በአበበ ተክለ ሃይማኖት (ሜጄር ጄኔራል)

በመጀመርያ የትግራይ ሕዝብ ባከናወነው የተፈጥሮ ሀብት ሥራ በዓለም ደረጃ የወርቅ ተሸላሚ በመሆኑ ለሕዝቡ፣ ለመስተዳድሩና ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝቦች እንኳን ደስ አለን ለማለት እወዳለሁ፡፡

አንዳንድ የትግል ጓዶች አሁንም በሥልጣን ላይ ያሉ ሌተና ጄኔራል ጻድቃንና እኔ የአገራችን ጉዳይ አሳስቦን በመጻፋችን ምን ፈልገው ነው? ይላሉ፡፡ የሚጠቅም ሐሳብ አለው የለውም ብለው ሳይመረምሩ፡፡ ሥልጣን ፈልገው? ተምረናል ለማለት? ወይስ ቂም ስላላቸው? ብለው በመመራመር ጊዚያቸውን ያባከናሉ፡፡ እስከ ምን ድረስ እንደወረዱ የሚያሳይ ነው፡፡ መልሱ ግን ሁሉም ስህተት ነው፡፡ የዛሬ 124 ዓመት ከተጻፈ ጥቅስ መልሱን ቢፈለጉት እንዴት ደስ ባለኝ!!

ሰሞኑን ከሃምሳ በላይ በሚሆኑ ተጠርጣሪዎች ላይ የተወሰደው ዕርምጃ የአገራችን ሕዝቦች ሰፊ መነጋገሪያ ሆኗል፡፡ ሙስና አገር አጥፊ ካንሰር በመሆኑ ወቅታዊ አጀንዳ መሆኑ ሲያንሰው ነው፡፡ ሕዝቡ ‹ሙሰኞችን መመንጠር ተገቢ ነው፣ መቀጠል ያለበት ጉዳይ ነው እያለ፣ ነገር ግን የጡት ልጅ በጥርጣሬ አስሮ የጡት አባት ሳይነካ እንዴት ነው ነገሩ? ይህ ደግሞ ሙስናን በሙስና መንገድ መሄድ አይደለም እንዴ?› በማለት ውኃ ቅዳ ውኃ መልስ ሆኗል እያለ ነው፡፡

ግማሹ ያህል ሚኒስትሮች ቢታሰሩ ችግሩ መሠረታዊ መፍትሔ የሚያገኝ የሚመስላቸው አልታጡም፡፡ በከፍተኛ ባለሥልጣናት ነው መጀመር ያለበት የሚለው ያስማማናል፡፡ ብቻውን ግን ለጊዜው ያቀዘቅዘው ካልሆነ በስተቀር መሠረታዊ መፍትሔ የሚያመጣ አይመስለኝም፡፡ በዘመቻ መልክ ብቻ ሳይሆን የመንግሥት የዕለት ተዕለት ሥራ ነው ሙሰኞችን መቆጣጠር፡፡ ነገር ግን ሥሩን/ግንዱን ሳትነካ ቅርንጫፉን ከቆረጥከው እንደገና ተጠናክሮ ‹‹የሚለመልም›› በመሆኑ መሠረታዊ መፍትሔው ላይ ብንወያይ ይሻላል ከሚል ነው፡፡ ለእኔ የጡት አባት ሲባል እነ እገሌ የሚባሉ ከፍተኛ ባለሥልጣናት አይደሉም፡፡ ፖለቲካዊ ሥርዓቱ ነው የጡት አባት፡፡ በጠራራ ፀሐይ ሲዘረፍ እያየ እንዳላየ፣ ግድ የላችሁም ቀጥሉበት የሚል ዓይነት ሥርዓት ነው፡፡

ሐሳቤን በዚህ መልክ አደራጅቼዋለሁ፡፡ በመጀመርያ የሙስና ዓይነቶች በተለይ የፖለቲካዊ  ሙስናና የገንዘብ/ንብረት ሙስና ያላቸውን ዲያሌክቲካዊ ትስስር ለመግለጽ እሞክራለሁ፡፡ ‹‹የሕግ የበላይነት በኢትዮጵያ›› በማለት ለሙስና መሠረት የሆኑ ጉዳዮችን እገልጻለሁ፡፡ በማናቸውም የኅብረተሰብ እንቅስቃሴ ከመሠረቱ ለመገምገም የሚያስችሉ መዋቅራዊ ድክመቶች/ተግዳሮቶችና መዋቅራዊ እሴቶች ያላቸውን ተያያዥነት አቀርባለሁ፡፡ ቀጥሎም በአጠቃላይ የሙስና ሁኔታን ከገለጽኩ በኋላ መቶ በመቶ የምርጫ አሸናፊነት የሙስና ትልቁ ምልክት እንደሆነ፣ ፖለቲካዊ ሙስና እንዴት ሁለት ዜጋ እንደሚፈጥር ለማብራራት እሞክራለሁ፡፡ በመጨረሻም የተቋሞቻችን መልፈስፈስ ለሙስና ካለው ትርጉም አንፃር አስተያየቴን አቀርባለሁ፡፡

ሕገ መንግሥታችን የኢትዮጵያውያንን ያለፈ ብሶት ዕውቅና የሚሰጥና የወደፊቱን የሰላም፣ የልማትና ዴሞክራሲ አቅጣጫ የሚያመለክት በመሆኑ የጽሑፉ ማጠንጠኛ ነው፡፡ ሕገ መንግሥታችን ሲተገበር ሙስና ይቀጭጫል፣ ሲጣስ ይቦርቃል፡፡ የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችን ብሶት ሎሬት ፀጋዬ ገብረ መድኅን በ1983 ዓ.ም. ሲገልጹ እስኪ ተቋደሱልኝ፡:፡ ይህ ‹‹ለወንድሜ ለማላውቅህ›› የሚለው ግጥም ማራኪ ሆኖ አግኝቼዋለሁ፡፡ የሁሉንም ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ስም በግጥሙ ይጠቅሳሉ፡፡ ግጥሙ ሰፊ ስለሆነ የተወሰነውን ልጋብዛችሁ፡፡

ማነህ

ገባር ነህ ሙክት ሳቢ

እረኛ ነህ ከብት አርቢ

አራሽ ነህ ያገር ቀላቢ

አማል ነህ የግመል ሳቢ . . .

ባክህ ማነህ ወንድምዬ፣ አንድም ቀን የማንወያይ በውል በጣይ ባደባባይ

በፎቶግራፍ ዓይን እንጂ፣ ዓይን ለዓይን የማንተያይ

እኔ ለወሬ አንተን መሳይ አንተ ለጭንቅ እኔን መሳይ

ማነህ እኮ የማላውቅህ

ማዶ ለማዶ ሩቅ ለሩቅ በመኪና ዓይን የማይህ

የማትቀርበኝ የማልቀርብህ

ጠረንክን የምጠየፍህ

በጋዜጣ በመጽሔት ወሬህን የምተርክህ

ሥዕልህን ፎቶግራፍህን ለአገር ጎብኚ የምሸጥህ፡፡

  1. ፖለቲካዊ ሙስናና የገንዘብ/ንብረት ሙስና

በርካታ ምሁራን ሙስናን በሁለት ከፍለው ለመተንተን ይሞክራሉ፡፡ አንዳንዶቹ ፖለቲካዊ ሙስና (Political Corruption) እና ቢሮክራቲክ ሙስና (Bureaucratic Corruption) ብለው ሲገልጹት፣ ሌሎቹ ደግሞ ትልቅና ትንሽ (Grand and Petty) ብለው ይጠሩታል፡፡ አንዳንዶቹ በግለሰብ ደረጃ ወይም በቡድን (Collective Corruption) ብለው ያስቀምጡታል፡፡ ሁሉም የተሳሰሩና የጡት አባትና ልጅነት ለመግለጽ በመሆኑ፣ ለአሁኑ ሐሳቤ እንዲመቸኝ ፖለቲካዊ ሙስናና የገንዘብ/ንብረት ሙስና በሚል ከፋፍዬዋለሁ፡፡

የገንዘብ/ንብረት ሙስና የሚወሰነው በፖለቲካ ሥርዓቱ ብልሽት ደረጃ ነው፡፡ በሁሉም ሥርዓቶች በተለያየ ደረጃ ሙስና ይታያል፡፡ ፍፁም (Perfect) የሆነ ሥርዓት ስለሌለ በዳበሩ ዴሞክራሲያዊ አገሮች በአሜሪካም በአውሮፓም ይከሰታል፡፡ ይሁን እንጂ ጠቅላላ እስከ ሥርዓት ማናጋት ሳይደርስ በቁጥጥር ሥር የመዋል ዕድሉ ከፍተኛ ነው፡፡

ባልተረጋጋና በሽግግር ላይ ባለ ፖለቲካዊ ሥርዓት ፖለቲካዊ ሙስና በከፍተኛ ደረጃ የመታየት ዕድል አለው፡፡ በመሆኑም የገንዘብና የንብረት ሙስናን ለመቆጣጠር አስቸጋሪ ነው፡፡ ፖለቲካዊ ሙስና የጡት አባት፣ የገንዘብና የንብረት ሙስና የጡት ልጅ መሆናቸው አይቀሬ ነው፡፡ ፖለቲካ ሙስና ማለት ፖለቲካዊ ተቋማትን፣ ሕጎችንና አሠራሮችን በማዛባት (Manipulate) ሥልጣን ከሕግ ውጪ ለማደላደል የሚደረግ እንቅስቃሴ ሆኖ፣ ፖለቲካዊ ሥርዓቱና ፖለቲካዊ ተቋማት ለመበስበስ አደጋ ይጋለጣሉ ይላሉ ምሁራን፡፡

አንዱ ወገን በዋናነት ለሚቆጠሩ የሚችሉ (Countable) እንደ ገንዘብ/ሀብትና (Fiscal Privileges) በከፍተኛ ደረጃ ተጠቃሚዎች ሲሆን፣ ሌላው ወገን ደግሞ ለዚያኛው እያመቻቸ በዚያ ድጋፍ የማይቆጠሩ (Uncountable) ጥቅሞች ማለትም ፖለቲካዊ ተፅዕኖ ለማሳደግና የሥልጣን ደኅንነት (Power Security) እንዲረጋገጥለት በመፈለግ በጋራ የሚሠሩ፣ ግን ለተለያዩ ዓላማዎች የሚሠሩ ሙሰኞች ናቸው፡፡ እነዚህን ወገኖች ለመለያየት አስቸጋሪ ነው፡፡ ከሁለቱም ወገን ገንዘብና ሥልጣን የሚፈልጉ ይኖራሉ፡፡ እዚህ ላይ ለመግለጽ እየተሞከረ ያለው ሥልጣናቸው እስከተረጋገጠ ድረስ የአገር ሀብት አሳልፈው የሚሰጡ ሙሰኞች እንዳሉ ነው፡፡

በአጠቃላይ ሲታይ ፖለቲካዊ ሙስናው በተነፃፃሪ አነስተኛ ከሆነ የገንዘብ/ንብረት ሙስናን ያቀጭጫል፡፡ ፖለቲካዊ ሙስና ከፍተኛ ከሆነ ግን የገንዘብ/ንብረት ሙስናን ለመቆጣጠር አስቸጋሪ ይሆናል፡፡ ፖለቲካዊ ተቋማትንና ሕጎችን በመጣስ የሚደረግ ሙስና ማለት፣ የሕግ የበላይነት ያልነገሠበት ሥርዓት ባለበት ሁኔታ ውስጥ በአብዛኛው የሚከሰት ነው፡፡

  1. የሕግ የበላይነትና ሙስና

የሕግ የበላይነት ስንል በዋናነት ሕገ መንግሥታችን ማክበርና ማስከበር ነው፡፡ ፖለቲካዊ ሥርዓቱ ሕገ መንግሥትን መሠረት አድርጎ ብቻ ይንቀሳቀስ ማለት ነው፡፡ ሕገ መንግሥቱን የሚፃረሩ ሕጎች/መመርያዎችና አሠራሮች ውድቅ ስለሆኑ ይታገዱ፣ ይወገዱ ማለት ነው፡፡  እንደሚታወቀው ሕገ መንግሥታችን ሁለት ዋና ክፍሎች አሉት፡፡

  1. ከ10 እስከ 44 ያሉት አንቀጾች የኢትዮጵያ ሕዝቦች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች በተሟላ መንገድ የሚያረጋግጥ ነው፡፡
  2. በክፍል አንድ ያሉትን መብቶች ባልተሸራረፈ መንገድ የመከላከልና አዎንታዊ ተግባር በመጨመርም ተግባራዊ የሚያደርግ የመንግሥት አወቃቀርና ፖሊሲዎች በሚመለከት ከ45 እስከ 105 ያሉት አንቀጾች ተካተዋል፡፡

      በእኔ አመለካከት የሕገ መንግሥቱ መንፈስ መንግሥትና ፖሊሲዎቹ የሕዝቦችን መብቶች ለማስከበርና ለመጠበቅ ብቻ ነው የተዋቀሩት፡፡ ከዚያ ውጪ መንግሥት ሌላ ሚና የለውም፡፡ የሕዝቦችን መብት ለመጠበቅ በፌዴራላዊ አወቃቀር አንዱ የመንግሥት አካል ብቻ ሥልጣኑን ከተቆጣጠረው የሕዝቦች መብት ሊጥስ ስለሚችል ሕግ አውጪ፣ ሕግ አስፈጻሚና ሕግ ተርጓሚ የራሳቸው ተነፃፃሪ ነፃነት እንዲኖራቸው ተደርገዋል፡፡ ግልጽነትና ተጠያቂነት ለማንገሥ በተለምዶ ‹አራተኛው መንግሥት› ለሚባለው መገናኛ ብዙኃን ግልጽ የሆነ ሕግ አስቀምጧል፡፡

    የሕዝቦች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ሲረጋገጡ ያለ ፍርኃትና መሸማቀቅ ሐሳባቸውን የመግለጽ፣ የመደራጀት፣ ሰላማዊ ሠልፍ የማድረግ በሕጉ መሠረት በሁሉም መስኮች መሳተፍ ሲጀምሩ፣ ፖለቲካዊ ሙስና ብሎም የገንዘብ/ንብረት ሙስና ይቀጭጫሉ፡፡ የሕዝቦች በጋራ የመተዳደር (Shared Rule) እና በራስ መተዳደር (Self Rule) ሲረጋገጥ፣ ለሙስና የሚሆን መሠረት እየጠበበ ነው ማለት ነው፡፡

      ሕግ አውጪው ከላይ የተገለጹትን ለማረጋገጥ ለሕገ መንግሥቱና ለህሊናው ማንነቱ (Integrity) ያረጋገጠ ሲሆን፣ ባለገንዘቡና ባለጡንቻው የሆነውን ሕግ አስፈጻሚውን ስለሚቆጣጠር ሙስናው በጣም የቀጨጨ ይሆናል፡፡ ሕግ አስፈጻሚና ሕግ ተርጓሚውም በተመሳሳይ መንገድ ሊታዩ ይችላሉ፡፡ የመገናኛ ብዙኃንን ተጠያቂነትና ግልጽነት ለማረጋገጥ የሚያስችል ቁመና ሲኖረው፣ የሕግ አስፈጻሚ የሥልጣን ብልግና (Abuse of Power) በአነስተኛ ደረጃ የሚታይበት ሙስናን በቁጥጥር ሥር ማዋል ይቻላል፡፡

ሕዝቦች የመሰላቸውን ሲገልጹ፣ በሰላማዊ ሠልፍና በሌሎች ሕጋዊ መንገዶች ሲደግፉ፣ ሕግ አውጪው ሲነቃቃ፣ ሕግ ተርጓሚው ፍትሕ በከፍተኛ መንገድ ሳያዛንፍ ሲቀር፣ መገናኛ ብዙኃን በአግባቡ ሲሠሩ የእነዚህ ድምር ውጤት ፖለቲካዊም ሆነ የገንዘብ/ንብረት ሙስና አልፎ አልፎ በጨለማ የሚታይ ክስተት ብቻ ይሆናል፡፡

ኢትዮጵያ ከአምባገነንነት ወደ ዴሞክራሲ ሽግግር ላይ ያለች አገር ናት፡፡ የሕግ የበላይነት ችግር ወይም በኢሕአዴግ አገላለጽ ‹‹ክፍተት›› አለ? ወይስ የለም? የሚለውን ሐሳብ ለመገምገም አይደለም፡፡ በሁሉም ሥርዓቶች ውስጥ ክፍተቶች አሉ፡፡ ስለዚህ የሕግ የበላይነት፣ ግልጽነት፣ ተጠያቂነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተረጋገጠ እየሄደ ነው? የሚታይ መሻሻል አለ? ወይስ ወደ ኋላ እየተንሸራተትን ነው? የሚለው መታየት ያለበት፡፡

  1. የሕግ የበላይነት ለማረጋገጥ ያሉት መዋቅራዊ ተግዳሮቶችና ዕድሎች

አንድ አገር በአንድ ሰው/ፓርቲ አይለማም፣ አይጠፋምም፡፡ የተሻለ የሚባል አመራር/ፓርቲ በኅብረተሰቡ  ውስጥ ያሉትን መዋቅራዊ ጠንካራ ጎኖችን እያጎላ መሠረታዊ ድክመቶችን እየታገለ ግሎባላይዜሽን የሚሰጠውን ዕድሎች በመጠቀም (Exploite)፣ ተግዳሮቶችን የሚያሸንፍ አገር ወደ ሰላም ልማትና ዴሞክራሲ ይመራል፡፡ ይህ ጉዞ ብዙ ውጣ ውረድ ያለበት ነው፡፡ ፀረ ሕዝብ አመራር በሚኖርበት ጊዜ ውጤቱ ተፃራሪ ይሆናል፡፡ ቀጥሎ ለሙስና መሠረት የሚሆኑትን መዋቅራዊ ኅብረተሰባዊ ድክመቶችን ቃኝተን ዕድሎች ምን እንደሚመስሉ እናያለን፡፡

ሀ. ከአምባገነናዊ ሥርዓት ወደ ዴሞክራሲ የሚደረግ ሽግግር

‹‹ሰማይ አይታረስ ንጉሥ አይከሰስ›› ይህ ገዥ አስተሳሰብ በአንድ ትውልድ የሚፋቅ አይደለም፡፡ ለረዥም ጊዜ ማንዣበቡ አልቀረም፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝቦች አምባገነናዊ ሥርዓት ታግለው ቢያስወግዱና የትግል ውጤታቸውን ማጣጣም ቢጀምሩም፣ ሕዝብ አሁንም ድረስ ያለው ግንዛቤ መንግሥት የሚቋቋመው ኅብረተሰቡን ለማገልገል ብቻ እንደሆነና ዝንፍ ሲል መቆጣጠርና ማስተካከል እንደሚችል በውል አልተገነዘበም፡፡ አፈናን በቀጣይነት ያለ መታገል አዝማሚያ ነው ያለው፡፡ መሸከም አቅቶት ወደ አመፅ እስኪያመራ ድረስ በሰላማዊና በቀጣይነት መብቶችን የማረጋገጥ ባህል ገና አልተገነባም፡፡ ገዥዎች በእንደዚህ ሁኔታ ሁሉም ነገር ሰላም እንደሆነ በመኩራራት ይዝናናሉ፡፡

Related stories   መከላከያ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ “ጁንታውን” ሙሉ በሙሉ መደምሰሱን አስታወቀ! በርካታ በቁጥጥር ስር ውለዋል

ወደ ዴሞክራሲ በሚደረገው ሽግግር በቁምነገራቸው (Essence) ያልነበሩ ወይም በተሟላ መንገድ የማይታወቁ ፖለቲካዊ ተቋማትን፣ የፖለቲካ ፓርቲዎችን፣ የሙያና የሲቪል ማኅበራትን እንደ አዲስ ማዋቀር ይጠይቃል፡፡ ሕገ መንግሥቱ ዴሞክራሲያዊ ቢሆንም ፖለቲካው እሱን የማያንፀባርቅ ከሆነ እንደ ግዑዝ ይቆጠራል፡፡ በዚህም ምክንያት ኦፊሴላዊ ሕገ መንግሥት (Official Constitution) እና ሕይወታዊ ሕገ መንግሥት (Living Constitution) ብለው ይመድቡታል፡፡ ሕገ መንግሥቱ ሕይወት የሚዘራው በፖለቲካው ነው ለማለት ነው፡፡

በዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ሕግ አውጭው፣ አስፈጻሚውና ሕግ ተርጓሚው፣ መገናኛ ብዙኃን፣ ፓርቲዎችና ማኅበራት በይዘታቸው ከአምባገነን ሥርዓት በመሠረቱ የተለዩ ናቸው፡፡ እነዚህ ልዩ እንክብካቤና ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው ጨቅላ (Infantile) ተቋማት ልክ እንደ ሕፃን ልጅ እየወደቁ፣ እየተነሱ፣ እሳትና ሌሎች አደጋዎች እንዳያጋጥማቸው መታደግና መንከባከብ ይጠይቃል፡፡ ተቃርኖው (Paradox) እነዚህ ተቋማት የሕዝቦች መብቶች ለማረጋገጥ የተዋቀሩ ሲሆኑ፣ ሕዝቦችን ደግሞ እነዚህ መዋቅሮች ሽባ እንዳይሆኑ መጠበቅ አለባቸው፡፡ በይዘታቸው አዲስ ስለሆነ ኅብረተሰቡ፣ የፖለቲካ ልሂቃን ጭምር በሚገባ የማይታወቅ በመሆኑ ላይና ታች፣ ወደ ኋላና ወደፊት መውጣቱና መንሸራተቱ አይቀርም፡፡ ከፖለቲካ ልሂቃንና ከኅብረተሰቡ የሚጠበቀው እነዚህ መዋቅሮች አንድ እግር ወደ ኋላ፣ ሁለት እግር ወደፊት በማለት አጠቃላይ ጉዞአቸው ግን ቀጣይ መሻሻል እንዲኖረው ማድረግ ነው፡፡ የዳበረ ፖለቲካዊ ሰብዕና፣ የድርጅት ልምድ ባለመኖሩና ልሂቃን ለራሳቸው ጥቅም ሲንገበገቡ ፖለቲካዊ ሙስናና ብሎም የገንዘብ/ንብረት ሙስና ይሰፋል፡፡

ሌላው ወደ ዴሞክራሲያዊ ጉዞ ለሚደረገው ሽግግር እንደ መዋቅራዊ ድክመት ከሚነሱት ጉዳዮች ውስጥ ዴሞክራሲን መሸከም የሚችሉ ባለሀብቶች፣ መካከለኛው መደብ (Middle Class) እና ላብአደሩ ገና ያላደጉና ኃላፊነታቸው መወጣት ስላልቻሉ፣ ዴሞክራሲያዊ ሊሆን የማይችል ኃይል የዴሞክራሲ ሞግዚት ሲሆን ነው፡፡ ሥርዓቱ ከፍተኛ መዋቅራዊ ድክመት የሚያንፀባርቀው አመፀኛው ትውልድ (በተቃዋሚውም በገዥው ፓርቲ) ያሉት ደረጃ ደረጃ ላይ ለተጠቀሱት ኃይሎች ማስረከብ ሲገባቸው፣ ‹‹ከእኛ በላይ ለአሳር›› ባለው ሥልጣኑን ሙጭጭ አድርገው ይዘዋል፡፡

ለ. እጅ ወደ አፍ (Subsistence) ኢኮኖሚ ወደ መካከለኛ ገቢ የሚደረግ ሽግግር

በኢኮኖሚያዊ ሽግግሩ መዋቅራዊ ድክመት ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓቱ ውጣ ውረድና ሙስናን ለመዋጋት እንቅፋት መሆኑ አልቀረም፡፡ በኢሕአዴግ የሚመራው መንግሥት ምሥጋና ይግባውና ከኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት በፊት ያውም በሰላምና መረጋጋት ችግር ውስጥ እያለ እስከ አምስት በመቶ ዕድገት፣ ከጦርነቱ በኋላም በዓለም ከፍተኛ ልማት የምናስመዘግብ አገር ሆነናል፡፡ እንዲቀጥልም ምኞታችን ነው፡፡ ብዙ ሀብት (Wealth) ተፈጥሮአል፡፡ እሰየው ነው፡፡ የሀብት ክፍፍሉ ግን መሠረታዊ መዋቅራዊ ጉድለት አለው፡፡ ፍትሐዊነቱ ላይ ብዙ ችግር ይታያል፡፡ በሀብታምና በደሃ መካከል ያለው ልዩነት መሆን ካለበት በላይ ሰፍቷል፡፡ ኃይለኛው በመንግሥት ሥልጣኑ ሆነ በገንዘብ የአንበሳው ድርሻ ይይዛል፡፡ ከላይ የተገለጹት ሕገ መንግሥታዊና ፖለቲካዊ ተቋማት ሽባ በሆኑበት ሁኔታ ለሙስና መስፋፋት ዕድሉ ይመቻቻል፡፡

ሌላው ለኢኮኖሚ ሽግግር ያለው መዋቅራዊ ድክመት ግብር ከመክፈል ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ለማንም መንግሥት የሕይወት ደም (Life Blood) ግብር ነው፡፡ በብድርና በዕርዳታ የሚመጣው ልማት በመጀመርያ አስፈላጊ ቢሆንም ጣጣው ግን አደገኛ ነው፡፡ እ.ኤ.አ. ኦገስት 12 ቀን 2017 ‹‹EPRDF’s Block›› ማስተማር፣ ማሻሻል፣ መቅጣት በሚል ርዕስ በ2008 ዓ.ም. የተሰበሰበው ግብር ከአገራዊ ጠቅላላ ዓመታዊ ምርት 13 በመቶ ብቻ እንደሆነ ይገልጻል፡፡ አያይዞም በማደግ ላይ ያሉ አገሮች ከ18 በመቶ እስከ 25 በመቶ ይሰበስባሉ ይላል፡፡ የእኛ በጣም አነስተኛ መሆኑን ለመግለጽ፡፡

ግብር ከፋይ ብቻ ነው መብቱን ለማረጋገጥ የሚችለው፡፡ ‹‹ግብር ከፋይ ነኝ›› ብሎ የሚኮራን ኅብረተሰብ የሚነቀንቀው የለም:: ግብር በታማኝነትና በፈቃደኝነት እንድንከፍል የሚያስገድደን አስተሳሰብ፣ ለዴሞክራሲያዊ መብቶቻችን ለመቆም የሚነዳን መሠረታዊ አስተሳሰብ ነው፡፡ ዴሞክራሲያችን በሁለት እግሩ መቆም ይጀምራል፡፡ ሙስናን ለመዋጋት መሠረታዊ ንጣፍ ያስቀምጣል፡፡ የውጭ ምንዛሪ መሠረቱ በአገር ውስጥ የሚመረቱ ምርቶችና አገልግሎት አለመሆናቸው ለሙስና ከፍተኛ በር ሊከፍት ይችላል፡፡ ተፈላጊውን ግብር ባለመክፈላችን የውጭ ምንዛሪ ግኝታችን በራሳችን አለመሆኑ፣ የራሳችን መንግሥት ተጠሪነቱ ለእኛ መሆኑ ቀርቶ ለውጭ መንግሥታትና ባለሀብቶች የመሆን አዝማሚያ ያሳያል፡፡ ማናቸውም ዕርዳታና ብድር ያለ ፖለቲካዊ ተፅዕኖ አይገኙም፣ በቀጥታ በተዘዋዋሪም፡፡

ከሌሎች አገሮች አንፃር ሲታይ የኢሕአዴግ መንግሥት በዋና ዋና ፖሊሲዎች ለምሳሌ መሬት፣ ባንክ፣ ኢንሹራንስ፣ ቴሌ፣ ወዘተ. ፕራይቬታይዜሽን እስካሁን ድረስ የውጭ ተፅዕኖን ተቋቁሟል፡፡ እሰየው የሚያሰኝ ነው፡፡ ከሕዝቦች መብት አንፃር ግን ጆሮው ወደ ውጭ ያቀናል፡፡ ሕዝቦች ‹መብታችን እየተነጠቀ ነው፣ በመልካም አስተዳደር ዕጦት እየተለበለብን ነው› ብለው ሲጮሁ የሚሰማቸው የለም፡፡ መንግሥት መስማት የተሳነው ሆኗል፡፡ እነዚያ ሊዮ ሊበራል የሚላቸው የውጭ ተቋማትና ሚዲያዎች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ ጉዳዮችን ሲያነሱ ከመቅፅበት ሰምቶ ይወራጫል፣ መልስም ይሰጣል፡፡ የአገር ገጽታ እንዳይበላሽ በሚል፡፡ ግን የገዥው ፓርቲ ገጽታ እንዳይበላሽ ነው፡፡

በ1997 ዓ.ም. ምርጫ ገዥው ፓርቲ በውጭ ኃይሎች ግፊትና በሕዝቡ ላይ የነበረው የተሳሳተ ግምት ‹እንከን የለሽ ምርጫ› አደርጋለሁ አለ፡፡ ዓላማው ለውጭ ኃይሎች በኢኮኖሚ ብቻ ሳይሆን በዴሞክራሲያዊ ግንባታ ሞዴል ነን፣ እንከን የሌለን ነን ለማለት ነበር የታሰበው፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ መብቶቹን ተጠቅሞ የፈለገውን ይምረጥ የሚል ይመስል ነበር፡፡ እርግጥም ተቃዋሚ ፓርቲዎች በተነፃፃሪ ነፃነት የሚንቀሳቀሱበት፣ የመንግሥት ሚዲያም በተነፃፃሪ ፍትሐዊ ሥርጭት የነበረበት፣ የግሉ ሚዲያም በተሻለ የዘገባበት፣ የሲቪል ማኅበራትም በስፋት የተሳተፉበት ነበር፡፡ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ያልተጠበቀ ውጤት ሲያገኙና ኢሕአዴግ ባላሰበው ሲሸነፍ ተወራጨና እውነተኛው ባህሪውን አጋለጠ፡፡ ተጠሪነቱ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ቢሆን ኖሮ ውጤቱ በፀጋ ተቀብሎ ዴሞክራሲያዊ ምኅዳሩን በቀጣይነት ያሰፋ ነበር፡፡ የሆነው ግን ተፃራሪ ነው፡፡ በምርጫ 2002 ደግሞ 96 በመቶ አሸነፍኩ አለ፡፡ በ2007 ዓ.ም. ምርጫ ደግሞ መቶ በመቶ አሸናፊ ሆነ እርፍ አለ፡፡ ብዝኃነት-Diversity, ኢትዮጵያ ውስጥ እንደሌለ ሁሉ፡፡

ኢሕአዴግ ልክ እንደ የኮሪያው ጄኔራል ፓርክ አምባገነናዊ በሆነ መንገድ ልማት አመጣሁልህ ብሎ እየተጋ ይገኛል፡፡ ቀጣይነቱ አጠራጣሪ ቢሆንም፡፡ ኮሪያና ኢትዮጵያ ግን የተለያዩ አገሮችና በተለያየ ዐውድ (Context) የሚገኙ ናቸው፡፡

ኢትዮጵያ የነፃነት አገር ናት፡፡ ሕዝቦቿ ፍትሕና ዴሞክራሲ በመሻት አምባገነንነትን ታግለው ባሸነፉበት መንግሥት በሚካሄድ ልማት ውስጥ ነው የምትገኘው፡፡ በብዙ ብሔርና ብሔረሰብ ያሸበረቀችና ከቀዝቃዛው ጦርነት በኋላ ልማትዋን ለማፋጠን የምትተጋ አገር ነች፡፡ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ ነፃነትዋን የተጎናፀፈችው ኮሪያ ሕዝቧ 96 በመቶ የአንድ ብሔር ነው፡፡ ለዕድገቷ መሠረት በቀዝቃዛው ጦርነት የምዕራቡ ዓለም በተለይ የአሜሪካ ሙሉ ተሳትፎ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ ልማትና ዴሞክራሲ ተነጣጥለው የሚታዩ አይደሉም፡፡

መንግሥት በእኛ ግብር የማይተዳደር ከሆነ፣ የውጭ ምንዛሪ ግኝቱ በአብዛኛው ከውጭ ከሆነ እኛ የምንቆጣጠረው መንግሥት አይሆንም፡፡ ስለሕግ የበላይነት፣ ተጠያቂነትና ግልጽነት ግድ የሌለው ብቻ ሳይሆን፣ ሆን ብሎ የሚጥስ መንግሥት ሊሆን ይችላል፡፡ በእዲህ ሁኔታ በሙስና መዘፈቅ የሥርዓቱ መገለጫ ይሆናል፡፡

ሐ. የኅብረተሰባችን መዋቅራዊ እሴቶችና ሙስናን ለመዋጋት ያለው ዕድል (Opportunity)

ሙስና ጥቂትን ሰዎችን ብቻ የሚጠቅም አብዛኛውን ሕዝብ ሰላም፣ ልማትና ዴሞክራሲ በማሳጣት ኅብረተሰቡን በቀጣይነት የሚጎዳ ክፉኛ ካንሰር ነው፡፡ በኅብረተሰብ ውስጥ ያሉ ኋላ ቀር አስተሳሰቦችን በተወሰነ ደረጃ የመሸከም አዝማሚያ ቢኖርም፣ በመዋቅራዊ ጥቅም ግን ሙሰኞችና ሕዝቦች በመሠረቱ የተለያየ አሠላለፍ ነው የሚኖራቸው፡፡ ሕዝቦች እስከገባቸው ድረስ ለፀረ ሙስና ትግል ይቆማሉ፡፡ ለሙሰኞች ግን የማንነታቸው መገለጫ ነው፡፡

በኢትዮጵያ አገር ምሥረታ ሒደት፣ በሃይማኖታዊና በባህላዊ ማንነት ምክንያት ሙስናን ለመዋጋት የሚያስችል ዕምቅ አቅም ያለው ሕዝብ ነው፡፡ አገር ወዳድነት (ለሕይወት መስዋዕትነት ዝግጁ መሆን)፣ እርስ በርስ መረዳዳት፣ ሌብነትንና ክፉ ድርጊቶችን መጥላትና ለሕግ ተገዥነት የመሳሰሉት እሴቶች ከሌሎች ከላይ ከተገለጹ ድክመቶች ጎን ለጎን የሚኖሩ ናቸው፡፡ አፈርና ወርቅ በአንድ ላይ በአንድ አካባቢ እንደሚኖሩ ሁሉ፡፡ መንግሥት በሌለበት ወይም መቆጣጠር በተሳነው በ1966 ዓ.ም.፣ በ1983 ዓ.ም. እና በ1997 ዓ.ም. ያሳየው የሌሎችን ገንዘብና ንብረት በመሠረቱ ያለመንካት የሕዝባችን እሴቶች መለኪያ ናቸው፡፡ ከማቴሪያል ጥቅምና ከባህላዊ እሴቶች መዳበር አንፃር ለፀረ ሙስና ትግል ሊሠለፍ የተዘጋጀ ሕዝብ ነው፡፡ የልሂቃን ግዳጅ (Task) ነው የሚጎድለው፡፡

ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማትን የምንደግፈውና የምናደንቀው አሳፋሪ የሆነውን ድህነትን ስለሚቀርፍ ብቻ አይደለም፡፡ ለዴሞክራሲ መሠረት ስለሚሆን ጭምር ነው፡፡

Huntington (1991: 316) “Economic Development Makes Democracy Possible Political Leadership Makes It Real” ይላል በዚህ መጽሐፍ በገጽ 311 ደግሞ፣ “Obstacles to Economic Development Are Obstacles to the Expansion of Democracy.”

ኢሕአዴግ እያሳየ ያለውን የአምባገነንነት ፖለቲካ መታገል ተገቢ ሆኖ ሳለ በኢሕአዴግ ላይ ባለ ጥላቻ ኢኮኖሚው እንዲወድቅ መንቀሳቀስ ግን፣ ላይ የገለጽናቸው መዋቅራዊ ግድፈቶች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ማድረግ ማለት ነው፡፡ ሕዝቡ በድህነት እንዲማቅቅ ማድረግ ነው፡፡ በሕዝብ መቀለድና ፀረ ኢትዮጵያ አቋም ነው፡፡

የአገሪቱ ኢኮኖሚ በከፍተኛ ደረጃ አደገ ማለት መላው ሕዝብ ተጠቃሚ ሆነ ብቻ ሳይሆን፣ ዴሞክራሲን በማስፋት ዕድገቱን የሚያቀጣጥሉ ባለሀብቶች፣ መካከለኛው መደብና ላብአደሩ በከተማም በገጠርም እየተፈጠረ ነው ማለት ነው፡፡ እናት ውኃ ለመቅዳት በየቀኑ ከሦስት ሰዓት በላይ የምትኳትንበት፣ እንጨት ለቀማ ሙሉ ቀን የምታጠፋበት፣ አንዱን ልጅዋን ለማሳከም ሌሎች ልጆቿን በትና ከተማ የምትንከራተትበት ሁኔታ ሲቀረፍ ለፖለቲካዊ መረጋጋት ያለው ትርጉም ከፍተኛ ነው፡፡ ለመብት የምትታገል ጀግና እናት እንድትሆን ያመቻቻል፡፡

በየዓመቱ ከአንድ መቶ ሺሕ በላይ ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት፣ ከዚያ ቁጥር በላይ ከሁለተኛ ደረጃ ተመረቁ ማለት (የጥራት ችግር እንዳለ ሆኖ)፣ በዚያ ላይ መገናኛ ትራንስፖርት ተስፋፋ ሲባል አምባገነንነት ብሎም ሙስናን ለመታገል ምቹ ሁኔታ እየተፈጠረ ነው፡፡ ወጣቱ በጥቃቅንና አነስተኛ ሲደራጅ፣ የተሳካለት መካከለኛ ባለሀብት ሲሆን፣ ወዘተ. ከኢኮኖሚ ጠቀሜታ ባሻገር ለዴሞክራሲ ሒደቱ ወሳኝ አመልካች ነው፡፡ የኢሕአዴግ መንግሥት ለማኅበራዊ ሚዲያ እንኳን እስከምን ድረስ እንደሚርበተበት የምናውቀው ነው፡፡ ኢሕአዴግ ከሁኔታው ጋር ለመሄድ ራሱን ከመሠረቱ መቀየርና ዴሞክራሴያዊ መሆን፣ ወይም ራሱ በፈጠረው ሁኔታ ወደ መቃብሩ የሚገባ ይሆናል፡፡ በአጠቃላይ ሲታይ ሙስናን ለመታገል መዋቅራዊ ድክመቶች እንዳሉ ሁሉ፣ መዋቅራዊ እሴቶችም ጎን ለጎን የሚኖሩ ናቸው፡፡ ሙስና የማያድግበት ተግዳሮት፣ በሌላ በኩል ሙስና የሚቀጥልበት ዕድል እናያለን፡፡ የሚቀረው የልሂቃን አዎንታዊ ሚና ነው፡፡

  1. የሙስና አጠቃላይ ሁኔታ
Related stories   ብርሃኑ ነጋ አቋማቸውን ቀየሩ፤ ኢዜማ ደርግ በግፍ የዘረፈውን የግል ሃብት ለተከራይ እንደሚሸጥ ይፋ አደረገ፤ የኢዜማ የ ” ፍትህ” ሩጫ

አሁን ስላለው ሙስና ከአንድ ወዳጄ ጋር ያደረግነውን ምልልስ እስኪ ላካፍላችሁ፡፡ ወዳጄ አሁን ያለው የሙስና ደረጃ በወታደራዊ አገዛዝም ሆነ በአፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመን ታይቶ አይታወቅም አለኝ፡፡ ፖለቲካዊ ሙስና ነው? ወይስ የገንዘብ/ንብረት ሙስና? ብዬ ጠየቅኩት፡፡ በሁለቱም በኩል በሚዛን የሚገናኝ አይደለም አለኝ፡፡ የፖለቲካ ሙስና ከሆነ ለማወዳደር አስቸጋሪ ይመስለኛል፡፡ ሥዩመ እግዚአብሔር መሠረቱ የሆነ ሥርዓትና ኢዴሞክራሲያዊ ሕገ መንግሥት ያለው አምባገነናዊ መንግሥት ከኢሕአዴግ መንግሥት ጋር በምን መመዘኛ ሊገናኙ አይችሉም፡፡ ኢፍትሐዊ የሆነ ጦርነት ከሚያካሄድ ሥርዓት በላይ ፖለቲካዊ ሙስና የለም፡፡ በደርግ ጊዜ በጦርነቱም ሆነ በቀይ ሽብር የጠፋው የሰው ሕይወት ብቻ ሳይሆን አንድ ትውልድ ነው፡፡ ያውም ማን እንደገደለው፣ ለምን እንደተገደለና የት እንደተቀበረ የማይታወቅ ትውልድ የወደመው ንብረትም ምን ያህል ሊሆን እንደሚችል መገመት የሚያስቸግር አይመስለኝም፡፡ የሰው ሀብትና ንብረት በከፍተኛ ደረጃ በማይታመን ደረጃ ያጠፋ ሥርዓት ነው፡፡

የፖለቲካዊ ሙስና ልዩነት በ1966፣ በ1977፣ በ2008 ዓ.ም. ያጋጠመውን ድርቅ ለመደበቅና ለመፍታት የተደረገውን እንቅስቃሴ መመዘን ነው፡፡ የንጉሠ ነገሥቱ 80ኛ ዓመት ልደት እንዳይቆሽሽ፣ የሠሰፓ ምሥረታ በዓል እንዳይጎድፍ የወሎና የትግራይ ረሃብ ተደበቀ ብዙ ሰው አለቀ፡፡ ከዚህ በላይ የሚሰቀጥጥ ሙስና የለም አልኩት፡፡ አሁን ያለውን ፖለቲካዊ ሙስና የከፋ ነው የምለው ካለፈው ጋር በማወዳደር ሳይሆን መሆን ካለበት ነው፡፡ የገንዘብ/ንብረት ሙስና ቢሆንም ለማወዳደር አስቸጋሪ ነው፡፡ ምክንያቱም ያለፉት ሥርዓቶች ድህነትን ኢፍትሐዊ በሆነ መንገድ ያካፍሉ ነበር፡፡ ከደሃው መዘንጠል ነው የነበረው፡፡ አሁን ከፍተኛ ሀብት ተፈጥሮ በቢሊዮኖች መዝረፍ ተጀመረ፡፡ ከአሥር ብር አንድ ብር መውሰድና ከአንድ ብር አምሳ ሳንቲም እንደ መውሰድ ነው፡፡ 10 በመቶና 50 በመቶ፡፡ በእነዚያ ሥርዓቶች የኢትዮጵያ ጠቅላላ ዓመታዊ ምርትና የዓመት በጀት አሁን ካሉት አንዳንድ ክልሎች ያነሰ እንደነበረ ማስተዋሉም አስፈላጊ ነው አልኩት፡፡ በደርግ ጊዜ ለሞት የላካቸውን ወታደሮች ስንቅ፣ ትጥቅና ደመወዝ የሚዘርፉ ጄኔራሎች ነበሩ፡፡ ይህንን ዘግናኝ ድርጊት የፈጸሙት ብዙዎች ላይሆኑ ይችላሉ ግን ምንም ዕርምጃ አልተወሰደም፡፡

በ77 ቢሊዮን ብር ደረጃ እኮ ነው በግልጽ በፓርላማ የሰማነው ካለኝ በኋላ፣ ሰዓቱን አየና ቀጠሮ ስለነበረው ሌላ ጊዜ እንወያይበት ተባብለን ተለያየን፡፡

በቅርቡ በጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ክስ በጥርጣሬ ከታሰሩት የመንግሥት ባለሥልጣናት፣ ባለሀብቶችና ደላሎች በቢልዮን የሚቆጠር ሀብት እንደተመዘበረ ተገልጿል፡፡ በአንዳንድ ተንታኞች አስተሳሰብ አለ የተባለው ሙስና የአጠቃላይ ሁኔታ ምልክት ወይም ጫፍ (The tip of the Iceburg) ነው፡፡ መንግሥት ቁርጠኛ ከሆነ በሙስና የጠፋው ሀብት እጅግ ከፍተኛ ሊሆን እንደሚችል ይገልጻሉ፡፡ ችግሩ ግን ላይ ብቻ የተንጠለጠለ ሳይሆን፣ በሁሉም የሥርዓቱ መዋቅሮች ከቀበሌ እስከ ፌዴራል ከጥበቃ እስከ ላይ ድረስ እንደ ካንሰር የተስፋፋ መሆኑ ነው፡፡ የ‹‹ሻይ›› ሳይባል ማናቸውንም አገልግሎቶች ለማግኘት አስቸጋሪ እንደሆነ ይገልጻሉ፡፡

መቶ በመቶ አሸናፊነት የፖለቲካዊ ሙስና ከፍተኛው ጫፍ አያስቀናም!!

በአንጎላ በቅርብ ጊዜ በተደረገው ምርጫ ገዥው ፓርቲ 61.1 በመቶ፣ ተቃዋሚው 26.7 በመቶ፡፡ ለፓርላማ ገዥው ፓርቲ ከ220 መቀመጫዎች 150 አግኝቷል፡፡ በኬንያ ተመራጩ ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ 54.2 በመቶ ሲያገኙ፣ የቅርብ ተቀናቃኙ ራይላ ኦዲንጋ 44 በመቶ የሕዝብ ድምፅ አገኙ፡፡ በዚህ ምርጫ ከ47 የካውንቲ (County) ገዢዎች 22 ያህሉ ቦታቸውን በምርጫ አጥተወል፡፡ ምርጫ ሁሉም ነገር ባይሆንም የፍትሐዊነትና የቅቡልነት ጥያቄዎች ቢኖርበትም፣ የአስተሳሰብና የብሔር ብዝኃነት ያንፀባርቃል፡፡ የእኛ መቶ በመቶ ምን ይባላል?

አንድ ቢሊዮን ወይም አሥር ቢሊየን ብር ከተመዘበረ እጅግ ከፍተኛ ሙስና ነው፡፡  ከደሃው መንጋጋ የሚወሰድ ብዙ አደጋ ሊያደርስ የሚችል ነው፡፡ መቶ በመቶ አሸናፊነት ግን ምናልባት ቢያንስ ከ40 እስከ 50 ሚሊዮን ሕዝብ ልብና መንፈስ የሰረቀ ነው፡፡ በግንቦት 2007 ዓ.ም. በተካሄደው ምርጫ ኢሕአዴግ መቶ በመቶ አሸነፍኩ አለ፡፡ ምርጫ ቦርድም አጨበጨበ፡፡

በመስከረም 2008 ዓ.ም. ያ አሸናፊነት ‹‹አስቂኝም አደገኛም›› ነው ብዬ ጽፌ ነበር፡፡ አደገኛነቱ በኅብረተሰቡ ውስጥ የነበረውን መንፈስ ስለሚያንፀባርቅ ነው፡፡ የታፈነ ሕዝብ በተለይ ወጣቱ ወደሌላ አቅጣጫ ወደ አመፅ ሊወስደው እንደሚችል በመገመት ነው፡፡ ቢያሳዝንም የሆነው ነገር እሱ ነበር፡፡ ስድስት ወራት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ በኦሮሚያ፣ በአማራ የተወሰኑ አካባቢዎችና በደቡብ ክልል አመፅ ተነስቶ ‹‹የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ›› እስኪታወጀ ድረስ ቀጠለ፡፡ ግን ለምን? ከመጀመርያ ሊገመት የሚቻል የነበረ ቢሆንም ወደ ኋላ ተመልሶ ቢተነተን (Counter Factual Analysis)፣ ምርጫው በየደረጃው የሕዝብን ፍላጎትና ስሜት የሚያንፀባርቅ ቢሆን ኖሮ ወይም በየደረጃው ባሉ ምክር ቤቶች (እስከ ወረዳ/ቀበሌ) ኢሕአዴግ 60 በመቶ፣ ተቃዋሚዎች 40 በመቶ ቢያገኙ ይህ አመፅ በአጭር ወራት ሊከሰት ይችል ነበር ወይ? መሠረታዊ መፍትሔ እንኳን ባያመጣ የተወሰነ የ‹‹ዕፎይታ›› ጊዜ አይሰጥም ነበር ወይ? ከምርጫው በኋላ ተከታትሎ ዓመፅ መነሳቱ እየተከማቸ የመጣውን ብሶት አቀጣጠለው እንዴ? አቀጣጣይ ነዳጁ ምርጫው ፍትሐዊና ቅቡልነት የለውም የሚል አመለካከት (Perception) ነበር ማለት ነው ወይ? የሚሉ ጉዳዮች ሊነሱ ይችላሉ፡፡

የምርጫው ሒደት ሲታይ ሕዝቡ የፈለገውን እንዳይመርጥ፣ የአመለካከትና ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት፣ የመሰብሰብ፣ ሰላማዊ ሠልፍ የማድረግ ነፃነት ገደብ በነበረበትና የመደራጀት መብትና የመዘዋወር ነፃነት አሜከላ በነበረበት ሁኔታ ነው፡፡ ከሁሉም በላይ አማራጭ ሐሳቦችን የማግኘት የሕዝብ መብት ያልተረጋገጠበት ነበር፡፡ የመንግሥት መገናኛ ብዙኃን መንግሥትና ኢሕአዴግ አንድ እንደሆነ አድርገው ሲቀሰቅሱ የሕዝቡን ምሬት እያፈኑ፣ የገዥውን ፓርቲ ትልቅነት ሲያወድሱ፣ ተቃዋሚዎችን እያገለሉና እያብጠለጠሉ የተገኘ መቶ ውጤት በመቶ ነው፡፡ የሕዝቦችን መብት ለማፈን፣ ተቃዋሚዎችን ለማጉላላትና በሕግ የተቀመጠለትን ሥራ ለማከናወን ከበጀቱ ቢሰላ ስንትና ስንት ይሆናል ኢሕአዴግን ለመደገፍ የጠፋው? ለመንግሥት መገናኛ ብዙኃን የኢትዮጵያ ሕዝብ፣ መንግሥትና ኢሕአዴግ አንድና አንድ ስለሆነ ማስላቱ ያስቸግራቸዋል፡፡ ሕዝቡ አማራጭ ሐሳቦች እንዳያገኝና በተለያየ መንገድ ግዳጁን እንዳይወጣ የግል ሚዲያው ታፈነ፡፡ ከሁሉም በላይ መቶ በመቶ ሲያሸንፍ እንደ መደንገጥና እንደማፈር ገዥው ፓርቲ በአሸናፊነት ጉልበት ሲንፈላሰስ መታየቱ አስገራሚ ነው፡፡ የምርጫ ቦርድ ገለልተኝነት አጠያያቂ በሆነበት ሁኔታ የቦርዱ ኃላፉ ገና ከቦርዱ ሳይሰናብቱ የአምባሳደርነት ‹ፖለቲካዊ› ሹመት መስጠት፣ ትዕቢቱንና ካለፈው የተማረ እንዳልሆነ የሚያሳይ ነው፡፡

ፖለቲካዊ ሙስና ሁለት ዓይነት ዜግነት እንዲኖር ያደረጋል

ከላይ እስከ ታች ያሉት ከስድስት እስከ ሰባት ሚሊዮን የሚደርሱ የኢሕአዴግ አባላት ያላቸው ሙሉ ጥቅም ምርጥ ዜጎች ያደርጋቸዋል፡፡ 90 ሚሊዮን የሚሆነው ሕዝብ ደግሞ ተራ ዜጋ፡፡ በሄደበት ሁለተኛ ዜጋ እንደሆነ በተግባር የሚገለጽለት ተራ ዜጋ! ከፌዴራል እስከ ቀበሌ በሁሉም የመንግሥት አካላት የኢሕአዴግ አባላት ከተመረጡ በኋላ፣ የቀረውም የገዥው ግንባር አባል ባይሆንም ለኢሕአዴግ ያለው አመለካከት መመዘኛ ይሆናል፡፡ በግሉ ተቃዋሚ ወይም የተቃዋሚ ድርጅት አባል ከሆነማ በጭራሽ አይታሰብም፡፡ ተራ ዜጋ ይሆናል፡፡ የኢሕአዴግ አባል ዋስትና ያለው ሥራ፣ ከአቅሙ በላይ ሥልጣንና ደመወዝም ያገኛል፡፡ ሁሉም አገልግሎት ቅድሚያ የሚሰጠው ልዩ ፍጡር፡፡ በኢሕአዴግ ተደራጅተህ እስከመጣህና የገዥውን ፓርቲ እስከ ደገፍህና ለሥርዓቱ ምቹ እስከሆንክ ድረስ፣ ካለህ አቅም ይልቅ ያለህ ፖለቲካዊ አመለካከት ስለሚመዘን ሥርዓቱ

አቅም ያላቸውን ሰዎች ያገለለ ሲሆን፣ በየዩኒቨርሲቲው ያሉ ተማሪዎች ከአቅማቸው ይልቅ ለፓርቲ አባልነት የተለየ ጥቅም እንዳለው እንዲያስቡ ተደርገዋል፡፡ በዚህ ምክንያት በራስ መተማመን ከዕውቀት ጋር ሰንቀው የሚወጡባቸው ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የዕውቀት ማዕከል ከመሆን ይልቅ፣ የፓርቲ አባላት የሚመለመሉበት ፖለቲካዊ ማዕከል ወደ መሆን አዝማሚያ ማምራታቸው በመማር ማስተማር ሒደቱ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ  አሳድሯል፡፡ ከላይ በተፈጠረው ሁኔታ ያለፉ ወጣቶችም ሆነ ሥርዓቱ በፓርቲና በመንግሥት መካከል ያለው ልዩነት የማይታወቅና ሁሉን አካታች የሆነ ዕይታ እንዲፈጠር አድርጓል፡፡

የመከላከያ ሠራዊታችን ‹‹ የአብዮታዊ ዴሞክራሲ ብሎም የኢሕአዴግ የመጨረሻ ምሽግ ነው›› ሲባል ትዕቢት የተላበሰ ፖለቲካዊ ሙስና አይደለም ወይ? እንኳን ሕዝቡ የኢሕአዴግ አባላት አብዮታዊ ዴሞክራሲ ምን እንደሆነ በማያውቅበት ሁኔታ (ከፍተኛ ባለሥልጣናት ይጨምራል) እንዴት ነው የአገር መከላከያ ሠራዊት የዚያ አይዲዮሎጂ ምሽግ የሚባለው? 50 ሚሊዮን የአብዮታዊ ዴሞክራሲን ምንነት አውቆና አምኖበት ቢሆንም እንኳን፣ 50 ሚሊዮን የሚሆነው ሕዝብ የመከላከያ ከለላ የለውም ማለት ነው? ምርጥ ዜጋ (ስድስት ሚሊዮን አባል) ኢሕአዴግ የሚከላከልለት፣ ሌላው 90 ሚሊዮን የሚሆን በመሀል ይኖራል ማለት ነው? አግላይ ሙስና ግን እዚያ አይቆምም፡፡ ከኢሕአዴግ ምርጥ ይኖራሉ፡፡ በተለይ የፓርቲ ክፍፍል በሚኖርበት ሁኔታ ሠራዊቱ የየትኛው አንጃ ምሽግ ይሆናል?

  1. ሙስናና የተቋሞቻችን መልፈስፈስ

ገዢው ግንባርና መንግሥት አንድና አንድ ናቸው የሚል አስተሳሰብ ባለበት ሁኔታ፣ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ከሕግ አግባብ ውጪ ኢሕአዴግን ማገልገላቸው አይቀርም፡፡ እኩል መወዳደሪያ ሜዳ (Space) በሌለበት ሁኔታ ተቃዋሚዎች እየተዳከሙ ለመሄዳቸው አንዱ ምክንያት የመንግሥት ሀብት ከሚጠቀም ግንባር ሥር ይሸጎጣሉ፣ ወይም ተጠሪነታቸው ከዚህም ከዚያም ሀብት ለሚያሰባስበው ፅንፈኛ ዳያስፖራ ይሆናል፡፡

Related stories   “ዶላር እናወርዳለን” የውጭ አገር ዜጎችን የዝርፊያ ድራማ ፖሊስ አለሳልሶ ይፋ አደረገው

በ2009 ዓ.ም. በነበረው የመንግሥት አወቃቀር ‹‹የዴሞክራሲ ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት›› ተቋቋመ፡፡ እሰየው አልን፡፡ የዴሞክራሲ ችግሮች ዙሪያ መፍትሔ ለማምጣት የተዋቀረ ነው በሚል እሳቤ፡፡ ይህ ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት በመላ አገሪቱ ሁሉንም አስተሳሰቦች፣ ሁሉንም ፓርቲዎችና የሲቪልና የሙያ ማኅበራት በእኩልነትና ፍትሐዊ በሆነ መንገድ ለማስተናገድ ታስቦ ነው በሚል ተስፋ፡፡ በዚያን ጊዜ በነበረው ወጣ ያለ ምሁራንን ለማሳተፍ በተደረገው በጎ ሙከራ መሠረት፣ ለማስተባበሪያው ብቃታቸውና ማንነታቸውን (Integrity) ያስመሰከሩ የፖለቲካ ሳይንቲስቶች፣ የሕገ መንግሥት ባለሙያዎች፣ ሶሶሎጂስቶች ወዘተ. ይመደባሉ ብለን ጠብቀን ነበረ፡፡ የሆነው ግን ያለ ‹‹ኢሕአዴግ መስመር ሁሉም የጥፋት መንገድ ነው›› ብሎ የሚያምን ተቋም ማለት በኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ጽሕፈት ቤት ሆነ (የግል አቋማቸውን ባናውቅም)፡፡ በትምህርት ምዘና ሲታይ ከላይ የተጠቀሰውን መሥፈርት የሚያሟሉ ናቸው፡፡

አብዛኛዎቹ ባለሥልጣናት ሁለት ባርኔጣ አላቸው፡፡ ለምሳሌ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ የኢሕአዴግ ሊቀመንበርነትና የጠቅላይ ሚኒስትርነት ባርኔጣ አላቸው፡፡ በመንግሥት የሥራ ጊዜ የጠቅላይ ሚኒስትር ባርኔጣ በማድረግ ብቻ ይሠራሉ ተብለው ይጠበቃሉ፡፡ በምርጫ ጊዜ ካልሆነ በስተቀር፡፡ የኢሕአዴግ ሊቀመንበርነት ባርኔጣ ማጥለቅ ያለባቸው ከመንግሥት የሥራ ሰዓት ውጪ መሆን ይገባዋል፡፡ የኢሕአዴግ ጽሕፈት ቤት ኃላፊና የዴሞክራሲያዊ ማስተባበሪያ ኃላፊ ግን የጥቅም ግጭት (Conflict of Interest) የሚታይበት ከመሆን በላይ፣ በትርፍ ጊዜ የሚሠራ ሥራ አይደለም፡፡ ስለዚህ በማናቸውም ጊዜ ሁለቱን ባርኔጣዎች እንዲያጠልቁ ይገደዳሉ፡፡ የኢሕአዴግ ጽሕፈት ቤት ሥራ በመንግሥት በሥራ ሰዓት ጭምር ይሠራል ማለት ነው፡፡ አራት በሚኒስትር ደረጃ ከፍተኛ አመራሮች ያሉበት የኢሕአዴግ ጽሕፈት ቤት በማን በጀት ነው የሚተዳደረው? የለየለት የገንዘብ/ንብረት ሙስና አይደለም እንዴ?

በቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ስም የተሰየመው አካዳሚ ተቋቁሞ በሥራ ላይ ይገኛል፡፡ አስፈላጊ ነው እንላለን፡፡ እዚያ አካዳሚ የሚሠለጥነው ማን ነው? የሥልጠና ማቴሪያሎች ምንድናቸው? ብለህ ስትጠይቅ ግን እዚህም ሙስና ይሸታል፡፡ ሠልጣኙ የኢሕአዴግ ካድሬ፡፡ የአብዮታዊ ዴሞክራሲ ታሪካዊ አመጣጥና ድርጅት ግንባታ የሥልጠናው ማጠንጠኛ ሲሆን፣ እንዴት በመንግሥት በጀት፣ ጊዜ፣ ወዘተ. የአንድ ፓርቲ አይዲዮሎጂ ማስፋፊያ ይሆናል? ‹‹Power Corrupts፣ Absolute Power Corrupts Absolutely›› (Lord Akton) በሥራ አስፈጻሚ አምባገነንነት የሚገለጽ የበላይነት መኖሩን ኅብረተሰቡ የሚያውቀው እንኳን ቢሆን፣ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሐፈት ቤት ሥር የሚገኘው ‹‹የፖሊሲ ጥናት ማዕከል›› ባደረገው ሰፊ ጥናት፣ በኅብረተሰቡ የሚታወቀው ጉዳይ ማስረጃ ታክሎበት ተረጋግጧል፡፡ የሕግ አስፈጻሚው ፍፁም የበላይነት!

በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 50/3 መሠረት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፌዴራል መንግሥት ከፍተኛ የሥልጣን አካል ነው፡፡ የክልሎችንም በተመሳሳይ መንገድ አንቀጽ 55 ለሕዝብ ተወካዮች ሰፋ ያለ ሥልጣንና ተግባር የሰጠ ሲሆን፣ በአንቀጽ 72/2 መሠረት ጠቅላይ ሚኒትሩና ካቢኔያቸው ተጠሪነታቸው ለተወካዮች ምክር ቤት ነው፡፡ ይህ ሁሉ ሥልጣን የተሰጠው ምክር ቤት ሥልጣኑን አሳልፎ ሲሰጥ የቁጥጥሩ (Check and Balance) ይጠፋል፡፡ ሙስና እንዲስፋፋ መሠረት ይሆናል፡፡ እንደሚታወቀው ባለፉት 22 ዓመታት የተወካዮች ምክር ቤት አንድም ቀን የቀረቡለትን ሕጎች፣ የሚኒስትሮችና የዳኞች ሹመት መሠረታዊ ለውጥ የሚያመጣ መሻሻል አድርጎ ሲመልስው ወይም ሕግና ሹመት (Reject) አድርጎ ሲመልስ አላየንም፡፡ በየጊዜው ሚኒስትሮችና ኮሚሽነሮች ሪፖርት ሲያደርጉ ከዚያ ተነስቶ የአቅጣጫ ለውጥ በሚያመጣ መልክ ሲቀጣጠር አላየንም፡፡ በዋና ኦዲተር የብዙ መቶ ሚሊዮን ብሮች ጉድለትና የአሠራር ዝርክርክነት ሲቀርብለት እንኳ፣ ተመጣጣኝ ዕርምጃ ወስዶ መሠረታዊ ለውጥ ለማምጣት አልቻለም፡፡

የስኳር ኮርፖሬሽን 77 ቢሊዮን ብር በጀት አስመልክቶ ከሜቴክ ጋር የነበረው ግንኙነት የቀረበውን ሪፖርትና የተወካዮች ምክር ቤትን ግብረ መልስ ስናይ፣ እስከምን ድረስ ሽባ መሆኑን ያሳያል፡፡ ያውም የ77 ቢሊዮን ብር ጉዳይ! ታዲያ ምክር ቤቱ አጣርቶና ሪፖርቱ ትክክል ካለሆነ አስተካክሎ፣ እውነት ከሆን ተመጣጣኝ ዕርምጃ ይወስዳል፣ ለሕዝብም በግልጽ ሪፖርት ያደርጋል ሲባል ይባስ ብሎ አንዳንድ ፋብሪካዎችን በመጎብኘት የምክር ቤቱ አባላት ለሜቴክ አድናቆታቸውን ሲገልጹ ታይተዋል፡፡ ከሁሉም በላይ ‹‹ሜቴክ ያሸማቅቀናል፣ ምንም ማድረግ እንደማንችል ታውቃላችሁ›› ሲባሉ ፖለቲካዊ አንድምታ አልገባቸውም፣ አልያም ፈርተው ትተውታል ማለት ነው፡፡ በተከበረው ምክር ቤት ፊት አንድ ኮርፖሬሽን ምንም ማድረግ እንደማንችል ታውቃላችሁ ማለቱ እንኳ ለምክር ቤቱ ትልቅ ስድብ ነው፡፡ አንዱ ኮርፖሬሽን ሌላውን ኮርፖሬሽን እንደፈለገው እያደረገ ነው የሚል ሪፖርት ሲቀርብ፣ እናንተም ምንም ማድረግ አትችሉም የሚል አንድምታ ይኖረዋል ብለው በቁጣና በእልህ ይነሳሳሉ ሲባሉ ዝምታ፡፡

ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ የስኳር ኮርፖሬሽን ሪፖርት ከተሰማ በኋላ ምን አደረገ? የሙስና ሸታ የለውም? ወይስ ትንሽ ነው ብሎ ተወው? ወይም ደግሞ የሚያሸማቅቅ ሁኔታ አለ? ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ተጠሪነቱ ለተወካዮች ምክር ቤት መሆኑ ቀርቶ ለሥራ አስፈጻሚው ቁንጮ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ መሆኑ ራሱ የአደረጃጀት ችግር አለበት፡፡ አሁን ያለው የተወካዮች ምክር ቤት ለውጥ ሊያመጣ ይችላል ከሚል ሳይሆን፣ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ ንፁህ እንኳ ቢሆኑ ፖለቲካዊ ሙስና ይሁን ትልቁ የገንዘብ/ንብረት ሙስና የሚፈጸመው በሥራ አስፈጻሚው ስለሆነ ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ተነፃፃሪ ነፃነት የሚያገኝበትን መንገድ መፈለግ ይኖርበታል፡፡ በእስራኤልና በቬንዙዌላ ያየናቸው ጠቅላይ አቃቤ ሕጎች በምሳሌነት ሊወሰዱ ይችላል፡፡ ለሕገ መንግሥቱና ለኢትዮጵያ ሕዝቦች ፍፁም ታማኝነት ያለው ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ፣ የፓርቲ ፖለቲካን በሁለተኛ ደረጃ የሚያይ የነፃነት አወቃቀርና ምደባ ያስፈልገዋል፡፡

የፍትሕ ሥርዓቱና ፐብሊክ ሰርቪስ

በአጠቃላይ ፍትሕ ከርትዕ ርቆ የጉልበተኞች መጫወቻ እየሆነ፣ በአጠቃላይ ዜጎች በፍርኃት የተሸበቡበት ፖለቲካዊ ድባብ ነው ያለው፡፡ የፍትሕ ሥርዓቱ በአስፈጻሚ አካል፣ በፌዴሬሽን ምክር ቤትና በፍርድ ቤቶች የሚካሄድ ሆኖ ሥራ አስፈጻሚው አምባገነን በሆነበት ሁኔታ፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤትና ፍርድ ቤቶች ነፃነታቸውን ባልጠበቁበት ሁኔታ ፍትሕ ሊረጋገጥ አይችልም፡፡

ሕግ አውጪው የሚያወጣቸው ሕጎች፣ ሕግ አስፈጻሚው እነዚህን ሕጎች ተግባራዊ ለማድረግ የሚዘረዝራቸው መመርያዎች፣ አደረጃጀቶችና አሠራሮች የሕግ አስፈጻሚ አካል በሆነው ፐብሊክ ሰርቪስ ነው ተግባራዊ የሚሆነው፡፡ በመሆኑም ፐብሊክ ሰርቪስ የራሱ ከፍተኛ ቦታ አለው፡፡ የአስፈጻሚ ክንድ በመሆን ከሕዝቡ ጋር በቀጥታ የሚያገናኝ ነው፡፡ ምሁራን የፐብሊክ ሰርቪስ ውጤታማነት የሚለካው በሚሰጠው አገልግሎት ዓይነት፣ በቢሮክራሲው ሁኔታ፣ በአባላት አጠቃላይ ብቃትና ፕሮፌሽናሊዝም በአንድ በኩል እንዲሁም የሲቪል ሰርቪሱ ተነፃፃሪ ነፃነትና አጠቃላይ የመንግሥት ፖሊሲዎችን ለመተግበር ያለው ቁርጠኝነት በሌላ በኩል ነው፡፡

የአገራችን ፐብሊክ ሰርቪስ ተነፃፃሪ ነፃነት የለውም፡፡ ማናቸውም በምርጫ ሥልጣን የያዘን ፓርቲ ለማገልገል ሳይሆን የአሁኑን ገዥ ግንባር ብቻ እንዲያገለግል ተብሎ ነው የሚሰራው፡፡ ገዥው ግንባር ‹‹ሲታደስ›› በዚያ ፖለቲካ እንዲታደስ የሚደረግ በመሆኑ መረጋጋት (Stability) የለውም፡፡ በገዥው ግንባር ያለው ችግር ትምክህትና ጠባብነት ከሆነ ፐብሊክ ሰርቪሱም በሰጠው አገልግሎትና ፕሮፌሽናሊዝም ሳይሆን ግንባሩን ለመምሰል በትምክህትና በጠባብነት ይገመገማል፡፡ ምልመላው ላይ ለመግለጽ እንደተሞከረው ካድሬዎቹ ለፕሮፌሽን ታማኝና ማንነቱን ጠብቆ የሚሄደውን በትምክህትና በጠባብነት ሰበብ ያዋክቡታል፡፡ በትንሽ በትልቁ ቀንና ሌሊት እየሠራ በፈጠረው ስህተት ያስሩታል፣ ወይም ያባርሩታል፡፡ ቀልጣፋ (Efficient) ወይም ውጤታማ (Effective) የሆነ ፐብሊክ ሰርቪስ ከተገነባ የገዥው ፓርቲ መዥገርነት ይላቀቃል፡፡ የመንግሥት ንብረትና ሀብትን ግንባሩ እንዳይጠቀምበት እንቅፋት ይሆናል፡፡ በዚህ ምክንያት በኢሕአዴግ የሚመራው መንግሥት የሕዝብ ሰፊ ተቃውሞ ከገጠመው በኋላ ከሙስና ጋር የተሳሰሩ በሁለት ሊከፈሉ የሚችሉ ማረጋጋት ያስገኛሉ ያላቸውን ዕርምጃዎች ወስዷል፡፡ ከሃምሳ በላይ የሚሆኑ ባለሥልጣናት፣ ባለሀብቶችና ደላላዎች ያለቸውን ተጠርጣሪዎች በማሰር በፍርድ ሒድት ላይ ይገኛሉ፡፡ ከክሶቹ ባህሪ ተነስቶ የገንዝብ/ንብረት ሙሱና ወይም ቢሮክራቲክ ሙስና ሊባል ይቻላል፡፡

አንድ ጊዜ መልካም አስተዳደር፣ ሌላ ጊዜ ጠባብነትና ትምክህት፤ በዋናነት ደግሞ ኪራይ ሰብሳቢነት (የመንግሥት ሥልጣንን ለግል ጥቅም. . .) የመሳሰሉ ፖለቲካዊ ችግሮች አለብኝ ብሎ የጥልቅ ተሃድሶ እንቅስቃሴ ከጀመረ ወደ አንድ ዓመት ገደማ ሆኖታል፡፡ ግምገማ፣ ሂስና ግለ ሂስ በዋናነት በታችኛው እርከን ባለሥልጣን ላይ በሚወስዱ ዕርምጃዎች ታጅቦ የተጠናቀቀ ይመስላል፡፡ መሠረታዊ ፖለቲካዊ ለውጥ (Reform) ሳያድርግ፣ ሰብዓዊና ዴሞክራሲዊ መብቶች የሚከበሩበት፣ ሕገ መንግሥታዊ ተቋማት ተልዕኮዎቻቸውን የሚወጡበት ሁኔታ ሳያመቻች፣ እንደ ድርጅት ያለውን መዥገርነት ሳያሰተካክል አገሪቷ ቅድመ 2008 ዓ.ም. እንደነበረው እንዲያውም በባሰበት ፖለቲካዊ ሙስና እየታመሰች ትገኛለች፡፡

ከእሱ ጋር የሚዛመድ አንድ ወንድም የላከልኝን ግጥም ላካፍላችሁ፡፡

            እልፍ ከሲታዎች ቀጥነው የሞጎጉ

            ሥጋችን የትሄደ ብለው ሲፈልጉ

            በየሸንተረሩ በየጥጋጥጉ

            አስሰው አስሰው በምድር በሰማይ

            አገኙት ቦርጭ ሆኖ ባንድሰው ገላ ላይ

                               በዕውቀቱ ሥዩም 2001 ዓ.ም.

አንዳንድ የትግል ጓዶች አሁንም በሥልጣን ላይ ያሉ ሌተና ጄኔራል ጻድቃንና እኔ የአገራችን ጉዳይ አሳስቦን በመጻፋችን ምን ፈልገው ነው? ይላሉ፡፡ የሚጠቅም ሐሳብ አለው የለውም ብለው ሳይመረምሩ፡፡ ሥልጣን ፈልገው? ተምረናል ለማለት? ወይስ ቂም ስላላቸው? ብለው በመመራመር ጊዚያቸውን ያባከናሉ፡፡ እስከ ምን ድረስ እንደወረዱ የሚያሳይ ነው፡፡ መልሱ ግን ሁሉም ስህተት ነው፡፡ የዛሬ 124 ዓመት ከተጻፈ ጥቅስ መልሱን ቢፈለጉት እንዴት ደስ ባለኝ!!

‹‹Who Saves his Country, Saves Himself, Saves All Things, and All Things Saved do Bless Him! Who Let’s His Country Die, Lets All Things Die, Dies Himself Ignobly, and all Things Dying Cursing Him!››   Senator Benjamin H.Hill Jr…1893

ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው የቀድሞ የኢሕአዴግ ታጋይና የአየር ኃይል ዋና አዛዥ የነበሩ ሲሆን፣ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል  አድራሻቸው gabebet@gmail.com ማግኘት ይቻላል፡፡

Share and Enjoy !

Shares

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *