VIA BBC Amharic – በርካቶች የዘንድሮውን የኢሬቻ በዓል በተሰበረ ስሜት ነው የሚያከበሩት። ከነዚህም መካከል አብዲሳ ቦረና ይገኝበታል። መስከረም 22/2009 ዓ.ም አብዲሳ ከነፍሰ-ጡሯ የትዳር አጋሩ ሲፈን ጋር ለመጀመሪያ ጊዜ የኢሬቻን በዓል ለማክበር ወደ ቢሾፍቱ አቀና። አብዲሳ ”ትዳር ከመሰረትን በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ የምንናከብረው የኢሬቻ በዓል ስለሆነ እጅግ ደስተኛ ነበርን። ሁለታችንም በባህል ልብስ አጊጠን የበዓሉ ተካፍይ ለመሆን ወደ ሥፍራው ሄድን” ይላል።

አብዲሳ በዓሉ በሚከበርበት ቦታ ላይ ከቢቢሲ ጋር ባደረገው ቆይታ ቀኑን እንዲህ ሲል ያስታውሳል ”በበዓሉ ሥፍራ ከሲፈን እና ከሌሎች ጓደኞቼ ጋር ሆነን ጥቂት ከቆየን በኋላ፤ ቀኑ ፀሃያማ ስለነበር ሲፈንም ነፍሰ ጡር ስለሆነች ለእሷ ደህንነት ስንል ዛፍ ጥላ ስር ለመሆን ቦታ ቀየርን።

ጥቂት እንደቆየን እኔና ወንድሜ ወደ ሃይቁ ተጠግተን ፎቶግራፍ ማንሳት ስለፈለግን፤ ሲፈን ከጓደኞቼ ጋር ወደ ከተማ ተመልሳ እዛው እንድንገናኝ ተስማምተን ተለያየን”።

Related stories   "ኢትዮጵያን የውስጥና የውጭ ጠላቶች ግንባር ፈጥረው ሊያጠፏት የተነሱበት ወቅት ላይ እንገኛለን፤ ሁሉም አንድ መሆን ይገባዋል – የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም

እስከ ወዲያኛው መለየት

አብዲሳ ባለቤቱን እንዲህ በቀላሉ የተለየው ዳግመኛ ዓይኗን ላያይ ነበር።

”እንደተለያየን ተኩስ ተጀመረ” ይላል አብዲሳ። ”ከመድረኩ ጀርባ ተኩስ ሲጀመር ሁሉም ህይወቱን ለማዳን ሩጫ ያዘ። ከዛ በኋላ እጅግ አሰቃቂ ነገር ተፈጠረ።”

”ባለቤቴ እና ጓደኞቼ ያሉበትን ሁኔታ ለማወቅ በተደጋጋሚ ስልክ ብሞክርም ሊሰራልኝ አልቻለም። ከብዙ ጥረት በኋላ የጓደኛዬ ስልክ በመስራቱ፤ ተጎድቶ ሆስፒታል እንደገባ ተነግሮኝ በፍጥነት ወደ ሆስፒታል አመራሁ” ይላል።

ሆስፒታል ደርሶ የጓደኛውን ስም እየጠራ ፍለጋ ጀመረ። እስከዛ ሰዓት ድረስ ግን ሲፈን ደህና እንደሆነች ነበር የሚያውቀው።

በድንገት ያልጠበቀውን ነገር ተመለከተ። ”የነፍሰ ጡሯ ባለቤቴን የሲፈንን አስክሬን ከሌሎች ሰዎች አስክሬን ጋር በአንድ ድንኳን ውስጥ አየሁ። ሰዎች ይዘው ሊያረጋጉኝ ሲሞክሩ አስታውሳለሁ። ከዚያ በኋላ ግን ምን እንደተፈጠረ የማውቀው ነገር የለም” ይላል።

የብዙዎች ደስታ ወደ ሃዘን የተቀየረበት ቅፅበት

‘ሂውማን ራይትስ ዋች’ የተሰኘው የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ቡድን የ2009 ዓ.ም የኢሬቻ በዓልን አስመልክቶ በቅርቡ ባወጣው ሪፖርት ”ፀጥታ ኃይሎች አስለቃሽ ጭስ በመጠቀማቸው እና መውጫ መንገዶችን በመዝጋታቸው በተፈጠረ ግርግር በመቶዎች ሊቆጠሩ የሚችሉ ሰዎች ተረጋግጠው ሞተዋል” ብሏል።

Related stories   አፍሪካ ህብረት ቁርጠኛነቱን አሳይቷል፤ አውሮፓ ህብረት ምርጫ አልታዘብም አለ

በባለ 33 ገፁ ሪፖርት ላይ እንደተጠቀሰው፤ ተረጋግጠው ከሞቱት ሰዎች በተጨማሪ በጥይት ተመተው የተገደሉም እንዳሉ ቡድኑ አረጋግጫለሁ ብሏል።

የኢትዮጵያ መንግሥት ለጠፋው ህይወት ፀረ-ሰላም ያላቸውን ኃይሎች ተጠያቂ አድርጎ ነበር። ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝም የፀጥታ ኃይሎችን ”ስላምና መረጋጋትን” አሰፍነዋል በማለት አመስግነው እንደነበር ሪፖርቱ አስታውሷል።

በዕለቱ የሞቱትን ሰዎች ቁጥር የኢትዮጵያ መንግሥት 55 ነው ሲል፤ የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ ደግሞ 678 ያደርሰዋል።

ሲፈንና አብዲሳImage copyrightABDISA BORENA
አጭር የምስል መግለጫሲፈንና አብዲሳ

ለሲፈን ሞት ተጠያቂው ማነው?

”ለበርካታ ሰዎች ሞት ምክንያት የነበርው ክስተት፤ ሆን ተብሎ እና ታቅዶ የተፈፀመ እንጂ በአጋጣሚ የሆነ ነገር አልነበረም።” የሚለው አብዲሳ፤ ለባለቤቱም ሆነ ለሌሎች ሰዎች ህይወት መጥፋት ተጠያቂ የሆነው አካል ለፍርድ እንዳልቀረበ በምሬት ይናገራል።

Related stories   የአሜሪካ ሴናተሮች የኢትዮጵያ ምርጫ እንዲራዘም ያቀረቡት ጥሪ ብልህነት የጎደለው እጅግ አደገኛ ነው - ሎረንስ ፍሪማን

ስለባለቤቱ አሟሟት በይፋ በመናገሩ ምክንያት ማንነታቸውን የማያውቃቸው ግለሰቦች ”አንተንም አንጨምርሃለን (ከሟቾች ጋር)” እያሉ ያስፈራሩት እንደነበረ ለቢቢሲ ተናግሯል።

ከዚህም በተጨማሪ የእሷ ህይወት ከማለፉ ከ5 ወራት ቀደም ብሎ ጅማ ዩኒቨርሲቲ ይማር የነበረ ታናሽ ወንድሟ በኦሮሚያ ክልል በነበረው ተቃውሞ ህይወቱ አልፏል።

በዚህም ምክንያት ሲፈንም ከፍተኛ ሃዘን ውስጥ እንደነበረች የሚያስረዳው አብዲሳ ”ከእኔ በላይ ደግሞ የሲፈን ቤተሰብ ሁለት ልጆቻቸውን በግፍ ተነጥቀዋል” ሲል ያማርራል።

”ህይወትን አብረን ጀምረን፣ ቤተሰብ መሥርተን፣ በስማችን የሚጠሩ ልጆች ወልደን ለመኖር ብዙ እቅድ ነበረን። የህይወቴ አቅጣጫ ግን እዚህ ቦታ ላይ ተቀየረ። ይህ ስፍራ ዓይኔን ያጣሁበት ቦታ ነው” ይላል አብዲሳ።

በተጨማሪም ባለቤቱ ሲፈንን ወደተነጠቀበት ሆራ አርሰዴ ሲሄድ ”ዓይኗን የማይ ስለሚመስለኝ፤ መቼም ለኢሬቻ በዓል አልቀርም።” በማለት በሃዘን የተሰበረውን ልቡን ይዞ ዘንድሮም ወደ ቢሾፍቱ ይሄዳል።

Share and Enjoy !

Shares

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *