ZAGGOLE – ዛጎል

“Our true nationality is mankind.”H.G.

ዝሆን ላይ የሚጮህ እብድ ውሻ ብቻ ነው! ህወሓትና ኢትዮጵያን የማፈራረስ ዓላማው!

የአዘጋጆቹ ማስታወሻ፤ ባለፉት ዓመታት ከህወሓት እየኮበለሉ የወጡ የቀድሞ አባላት በርካታ ናቸው። እንዳንዳቸው የሚወጡበት ምክንያት ቢኖራቸውም ህወሃትን በማጋለጥና ማንነቱን ለኢትዮጵያ ሕዝብ በማሳወቅ የአቶ ገብረመድኅን አርአያን ያህል ታላቅ ሥራ የሠራና መስዋዕትነት የከፈለ አለ ለማለት ያስቸግራል። አብዛኛዎቹ የቀድሞው አባላቱ የህወሓትን ምሥጢራዊ አሠራር እና እጅግ አረመኔያዊ ግፍ፤ ኤፈርት በኢትዮጵያ ሐብት ላይ የፈጸመውንና እስካሁንም እየፈጸመ ያለውን የኢኮኖሚ ግፍ፣ ዝርፊያ፣ ሌብነት፣ … የመሳሰሉ ጉዳዮች በአደባባይ ከመናገር ሲቆጠቡ ተስተውለዋል። አንዳንዶቹም በህወሓት ከፍተኛ አመራር ላይ የነበሩ የቀድሞ አባላት ቢሆኑም፤ ኤፈርትም ሲያስተዳድሩ የቆዩ ቢሆኑም ስለጉዳዩ ሲጠየቁ የሚሰጡት ምላሽ አባይ ጸሐዬ ወይም ስብሃት ነጋ ከሚሰጡት ምላሽ ያልተለየ ሆኖ ተገኝቷል። አቶ ገብረመድኅን አርአያ “ዝሆን ላይ የሚጮህ እብድ ውሻ ብቻ ነው” በሚል ርዕስ ያቀናበሩትን ዳጎስ ያለ ሠነድ በድረገጻችን ላይ እንድናትመው በላኩልን መሠረት ከዛሬ ጀምሮ በተለያዩ ክፍሎች ከፋፍለን እናቀርባለን። የዝግጅት ክፍላችን ለአቶ ገብረመድኅን ምስጋናውን እያቀረበ ሌሎችም የህወሓት የቀድሞ አባላት ተመሳሳይ እርምጃ እንዲወስዱና በዚህ መልኩ ከሕዝብ ጋር እንዲታረቁ ሃሳብ እንሰጣለን። ያለ እውነት ዕርቅ የለም፤ ያለ ዕርቅ አብሮ መኖር የለም።


ዝሆን ላይ የሚጮህ እብድ ውሻ ብቻ ነው: ህወሓት እና ኢትዮጵያን የማፈራረስ ዓላማ (ክፍል 1)

የኢትዮጵያ ሕዝብ ከህፃናት እስክ አዋቂው (የወያኔው)፡ ህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (የትግራይ ሕዝብ ነጻ አውጪ ግምባር) ማንነት ካወቁ ብዙ ዓመታት አስቆጥረዋል። ህወሓት ከየት መጣ፣ አላማውስ ምንድን ነው? የሚሉ ጥያቄዎች የሕዝብ መነጋገሪያ ከሆነ አመታት ያስቆጠረ ነው። የኢትዮጵያ ህዝብ፤ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ደሙ አፍስሦ አጥንቱን ከስክሶ አንዲት ሉዓላዊት ኢትዮጵያ ያደረገ ህዝብ፤ በቋንቋ በሃይማኖት በዘር ያልተነጣጠለ ያልተከፋፈለ ህዝባዊ አንድነቱ ተፋቅሮ ተዋዶ በጋብቻ ተጋብቶ ፍቅርና ሰላም ገንብቶ ለስንት ሺህ ዘመናት ከትውልድ ወደ ትውልድ እየተሸጋገረ የመጣ ኢትዮጵያዊነት ጠብቆ፤ የመጣ ኩሩ ህዝብ ኢትዮጵያዊ ነው። የኢትዮጵያ ህዝብ፤ አረንጓዴ፤ ቢጫ፤ ቀይ ሰንደቅ ዓላማው ከስንት ሺህ ዘመናት ተረክቦ የማንነቱ መግለጫ አርማው፤ ተንከባክቦ ሲጠብቃት ጠብቆም ከትውልድ ወደ ትውልድ እያሸጋገር ሰንደቅ አላማችን የሃገርና የህዝብ ኩራት ደማቅ መለያችን ኩራታችን በመሆን የተስፋችን ሕይወት ሆና ኑራለች።

የውጭ ባእዳን ጠላቶች ኢትዮጵያን በመውረር ግብጽ፤ ሱዳን፤ ጣልያን፤ ሊብያ፤ ወ.ዘ.ተ. በተደጋጋሚ ኢትዮጵያን ለማጥቃትና ለመውረር ያደረጉት ብዙ ሙከራዎች በህዝብዊ አንድነትና አኩሪ ጀግንነት ኢትዮጵያዊ የመጡበት ጠላቶች ፊት ለፊት በጦር ሜዳ ተዋግቶ አሸንፎ ወራሪ ገድሎ ቀሪዉም ወደ መጣበት እንዲሸሽ በማድረግ የሚታወቅ የማይበገር ህዝብ ነው። ኢትዮጵያ በባእዳን ጠላቶች አትደፈርም ብሎ ዘብ የቆመው የኢትዮጵያ ህዝብ በታሪክ ማህደር ውስጥ በጠላት የማትደፈር ኢትዮጵያ፤ በዓለም ውስጥ ቀዳሚው ምዕራፍ ይዛለች።

ኢትዮጵያ ብዙ ጠላቶች አሏት፤ በመሬቱ ተፈጥራዊ አቀማመጥም በጠላቶችዋ የተከበበች ናት፤ቢሆንም ቅሉ ጠላቶቿ የኢትዮጵያ ህዝብ ጀግንነት በጦር የማይቀለበስ ህዝብ፤ ወራሪ ጠላት ቢመጣበትም በአንድነቱ ተሰባስቦ ለጠላት እሾህ ተዋጊ ደፋር ህዝብ መሆኑም በሚገባ ስለሚያውቁ፤ እንደ ድሮው ሠራዊታቸው አስከትለው ኢትዮጵያን ወረው የኢትዮጵያን አንድነት ለማናጋት፤ ችሎታና አቅም እንደሌላቸው በመገንዘብ፤ ከምዕራባውያን በተለይ እንግሊዝና አሜሪካ በመተባበር እነ ሱዳን፤ ግብጽ፤ ኢራቅ፤ ሶሪያ፤ ጣልያን፤ ሊብያ፤ ሶማሊያ፤ ወ.ዘ.ተ. ተባብረው ኢትዮጵያን የምናፈርሳት የምንበታትናት በራስዋ ዜጎች በቻ ነው፤ ይህም አስታጥቀን  በተለያዩ ዘዴዎች እየደገፍን የብሄር ጥያቄ፤ እስከ ነፃነት ጥያቄ የሚታገሉ መፍጠር ብቻ ነው ብለው የፖሊሲ አማራጭ አድርገው ባወጡት እቅድ፤ ማ.ገ.ብ.ት. ወይም ማሕበር ገስገስቲ ብሔረ ትግራይ የዚህ ፍሬ ሊሆን በቅቷል። ለዚሁም የመጀመሪያ ተማራኪው አረጋዊ በርሄ ሲሆን ጋሻ ጃግሬው ግደይ ዘርዓጽዮን አስከትሎ ነው።

ህወሓት የትጥቅ ትግሉን ከመጀመሩ በፊት ተዘጋጅቶ ወደ ትጥቅ ትግሉ የገባበት ምክንያት አሉት።

 1. የኢትዮጵያን አንድነትና ሉዓላዊነት ለማፍረስ ብሎም ለመበታተን፤
 2. ሕዝቧ በቋንቋው ሃይማናትና ዘርን ማዕከል በማድረግ የኢትዮጵያን አንድነት በሚያዘጋጀው ፖሊሲ ለመከፋፈል ለመበታተን ከዚሁ መነሻ ህዝቡ በእርስበርስ ጦርነት እንዲተላለቅ አመቺ ነው ብሎ ስላመነበት፤
 3. ተሓህት (ተጋድሎ ሓርነት ሕዝቢ ትግራይ)–ህወሓት የተነሳለት ዓላማ የኢትዮጵያን ሉዓላዊ አንድነት ከፈረስ ህዝቧም እርስበራሱ ወደ ማያባራው ጦርነትና መተላለቅ ከገባ ነፃ የሆነች ትግራይ ወይም የትግራይ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ መንግስት ለመመስረት አመቺና ጥሩ ሁኔታ ይፈጥራል ብሎ ስለሚያምን፤
 4. የህ.ወ.ሓ.ት መስራችና አመራር በትልቁ በአቋም ደረጃ የያዙት ኢትዮጵያን ለመበታተን ህዝቡን መከፋፈል ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር የአማራው ህልውና በማያዳግም ሁኔታ መመታትና ከመሬት መጥፋትና መደምሰስ አለበት ብሎ የሚያምን በመሆኑ ነው፤

ከዚሁም ጎን ለጎን ህወሓት የተነሳበትና መጠቀስ ያለበት ሌላው ዓላማ፤ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ክርስትናም ሆነ የአማራው ቋንቋ የሆነው አማርኛ አብሮ እንዲከስም ማድረግም አለብን፤ የኢትዮጵያን እስልምና ሃማኖትም አብሮ እንዲጠፋ ማድረግ አለብን ብሎ በማመን ነበር። ይህን በተግባር ስንጀምረው ኢትዮጵያዊነት የሚለው የአማራው ካባውም አብሮ ይከስማል ይጠፋል የሚል ነበር። (በህወሓት ፕሮግራም ቀዳሚ ምእራፍ በመስጠት ይህንን በጽሁፍ አስቀምጦታል።)

ህወሓት የትጥቅ ትግሉ እንደጀመረም በሰሜን ኢትዮጵያ የሚገኘው ሕዝብ በተለይ የትግራይ ሕብረተሰብ በግልጽ በማያሻማ መልኩ ከመነሻው ጀምሮ ተቃውሞታል። ህወሓት የተባለው ድርጅትና ፕሮግራሙን አልተቀበለውም ነበር። ከዚሁም የተነሳ የህ.ወ.ሓ.ት. አመራር ቂም በቀል በመያዝ በሰነዘሩት የጥቃት እርምጃ የትግራይ ሕብረተሰቡ በጣም ብዙ የሕይወት መስዋእትነት ከፍሏል፤ ሃብት ንብረቱ በህ.ወ.ሓ.ት. እየተዘረፈ ውርስ ሆነዋል ተብሎ የፈረሰው ቤት ከህ.ወ.ሓ.ት. ግድያ ያመለጠ ትንሽ ቢሆንም ወደ ጎንደር ሸዋ ጎጃም ተበትኗል።

በየካቲት ወር 1968 የተዘረጋው የህወሓት ጸረ-ኢትዮጵያና ጸረ-ሕዝብ ፕሮግራሙ በመጀመሪያ ተቃውሞ የገጠመው በትግራይ ሕዝብ ነበር። በዚሁም የተነሳ የትግራይ ሕዝብ ከፍተኛ የመስዋዕትነት እዳ ከፍሎበታል። በህወሓት አመራር ሕዝቡ ከየቤቱ ከተገኘበት በህወሓት የሃለዋ ወያኔ አባላት እየተያዘ ተረሸነ፣ ንብረቱ ተወረሰ፣ ቤቱ ፈረሰ፣ ሕፃናት አሳዳጊና ወላጅ በማጣት ተበታትነዋል። ፕሮግራሙ እውቅና አንሰጥም፣ እናንተ አሁን በትጥቅ ትግል ተሰማርተናል የምትሉትን ማንነታችሁን አናውቅም፤ በግልጽ የሚታየው በፕሮግራም አቋማችሁ ጸረ-ኢትዮጵያ ሉአላዊነት መነሳታችሁ ይናገራል። እኛ የትግራይ ኢትዮጵያውያን ኢትዮጵያ ሃገራችን በተደጋጋሚ በግብጾች፣ ቱርኮች፣ የሱዳን ማህዲስቶች፣ በጣልያን ስትወረር ሃገራችንን ከጠላት ለመከላከል ሁላችን ኢትዮጵያውያ አማራ፣ ኦሮሞው፣ አፋሩ፣ አሩሲው፣ ወለጋው፣ ትግሬው፣ ወላይታው፣ ሲዳማው፣ ኦጋዴው፣ ከምባታው፣ ወ.ዘ.ተ. ሁሉም ኢትዮጵያዊ አንድም ሳይቀር በዘር በቋንቋ በሃይማኖት ሳንከፋፈ በአንድነት በኢትዮጵያዊነታችን ተባብረን ተደጋግፈን ሃገራችን ኢትዮጵያ በጠላት እንዳትወረር ደማችንን አፍሰን አጥንታችንን ከስክሰን ነፃነቷን የጠበቀች ኢትዮጵያን ለልጆቻችን አስረክበናል። ተ.ሓ.ህ.ት. የምትሉት የምትናገራት  ነጻዋን በታሪኳ ገናናዋን ኢትዮጵያ የቀይ ባህር ባለቤት፣ የቀይ ባህር ንግሥት ኢትዮጵያ በመካድ ኢትዮጵያ የተፈጠረችው በዳግማዊ ምኒሊክ ታሪኳ ከ100 ዓመት ያነሰ ነው፤ ኢትዮጵያ የምትባል ሃገር እንዳልነበረች በየቦታው እየተዘዋወራችሁ ለትግራይ ህብረተሰብ ትሰብካላችሁ፤ አማራ የትግራይ ህዝብ ጠላት ደመኛ ጠላት የምትሉት ለኛ ጠላት ሳይሆን ወንድማችን  ሥጋችን ኢትዮጵያዊ ወንድማችን ነው እያለ የትግራ ሕዝብ ገና ከጅምሩ ይቃወም ነበር።

Related stories   በአዲስ አበባና በኦሮሚያ ከተሞች የሽብር ጥቃት ለመፈፀም ሲንቀሳቀሱ የነበሩ የሽብር ቡድን በቁጥጥር ስር ዋለ- ትህነግ “ክብሪት” የተባለ ገዳይ ቡድን ማቋቋሙ ታወቀ፣

በመቀጠልም፤ ዛሬ ለትግራይ ሕዝብ ታግለን ትግራይን ነፃ አውጥተን የራሷን መንግሥት ትመሰርታለች የምትሉት የተሓህት-ህወሓት መሪዎች ጣልያን ኢትዮጵያን በወረረበት ይህን በናንተ ፕሮግራም የተካተተውን ለአስተዳደሩ ለቅኝ ገዥነት እንዲመቸው ያስቀመጥው ሃገርና ሕዝብን ከፋፍሎት የነበረውን በጣልያን እቅድ የኢትዮጵያን አንድነት ለማጥፋትና ለመደምሰስ ነው። ታዲያስ እናንተ ከጣልያን የከፋችሁ እንጂ የተሻላችሁ አይደላችሁም፤ በማለቱና በግልጽ በመናገሩ ከሐምሌ 1968 ጀምሮ የህወሓት መሪዎች ሰፊ የመግደልና የማጥፋት እርምጃ  በትግራይ ሕብረተሰብ ላይ በማጠናከር ሕዝቡን አጠፉት፤ ሃብት ንብረቱ ወረሱት፤ ቤቱ አፈረሱት፤ አወደሙት።

በዚህ ወቅት የነበሩት ዋና አመራሮች፤

አረጋዊ በርሄ፣ የድርጅቱ ሊቀመንበርና ወታደራዊ አዛዥ፤

ግደይ ዘርአጽዮን፣ ም/ሊቀመንበር፤

አባይ ፀሃየ፣ የፖለቲካ መሪ፤

ስብሃት ነጋ፣ የአረጋዊ በርሄ አማካሪና የሃለዋ ወያነ ሃላፊ፤

ስዩም መስፍን እና ተጨማሪ ዋና ተባባሪ መለስ ዜናዊ ነበሩ።

እነዚህ ስድስቱ ታጋዮች በሕዝብ ላይ የሚወስዱትን እርምጃ ተመካክረው በአንድነት ተሰባስበው ይወስናሉ፣ በተግባርም ይፈጽማሉ። በ1969 የፈጸሙትን የግፍ ግፍ ለመጥቀስ፤ ጣልያን 1928ዓም ኢትዮጵያን ዳግም በወረረበት ጊዜ ኢትዮጵያውያን ከተለያዩ የሃገሪቱ ክፍል ክተት በማለት ሃገራቸውን ከወራሪ ጠላት ለመከላከል በሞላው ሃገራችን በተለያዩ የጦርነት አውድማ ተሰልፈው ወራሪውን ጠላት በአምስት ዓመት የአርበኞች ታጋድሎ ተሸንፎ ጓዙን ሳይጠቀልል በውርደትና በሃፍረት ተሸንፎ ወደመጣበት ሃገሩ ጣልያን እንደሸሸ ከገድላዊ ታሪካችን ተምረናል። የትግራይ ሕዝብ ከወንድሞቹ ኢትዮጵያውያን ጎን ተሰልፎ ለሃገር ሉዓላዊነትና ክብር ሲል መስዋእትነት ከከፈሉት ኢትዮጵያውያን አንዱ ነው። የተሓህት-ህወሓት መሪዎች ይህ የሃገር ክብር የተቀደሰ ጀግንነት አልተቀበሉትም። ለምን የትግራይ ሕዝብ ጸረ-ጣልያን ሆኖ ተሰለፈ በማለት የተናደዱት በአረጋዊ በርሄ የሚመሩ የተሓህት-ህወሓት መሪዎች አርበኞች አዛውንቶችን ከየቤታቸው በመልቀም ከያሉበት በማሰር በቀን ከእርሻ ቦታው ሌሊት ከቤቱ በማፈን ሃለዋ ወያነ አስገብተው ደብዛቸው በማጥፋት ማንነታቸው የውሃ ሽታ ሆኖ እንዲቀር አድርገዋል። ከነዚህ ከተገደሉት ብዛታቸው ባይታወቅም ለአብነት ከሚጠቀሱት መካከል፤

ፊታውራሪ በጹእ ወ/ጊዮርጊስ፤ የ82 ዓመት አዛውንት፣

ደጃዝማች ዘገየ አዛውንት ከነልጆቻቸው፣ ባቡ ዘገየ፣

ፊታውራሪ እምብዛ፣

ፊታውራሪ አጽብሃ፣

አስር አለቃ ገብረሥላሴ፣ አስር አለቃ ገብረዝጊ አለማየሁ እነዚህ ለአብነት ይበቃሉ።

እነዚህ የኢትዮጵያ አርበኞች ከያሉበት እየተያዙ የተገደሉት ከጣልያን ጋር ለምን ጦርነት ገጠማችሁ ተብለው እንጂ አዛውንቶቹ ያጠፉት አንድም ጥፋት የለም። ይህ ሲሆን እውነት ተሓህት-ህወሓት ለትግራይ ሕዝብ የቆሞ ነው? መልሱ፣ አይደለም ነው። ተሓህት-ህወሓት በፀረ-ኢትዮጵያ ባእዳን የተመሰረተ ድርጅት ነው። ለስልጣን ያበቁትም እነሱ ናቸው። ተሓህት-ህወሓት በትግራይ ሕዝብ ላይ የፈጸመው ግፍ እጅግ ዘግናኝ ስለሆነ ሌላው ቀርቶ ፈዳያን ወይም አትፍቶ ጠፊ አሸባሪ (terrorist) ቡድን በማቋቋም በየአውራጃ ያፈሰሰው ደም የትናንት ትዝታ ነው። የትግራይ ሕዝብ በተሓህት-ህወሓት ንብረቱ ተዘረፈ፣ መሬቱ ተነጠቀ፣ ቤቱ ፈረሰ፣ ለችግርና መከራ ተዳረግ፣ ተገደለ፣ ተሰደደ።

ለዚህ ዋና ተጠያቂዎቹ የህወሓት አመራር፣

አረጋዊ በርሄ፣

ግደይ ዘርአጽዮን፣

አባይ ፀሃየ፣

ስብሃት ነጋ፣

ስዩም መስፍን እና መለስ ዜናዊ ናቸው።

እነዚህም ቢሆኑ ተከታትለው የመጡ፤

ስየ አብርሃ፣

                                                                           አውአሎም ወልዱ፣

ገብሩ አስራት፣

ዘርአይ አስገዶም፣

ጻድቃን ገብረተንሳይ፣

አስፍሃ ሃጎስ፣

አርከበ እቁባይ፣

ተወልደ ወ/ማርያም ናቸው። እነዚህ ደግሞ በሕብረተሰቡ ውስጥ ግድያ በመፈጸም እና ሕዝቡ ጥሮ ግሮ ያፈራውን ሃብት ንብረት ለህ.ወ.ሓ.ት ውርስ ተደርጓል በማለት በመዝረፍ ተባባሪና አስተባባሪ በመሆን በትግራይ ሕዝብ ወንጀል ፈጽመዋል። በታጋዩ ላይ በፈጸሙት ወንጀል ተጠያቂ ናቸው። በፈፀሙት አሰቃቂ ተግባራቸው በወንጀሉ ይጠየቃሉ። በተለየ ደግሞ የኢትዮጵያን ሉአላዊነት በተመለከተ ከላይ የተጠቀሱት ዋና መሪዎች የኢትዮጵያን አንድነት፣ ሉአላዊነት፣ መሬት አሳልፎ ለሱዳን በመሸጥ የወያኔ አመራር ቀዳሚ ተግባራቸው አደርገው ሲንቀሳቀሱ፣ እነዚህ የተጠቀሱት የማ/ኮሚቴ አባላት ተባባሪ በመሆን በኢትዮጵያና ሕዝቧ ላይ በርካታ የካሃዲነት ተግባራት ሲፈጽሙ የቆዩ ናቸው። የኤርትራን መገንጠልም ተባብረው ከነአረጋዊ በርሄ ጋር በመወገን ኤርትራን በማስገንጠል በሃገር ላይ ጉዳት አድርሰዋል። ለጊዜያዊ ጥቅም ብለው ከሱዳን መንግሥት በጀነራል ጃፋር ኒሜሪ (የሱዳን ፕሬዚዳንት ከመሆኑ በፊት በወቅቱ የነበረው የገዳሪፍ ገዥ) በ1975ዓም መስከረም ወር ከላይ የተጠቀሱ የህ.ወ.ሓ.ት መሪዎች እና የሱዳን ባለሥልጣናት በቋጩት ውል መሰረት የኢትዮጵያ ለምና ታሪካዊ መሬት በጸረ ኢትዮጵያዊነት የተነሱት የወያኔ መሪዎች አሳልፈው ለባእድ ሃገር ለጊዜዊ ጥቅም ሽጠዋል።

ይህም ምንም ህዝባዊ ውክልና ሳይኖራቸው ትግራይን ለማስገንጠል የተነሱ ከሃዲ ባንዳዎች፤ ዛሬ ኢትዮጵያን እየገዛ ያለው ቅኝ ገዢ ወያኔ ህወሓት ለሱዳን ለመስጠት ደፋ ቀና እያሉ ይገኛሉ። በዚሁስ የኢትዮጵያ ህዝብስ የሚወዳት የታሪክ ባለቤት ሃገሩ እየተሸራረፈች  ለባዕድ ሃገር ለሱዳን እየተሸጠች ባለችበት ጊዜ ምን እያለ ነው? የህ.ወ.ሓ.ት. አመራር ድሮ የነበሩ አሁንም ያሉ የኢትዮጵያን ሉዓላዊንት የኢትዮጵያን ዳር ድንበር በዓለምአቀፍ የተከበረ ወሰን በወያኔ ባንዳ መሪዎች ለባእድ አሳልፎ መስጠት ከባድ ክህደት ኢትዮጵያና የኢትዮጵያ ህዝብ ሃገርና ህዝብ አሳልፎ መሸጥ ተፈጽሞበታል። ወያኔው ህ.ወ.ሓ.ት. ኢትዮጵያና ህዝቧን አጠፋለሁ በማለት ከደደቢት በረሃ ይዞት በመጣ ጸረ ኢትዮጵያ አቋሙ ሥልጣን ከያዘበት ኢትዮጵያን በቅኝ ግዛቱ ውስጥ ከተቆጣጠረ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ያወደመ ያፈረሰ ስርዓት ነው።

Related stories   የፌደራልና የክልል ፖሊስ አዲስ የአደረጃጀት ሰነድ ለጠቅላይ ሚንስትሩ ቀረበ

በህ.ወ.ሓ.ት. የፖለቲካ ወይም የፖሊሲ ልዩነት ተፈጥሮ ወይም ታይቶ አያውቅም፤ ህወሓት የሚከተለው ፖሊሲ ያው ነች፤ ፀረ ኢትዮጵያ ሉዓላዊነት፣ ፀረ ህዝብ ከፋፋይነት፤ ፀረ-ዲሞክራሲ ነው፤ አሁንም በሥልጣን ያሉትን ጨምረን አንድም የራእይ ልዩነት ያለው ግለሰብ አመራር የነበረው የለም። ችግራቸው የሥልጣን ሽኩቻ ነው፤ ይህም ገና ከትግሉ መነሻ ጀምሮ በማያቋርጥ እስከ አሁኑ ጊዜ በግልጽ የሚታየው ነው። በአሁኑ ጊዜ አረጋዊ በርሄም ሆነ ሌሎቹ የተባረሩ የሚናገሩት ለኢትዮጵያ ህዝብን ለማታለል፤ በትግሉ ጊዜ ብዙ ልዩነት ነበረን ሲሉ ይደመጣሉ፤ ልዩነታችሁ ምን ነበር ተብለው ቢጠየቁ ግን መልስ የላቸውም። በተለይ አረጋዊ በርሄ ከድርጅቱ እስከ ተባረረ ሓምሌ ወር 1977ዓ.ም. በዋናነት፣ በበላይነት ሲመራው የነበረ እርሱ ነው፤ ፕሮግራሙን ተንከባክቦ ያቆየው እሱ ነው፤ የሚወጡ አዳዲስ ፖሊሲ በሱ ነው የተፈጸመው፤ በድርጅቱ ውስጥ አንድም አመራር የአረጋዊ በርሄ ሃሳብ የሚቃወም የለም፤ ሁሉ በእጁ ስለሆነም ዛሬ የሚናገረው ውሸት መሆኑ መታወቅ አለበት። ይህ ሁሉ የሚዘባርቀው፤ህ.ወ.ሓ.ት. ወንጀለኛ ድርጅት ነው በዘር ማጥፋት ወንጀል ይጠየቃል፤ ለወልቃይት ጠገዴ በጉልበቱ በመሪነት፤ እንዲሁም የሰሜን ወሎ ወደ ትግራይ በማካለል የመሬት መስፋፋትና ወረራ የፈጸመው እሱ ስለሆነ ከተጠያቂነት ለማምለጥ ባፈሰሰው የንፁሃን ዜጎች ደም ተጠያቂነት ለመሸሽ፤ በፈጠረው ዘዴ ህዝብ መታለል የለበትም።

አረጋዊ በርሄ በህወሓት ወስጥ ፈላጭ ቆራጭ ሆኖ የመጣበት ማህበረ ገስገስቲ ብሄረ ትግራይ (ማገበት) ከተመሰረተበት እለት መስከረም 1967 ጀምሮ ተሓህት-ህወሓት የትጥቅ ትግሉን ከጀመረበት የካቲት 11፣ 1967 አንስቶ እስከ 1977 መጨረሻ ህወሓትን የሚዘውረው የነበረ  በዚሁ ፀረ-ኢትዮጵያ አንድነትና ፀረ-ሕዝብ ግለሰብ ነበር። በድርጅቱ የሚፈጸሙ ጉዳዮች የሱን ይሁንታ ማግኘት አለባቸው እሱ ካልፈቀደ ደግሞ ይሰረዛል።

አረጋዊ በርሄ ገና ትግሉ ሳይጀመር የድርጅቱን ፕሮግራም በዋና ሃላፊነት ያዘጋጀ ነው። ይህ ፕሮግራምነው ዛሬ ኢትዮጵያ እያፈረሰ እየበወዘ ሃገራችን ኢትዮጵያ በማትወጣው ችግር  ዳርጓት ያለው። የሰሜን ጎንደር ግዛቶችን አማራው የሚኖርበት ለብዙ ሺህ ዓመታት የአማራ መሬት ከዘር እስከ ዘር ከትውልድ ወደ ትውልድ እየተሸጋገር የመጣው የአማራው ባህልና ማንነት እየጠበቀ የመጣው የትግራይ መሬት በሚል አጉል የመስፋፋት ዘይቤ አማራውን ዘሩ በማጥፋት ያለቀው በህ.ወ.ሓ.ት. አመራር ታሪክ ዘግቦታል። ለዚሁ የሰው እልቂት ዘር ማጥፋት ተጠያቂው የህ.ወ.ሓ.ት መሪዎች ከ1967 ዓ.ም. እስከ ዛሬዋ እለት ያሉትን አመራር ተጠያቂ ናቸው። ነብሱን አይማረውና ባለቀንዱ የባንዳ ዘር መለስ ዜናዊ እና ሌሎች የሞቱም በወንጀሉ ይጠየቃሉ ማለት ነው። ጠገዴ፣ ጠለምት፣ ወልቃይት፣ ቃፍታ፣ ሁመራ፣ ህ.ወ.ሓ.ት በፕሮግራሙ ውስጥ (የእጅ ጽሁፉ የአቶ አረጋዊ በርሄ ነው) ከሰሜን ወሎም ራያና ቆቦ፣ ወልዲያ፣ አፍላ ደራ ወዘተ አጠቃላይ አለውሃ ምላሽ ተብለው የሚታወቁት የወሎ ግዛት ወደ ትግራይ አጠቃሎ ካርታውን ያዘጋጀው፣ መልክአ ምድሩን የለወጠው አሁን በትግራይ ክልል የተጠቃለሉት በአረጋዊ በርሄ የተዘጋጀው ነው። ይህን ለማረጋገጥ መቅድም  በሚለው (v) ቁጥር ነው (ገጽ 5) እንመልከት።

ህወሓት ትግሉን እንደጀመረ የቅድሚያ ትኩረት የሰጠው ሰሜን ጎንደርን ነበር። ይህንን የሰሜን ጎንደር ለም መሬት ለመያዝና ወሮ ወደ ትግራይ ለማጠቃለለ በወቅቱ መጠሪያው ተጋድሎ ሓርነት ህዝቢ ትግራይ (ተሓህት) አስቀድሞ በመዘጋጀት ከነዚህም የሚታዩት ከነበሩት ተጨባጭ ሁኔታዎች፤ (ጊዜው ከ1969 ዓ.ም መጀመሪያ ጀምሮ ነው)፤

 • የዚህ ድርጅት የሕዝብ ግንኙነት አባላት ሰርገው በመግባት በየቦታው የሚኖሩትን አማራ ታላላቅ ሰዎች የቦታው ታሪካዊ ጥናት የሚያውቁ፤ በህዝቡ ተቀባይነት ያላቸው፤ተናግረው ህብረተሰቡ የሚቀበላቸው ጥናት በማካሄድ፤
 • የታጠቁ ሰዎች ብዛታቸውም ሆነ ስሜታቸውን ማጥናት፣ ያላቸውን ሃብትና ንብረት የአካባቢውን ኗሪ ብዛትም ጭምር ማጥናት፣ ይህ የትግራይ መሬት ነው ቢባሉ የሚያስከትሉት ችግር ማወቅ ማጥናት በተናጠል ማነጋገር ወ.ዘ.ተ. የሚሉትን ተሸክመው መንቀሳቀስ ተጀመረ፤
 • ይህንን የሰሜን ጎንደር ለም መሬት በጉልበትና በሃይል ለመውረር በአማራው ላይ ከባድ ጥቃት መፈጸም ግዴታ መሆኑ አስቀድሞ ተይዞ የትግራይን ሕዝብ ድጋፍ የሚፈልጉ የተሓህት አመራር በወቅቱ የነበሩ አመራር፣ አረጋዊ በርሄ፣ ስብሃት ነጋ፣ አባይ ፀሃየ፣ ስዩም መስፍን፣ ግደይ ዘርአጽዮን፣ በአራቱ መአዘን ተበታትነው አማራ የትግራይ ሕዝብ ጠላት መሆኑን፣ የትግራይን መሬት ነጥቀው የትግራይን ሕዝብ ለችግርና መከራ የደረጉት ደመኛ ጠላቶችህ ሲሆኑ የነጠቁህን መሬትህ ወልቃይት፣ ጠገዴ፣ ጠለምት፣ ቃፍታ፣ ሁመራ፣ እንዲሁም በሰሜን ወሎ ከአለ ውሃ ምላሽ የተነጠቅነውን መሬታችንን ለማስመለስ የትግራይ ሕዝብ የፈጠርከው መሪ ድርጅትህ ተሓህት ድጋፍህን እና እርዳታህን እንፈልጋለን፣ እያሉ ሕዝብ እየሰበሰቡ ተቆርቋሪ በመምሰል እያለቀሱ የትግራይን ሕዝብ አስተሳሰብ ለመቀየር ከፍጠኛ እንቅስቃሴ አደረጉ። ቢሆንም ከትግራይ ሕዝብ ያገኙት መልስ የሚከተሉት ነበሩ።
 • አማራ ጠላታችሁ ነው የምትሉን ከእውነት የራቀ ነው። አማራ የትግራይ ሕዝብ ጠላት አይደለም፣ ሆኖም አያውቅም። በአንድነት ሁነን ኢትዮጵያን ከብዙ የውጭ ወራሪ ሃይል አድነናል ተከላክለናልም። በዚህም አማራና ትግሬው ኢትዮጵያዊ ማተባችን በጋብቻና በባህል የተሳሰረ ሕዝብ ነው። ስለዚህ አማራ የኛ ወገን ትግሬውም የአማራ ወገን ነው።ልዩነት ጥላቻ ቅራኔ የለንም አንድ ኢትዮጵያዊ ህዝብ ነን። ለወደፊቱ አይኖርም፤ አብረን እንኖራለን ።
 • ስለመሬቱ የምትናገሩት የትግራይ አልነበረም፤ ሆኖም አያውቅም። ስለሆነም የሰሜን ጎንደርና የሰሜን ወሎ የትግራይ መሬት አልነበረም፤ አሁንም አይደለም፤ ከትግራይ የተነጠቀ መሬት የለም። የራሳቸው መሬት ነው። የኛ የትግራይ አይደለም፣ አልነበረም። የትግራይ ሕዝብ በተናገረው እውነተኛ ሃሳቡ ቀጠለ። ከሃቀኛ ሃሳቡ ፍንክች ባለማለቱ የወያኔው አመራር ግራ ተጋባ ጸረ ትግራይ ህዝብም መንቀሳቀስ ተጀመረ፤
 • ስለ ተሓህት የትግራይ ሕዝብ ድርጅት ነው የምትሉት፣ የታጠቀ ሃይል የትግራይ ሕዝብ ድርጅት አይደለም፣ አናውቀውም፤ የራሳችሁ የናንተው ነው፤ የትግራይ ሕዝብ ይህንን ድርጅት ከየት እንደመጣ፣ ማን እንደፈጠረው የምናውቀው ነገር የለም፣ እውቅናም አንሰጥም፣ በማለት የማያወላውል መልስ አግኝተው ራሳቸውን ደፉ። በዚሁ ጊዜ ግንቦት ወር 1968ዓ.ም አካባቢ የትግራይ ህዝብን በተናጠል ለማጥቃት የተነሱት እነ አረጋዊ በርሄ፤ እነዚህ የተህሓት መሪዎች በትግራይ ሕዝብ ላይ አጸፋዊ ጥቃት በተቀናጀ መልኩ እንዲፈጸም ፖሊት ቢሮ፣ ማለትም በአረጋዊ በርሄ በሚመራው ግደይ ዘርአጽዮን፣ አባይ ፀሃየ፣ ስብሃት ነጋ፣ ስዩም መስፍን ተሰብስበው በሶስት እቅዶች ላይ ተሰማሙ፡
  • የከተማውንና የገጠር ሕዝብ ግንኙነት በሕዝቡ ሙሉ የጥናት ክትትል እያደረጉ ለግደይ ዘርአጽዮን አንዲያቀርቡ፤
  • የከተማውን ኗሪ የሚያጠቃ ፈዳያን “አጥፍቶ ጠፊ” አሸባሪ (terrorist) እንዲቋቋም፣ ስልጠናም እንዲያገኝ፣
  • ክብሪት የሚባል ጉጅሌ ገዳይና አፋኝ ቡድን እንዲቋቋም ተስማሙ። ይህ ጉጅሌ 12 ሰዎች የያዘ ሲሆን 7 ታጋዮች 5 ሚሊሽያ ሆኖ ተመሰረተ። የሚሊሽያው ዋና ተግባሩ መንገድ መሪ የሚፈለጉ ሰዎች ጠቁሞ ከተራ ቁጥር 1 እስከ 3 የተጠቀሱትን ተግባራዊ እንዲሆኑ ተደረገ ።
Related stories   አውሮፓ ህብረት እየተሽኮረመመ ታዛቢ ሊልክ ነው

በዚሁም ጊዜ  የነበሩት (06) ሓለዋ ወያነ፣ ቀደም ሲል የነበሩት ሰፋፊ ቤቶች እየተፈለጉ ነዋሪውን በማባረር ሲጠቀሙበት የነበሩትን በመተው ሰው በማይንቀሳቀበት ቦታ ተመረጡ፤ እነዚህም፤ ሽራሮ ወረዳ ሸሸቢት ቡምበት፣ ሱር፣ ወርዲ፣ ፃኢና አዲበቅሎ፣ ዓዴት፣ ዓዲ ጨጓር፣ በለሳ፣ ማይሃምቶና ባኽላ ሳምረ ናቸው። እነዚህን ሰፋፊ መግደያ ቦታዎች በአዲስ ዘዴ  በመስራት ተገነቡ። ይህም በግደይ ዘርአጽዮን መሪነት ከመሬት በታች 2 ሜትር ተቆፍረው እንዲሰሩ ከ200 ያላነስ እስረኛ የሚታሰርበት አንዲት ጠባብ መስኮት ያላት ሆኖ እንዲሰራ  በህ.ወ.ሓ.ቱ. ም/ሊቀመንበር ግደይ ዘርዓጽዮን ትእዛዝ መሰረት ከላይ በተጠቀሱ ቦታዎች ለመጀመሪያ ጊዜ ተሰሩ። በትእዛዙ መሰረትም ሥራው ተጠናቀቀ። ይህ ጊዜ 1969ዓም መጨረሻ ነበር። የትግራይ ህዝብም ያለቀው የተገደለው በእነዚህ ቦታ ነው። ዛፍ በእርጥቡ እየተቆረጠ ተፈልጦ በእሳት በማቀጣጠል በጠባብዋ መስኮት በመልቀቅ የሰው ልጅ ፍጡር በጢሱ ታፍኖ ያለቀው አምላክ ይቁጠረው። የዚች አሰቃቂ ግድያም የግደይ ዘርዓጽዮን ብልሃት ናት። ለዚህ ክፉ የወንጀል ግድያም ይጠየቅበታል። ይህ ክፉ አገዳደል በተለይ በአማራው ህዝብ በስፋት የወያኔ መሪዎች በመጠቀማቸው የአማራውን ዘር አጥፍተዋል።

ክብሪት ተንቀሳቃሹ ጉጅሌ፡ ሆኖ ሲመሰርቱ፣ በ16 ጉጅሌ ነበር የተመሰረተው። የእነዚህ መሪዎችም በአርከበ እቁባይ፣ አሰፋ ማሞ፣ ሰአረ መኮንን፣ ሽሻይ በላይ (አመደ)፣ ታደሰ ጋውናይ፣ ወዘተ በመደራጀት በየገጠሩና በየከተማው አካባቢ እንዲሁም በየወረዳው በሌሊት ተሽለኩልከው በመግባት የሚፈልጉትን ሰው ወንድ፤ ሴት አፍነው በማውጣት ሃለዋ ወያነ ታስሮ/ታስራ በማስገባት እዛው እርምጃ ይወሰድበታል። (06) ሓለዋ ወያኔ የገባ ሰው ሁሉ በሕይወት ወደ ቤቱ አይመለስም። ሕዝብ የሚገደልበት መግደያ የሲኦል ገሃነብ ነው። በገጠሩ ነዋሪ በፈለጉት ሰአት በመሄድ ኗሪውን ሰላማዊ ዜጋ ኢትዮጵያዊ በማሰር ንብረቱን በመውረስ እየታሰረ ሃለዋ ወያኔ ገብቶ ይገደላል፤ ቤት ፈረሰ ልጆች ካለ አባትና እናት ተበታትነው ቀሩ፤ በጅምላ ጉድጓድ በጥይት ይረሸናሉ። መግደያ ጉድጓዳቸውም የሚቆፉራት ራሳቸው ተገዳዮቹ ናቸው።

ፈዳያን የተባለው በብስራት አማረ የሚመራው አጥፍቶ ጠፊ ሽብርተኛው ክፍል የተመሰረተው ከሓምሌ ወር 1969 ዓ.ም ጀምሮ በየከተማው አውራጃዎች አድዋ፤ መቀሌ፤ ሽሬ፤ አክሱም አዲግራት፤ ውቅሮ ሁለት አውላእሎ፤ ወዘተ እንዲሁም በወረዳዎች እየገባ በመቶዎች የሚቆጠሩ በየከተማውና በወረዳው በቀን ተመሳስሎ በመግባት በየመጠጥ ቤቱ ሻይ ቤት በማኸል ከተማ  ቤተ ክርስትያን ውስጥ አጋጣሚው ሲመችለት አፍኖ በማስወጣት የስንቱን ንጹሃን ዜጎች በጠራራ ቀን ደማቸው ፈሰሰ፤ ተገደሉ።

በዚሁ ፈዳያን የተሰማሩ አመራር፣ አረጋዊ በርሄ፣ አድዋ፣ አባይ ፀሃየ፣ አክሱም፣ አርከበ እቁባይ፣ አዲግራት፣ ስዩም መስፍን፣ ውቅሮ፣ ስብሃት ነጋ፣ ተምቤን፣ በሽብርተኝነት ተሰማርተው ሰዎች ገድለዋል። ግደይ ዘርአጽዮን እንትጮ፣ ሰለክላካ፣ ራማ፤ ኩሓ የስንት ሰው ሕይወት ከግብረአበሮቹ ፈዳያን ጋር አጠፋ። ይህ የወያኔ ጥቃት ከተሓህት-ህወሓት በትግራይ ሕዝብ የማጥቃት  ዘመቻው በተለያየ መልኩ ቀጠለ። ግደይ ዘርዓጽዮን አክሱም ከተማ የጉጅሌ መሪ በመሆን ሁለት የአብርሃ ወአፅብሃ ሁለተኛ መለስተኛ ደረጃ አስተማሪዎች መምህር አበበ፤ መምህር መላኩ መንገሻ የተባሉ አስተማሪዎች በመግደሉ ተወገዘ። ተመልሶ አክሱም የሚገባበት እድልም የለውም። ይህ ሰው በተፈጠረው ውግዘት ለወላጆቹም ግደይ በፈጸመው ወንጀል ቁርሸው ትቶ አልፈዋል። የግደይ ጣጣ በዙ ነው፤ ግደይ ዘርዓጽዮን ሱር ሓለዋ ወያኔ ታስረው የነብሩት ብዙዎቹ አማራ ቀሪዎቹ የትግራይ ሰዎች በየታሰሩበት ከመሬት በታች የጉድጓድ እስር ቤቶች የዓየ እንጨት በማቀጣጠል እንጨቱ እየተቀጣጣለ በትንሽዋ ቀዳዳ መስኮት የገባው ጢስ እዛው ጉድጓዱ የታሰረው ንፁሃን ዜጎች በጢሱ ታፍነው ሲያልቁ የተመለከተው በህዝብ ግኙኝነት ክፍል የሚሰራ ታጋይ ዓለም ወልደገሪማ የሚባለው የቀ.ኃ.ሥ. ዩኒቨርሲቲ የ4ኛ ዓመት ኢኮኖሚክስ ተማሪ የነበረው፤ ግደይ ዘርዓጽዮንን ኢሰብአዊና አረመኔያዊ ግድያ ህዝቡ ላይ ሲፈጽም፣ ሕዝቡን ሲፈጅ በዓይኑ በማየቱ በድርጊቱ አወገዘው። ግደይ ግን ቂሙን ቋጥሮ ቆይቶ፤ በስራ ምክንያት ዓለም ወልደገሪማ ወደ ሪጅን 2 የሚሄድ መሆኑ ስላወቀ ዓዴት የሚገኘ ሓለዋ ወያኔ 06 ለብስራት አማረ ደብዳቤ ፅፎ፤ የደብዳቤዋ የውስጥ ይዘትዋ፤ ዓለም ወልደገሪማ ይህች ደብዳቤ እንደሰጠ ተቀብለህ ወዲውኑ እሰረው፣ ከዛ ረሽነህ ግደለው የምትል ነበረች። ዓለም ወልደገሪማም የመገደያውን የፍርድ ወረቀት ተሽክሞ ሂዶ አዲበቅሎ ዓዴት ወዲያውኑ በጥይት ተደብድቦ ተገደለ። ይህች የግፍ ግድያ ብዙም ሳትቆይ እጃቸው ለደርግ የሰጡ የአክሱም ልጆች ታጋይ ነበር፤ ዓለም ወልደገሪማ በግደይ ዘርዓጽዮን እንደተገደለ ለወላጅ አባቱ ነገሯቸው። ምህረይ (ቄስ) ወልደገሪማም የአክሱም ህዝበ አዳም በልጃቸው በህ.ወ.ሓ.ት. መሪው የተፈጸመው ግፍ በየቤተክርስትያኑ ከማጋለጥ ቀጠሉበት። የዓለም ወልደገሪማ ወንድሞች ደማቸው ለመበቀል፤ ጊዜያቸው እየጠበቁ ናቸው። ወደ ዋናው ርዕሳችን ስንመለስ። (በቀጣይ እናትማለን)።

ገብረመድህን አርአያ፣ ፐርዝ፣ አውስትራሊያ

ምስጋና ለጎልጉል ድረ ገጽ ጋዜጣ