ታማኝ የዜና ምንጮች ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ አይሲኤል የኢትዮጵያ መንግሥት በኢንቨስትመንቱ ላይ ላደረሰበት ጉዳት 198 ሚሊዮን ዶላር ካሳ እንዲከፈለው በኔዘርላንድ ዘ ሔግ ዓለም አቀፍ የግልግል ፍርድ ቤት አመልክቷል፡፡

አይሲኤል ለሪፖርተር በላከው መግለጫ ክሱን በኔዘርላንድ ሊመሠርት የቻለው፣ የአይሲኤል ዩሮፕ መቀመጫ ኔዘርላንድ በመሆኑና የኢትዮጵያ መንግሥት በኔዘርላንድና በኢትዮጵያ መካከል የተፈረመውን የኢንቨስትመንት ማበረታቻና ከለላ ስምምነት በመጣሱ እንደሆነ አስታውቋል፡፡ የፖታሽ ማዕድን ልማት ፕሮጀክቱ ሊጨናገፍ የቻለው፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ሕገወጥ የታክስ ጥያቄ በማቅረቡና ለፕሮጀክቱ የሚያስፈልገውን መሠረተ ልማት ማሟላት ባለመቻሉ እንደሆነ ኩባንያው አስታውቋል፡፡ አይሲኤል ከግብር ጥያቄ ጋር በተያያዘ የፖታሽ ልማት ፕሮጀክቱን በጥቅምት 2009 ዓ.ም. አቋርጦ መውጣቱ ይታወሳል፡፡

 

Israel’s ICL Cancels its Ethiopian Potash Project

በአፋር ክልል በዳሎል አካባቢ የሚገኘውን ከፍተኛ መጠን ያለው የፖታሽ ማዕድን ክምችት ለማልማት ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር ውል ተፈራርሞ ሲሠራ የቆየው አላና ፖታሽ የተባለ የካናዳ ኩባንያ ነበር፡፡ ለአምስት ዓመታት ያህል ጥናት ያካሄደው አላና ፖታሽ 3.2 ቢሊዮን ቶን የፓታሽ ማዕድን ክምችት መኖሩን አረጋግጦ፣ ማዕድኑን ለማልማት የሚያስችለው ከፍተኛ የማዕድን ልማት ስምምነት እ.ኤ.አ. በ2013 ከማዕድን ሚኒስቴር ጋር ተፈራርሟል፡፡

Related stories   አሳሳቢው የእስራኤልና ፍልስጤም ግጭት

አላና ፖታሽ ኢትዮጵያ ውስጥ ይንቀሳቀስ የነበረው አላና ፖታሽ አፋር የሚል ኩባንያ ኢትዮጵያ ውስጥ ካቋቋመ በኋላ ነበር፡፡ በዓለም አቀፍ ገበያ የፖታሽ ዋጋ በማሽቆልቆሉ ምክንያት አላና ፖታሽ በዳሎል የሚገኘውን የፖታሽ ማዕድን ልማት ፕሮጀክት ለማካሄድ የሚያስፈልገውን 700 ሚሊዮን ዶላር ማምጣት ባለመቻሉ፣ እ.ኤ.አ. በ2015 የአላና ፖታሽ አክሲዮን በ150 ሚሊዮን ዶላር ሙሉ ለሙሉ ለአይሲኤል ተሸጧል፡፡

ኤይሲኤል የአላና ፖታሽ የማዕድን ልማት ፈቃድ ስም እንዲዛወርለት ለማዕድን ሚኒስቴር ጥያቄ አቅርቦ በመታየት ላይ ሳለ፣ ሥራውን ግን በአላና ፖታሽ አፋር ኩባንያ ስም ሲያካሂድ ቆይቷል፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን አላና ፖታሽ አፋር 50 ሚሊዮን ዶላር ግብር እንዲከፍለው ጥያቄ አቅርቧል፡፡

ከዚህ ውስጥ አሥር ሚሊዮን ዶላር የተጨማሪ እሴትና የዊዝሆልዲንግ ታክስ ሲሆን፣ 40 ሚሊዮን ዶላር ደግሞ የካፒታል ዕድገት ግብር ጥያቄ ነው፡፡

Related stories   መካከለኛዉ ምሥራቅ ሌላ ዘመን ሌላ ጥፋት

የአይሲኤል ቦርድ የግብር ጥያቄውን በመቃወም ፕሮጀክቱን አቋርጦ ለመውጣት መወሰኑን በጥቅምት 2009 ዓ.ም. አስታውቋል፡፡ ከዚያም ኩባንያው ሥራውን አቋርጦ ጓዙን ጠቅልሎ ከኢትዮጵያ ወጥቷል፡፡

            አይሲኤል የፖታሽ ማዕድን ማውጫና ሦስት የማዳበሪያ ፋብሪካዎች በአንድ ቢሊዮን ዶላር ኢንቨስትመንት ለመገንባት ሲንቀሳቀስ እንደቆየ ይታወቃል፡፡ ይህን ፕሮጀክት የኢትዮጵያ መንግሥት ያላግባብ የግብር ጥያቄ በማቅረብና አስፈላጊውን መሠረተ ልማት ባለሟሟላት አስተጓጉሎብኛል ሲል የ198 ሚሊዮን ዶላር ካሳ ጥያቄ አቅርቧል፡፡ በአፋር ዳሎል የኩባንያው ተሽከርካሪዎች፣ ማሽኖችና ሌሎች ንብረቶች እንደባከኑበት ገልጿል፡፡

የማዕድን፣ ነዳጅና የተፈጥሮ ጋዝ ሚኒስትር አቶ ሞቱማ መቃሳ፣ አይሲኤል በዓለም አቀፍ የግልግል ፍርድ ቤት ክስ መመሥረቱን ለሪፖርተር አረጋግጠዋል፡፡ አላና ፖታሽ አፋር ጥሎ የወጣውን የፖታሽ ማዕድን ይዞታ መንግሥት መረከቡን የገለጹት አቶ ሞቱማ፣ ጉዳዩ በሕግ የተያዘ በመሆኑ አስተያየት ከመስጠት ተቆጥበዋል፡፡

መንግሥት የማዕድን ይዞታውን በቀጣይ ምን ለማድረግ አስቧል ለሚለው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ፣ ጉዳዩ በሕግ የተያዘ በመሆኑ የፍርድ ሒደቱ ሲጠናቀቅ እንደሚታይ ገልጸዋል፡፡ ‹‹በጨረታ ነው ወይስ በድርድር ለሌላ ኩባንያ የሚሰጠው የሚለው የፍርድ ሒደቱ ሲጠናቀቅ የሚወሰን ይሆናል፤›› ብለዋል አቶ ሞቱማ፡፡

ሪፖርተር ያነጋገራቸው አንድ ከፍተኛ የሚኒስቴሩ ኃላፊ መሥሪያ ቤቱ የሚያውቀው አላና ፖታሽን እንጂ አይሲኤልን እንዳልሆነ ገልጸው፣ ኩባንያው ለቀረበበት የታክስ ክፍያ ጥያቄ አቤቱታውን ለኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ማቅረብ ሲችል ፕሮጀክቱን ለማቋረጥና ወደ ፍርድ ቤት ለመሄድ መጣደፉን ተናግረዋል፡፡ ‹‹በታክሱ ጉዳይ ይግባኝ መጠየቅ ይችሉ ነበር፡፡ ችግሩን በድርድር ለመፍታት በውጭ ጉዳይና በኤምባሲያቸው በኩል ጥሪ ብናደርግላቸውም ሊሰሙን አልቻሉም፤›› ያሉት ኃላፊው፣ መንግሥት ዳሎል አካባቢ አስፈላጊውን መሠረተ ልማት ለሟሟላት ከፍተኛ ቁርጠኝነት እንደነበረው አስረድተዋል፡፡

Related stories   ኦሮሞ ኦሮሞን አድፍጦ እየገደለ ነው፤ ኦነግ ሸኔ ለስራ የሚጓዙ አምስት ኦሮሞዎችን ገደለ

መንግሥት የፖታሽ ምርቱን ወደ ጂቡቲ ታጁራ ወደብ ማጓጓዝ የሚያስችል የመንገድና የባቡር ሐዲድ ግንባታ ለማካሄድ በዝግጅት ላይ ሳለ፣ ኩባንያው ሥራውን አቋርጦ እንደወጣ ኃላፊው ገልጸዋል፡፡

‹‹የሚኒስቴሩ ኃላፊዎችና የመንግሥት የበላይ አመራር ጭምር ከኩባንያው ጋር ችግሩን በጠረጴዛ ዙሪያ ለመፍታት ፈቃደኝነቱ ነበር፣ ጥረትም ተደርጓል፡፡ የኩባንያው ኃላፊዎች ግን ወደ አዲስ አበባ ለመምጣት ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተዋል፤›› ብለዋል፡፡

አገሮች ወደ ዓለም አቀፍ የግልግል ዳኝነት ለመሄድ ፈቃደኛነታቸው በቅድሚያ ይጠየቃል፡፡ ይሁንና የውጭ ኢንቨስተሮች ከአገሮች ጋር በሚያደርጉት የሁለትዮሽ የኢንቨስትመንት ስምምነት አለመግባባት ከተፈጠረ፣ ወደ ዓለም አቀፍ የግልግል ዳኝነት እንዴት መሄድ እንደሚቻል አስቀደመው ይደነግጋሉ፡፡

ሪፖርተር አማርኛ – ቃለየሱስ በቀለ