· ጠ/ሚኒስትሩ የምርጫ ቦርድ ኃላፊን ለማሾም ከሁሉም አገር አቀፍ
ፓርቲዎች ጋር ምክክር እንዲያደርጉ የማሻሻያ ሃሳብ ቀርቧል

ሁለተኛው የገዥው ፓርቲና የተቃዋሚዎች ድርድር፣ የፊታችን ሐሙስ የሚካሄድ ሲሆን ኢህአዴግ እስከ ዛሬ ድረስ በስራ ላይ የቆየው የአብላጫ ድምፅ የምርጫ ሥርአት በ “ቅይጥ” እና “ትይዩ” የምርጫ ሥርአት እንዲለወጥ የማሻሻያ ሃሳብ ማቅረቡን ምንጮች ለአዲስ አድማስ ጠቆሙ።
ኢህአዴግ በምርጫ ህጉ ላይ ሁለት ማሻሻያዎችን እንዳደረገ የሚገልፅ የመደራደሪያ ሰነድ እንደደረሳቸው የተናገሩ የተቃዋሚ አመራር፤ገዢው ፓርቲ የምርጫ ሥርአቱ በዋናነት “ቅይጥ – ትይዩ” (mixed – parallel) እንዲሆን የሚጠይቅ ማሻሻያ ማቅረቡን ገልጸዋል፡፡
ባለፉት ዓመታት በአገሪቱ የተደረጉ አምስት ብሔራዊ ምርጫዎች፣ የአብላጫ (50+1) ድምፅ ያገኘ መንግስት ይመሰርታል በሚለው የምርጫ ሥርዓት መሰረት የተከናወኑ መሆናቸው ይታወቃል። ይሄ የምርጫ ሥርዓት ከፓርቲዎች ጋር በመሆን እንደሚሻሻል ባለፈው ዓመት መግቢያ ላይ የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ሙላቱ ተሾመ፣ በፓርላማ መክፈቻ ንግግራቸው ላይ መግለጻቸው አይዘነጋም። ይህ የምርጫ ሥርዓት ለውጥ ግን በቀጥታ ስለ ምርጫ ስርአቱ የሚደነግገውን የህገ መንግስቱን አንቀፅ 55 የሚቃረን በመሆኑ የህገ መንግስት ማሻሻያ እንደሚጠይቅ የህግ ምሁራን ይገልጻሉ፡፡
በሌላ በኩል፤ በ2008 ክረምት ላይ የኢህአዴግ አንጋፋ መሪዎች ከኢቢሲ ጋር ባካሄዱት ውይይት፣የጠ/ሚኒስትሩ አማካሪ አቶ በረከት ስምኦን፣ በምርጫ ዙሪያ ባነሱት ሃሳብ፣ ፓርላማው በገዢው ፓርቲ አባላት ብቻ የተሞላው ህዝቡ ስለመረጠው መሆኑን ጠቅሰው፣ አገሪቱ በምትከተለው የምርጫ ሥርዓት የተነሳ ተቃዋሚዎች ያገኙትን ያህል ድምጽ ይዘው በፓርላማ የመረጣቸውን ህዝብ መወከል እንዳልቻሉ አስረድተዋል፡፡ አቶ በረከት አክለውም፣ ኢትዮጵያን የሚያህል ህዝብ በአንድ ፓርቲ ብቻ ሊወከል እንደማይችል በመግለጽ፣ ተቃዋሚዎችን የመረጠው ህዝብም በፓርላማ መወከል እንዲችል የምርጫ ሥርዓቱን ማሻሻል አስፈላጊ መሆኑን  ተናግረው ነበር፡፡
እንደ ኢህአዴግ ሁሉ፣ በድርድሩ ላይ የሚሳተፉ ተቃዋሚ ፓርቲዎችም፣በምርጫ ህጉ ላይ የማሻሻያ ሃሳቦችን በዝርዝር ማቅረባቸውን ይገልጻሉ፡፡ አስራ ሁለት ሆነው በሦስት የጋራ ተደራዳሪዎች ለመወከል የወሰኑት ኢዴፓ እና መኢአድ ያሉበት ቡድን፤ በምርጫ ህጉ ላይ ጠ/ሚኒስትሩ የምርጫ ቦርድ የስራ ኃላፊዎችን ለማሾም ለፓርላማው ከማቅረባቸው በፊት በምክር ቤት መቀመጫ ካላቸው ፓርቲዎች ጋር ይመካከራሉ የሚለው አንቀጽ፤ “የፓርላማ መቀመጫ ካላቸው ጋር ብቻ ሳይሆን ከሁሉም አገር አቀፍ ፓርቲዎች ጋር በቂ ምክክር ያደርጋሉ” በሚል እንዲሻሻል ሀሳብ ማቅረባቸው ተጠቁሟል፡፡ በዚህ ማሻሻያ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያመኑበት ግለሰብ ሳይሆን ሁሉም ፓርቲዎች በጋራ ያመኑበት ግለሰብ እንዲሾም ያስችላል ብለዋል – በድርድሩ ተሳታፊ የሆኑ የተቃዋሚ አመራር፡፡
የምርጫ ኮሚሽኑ የአመራር አባላት አመራረጥም በስብጥር እንዲሆን የማሻሻያ ሃሳብ ቀርቧል፡፡ አስራ አምስት የቦርድ አመራሮች የሚመረጡ ከሆነ ኢህአዴግ ሁለት፣ ተቃዋሚዎች ሦስት እንዲያቀርቡ፣ የሲቪክ ማህበራትና ገለልተኛ ተቋማትም አመራሮችን በማቅረብ እንዲሣተፉ በማሻሻያ ሃሳቡ ተጠቁሟል፡፡
ማንኛውም እጩ ተወዳዳሪ፣ ከውድድር በፊትና ከውድድር በኋላ፣ በምርጫው አሸነፈም ተሸነፈም የህግ ከለላ እንዲደረግለት የሚጠይቅ ተጨማሪ አዲስ አንቀፅም አስራ ሁለቱ ፓርቲዎች ማካተታቸው ታውቋል፡፡ እስከ ዛሬ በነበረው ልምድ በምርጫ የተሸነፈ እጩ ተወዳዳሪ፣ በፖለቲካ ልዩነት አድሎ ይደረግበታል፣ ይታሰራል፣ ይዋከባል፣ ንብረቱን የመቀማት እጣ ፈንታ ይገጥመዋል፤ ለስደትም ይዳረጋል  ያሉት አንድ የተቃዋሚ ፓርቲ መሪ፤ ይህ አንቀፅ መካተቱ እነዚህን ሁሉ በደሎች በማስቀረት፣ ተመርጦ ፓርላማ ከገባው እኩል ህጋዊ ከለላና ዋስትና እንዲያገኝ ያደርገዋል ብለዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የስም ለውጥ እንዲደረግ የማሻሻያ ሃሳብ የቀረበ ሲሆን “የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ጽ/ቤት” የሚለው “የኢትዮጵያ ምርጫ ኮሚሽን” በሚል እንዲቀየር ጠይቀዋል – ፓርቲዎቹ፡፡

Related stories   ም.ጠ.ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ከካናዳው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር - ሳህለወርቅ ዘውዴ ከኬንያው ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ ጋር ተወያዩ

Share and Enjoy !

Shares

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *