አሳዛኙ ጉዳይ ህዝብ እያለቀ መሆኑ ነው። አስነዋሪው ጉዳይ ህዝብ እየተፈናቀለ መሆኑ ነው። ልብ የሚሰብረው ጉዳይ ህዝብ የሚጠብቀው አካል ማጣቱ ነው። የተወሰኑ ክፍሎች ምንም ሳይሆኑ የኑሮ ዋስትና ይጠየቅላቸዋል። ካሳ ይቆረጥላቸዋል። ሌሎች ይታረዳሉ። የገደላሉ፣ ይፈናቀላሉ፣ የተቀሩትም ዋስትና እንደሌላቸው በተስፋ መቁረጥ ውስጥ ሆነዋል። ሁሉ ቦታ እሳት የጨሳል። ኢትዮጵያ ” ክፍታ ላይ ወጣች” ተብሎ ይደገሳል። አስረሽ ምቺው ይባላል። ከ9 ፣ኢሊዮን ህዝብ በላይ ህዝብ በችጋር ይጠበሳል። አገሪቱ ወዴት እየሄደች ነው? አማራ ክልል ህዝብ በግድ ያልሆነውን እንዲሁን አፈ ሙዝ ተደግኖበት መከራውን እያየ ነው… ነገሩ ሁሉ ግራ የሚያጋባ ነው፤ 

IMG_1095

” አደጋ ውስጥ ነን። እኛም ዋስትና የለንም። ኦሮሞ የሆኑ በሙሉ እየተለቀሙ እየተባበሩ ነው። በጅጅጋ ያለው ነገር ሙሉ በሙሉ አያምርም። ፈርተናል። ዝርፊያና አጓጉል የሆኑ ድርጊቶች እየታዩ ነው…” ሲል አንድ የጅጅጋ ነዋሪ ይናገራል። ይህ ነዋሪ ለዛጎል በላከው መልዕክት ያነሳቸው ሰፊና ለማመን የሚያስቸገሩ ጉዳዮች በሶማሌ ክልል እየተፈጸመ ነው። መረጃዎቹ ማጣራት የሚያስፈለጋቸው  በመሆናቸው ለጊዜው እንዳሉ አላተምናቸውም። በሁለት የኦሮሞ ብሄር አባላት ላይ ተወሰደ ያለውን አስነዋሪ የግድያ ርምጃ የዘረዘረው መልዕክት መንግስት በቀጥታ ጣልቃ ገብቶ ችግሩን ማስቆም አለመቻሉ ሁሉንም ወገን እንዳስደነገጠም ይገልጻል።

በትናንትናው እለት መንግስት ” በቁጥጥር ስር ውሏል” ሲል ያስታወቀው ይህ ፈሩን የለቀቀ የሁለት ወንድማማች ህዝብ መተላለቅ ዛሬ ሶስት አንደበት ስፖርት እየሰሩበት ነው። የሶማሌ ክልል፣ የኦሮሚያ ክልል፣ እንዲሁም የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጽህፈት ቤቶች እርስ በእርስ የሚቧቀስና አሳፋሪ ሊባል በሚችል ደረጃ መረጃ እያሰራጩ ነው።

የሶማሌ ክልል በማስታወቂያ ቢሮ ኃላፊ ኢንጂነር ኢድሪስ ኢስማኤል አማካይነት በፌስ ቡክ ህጋዊ ገጻቸው የተሰራጨው ዜና የኦሮሚያ ክልል ማስታወቂያ ቢሮ ኃላፊ የሆኑት አቶ አዲሱ አረጋን “ኦነግ” ሲል የሰደበ ሲሆን፤ በዓላማ ደረጃ ከኦሮሚያ ኔት ዎርክ ዳይሬክተር አቶ ጃዋር መሐመድ ጋር “ተመሳሳይ አቋም ያላቸው” ሲል አሸባሪ ተበሎ ከተፈረጃ አካል ጋር መድቧቸዋል። በዚህም ብቻ አያበቃም ሙሉውን ከዚህ በታች ያንብቡ

የኢትዮ.ሶማሌ ክልል ህዝብና መንግስት የሀገራችን የፌደራል ስርዓታችን በመጠበቅ ስርዓቱ ዘብ በመሆን መቆየቱ የሚታውቅ ነው:: የክልላችን ህዝብና መንግስት በብዝሀነት ላይ የተመሰረተውን ልዩነት በማክበር በመቻቻልና በመፈቃቀር ለዘመናት ከብሔሮች፣ብሔረሰቦችን ህዝቦች በጋራና በጥሩ ጉርብትና አምኖና ተግብሮ የሚኖር ጨዋ ህዝብ ነው::ታዲያ ሰሞኑን ክልላችን ከኦሮሞ ክልል ጋር በሚዋሰንበት አከባቢዎች በክልሉ መንግስት የሚደገፍና በክልሉ በታጠቁ ሀይሎች፣ በክልሉ ፓሊስ፣ ሚሊሽያና የአሽባሪው የኦነግ ቄሮ አባላት በተደጋጋሚ ጥቃት ሲፈጽሙና ወረራ ሲያካሂዱ የቆዩ ሲሆን በዚህም የክልሉ መንግስትና የአሸባሪው ኦነግ አንድ አቋም በመይዝ በግልጽ #ጆሀር መሀመድና እና የኦሮሞ ክልል ኮሚኒኬሽን ቢሮ ሀላፊ #አዲሱአረጋ ተመሳሳይ አቋም ያሳዩበትና #አዲሱ አረጋም በግልጽ የኦነግ አባልነቱን ያረጋገጠ ሆኖ ተግኝቷል:: ታዲይ ይህ መንገድ አልሳካ ብሎ ሲቀር ፊቱን በክልሉ ነዋሪ በሆኑ የሶማሌ ተወላጆች ላይ የዘረኝነት ጭፍጨፋን የጀመረ ሲሆን በተለይ በአወዳይ ከተማ በትላንትናው እለት ከ50 በላይ የሆኑ ንጹሀን ዜጎች ላይ በአሰቃቂ ሁኔታ እስከዛሬ ድረስ በሀገራችን ታይቶ በማይታወቅ መልኩ አካላታቸውን በመቆራረትና በእሳት በማቃጠል ህይወት የቅጠፉ ሲሆን ከ300 በላይ የሚሆኑ ደግሞ በመከላከያ ሰራዊት ሀይል ህይወታቸውን በማትረፍ ወደ ሀረር እንዲገቡ ተደርጏል:: በዛሬው እለትም 30 የሚሆኑ የዜጎች የተቆራረጠና የተቃጠለ ሬሳ የመጣ ሲሆን በነገው እለት በክብር ግብአተ ግብራቸው ይፈጸማል::
በአሁኑ ሰአት የክልሉ መንግስት የተቆጣውን የክልሉ ህዝብ በማረጋጋት በክልሉ የሚገኙ የኦሮሞ ተወላጆችን በማሰባሰብ ጉዳት እንዳይደርስባቸው ከለላ በመስጠት ምግብና መኝታን በመስጠት ህዝባዊነቱን፣ ሰላም ወዳድነቱንና ወገን አክባሪነቱን ያሳየ ሲሆን በተቃራኒው የኦሮሞ መንግስትና የጽጥታ ሀይሉ በኦሮሞ ክልል ላይ ከ20 አመት በላይ የኖሩ ከክልሉ ማህበረሰብ ጋር በደም የተዛመዱ የሶማሌ ተወላጆች ላይ የወሰደው እርምጃ የክልሉን ህዝብና መንግስት በእጅጉ ያስቆጣና ይህንንም በሀገራችን ህግና ደንብ መሰረት ጉዳት አድራሾቹ ለህግ ተጠያቂ የሚሆኑበት መንገድ የክልሉ መንግስት አጥብቆ ይሰራል::
የተከበራችሁ የክልሉ ነዋሪዎች የሀገራችን ብሎም የክልላችን ሰላም ለማስጠበቅና ፈጣኑ ልማታችንን ለማስቀጠል የተለመደውን የክልሉ ባህልና ሀይማኖታዊ ስርአት የሆነውን ሌሎችን አለመጉዳት ባህላችንን በማስቀጠል እነሱ ተሳስተዋል ብለን እኛም ተሳስተን በኦሮሞ ተወላጅ ላይ ምንም እርምጃ እንዳትውስዱ እናሳስባለን::
በመጨረሻም የዚህ እጅግ ዘግናኝ በሆነ መንገድ ህይወታቸውን ላጡ ዜጎች ነፍስ ይማር እያልን ለቤተሰቦቻቸው ደግሞ መጽናናትን እንመኛለን::
የኢትዮ. ሶማሌ ክልል መንግስት ኮሚኒኬሽን ቢሮ.

አቶ አዲሱ አረጋ በፌስ ቡክ ገጻቸው ባሰራጩት መግለጫ “አንድ የፌዴራሊዝም ዘብ ነኝ የሚል መንግስት በምን ስሌት ልዩ ሃይል አደራጅቶ ሰላማዊ ዜጎች ላይ ጥቃት ይፈጽማል” ሲል ይጠይቃል። ክልሉ ያወጣው መግለጫ እጅግ አሳፋሪና ሃላፊነት የጎደለው መሆኑንን ያትታል። የሶማሌ ክልል የመንግስት የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ደካ ቁመናና ዝቅተኛ ደረጃ ያለው ሲል መዝኖ ይከሳል። የክልሉን ሃላፊዎች በኦነግና በአሸባሪነት ደረጃ መፈረጅና ማጣጣል ዘመኑ ያለፈበት ተረት እንደሆነም ያትታል። የኦሮሞ ክልል የሚባል ስያሜ መሰጠቱ አደገኛ አካሄድ እንደሆነ የጠቆመው መግለጫ ” ኦሮሚያ የሁሉም ህዝቦች አገር፣ የአንድነት መሰረት መሆኗን …” ህዝብን ምስክር አድርጎ ያቀርባል።

Related stories   አፍሪካ ህብረት ቁርጠኛነቱን አሳይቷል፤ አውሮፓ ህብረት ምርጫ አልታዘብም አለ

በኦሮሚያ ክልል የአማራ ክልል ተወላጆች እየተለቀሙ ሲባረሩ እንደነበርና፣ በበደኖና በአርባ ጉጉ እንዲሁም በተለያዩ ስፍራዎች እንደ ባእድ ተቆጥረው የደረሰባቸውን ግፍ በይቀርታ እንኳን ያላካተተው የኦሮሚያ ክልል መግለጫ፣ከዚህ የሚከተለው ነው

ይድረስ ለሶማሌ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ

የሶማሌ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ በኦሮሚያ እና በኢትዮጵያ ሶማሌ አዋሳኝ አካባቢዎች ሰሞኑን ከተከሰተዉ ችግር ጋር አያይዞ በትናንትናዉ ዕለት በአማርኛ ቋንቋ መግለጫ አዉጥቷል፡፡ የወጣዉ መግለጫ እጅግ በጣም አሳፋሪ እና ሀላፊነት በጎደለዉ መልኩ የቀረበ ነዉ፡፡ መግለጫዉ አሁን ያለዉን ችግር ከማርገብ ይልቅ ወደ ሌላ አቅጣጫ ሊወስድ የሚችልና ሀገርን ከሚያስተዳድር ትልቅ የመንግስት መስሪያ ቤት ይሰጣል ተብሎ የማይጠበቅ አሳፋሪ መግለጫ ነዉ፡፡ የወጣዉ መግለጫ የሶማሌ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ የተጣለበትን ህዝባዊ እና መንግስታዊ ሃላፊነት ከመሸከም አንጻር ያለበትን ደካማ ቁመናና ዝቅተኛ ደረጃ ፍንትዉ አድርጎ የሚያሳይ ነዉ፡፡ 

ከመግለጫዉ ስህተቶች የሶማሌ ክልላዊ መንግሰትን የፌዴራል ስርዓቱ ብቸኛ ዘብ እና ጠባቂ እድርጎ የማቅረቡ ጉዳይ ነዉ፡፡ በእኛ እምነት አሁን ላለዉ ህብረ ብሄራዊ ፌዴራላዊ ስርዓት ሁሉም የኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦች እና ህዝቦች እኩል መስዋዕትነት የከፈሉበት የትግላቸዉ ዉጤት ነዉ፡፡ ስለሆነም አሁን እየገነባን ላለነዉ ህብረ ብሄራዊ ፌዴራላዊ ስርዓት ዘቦች ሁሉም የኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦች እና ህዝቦች ናቸዉ፡፡ የመግለጫዉ ሀሳብ በተጨባጭ ተግባር የሚገለጽ ቢሆን ኖሮ ደግሞ እሰየዉ ነበር፡፡ አንድ የፌዴራሊዝም ዘብ ነኝ የሚል መንግስት በምን ስሌት ልዩ ሃይል አደራጅቶ ሰላማዊ ዜጎች ላይ ጥቃት ይፈጽማል? ሰሞኑን በተፈጠረ ግጭት እንኳ ስንት ሰላማዊ ዜጎች በኦሮሞነታቸዉ ብቻ ቄያቸዉን ጥለዉ እንዲሰደዱ እየተደረገ አይደለምን? ከዚህ አንጻር የሶማሌ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ የክልሉን መንግስት የፌዴራሊዝም ዘብ ነኝ ብሎ ራሱን ማቅረቡ ከተግባሩ ጋር የሚሄድ አይደለም፡፡

በሁለተኛ ደረጃ የቢሮዉ መግለጫ የኦሮሚያ ብሄራዊ ክልልን “የኦሮሞ ክልል” ብሎ ከህገ መንግስቱ ዉጪ መሰየሙ ነዉ፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ “የኦሮሞ ክልል” የሚባል ክልል የለም፡፡ መግለጫዉ ይህን አጻጻፍ የተከተለዉ የኦሮሚያ ብሄራዊ ክልልን “የኦሮሞዎች ብቻ” እንደሆነችና ሌሎች የኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦችን የማታቅፍና አግላይ አስመስሎ ማቅረብ የሞከረበት አደገኛ ተልዕኮ ያለዉ አጻጻፍ ነዉ፡፡ በኦሮሚያ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት እምነት የኦሮሚያ ክልል የሁሉም ኢትዮያዊያን ናት፡፡ ለዚህ ደግሞ የክልሉ፣ ስያሜ “የኦሮሞ ክልል” የማይሆንበት ምክንያት ሁሉም የኢትዮጵያ ህዝቦች በወንድማማችነት እና በአንድነት በፍቅር የሚኖሩባት ክልል እንደሆነች ምስክር መጥራት አያስፈልገንም፡፡ 

ሶስተኛዉ መሰረታዊ ስህተት የክልሉን መንግስት በአሸባሪነት እና በኦነግነት መፈረጁ ነዉ፡፡ የኦሮሚያ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት አመራሮች በኢትዮጵያ አንድነት እና በህዝቦች ወንድማማችነት ላይ የማያወላዉል ጽኑ አቋም እንዳለን መላ የኢትዮጵያ ህዝብ ምስክራችን ነዉ፡፡ ኦሮሚያ እና የኦሮሞ ህዝብ የኢትዮጵያ አንድነት ምሶሶዎች ናቸዉ፡፡ የክልሉ አመራሮችም ለፌዴራላዊ ስርዓታችን ማበብና መጎልበት የህዝቦች ወንድማማችነት እና እኩል ተጠቃሚነት እንዲሰፍን ለማድረግ እየታገሉ መስዋዕትነት እየከፈሉ ያሉ ዉድ የኢትዮጵያ ህዝብ ልጆች እንጂ በአሸባሪነት እና በኦነግነት የሚፈረጁ አይደሉም፡፡ መግለጫዉ ከዚህ አንጻር ሀላፊነት በጎደለዉ አግባብ የተጻፈና ወንጀልም ጭምር በመሆኑ ህገ መንግስቱን ተከተለን ህጋዊ እና አስተዳደራዊ መንገድ የምንጠይቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡ ከዚህ ባለፈ የኦሮሞ ተወላጆችን እና የክልሉን አመራሮች በኦነግነት ሌብል ማድረግ ለማሸማቀቅ መሞከር ከበርካታ አመታት በፊት ሲደረግ የነበረ አሁን ግን ጊዜዉ ያለፈበት ተራ ሌብሊንግ መሆኑን ለመግለጽ እንወዳለን፡፡

የመግለጫዉ ሌላኛዉ ይዘት ግጭትን የሚያባብሱ አደገኛ ቃላት እና በተጋነኑ ዉሸቶች መሞላቱ ነዉ፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ ሰሞኑን በተከሰተዉ የጸጥታ መደፍረስ ክቡር የሰዎች ህይወት አልፏል፡፡ በዚህ ረገድ የኦሮሚያ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ኦሮሞም ይሁን ማንም ሰዉ መሞት የለበትም ብሎ ያምናል፡፡ በሰሞኑ ሁኔታ ከሁለቱም ወገን ህይወታቸዉ ላለፉት ዜጎች የተሰማዉን ጥልቅ ሀዘን ይገልጻል፡፡ ከዚህም በላይ በንጹኃን ዜጎች ላይ የህይወት ማጥፋት አና አካል የማጉደል ወንጀል የፈጸሙ ሰዎች ለህግ መቅረብ አለባቸዉ ብሎ ያምናል፡፡ ከዚህ በተረፈ ሰሞኑን ስለነበረዉ እዉነታ ሀቁን ለህዝባችን መግለጹ አስፈላጊ ነዉ፡፡ መስከረም 1/2010 ከጉርሱም ወደ ወደ ሀረር እየተጓዙ ያሉ ሰላማዊ የኦሮሞ ተወላጆችን የሶማሌ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት የጸጥታ አካላት ቦምባስ ከተማ ኬላ ላይ ይዘዉ ያስራሉ፡፡ እነዚህ ታሳሪዎች አቶ ሳላህ መሀመድ (የጉርሱም ወረዳ አስተዳዳሪ የነበረ)፣ አቶ ታጁዲን ጀማል እና ሌሎች ሌሎች ሁለት ሰዎች፣ በነጋታዉ በደረሰባቸዉ ድብደባ መሞታቸዉ ተሰማ፡፡ ይህ ሰላማዊ ሰዎች ከላይ ተፈጸመዉ ግድያ የምስራቅ ሀረርጌ ነዋሪዎችን በማስቆጣቱ በምስራቅ ሀረርጌ ዞን አወዳይ፣ ደደር፣ ቆቦ እና መልካ ራፉ ከተሞች ያልተጠበቀ የህዝብ ቁጣ እና ሰልፍ አስከተለ፡፡ በተለይ አወዳይ የነበረዉ ሰልፍ ወደ ግርግር ተሸጋገረ፡፡ የበተፈጠረዉ ግርግርም የ18 ሰዎች ህይወት ሊያልፍ ችሏል፡፡ በዚህ ግርግር ዉስጥ ህይታቸዉ ካጡ 18 ሰዎች 12 የሶማሌ ተወላጅ ወንድሞቻችን ሲሆኑ 6ቱ ደግሞ የጃርሶ ጎሳ ተወላጅ ኦሮሞዎች ናቸዉ፡፡ እነዚህ ሰዎች ድንበር ላይ እየተፈጸመ ካለዉ ጥቃት ጋር ምንም ተያያዝነት የሌላቸዉ፣ በላባቸዉ ሰርተዉ የሚያድሩ ሰላማዊ ዜጎች ናቸዉ፡፡ በዚያ ግርግር የእነዚህ ወንድሞቻችን ህይወት ማለፍ በእጅጉ አሳዝኖናል፡፡ በድርጊቱ ተሳትፎ አላቸዉ ተብለዉ የተጠረጠሩ ከ200 ሰዎች በላይም ቁጥጥር ስር ዉለዉ ምርመራ እየተደረገባቸዉ ነዉ፡፡ እዉነታዉ ይህ ሆኖ ሳለ የሶማሌ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ይህን ጉዳይ ግጭትን በሚያባብሱ ስሜታዊ ቃላት እና ዉሸትን ጨምሮ አጋኖ ማቅረብ ግጭቱን ከማባባስ ያለፈ ምንም ጠቀሜታ አይኖረዉም፡፡

ከዚህ በፊት በተደጋጋሚ ስንገልጽ እንደነበረዉ የኢትዮጵያ ሶማሌ እና የኦሮሞ ህዝቦች ወንድማማች ህዝቦች ናቸዉ፡፡ በጋብቻ እና በደም የተሳሰሩ፣ ተመሳሳይ የአኗኗር ዘይቤ፣ ተመሳሳይ ስነ ልቦና ያላቸው ህዝቦች ናቸዉ፡፡ አሁን እየተከሰተ ያለዉ የሰላም መደፍረስ የሁለቱ ህዝቦች ፍላጎት እንዳልሆነ ግልጽ ሊሆን ይገባል፡፡ ከዚህ ግጭት ጀርባ ያሉ አካላት ተጣርተዉ ወደ ህግ እንደሚቀርቡና የስራቸዉን ዋጋ እንደሚያገኙ ምንም ጥርጥር የለንም፡፡
የኢትዮጵያ ሶማሌ እና የኦሮሞ ህዝቦች ወንድማማችነት ለዘለዓለም ይኑር!

መስከረም 4/2010
ፊንፊኔ ኦሮሚያ

Share and Enjoy !

Shares

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *