1. የኢትዮጵያ ህዳሴ ወደ ስልጣኔ ማማ የሚደረግ ጉዞ ነው

ኢትዮጵያ ጉዟ ወደ ከፍታ መሆኑ አዲስ የሚፈረም መተማመኛ ሰነድ የለም፡፡ ኢህአዴግና የኢትዮጵያ ልማታዊ መንግስት የኢትዮጵያ  ህዳሴ በሚል የሚታወቀው ኢትዮጵያን ወደ ጥንታዊ የስልጣኔ ማማ የማድረስ የ40 ዓመት ፍኖተ ካርታ ለዓለም ማህበረሰብ ይፋ ካደረጉት ከአስርት ዓመት በላይ ተቆጥረዋል፡፡ በተለይም ይህንን ትልቅ ነበርን ትልቅም እንሆናለን በማለት በርካታ የጥበብ ሰዎችና የማህበረሰብ ሳይንስ ምሁራን ጭምር ያቀነቀኑት የብሩህ ዘመን ብስራት በታወጀበት የኢትዮጵያ የሶስተኛ ምዕተ ዓመት መባቻ ኢትዮጵያን በምዕተ ዓመቱ አጋማሽ ከበለፀጉ ሃገራት ጎራ ትቀላቀላለች የሚለውን ራዕይ ሃገራዊ መግባባት የተደረሰበት ነበር፡፡

  1. በሚሊኒየሙ ስለ ኢትዮጵያ የተቀመጡ መሰረተ ሃሳቦች

አዲሱ ሚሊኒየም በተከበረበት ወቅት በታተመ የኢህአዴግ የንድፈ ሃሳብ መፅሄት አዲስ ራእይ ላይ ኢህአዴግ ኢትዮጵያን አስመልክቶ አራት መሰረታዊ ግምገማዊ ድምዳሜዎችን አስቀምጧል፡፡

eprdf

እነርሱም ኢትዮጵያ፡-

  • – ሃገራዊ ነፃነቷን አስጠብቃ የቆየች ሃገር
  • – ከገናና ስልጣኔ ወደ ማሽቆልቆልና ውድቀት ያመራች ሃገር መሆኗን
  • – ብዙሃነትን ማስተናገድ ተስኗት የኖረች የብዙ ህዝቦች ሃገር መሆኗን
  • – ነፃነቷን በሁሉም ትውልዶች ትግል አስጠብቃ የቆየች ሃገር የሚሉ ጥልቅ ትንታኔ የተሰጠባቸው ሃሳቦች ናቸው፡፡

የእነዚህ 4 ድምዳሜዎች ሃሳቦቹን ላነበበው መልእክቱ ግልፅ ነው፡፡ በተራ ቁጥር አንድና ቁጥር 4 የተቀመጡ ድምዳሜዎች በአዲሱ ሚሊኒየም የኢትዮጵያ ቀጣይ ትውልዶች አስጠብቀው መቀጠል ያለባቸው የኢትዮጵያ ህዳሴ እውን መሆን የመሰረት ድንጋይ የሆኑ እሴቶች መሆናቸውን የሚያመለክቱ ናቸው፡፡

በተራ ቁጥር 2 እና 3 የተቀመጡ ደግሞ የኢትዮጵያ ህዳሴ እውን እንዲሆን ከመልካሙ ጥንታዊ ዘመኑ የይቻላል ትምህርት ሰንቀን ከኋለኛው ዘመን ስህተቶቹ ትምህርት በመውሰድ በማረም ለሃገራዊ ህዳሴ ኢትዮጵያውያን መነሳሳት እንደሚኖርባቸው ያመለክታሉ፡፡

በቁጥር 2 በመፅሄቱ በንኡስ ርእስ የተተነተነው የኢትዮጵያ በአንድ ወቅት በከፍታ ላይ እንደነበረች በታሪካዊ ማስረጃዎች አስደግፎ ያብራራል፡፡ በተለይም በአክሱም ዘመነ መንግስት በአለማችን ከነበሩ በጣት ከሚቆጠሩ ስልጣኔዎች አንዱ መሆኑና የገናና ስልጣኔ ባለቤት የሆኑ ህዝቦች የነበሩባት ምድር መሆኗ በስልጣኔያቸውም ኢትዮጵያ በስልጣኔ ማማ ከፍ ብላ የምትታወቅ እንደነበረች ይተነትናል፡፡ይህ ስልጣኔ ከጊዜ ወደ ጊዜ ገናናነቱ እየተንገዳገደ እስከ የጎንደር ስልጣኔ ቢቀጥልም ከዛ በኋላ ኢትዮጵያ አስከፊ በሆነ መልኩ እያሽቆለቆለች የመጣችበትና በ20ኛ ክ/ዘመን ሁለተኛ አጋማሽም ጭራሹኑ ለመበታተን ቋፍ መድረስዋን ያስቀምጣል፡፡ትንታኔው መጨረሻም ይህንን የውድቀት ጉዞ መቀልበስና ወደ ገናና የስልጣኔ ማማ ማውጣት እንዳለብን ይደመድማል፡፡

‹‹ ከጎንደር መንግስት መዳከምና በዚህ መንግስት ይሸፈን በነበረው አካባቢ ዘመነ መሳፍንት ተብሎ የሚታወቀው ዘመን ከመከተሉ ጋር ተያይዞ ባለው ጊዜ ውስጥ በኢትዮጵያና በሌሎች የሰለጠኑ ሃገራት መካከል ከፍተኛ መራራቅ እየታየ የመጣበት ሁኔታ ተፈጠረ አውሮፓውያን የኢንደስትሪ አብዮት ለማካሄድ ያስቻላቸው የተለያየ የኢኮኖሚ የማህበራዊና ፖለቲካዊ ለውጥ ስራ ሲያካሂዱ ቆይተው እንግሊዝ ከ18ኛው ክ/ዘመን ማጠናቀቅያ ጀምሮ ሌሎች ከ19ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ በስልጣኔ በእጅጉ መምጠቅ ሲጀምሪ ኢትዮጵያ ግን ግፋ ቢል ባለ፤ችበት መቆም ከዚያም አልፎ የኋሊት መጓዝ የጀመረችበት ይህ ማሽቆልቆል ሂደት ያለማቋረጥ ቀጥሎ ከ20ኛው ክ/ዘመን የሁለተኛው አጋማሽጀምሮ አገራችን በአለም ደረጃ የድህነትና የተመፅዋችነት ተምሳሌት የምትሆንበት ደረጃ ላይ ደረሰች›› (አዲስ ራዕይ መስከረም 2000 ገፅ 6)

Related stories   የደህንነትና ፀጥታ የጋራ ግብረ ኃይል አገር ለማተራመስ በህቡዕ የተደራጁ በርካታ ግለሰቦችን ከነመዋቅራቸውና መስሪያዎቻቸው በቁጥጥር ስር አዋለ፤

የኢትዮጵያ ህዳሴ በታወጀበት ጊዜ ግልፅ እንደተደረገው ኢትዮጵያ ወደ ነበረችበት የስልጣኔ ማማ እናደርሳታለን ሲባል ድሮ የነበረው እንዳለ እንደግማለን ማለት እንዳልሆነም ግልፅ ተደርጓል፡፡

‹‹አዲሱ የኢትዮጵያ ሚሊኒየም የኢትዮጵያ ህዳሴ ዘመን (Ethiopian Renaissance) ይሆናል ስንል ገናናው ታሪካችንን መልሰን እንደግማለን፣ የአክሱምን፣ የላሊበላን፣ የሀረሪን ወዘተ… ስልጣኔዎች እንዳሉ እንደግማለን ማለት አይደለም ፡፡ የዘመነ ግሎባላይዘሽን ቴክኖሎጂና ዕድገት መሰረት አድርገን ዴሞክራሲን እውን በማድረግና ነፃነታችንን በአዲስ መሰረት ላይ በመገንባት በአክሱም፣ በላሊበላ፣ሃረር ወዘተ ስልጣኔዎች ወቅት እንደነበረው ሁሉ ሀገራችን ከሰለጠኑት ሀገራሮች ተርታ እናስቀምጣለን ማለታችን ነው፡፡›› (ኢዲስ ራዕይ፣ መስከረም 2000፣ገፅ 42)

  1. ህዳሴውን ለማደብዘዝ የጨለምተኞች ሩጫ

በመግቢያው እንደተጠቀሰው ይህን ትልቅ ሀሳብ በመሰረቱ ሀገራዊ መግባባት የተደረሰበት ነበር፡፡ በርካታ የሀገራችን ምሁራንም በየሚዲያው ሀሳቡን በመደገፍና በማድነቅ ከአለም ታሪክና ከኢትዮጵያ እውነታ ጋር አያይዘው ሰፊ ድጋፋዊ ትንታኔ ሰጥተውበታል፡፡ ይህ ሲባል በአንድ በኩል ‹‹በአይቻልም›› መንፈስ የተሸነፉ ጨለምተኞች፣ በሌላ በኩል የሚቻል ከሆነም ምንም ይሁን ምንም ኢህአዴግ በሚመራው መንግስት መምጣት የለበትም በሚል ጭፍን ጥላቻ የተቸከሉ የተሸነፈ ርዕዮት አራማጆች ‹‹የኢትዮጵያ ህዳሴ›› የሚለውን ወርቃማና ህዝቡን በተስፋ ያነቃቃ መፈክርን/መሪ አስተሳሰብ/ በተጣመመ መንገድ በመተርጎም ሊያደበዝዙ ቢሞኩርም ሳይሳካላቸው ቀርቷል፡፡

እነዚህ ጨለምተኛና የተቸከሉ ሃይሎች ‹‹የኢትዮጵያ ህዳሴ›› እውን መሆን ይችላል አይቻልም በሚለው መሰረታዊ የክርክር ይዘት ከመነጋገር ይልቅ የአጀንዳውን ፈር ለማስለቀቅ ኢህአዴግ 40 ዓመት መግዛት ይፈልጋል በሚል እየዬ ነበር የተጠመዱ፡፡ ይህንን ያደረጉት የኢህአዴግ ራዕይና ስትራቴጂ በሚገባ የተተነተነና ነጥብ በነጥብ እያነሱ ሊያፈርሱት ቀርቶ ሊገዳደሩት እንደማይችሉ ያውቁት ስለነበረ ነው፡፡ አልፎ ተርፎም ከውጭ ጠላቶቻችንና ርዕየተአለማዊ ልዩነት አለን ብለው ከሚሉ የቀለም አብዮት አራማጆች ጋር በሀሳብ፣ በተግባርና በስምሪት  ኩታገጠም በመሆን የልማትና የብልፅግና የሆነውን የኢትዮጵያ ህዳሴን ‹‹የህዳሴ አብዮት›› በሚል የቀለም አብዮት ለማክሸፍ እጅግ በተቀናጀ፣ በተደራጀና በከፍተኛ የአለም አቀፍ የሰብአዊና የዴሞክራሲ ተቋማት ነን የሚሉ የፋይናንስና የስለላ ተደግፎ ብዙ ደክመውበታል፡፡ አዲስ አበባን ማዕከል ያደረጉ በርካታ የሽብር ተግባር ለመፈፀም የመንገድ መሪና አስፈፃሚ በመሆን ተሰማርተዋል፡፡ በሰላም ወዳዱ ህዝባችን ቢከሽፉም በስፖርት ስታዲዮም ሳይቀር እልቂት እንዲፈፀም፣ ትልቁ ገበያ መርካቶን በማቀጣጠል አዲስ አበባን እንደ ባግዳድ ለማውደም፣ መዲናችን ወደ ደም ምድር ለመለወጥ ‹‹የአኬልዳማ›› እልቂት ለመፈፀም ታሪክ የማይዘነጋው ክህደት ፈፅመዋል፡፡

እነዚህ ፀረ የኢትዮጵያ ህዳሴ ሃይሎች በአለም አቀፍ በተከሰቱ የፋይናንስና የኢኮኖሚ ቀውሶች፣ በመካከለኛ ኤሽያና በሰሜን አፍሪካ የጋጠሙ የፀደይ አብዮት በመባል የሚታወቁ ቀውሶችን ለቀለም አብዮት ፍላጎታቸው መሳሪያ ለማዋል ወደ ሃገር ውስጥ ኢምፖርት ለማድረግ የሚታወቅ ስፖንሰር በሌላቸው በየሳምንቱ የሚታተሙ የመፅሄትና የመፅሃፍት ህትመቶች በእጅጉ ፅፈውበታል፡፡ ቀስቅሰውበታል፡፡ በዚህ ህትመት የተሰማሩ ግለሰቦች ያንን ወጪ ለመሸከም የሚያስችል ግለሰባዊና ቤተሰባዊ ዳራ እንደሌላቸው ይታወቃል፡፡

ኮሙዩኒዝምን አድንቆ መፃፍ ውግዝና ወንጀል በሆነባት አሜሪካ ፣ ናዚን በአደባባይ አሞካሽቶ መጥራት ዘብጥያ በሚያስወረውር ጀርመን፣ ፋሽዝምን በስህተት መጥራት በድንጋይ በሚያስወግርበት አውሮጳ ላይ የመሸጉ የቀለም አብዮቱ ቀማሪ ምሁራን ተብዬዎች በሚቀርፁት ስልት በኢትዮጵያ ግን በህዝቦች ትግል የተሸነፉትን ነገስታትና ደርግን በማጀገን ህዝቡን ወደፊት ከሚያደርገው ጉዞ በተፃራሪ በሁሉም የህዝብ ግንኝነት መሳሪያዎች አሳፋሪ ፕሮፓጋንዳ ሲዘሩ ከርመዋል፡፡ እነዚህ ከኢትዮጵያ አብዮት በተቃራኒ የቆሙ የተቸከሉ ሃይሎች ከጊዜ ወደ ጊዜ ከህዝቡ እየተነጠሉ እና እየተተፉ ከመሄድም አልፎ ህዝቡም በግልጽና በአደባባይ በማውገዝ መንግስት እርምጃ እንዲወስድ ነበር የጠየቀው፡፡ በ2002 ምርጫ ማግስት የአዲስ አበባ ነዋሪዎች የውስጥና የአዓለም አቀፍ የቀለም አብዮት አራማጅ ሃይሎችና አክራሪዎችን በማውገዝ ያደረገው አንገታቸው ያስደፋ ሰልፍ ለአብነት ማውሳት ይቻላል፡፡

  1. አለም ሲለወጥ ቆሞ የቀሩ ‹‹የኛዎቹ››
Related stories   የኮሚሽነር አበረ ህልፈት "በነጋዴዎች" እይታና ፤ የሃኪም ትክክለኛው መረጃ " ቸልተኛነት አይተናል"

እነዚህ የጥፋት ሃይሎች የኢትዮጵያ ህዳሴ ራዕይ ግብ የሆነው ኢትዮጵያ ብምዕተ ዓመቱ አጋማሽ ከበለፀጉ ሃገራት ተርታ ትሰለፋለች የሚለውን መልካም ሃሳብ ለማደናቀፍ ቢነሱም የህዝቡን ማዕበል መግታት የሚችል ቁመናም ብቃትም አልነበራቸውም፡፡ ለአለም አቀፍ ማህበረሰብም የኢትዮጵያን ገፅታ በተበላሸ መልኩ ለመሳል ያልሞነጫጨሩት የስዕል ንድፍ የሌለ ቢሆንም በፍጥነት እየደበዘዘ ነበር የሄደው፡፡ አለም አቀፍ የፋይናንስና የኢኮኖሚ ተቋማት፣ የልማትና የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ የምክክር ፎረሞች ኢትዮጵያ እንደሃገር አጋር ብቻ ሳትሆን የአፍሪካ ድምፅ ነች የሚል አመለካከትም በፍጥነት ተገነባ፡፡ በማንኛው ዓለም አቀፍ ጉዳዮች የአፍሪካ አቋም ለመገንዘብ ኢትዮጵያን ቀድሞ ማግኘት አስፈላጊ ነው የሚል እምነት በመፈጠሩ ሃገረችን በመንግስታት፣ አለም አቀፍ ተቋማትና ኢንቨስተሮች ልኡካን መጥለቅለቅ ጀመረች፡፡ ወዳጆቻችን ብቻም ሳይሆኑ ገባ ወጣ የሚል አቋም የሚያራምዱም ሳይቀሩ የመድብለ ፓርቲ ስርዓት የምትከተልና የማይዛነፍ ምርጫ የምታካሂድን አገር እንደማንኛውም ጀማሪ ዴሞክራሲ በርካታ ድክመቶች ይኖረው እንደሆነ እንጂ በፍፁም የአንድ ፓርቲ ስርዓት አይደለም የሚል እቅጩን መናገር ጀመሩ፡፡ ይህ ለቀለም አብዮት አራማጆች አከርካሪ የሰበረው የአለም አቀፍ ማህበረሰብ እይታ ባለፉት 10 ዓመታት ሃገራችን ኢትዮጵያ ላስመዘገበችው ፈጣንና ተከታታይ እድገት ትልቅ ትርጉም ነበረው፡፡

የሀገራችን አያያዝ ያማራቸው ብቻ ሳይሆን ያስጎመጃቸው የልማት ሃይሎች/ሀገራትና ባለሃብቶች/ በእርግጥም ኢትዮጵያ በአዲሱ ሚሊኒየም ከዓለም ማህበረሰብ ያላት ግንኝነት ከምፅዋት ተቀባይነትና ሰጪነት ወደ ልማት አገርነት መቀየሩ ለመገምገም ግዜ አልፈጀባቸውም፡፡ የአትዮጵያ መንግስት ያወጀው ‹‹የኢትዮጵያ ህዳሴ›› እንዲሁ ሽለላ ሳይሆን በተግባር የሚመነዘር እውነታ መሆኑ በተሰራ ከፍተኛ የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ የአለም ማህበረሰብ እየተማመነ የመጣበት ሁኔታ ተፈጠረ፡፡ ይህ የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ ግን እንዲሁ በባዶ እጅ ደጃፋቸው በማንኳኳት የተፈጠረ ሳይሆን የልማት አጋሮቻችን በሀገሪቱ በመገኘት የሃገሪቱ ፈጣን እድገት አይተው መመስከርና መተማመን በመቻላቸው ነው፡፡ በድምር ባለፉት 10 ዓመታት ብቻ ከአገር ውስጥ የግል ሴክተር ማህበረሰብ በጋራ በመቀናጀት በኢትዮጵያ እና በተለያዩ ሃገራት ከ100 በላይ የኢኮኖሚ ፎረሞች ተከናውነዋል፡፡ እነዚህ ፎረሞች 1071 የሀገራችን የግል ኩባንያዎች ከውጭ አቻዎቻቸው የቢዝነስ ትስስር እንዲፈጥሩ ከማስቻሉም በላይ በኢትዮጵያ ቢዝነስ ዕድሎች እውቀትና ትምምን እንዲኖራቸው አድረጓል፡፡ የመተማመናቸው መገለጫም እያደገ ያለው የቀጥተኛ ኢንቨስትመንት የማያወላዳ ማሳያ ነው፡፡ ለዚህ ማሳያ የዋና ዋናዎቹና ጎላ ያሉትን መጥቀስ ካስፈለገ በአሁኑ ወቅት ቁጥራቸው 481 የቻይና ፕሮጀክቶች ወደ ስራ ገብተው ምርት ላይ ይገኛሉ፡፡ ለ62 ሺህ 757 ዜጎች የስራ ዕድል ፈጥረዋል፡፡ በተጨማሪም 245 የቻይና ባላሃብቶች ፕሮጀክቶች ወደ ስራ ለመግባት በዝግጅት ላይ ናቸው፡፡እነዚህ የቻይና ፕሮጀክቶች በድምር በ16.979 ቢሊዮን ብር ካፒታል ያስመዘገቡ መሆናቸው ይታወቃል፡፡

Related stories   ሱዳን በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ላይ የሉዓላዊነት ጥያቄ እንደምታነሳ አስጠነቀቀች፤ "ብሄራዊ የጀግንነት ጥሪ ያፈልጋል"

በተመሳሳይ በ7. 773 ቢሊዮን ብር ካፒታል ካስመዘገቡ 155 የቱርክ ፕሮጀክቶች 84 ወደ ስራ ከገቡ ቆይተዋል፡፡ ፕሮጀክቶቹ ለ16 ሺህ 280 ዜጎች በቋሚና ጊዚያዊ የስራ ዕድል ፈጥረዋል፡፡ ቀሪ 34 ፕሮጅክቶች ደግሞ ወደ ሥራ ለመግባት ዝግጅት ላይ ናቸው፡፡

5 ነጥብ 987 ቢሊዮንና 5.417 ቢሊዮን ብር ካፒታል ያስመዘገቡ 73 የሳዑዲ አረቢያ እና 268 የህንድ ፕሮጀክቶች ገሚሶቹ ወደ ስራ የገቡ ሲሆን እስካሁን በድምር ወደ 40 ሺህ ቋሚና ጊዚያዊ የስራ ዕድል ፍጠረዋል፡፡ የውጭ ባለሃብቶች በግላቸው ከሚያደርጉት ስምሪት በተጨማሪ ከሀገር ውስጥ ባላሃብት በጋራ መስራት ጀምረዋል፡፡ ለአብነት 4.4 ቢሊዮን ካፒታል ያላቸው የኢትዮ ሳዑዲ ኢንቨስትመንት ተጠቃሽ ሲሆን በዚህ ኢንቨስትመንት የተቋቋሙ 76 ፕሮጀክቶች ለ20ሺህ ገደማ ዜጎች የስራ ዕድል መፍጠር ችለዋል፡፡

በአጠቃላይ የቻይናው ሁጃን ጫማ ፣ የቱርክ አይካ አዲስ፣ የህንዱ ሪይሞንድ፣ የስዊድን ኤች ኤንድ ኤም፣ የእንግሊዞቹ ዲያጎ፣ ሄኒከን፣ ዩኒሊቪዬር፣ የአሜሪካው ጀነራል ኤለክትሪክ፣ የናይጀሪያው ዳንጎቴ የመሳሳሉ ታላላቅ ኩባንያዎች ጨምሮ በርካታ የቢዝነስ ኩባንያዎች የአፍሪካ የትንሳኤ ተስፋ ባሏት ኢትዮጵያ መዋእለ ንዋያቸው በማፍሰስ እየሰሩ ይገኛሉ፡፡

መሆኑም የኛዎቹ ጨለምተኞችና የቂምና በቀል ፖለቲካ አራማጆች ‹‹ብትበርም ባትበርም ፍዬል ናት›› በሚል የድርቅናና የኋላቀር አቋማቸው ተቸክለው ሲቀሩ ጥቅማቸውን አማትረው ከርቀት የሚያዩ የአለም አቀፍ ባላሃብቶችና ባለፀጎች ግን ከኢትዮጵያ ዕድገት ለመቋደስ በበርካታ ቢሊዮን ዶላር ኢንቨስት እያደረጉ ይገኛሉ፡፡ እነዚህ አለም አቀፍ ኢንቨስተሮች ይህንን ውሳኔ የደረሱና ወደ ተግባርም የገቡ የኢትዮጵያ ጉዞ ወደ ፊት ወደ ከፍታ መሆኑ ባላቸው አለምአቀፍ የደለበና የረጂም ጊዜ የቢዝነስ ትንተና፣ ጥናትና ልምድ የሚመሰረት ነው፡፡ በካፒታሊዝም ቤት ለትርፍ እንጂ ለኪሳራ የሚደረግ ጨዋታ አይሰራም፡፡ እናም ኢትዮጵያን ሲመርጡ ኢትዮጵያ በእርግጠኝነት ከ19ኛውና ከ20ኛው ክፍለዘመን የተለየች ኢትዮጵያ መሆኗ እርግጠኛ በመሆናቸው ነው፡፡

  1. ማጠቃለያ፣

በአጠቃላይ የኢትዮጵያ ህዳሴ የከፍታ ህዳሴ ነው፡፡ ኢትዮጵያ በተለይም ባለፉት 500 ዓመታት ያጋጠማትን የቁልቁለት ጉዞ በመግታት ከዚሁ ተቃራኒ ወደ ሆነው ወደ ከፍታ ማማ ማወጣት ነው፡፡ ይህ መልካም ሀሳብ ወደ ተግባር መመንዘር ከጀመረ ከአዲሱ ሚሊኒየም ብቻ 10 ዓመታት ሞልቶታል፡፡ ይህንን መልካም ሃሳብ ድህነትን መገዳደር ጀምሯል፡፡ እስካሁን በተገኘ ውጤትም በሀገሪቱ ህዝብ ተስፋን ጭሯል፡፡ በአለም አቀፍ የልማት አጋሮች ዘንድም ትኩረት ስቧል፡፡ ኢትዮጵያውያን የኢትዮጵያ ህዳሴ እውን ይሆናል የሚል ቃል በየዕለቱ የሚደጋግሙት ቃል ሆኗል፡፡ በእርግጥም ማንኛውም ለኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን በጎ የሚመኝ ባለሃብት፣ ምሁር፣ አርቲስት፣ ፖለቲከኛ ፣ የሃይማኖት ሰው «መጪው ዘመን የኢትዮጵያ ህዳሴ ይሆናል፣ ኢትዮጵያ ወደ ከፍታ ማማ  እናደርሳታለን›› ቢል በምልአተ ህዝቡ መነቃቃት የሚፈጥር እንጂ ከጤናማ ወገን ውግዘት ሊደርስበት የሚገባ ሃሳብ አይደለም፡፡

አዲስ አበባ ኢህአዴግ

Share and Enjoy !

Shares

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *