• 450 ሺሕ ያህል ታካሚዎች አሉ

ለቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሌኒየም ሜዲካል ኮሌጅ የልብ ሕክምና ማዕከል በ120 ሚሊዮን ብር የተገዛው የልብ ሕክምና ማሽን (ካትላብ) መስከረም 8 ቀን 2010 ዓ.ም. ተመርቆ አገልግሎት መስጠት ጀመረ፡፡ በዓይነቱ ዘመናዊ የሆነው ይህ ማሽን ተመርቆ አገልግሎት መስጠት የጀመረው በቅዱስ ጴጥሮስ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ውስጥ ነው፡፡

በሆስፒታሉ የተተከለው ይህ ማሽን ከልብና ከደም ሥር ጋር የተያያዙ ሕክምናዎችን የሚሰጥ ሲሆን፣ በአምስት ቀናት ውስጥ ከ30 እስከ 40 የሚሆኑ ታካሚዎችን ያዳርሳል፡፡

የልብ ሕክምና ክፍሉ የጽኑ ሕሙማን፣ የማገገሚያና ለልዩ ልዩ ሥራዎች የሚውሉ ክፍሎች ያሉት ሲሆን፣ በአገር ውስጥና በውጭ አገር የሠለጠኑ 21 ስፔሻሊስት ሐኪሞችና ነርሶች እንዲሁም ሌሎች የጤና ሠራተኞች ተመድበውለታል፡፡ የባዮ ሜዲካል ኢንጂነሮች በዚሁ ማሽን ዙሪያ ለመሠልጠንም አጋጣሚ ተፈጥሮላቸዋል፡፡

የጤና ጥበቃ ሚኒስትር ይፍሩ ብርሃነ (ፕሮፌሰር) ማሽኑን ከመረቁ በኋላ እንደገለጹት፣ ኢትዮጵያ ውስጥ በዚህ ዓይነት ማሽን መገልገል የሚፈልጉ ታካሚዎች ቁጥር ወደ 450 ሺሕ ይጠጋል፡፡

በቅዱስ ጴጥሮስ ሆስፒታል ውስጥ ከተተከለው የልብ ሕክምና ማሽን ቀድሞ በመቐለ አይደርና በጥቁር አንበሳ ሪፈራል ሆስፒታሎች ተተክለው አገልግሎት እየሰጡ እንደሚገኙ ሚኒስትሩ ጠቁመው፣ በቀጣይም ተመሳሳይ ማዕከላትን በመገንባት ለሕሙማኑ ተደራሽ እንዲሆን ይሠራል ብለዋል፡፡

እንደ ሚኒስትሩ አገላለጽ፣ በኢትዮጵያ ዓይነታቸው ብዙ የሆኑ የሕክምና መሣሪያዎች በዕርዳታና በግዥ ቢገቡም፣ በጥገና በመለዋወጫ ዕጦት ይፈተናሉ፡፡ ይህንን ለመቅረፍ የባዮሜዲካል ኮሌጅ ኢንጂነሪንግ ተማሪዎች መሣሪያዎችን እየተለማመዱና እየሠለጠኑበት ወደ ሥራ የሚገቡበት ሁኔታ እየተመቻቸና ግዢ ላይም የሕክምና መሣሪያ ከአንድ ቦታ ብቻ የሚመጣበትና ተማሪዎች በዚሁ የሚሠለጥኑበት ሁኔታ እየተፈጠረ በመሆኑ ችግሩ ይቀላል፡፡

የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሌኒየም ሕክምና ኮሌጅ የሕክምና ዘርፍ ምክትል ፕሮቨስት ብርሃኔ ረዳኢ (ዶ/ር) የዓለም ጤና ድርጅት ሪፖርትን ዋቢ በማድረግ እንደገለጹት፣ በልብና በካንሰር በሽታዎች ላይ ከወዲሁ አስፈላጊው ዕርምጃ ካልተወሰደ ከአሥር ዓመታት በኋላ በወረርሽኝ ደረጃ ይስፋፋል፡፡

የሕክምና ኮሌጁ የልብ ሕክምና ማዕከል ከልብና ከልብ ጋር ለተያያዙ ፕሮግራሞች የስፔሻላይዜሽን ፌሎሺፕ ሥልጠና ለመስጠት ዝግጁ መሆኑን ዶ/ር ብርሃኔ አመልክተው፣ ለዚህም እውን መሆን 250 የመኝታ ክፍሎች ያሉት ሕንፃ በመገንባት ላይ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ም

ምስጋና ሪፖርተር አማርኛ

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *