለዚህ ፕሮፖጋንዳዬ ሞምባሳ መቼ መጥቼ ልዝናና ታዲያ?)
ፕሮፖጋንዳ?
የምን ቀን የምን ቀን ይሉት ፕርፖጋንዳ ላለመስማት…ኡጋንዳም ቢሆን በሄድኩ ለቀናቱ ስያሜ ሰጥቶ የፍቅር ቀን ስላሉት ከ’ቫለንታይን ደይ’ የተለየ አይሆን…ፍቅርማ ከቀን ያልፋል፡፡ ፍቅር በተግባር ነው፡፡ አለመዋሸት ፣ አለማጭበርበር ፣ ያለአድሎ መፍረድ ነው፡፡ እናቶችና የህፃናት ቀን መባሉ በየሜዳው ለወደቁት ህፃናት የአንድ ቀን እራት አይሆናቸው፡፡ እድሜ መማሪያ እና ማስተማሪያ ሳይሆን መድከሚያ እና መገፊያ በሆነበት ስርዓት ፤ ማህበራዊ ዋስትና ያጡ አረጋውያን በሞሉባት ሐገር የአረጋውያን ቀንን መሰየም ከፌዝ የተለየ አይሆንም፡፡ የጋራ መኖሪያ ቤት ሲገነቡ ‘የበግ ማረጃ ቤት’ አሰናድተው ፤ ቤተመፃህፍት ትዝ ያላላቸው ሰዎች ጠቅላይ ሚኒስቴሩ ለልጆች ተረት ስላነበቡ የንባብ ባህል ይዳብራል ቢሉን ዘበት፡፡
ንባብ?
መፅሐፍ አዟሪው ከተሸከመው መፅሐፍ እየመዘዘ ያሳየኛል፡፡ የምፈልገውን አገኝ እንደሁ ከቁልሎቹ መካከል አስሳለሁ…
“የመለስ አለህ?”
“አዎ ክስተት?”
“ኧረ የምን ክስተት? ልቃቂት”
ገለማምጦኝ ሄደ፡ አጠገቤ የቆመው…
“ታነቢያለሽ ማለት ነው? ጥሩ ነው … እኔምኮ አንባቢ ነኝ ስራዬ ነው …ቀላል ሙሉ ሰው አድርጎኛል እንዴ? ከሰው እኩል ቁጭ ብዬ የማወራው በማንበቤ ነውኮ”
“ኧረ? በጣም ጥሩ ነው፡፡ ደስ ይላል”
ቀጥዬም “እስካሁን ምን ምን አንብበሃል?”
“ያው የመብራት ቆጣሪ”

Teym Tsigereda Gonfa   Face book

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *