በትናንትናው ዕለት “በኦነግና በአህአዴግ መካከል የተካሄደው የመጀመሪያ ጦርነት” በሚል ርዕስ ባቀረብኩት ጽሑፍ ውስጥ በደርግ መንግሥት ውድቀት ማግሥት የተመሰረተውን የሽግግር መንግሥት ጠቀስ አድርጌ ነበር፡፡ ወደ ቀጣዩ ክፍል ከማለፋችን በፊት ስለዚያ ሽግግር መንግሥት ጥቂት እናውጋ፡፡

Ethiopian-T-55s-outside-the-presidential-palace-in-Addis-Ababa

የሽግግር መንግሥቱ የተመሰረተው በግንቦት 19-20/1983 በተካሄደው የለንደን ኮንፈረንስ በተደረሰበት ውጤት መሰረት ነው፡፡ በለንደኑ ኮንፈረንስ ዋነኛ ተሳታፊ የነበሩት አዲስ አበባን ጨምሮ አብዛኛውን የሀገሪቱን ክፍል የተቆጣጠረው ኢህአዴግ፣ በሀገሪቱ ምስራቅና ምዕራብ አካባቢዎች ብዙ ቦታዎችን የያዘው ኦነግ እና ኤርትራን ሙሉ በሙሉ የያዘው ህግሓኤ ናቸው፡፡

ይህ ፎቶግራፍ የተወሰደው የለንደኑ ኮንፈረንስ በተጠናቀቀበት ወቅት ሲሆን በፎቶው ላይ የሚታዩት (ከግራ ቀደ ቀኝ)

1. ሚስተር ኸርማን ኮኽን፣ በዘመኑ የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካ ጉዳዮች ምክትል ሚኒስትርና የለንደን ኮንፈረንስ ዋና አዘጋጅና አደራዳሪ

2. አቶ መለስ ዜናዊ፣ የህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት) እና የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዲሞክራሲያዊ ግንባር (ኢህአዴግ) ሊቀመንበር፣

3. አቶ ሌንጮ ለታ፣ የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) ምክትል ዋና ጸሐፊ፣

4. አቶ ኢሳያስ አፍወርቂ፣ የህዝባዊ ግንባር ሓርነት ኤርትራ (ህግሓኤ) ዋና ጸሐፊ

ናቸው፡፡ ከአቶ መለስ ጀርባ ደግሞ ለረጅም ጊዜ የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በመሆን ያገለገሉት አቶ ስዩም መስፍን ራቅ ብለው ይታያሉ፡፡
*****
በለንደን ኮንፈረንስ በተደረሰበት ውጤት መሰረት ኢህአዴግ በሽግግር መንግሥቱ የመሪነት ሚና እንዲኖረው የተወሰነ ሲሆን ኦነግ ደግሞ በመንግሥቱ ውስጥ ዋነኛው የስልጣን ተጋሪ ነበር፡፡ አህአዴግ የሽግግሩ መንግሥት የተወካዮች ምክር ቤት ከነበሩት 87 መቀመጫዎች መካከል ሠላሣ ሁለቱን ሲያገኝ ኦነግ ደግሞ አስራ ሁለት መቀመጫዎች ነበሩት፡፡

በዚህ የወንበር ክፍፍል የኢህአዴግ መቀመጫ የበዛው በስሩ የነበሩት ህወሐት፣ ኢህዴን እና ኦህዴድ እያንዳንዳቸው አስር መቀመጫዎች ስለተሰጣቸው ነው፡፡ ሁለቱ መቀመጫዎች ደግሞ በኢህአዴግ ስር ለነበረው የኢትዮጵያ ዲሞክራቲክ መኮንኖች አብዮታዊ ንቅናቄ (ኢዴመአን) ለተባለ ድርጅት ነው የተሰጡት፡፡ (በነገራችን ላይ ይህ ኢዴመአን የተባለ ድርጅት በ1985 ህልውናው አብቅቷል፤ ታጋዮቹም በየብሄራቸው ለህወሐት፣ ኢህዴንና ኦህዴድ ተሰጥተዋል፣ በኢዴመአን ፈንታ በዚያው ዓመት የተመሰረተው የደቡብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ዲሞክራሲያዊ ንቅናቄ የኢህአዴግ አባል ድርጅት ሆኗል)፡፡

ከኢህአዴግና ኦነግ የተረፉት 43 መቀመጫዎች 30 ለሚሆኑ ድርጅቶች ተከፋፍለዋል፡፡ ከነዚያ ድርጅቶች መካከል ጎላ ብለው የሚጠቀሱት ሶስት መቀመጫዎች የነበሩትና በዶ/ር በየነ ጴጥሮስ የሚመራው የደቡብ ህብረት፣ በተመሳሳይ መልኩ ሶስት መቀመጫዎችን ያገኘውና በጃራ አባገዳ የሚመራው የኦሮሞ ነጻነት እስላማዊ ግንባር፣ ሁለት መቀመጫዎች የነበሩትና በአቶ አሰፋ ጫቦ የሚመራው የኦሞቲክ ነጻነት ግንባር፣ እንዲሁም ሁለት መቀመጫዎች የነበሩት የቤኒሻንጉል ነጻነት ግንባር ይጠቀሳሉ (የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ የፋብሪካ ላብ አደሮች እና ሴቶችም አንዳንድ መቀመጫ ተሰጥቷቸው ነበር)፡፡
*****
አቶ መለስ ዜናዊ የሽግግር መንግሥቱ የተወካዮች ም/ቤት ሰብሳቢ ሆነው የተመረጡ ሲሆን የጉራጌ ህዝብ ዲሞክራሲያዊ ግንባር የወከላቸው ዶ/ር ፈቃደ ገዳሙ ደግሞ ምክትል ሰብሳቢ ሆነዋል፡፡ የምክር ቤቱ ዋና ጸሐፊ በመሆን የተሰየሙት ደግሞ የሀዲያ ዲሞክራሲያዊ ድርጅት የወከላቸው አቶ ተስፋዬ ሐቢሶ ነበሩ (ዶ/ር ፈቃደ ገዳሙ የሽግግር ዘመኑ ካበቃ በኋላ በካናዳ የኢትዮጵያ አምባሳደር ሆነው አገልግለዋል፡፡ አሁን የት እንዳሉ ግን መረጃው የለኝም፤ አቶ ተስፋዬ ሐቢሶ በደቡብ አፍሪቃና በኡጋንዳ በአምባሳደርነት ካገለገሉ በኋላ የመንግሥት ስራ በመልቀቅ በግላቸው እየሰሩ ይገኛሉ)፡፡ አቶ መለስ ዜናዊ ከሽግግሩ ም/ቤት ሰብሳቢነታቸው በተጨማሪ የመንግሥቱ ፕሬዚዳንት ናቸው፡፡ የሽግግር መንግሥቱ ምክትል ፕሬዚዳንት በይፋ ባይሰይምም እንደ ምክትል ፕሬዚዳንት ሆነው ሲሰሩ የነበሩት የኦነግ ም/ዋና ጸሐፊ አቶ ሌንጮ ለታ ናቸው፡፡

የሽግግር መንግሥቱ ካቢኔ ሲቋቋም ኢህአዴግ የጤና (ዶ/ር አዳነች ኪዳነ ማሪያም)፤ የውጭ ጉዳይ (አቶ ስዩም መስፍን)፤ የመከላከያ (አቶ ስየ አብረሃ)፤ የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ (ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ)፣ የሀገር ውስጥ ጉዳይ (አቶ ኩማ ደመቅሳ) ጨምሮ ሰባት የካቢኔ ሹመቶችን አግኝቷል፡፡ ኦነግ በበኩሉ አራት የሚኒስትርነት ሹመቶችን ያገኘ ሲሆን እነርሱም የግብርናና ተፈጥሮ ጥበቃ (አቶ ዘገዬ አስፋው)፤ የማስታወቂያ (አቶ ዲማ ኖጎ)፣ የንግድና ቱሪዝም (አቶ አሕመድ ሑሴን) እና የትምህርት (አቶ ኢብሳ ጉተማ) ናቸው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩም አቶ ታምራት ላይኔ (ኢህአዴግ) ነበሩ፡፡ የደቡብ ህብረቱ ዶ/ር በየነ ጴጥሮስ የትምህርት ሚኒስቴር ምክትል ሚኒስትር ሲሆኑ የኦሞቲክ ነጻነት ግንባሩ ፊታውራሪ መኮንን ዶሪ የማስታወቂያ ምክትል ሚኒስትር ነበሩ፡፡

የሱማሌ ህዝብ ዲሞክራቲክ ሊቀመንበር የነበሩት ዶ/ር አብዱልመጅድ ሑሴን የትራንስፖርትና መገናኛ ሚኒስትር፣ የአፋሩ አቶ ሐሰን አብደላ የቡናና ሻይ ልማት ሚኒስትር የነበሩ ሲሆን ቀሪዎቹ ሚኒስትሮች ግን በሙያቸው እንጂ በድርጅት ተወክለው የተመረጡ አልነበሩም፡፡ ከነርሱም መካከል የማዕድንና ኢነርጂ ሚኒስትሩ አቶ ኢዘዲን ዓሊ (በደርግ ዘመንም ሚኒስትር የነበሩ) እንዲሁም የስራና ከተማ ልማት ሚኒስትሩ አቶ ሃይሌ አሰግዴ ይጠቀሳሉ፡፡

ኦነግ ሰኔ 16/84 የሽግግር መንግሥቱን ለቆ የወጣ ሲሆን የደቡብ ህብረትና ሌሎች ድርጅቶች ደግሞ በመጋቢት ወር 1985 በነ ኢህአፓና መኢሶን አዘጋጅነት በተካሄደው የፓሪስ ኮንፈረንስ ላይ በመሳተፋቸው ከሽግግር መንግሥቱ እንዲወጡ ተደርገዋል፡፡ የሽግግር መንግሥቱ በኦፊሴል ሁኔታ ያበቃው ግን በነሐሴ ወር 1987 ነው፡፡
አፈንዲ ሙተቂ መስከረም 12/2007

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *