በወቅታቂ ጉዳዮች ላይ ከመላው ዐማራ ሕዝብ ድርጅት የተሰጠ የአቋም መግለጫ

በወቅታቂ ጉዳዮች ላይ ከመላው ዐማራ ሕዝብ ድርጅት የተሰጠ የአቋም መግለጫ
አንድ ስንዝር መሬት ከዐማራው ታሪካዊ ቦታዎች ላይ ለማንም ተላልፎ አይሰጥም!
ወልቃይት ጠገዴ-ራያ-መተከል ትናንትም ዛሬም ዐማራ ነው!

መዐህድ

የዐማራ ሕዝብ እና የቅማንት ማህበረሰብ ለዘመናት ሳይነጣጠሉ ማህበራዊ እሴቴቶቻቸውን እየተጋሩ አብረው ኖረዋል። በደስታቸው ወቅት አብረው ተደስተው በሃዘናቸውም ጊዜ አብረው አዝነዋል። እርስ በርሳቸው የጋብቻ ትስስርን ፈጥረው ልጆችን በጋራ አፍረተዋል። አገራቸውን በህብረት ከጠላት ወረራ ተከላክለዋል። ለዚህ ማስረጃ ከቢትወደድ አዳነ አባደፋር ጎን ተስልፎ ጣልያንን የወጋው የፊታውራሪ አየለ አባጓዴ የአረበኝነትን ተጋድሎ መጥቀስ በቂ ነው። የዐማራ ሕዝብ ያለውን ባህላዊ እሴቶች ሁሉ የቅማንት ማህበረሰብ ይጋራል። ዐማራን ዐማራ የሚያሰኙት ነገሮች ሁሉ በቅማንቱም ላይ አሉ። የቅማንት ማህበረሰብ ትናንት በትግሬ መራሹ አገዛዝ አልተፈጠረም። የቅማንት ማህበረሰብ ትናንትም አለ ነገም ይኖራል። የአማራ ሕዝብ ለቅማንት ማህበረሰብ የዘመናት አጋሩ ወንድሙና አብራኩ እንጅ ጠላቱ ሆኖ አያውቅም።

“የቅማንት የማንነት ጥያቄ” ስያሜን የተሰጠው ስውር ሴራ “የታላቋ ትግራይ” ምስረታ ሂደት አንዱ አካል ነው። ያ ማለት ግን ቁጥራቸው ጥቂት የማይባል ስልጣን ፈላጊ የቅማንት ተወላጆች ከጉዳዩ ጀርባ የሉም ማለት አይደለም። ከማንነቱ እና ከግዛት ይገባኛል ጥያቄው ጀርባ ካድሬዎችን ከማሰልጠን እስከ የአማራን ጥላቻ መዝራት ሌት ተቀን የሚታትሩ የትግሬ ተስፋፊዎች አሉበት። ከማንነቱ ጥያቄ የቅማንት ማህበረሰብ የሚጠቀመው አንዳች ነገር የለም ብለን እናምናለን። በስተመጨረሻ ያለምንም ኪሳራ ተጠቃሚነቱን የሚወስዱት የትግራይ ተስፋፊዎች ናቸው። የዐማራ ሕዝብ እንደ ሕዝብ ማንኛውንም ሕዝብ አልበደለም። ከአንዳንድ በህወሃት በሰለጠኑ ስልጣን ፈላጊ የቅማንት ተወላጆች የሚናፈሰው የበደለኝነት ስሜት ከሃቅ የራቀና ከህወሃት የአዕምሮ እጥበት ጋር የሚያያዝ ነው። የህወሃት አላማው አንድ ነው፤ እሱም በፍኖተ መርሁ በግልጽ እንደተቀመጠው በዐማራው መቃብር ላይ “የታላቋን ትግራይ” መመስረት ነው። ይህ ለቅማንት ማህበረሰብም አደገኛ ነው። ዛሬ ላይ አጋር መስለው የቀረቡ ቢመስሉም ኋላ ላይ ግን የተንቤን አገዎችን፣ የሳሆዎቹን፣ የኩናማዎችን እጣ ፋንታ በቅማንቱም ላይ መጫናቸው አይቀርም።

ለቅማንት ማህበረሰብም ሆነ ለዐማራ ሕዝብ የሚበጀው ልክ እንደበፊት ወንድማዊነቱን አጠንክሮ መቀጠል እና ውጫዊ ጠላትን በጋራ መከላከል ነው። በዚህ ጉዳይ ላይ በህወሃት መሪነትና ጥቂት በማይባሉ የቅማንት ተወላጆች አባሪነት ከ10 አመት በላይ የሕዝባችን ዘላቂ ሰላም ለማናጋትና በሚፈጠረውም አለመግባባት ህወሃት የበላይነትን ይዛ ለመቀጠል በማሰብ ብዙ የፀረ ዐማራ ድርጊቶች እንደተፈፀሙ የሚታወቅ ሲሆን በተቃራኒው የዐማራ ህዝብ ይህን ሴራ ተረድቶና ታግሶ ዛሬ ላይ መድረሱ ይታወቃል። ህወሃት ካለው የገንጣይ አስገንጣይ አጀንዳ አንጻር እንደውጭ ወራሪ የሚቆጠር ስለሆነ የቅማንት ማህበረሰብ የዚህን የወራሪ ቡድን እኩይ ተግባር ከወገኑ የዐማራ ሕዝብ ጎን ተሰልፎ ሊዋጋው ይገባል። ከዚህ ባለፈ በህወሃት አቀጣጣይነት የሚነሳ የሁለቱ ወገኖች ግጭት ጉዳቱ ለሁለቱም ነው።

ይህ አልበቃ ብሎ የትግሬ አፓርታይድ አገዛዝ ልሳን በሆኑ የሀገሪቱ የተለያዩ መገናኛ ብዙሃን እና በአገልጋዩ ብአዴን በኩል ግጨውና ጎቤ የተባሉ በሰሊጥና በማሽላ ምርት የሚታወቁ አካባቢዎች ተላልፈው ለትግሬ መሰጠቱ ተነግሯል። እነዚህ አካባቢዎች በነዋሪዎች ተጋድሎ እስካሁን የዐማራ ሆነው ቢቀጥሉም “በዐማራ ክልል” የህወሃት ስራ አስፈጻሚ በሆነው በብአዴን ይሁንታ ተላልፈው ተሰጥተዋል።

የመላው አማራ ሕዝብ ድርጅት (መዐሕድ) በዐማራው ሕዝብ ላይ የሚከናወኑ ሴራዎችን በሙሉ በአንክሮ ይከታተላል። እነዚህንና መሰል የትግሬ-ወያኔ እኩይ ተግባራት በጥብቅ በማውገዝ ድርጅታችን የሚከተለውን አቋም ወስዷል።

፩) ዐማራው በምንም አይነት መልኩ በአባቶቹ ርስት ላይ በትግሬ ወያኔ አጋፋሪነትና “በቅማንት የማንነት ጥያቄ” ስያሜ ሊካሄድ የታሰበውን የመሬት ዝርፊያ ሊያከሽፍ እንደሚገባው መዐሕድ ያሳስባል። በማንኛውም መልኩም ከሕዝቡ ጎን ይቆማል!
፪) ምንም እንኳን በጥቅማጥቅም ተታለውና የትግሬ-ወያኔን መሰሪ ተንኮል በውል መረዳት የተሳናቸው የቅማንት ተወላጆች በስህተቱ እየተሳተፉ እንዳሉ ብናውቅም፤ ይህ የጥፋት አጀንዳ በዋነኝነት ትግሬ-ወያኔ “ታላቋን ትግራይ” ለመመስረት የሚያካሂደው የመስፋፋት እቅድ አካል መሆኑን አበክረን እንረዳለን።

፫) ትግሬ-ወያኔ ትግራይን ለማስፋፋትና እኩይ አላማውን ለማሳካት የዐማራን መሰረታዊ ጥቅሞችና ሃብቶች መዝረፍና አማራውን ማዳከም ስልቱ እና በፍኖተ መርሁ ላይ በግልጽ የሰፈረ አላማው እንደሆነ ይታወቃል፤ ይህ ቅማንትን እንደ መሣሪያ ተጠቅሞ የዐማራን ህዝብ ውስጣዊ አንድነት በማናጋት መረጋጋት እንዳይኖር ለማድረግ የሚያካሂደው ሴራ በዐማራ ህዝብ ላይ የሚከተለው የጠላትነት ተግባር አካል መሆኑንም መዐሕድ ይገነዘባል።
፬) ስለሆነም መላው ዐማራ እያንዳንዷን የትግሬ ወያኔን የጥፋት ሴራ በአንክሮ መከታተልና በለመደው ራሱን የመከላከልና ጥቅሙን የማስጠበቅ ወኔ እየተመራ ራሱን በተፈላጊ አደረጃጀቶችና ድርጅቶች እያደራጀ የህወሃትን የአፈናና የስለላ መዋቅር በቁርጠኝነት እንዲፋለም መዐሕድ በትጋት ይሰራል።

፭) በጎንደርና አካባቢው እየተደረገ ያለው የፀረ ዐማራ እንቅስቃሴ ከአማራ ህዝብ ባላነሰ የቅማንት ማህበረሰብንም እንደሚጎዳ እናውቃለን፤ ባንጻሩ በእኛ ኪሳራ አትራፊው ትግሬ ወያኔ ብቻ ነው። ስለሆነም በተለያየ ምክንያት ተጠልፋችሁ ትግሬ-ወያኔ ጉድጓድ ውስጥ የገባችሁ የቅማንት ተወላጆች ከአድራጎታችሁ በአስቸኳይ ወጥታችሁ ከሕዝባችሁ ጥቅምና ዘላቂ ሰላም ጎራ በመሰለፍ የትግሬ-ወያኔን ሴራ ለማክሸፍ በሚደረገው ረድፍ እንድትገቡ በጥብቅ ለማሳሰብ መዐሕድ ይወዳል።

፮) ትግሬ-ወያኔ ለፊታችን መስከረም 7 2010 ዓ.ም በሕዝበ ውሳኔ ሰበብ የጎንደር ዐማራን ለምና ጠረፋማ መሬቶችን ለመውሰድ የሚያካሂደው ሩጫ መላ ሕዝቡ በየአቅጣጫው ተንቀሳቅሶ ሴራውን ማክሸፍና ሕዝበ ውሳኔውን ፍጹም መፍቀድ እንደሌለበት መዐሕድ አበክሮ ያሳስባል።

፯) አሁን ባለው ፋሺስታዊ አገዛዝ የዐማራ ሕዝብ የመረጠው ህጋዊ ተወካይ ስለሌለው በስሙ የሚደረጉ ማንኛቸውም ስምምነቶች ሁሉ ከፈቃዱ ውጭ የሆኑ መሆናቸውን ልናስገነዝብ እንወዳለን። ስለሆነም በህወሃት የተሰየመው ብአዴን ለትግሬ አሳልፎ የሰጠውን መሬት ከሌሎቹ የወልቃይት-ጠገዴ-ቃብትያ-ሁመራ እና ራያ አዘቦ መሬቶች ጋር ሕዝባችን የሚያስመልስ መሆኑና በትግል ሂደቱም ከሕዝባችን ጎን መሆናችን እናሳውቃለን።

፰) በመጨረሻም የመላው ዐማራ ሕዝብ ድርጅት ራሱን በአገር ውስጥና በውጭ፤ መላው አማራን በማደራጀት፤ ትግሬ-ወያኔ በሕዝባችን ላይ የደቀነውን የህልውና አደጋ በመቀልበስ የአማራውን መብትና ጥቅም ለማስከበር በቁርጠኝነት እየሰራ ያለ የህዝብ ድርጅት ነው። ድርጅታችን በተለይም ትግሬ-ወያኔ የቅማንትን ማህበረሰብ እንደ መጠቀሚያ በመውሰድ ሊፈጽም ያሰበውን ሴራ በቅርበት እየተከታተለ ከሕዝባችን ጋር በመሆን የጥፋት እቅዱን ለህዝባችን ያገኘውን አጋጣሚ ሁሉ በመጠቀም ርስቱን ከነጣቂዎች ይከላከላል ያስጥላልም።

ድል ለዐማራ ሕዝብ!

የመላው ዐማራ ሕዝብ ድርጅት –  ጳጉሜ 3 2009 ዓ.ም

በወቅታቂ ጉዳዮች ላይ ከመላው ዐማራ ሕዝብ ድርጅት የተሰጠ የአቋም መግለጫ

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *