ዮሃንስ ሰ Via –  addisadmass

• መዳን ከፈለግን ግን፤ ዙርያችንን አስተውለን፣ የሚሆነውን እናድርግ!
• ስለ ሰሜን ዋልታ በረዶ መቅለጥና አለመቅለጥ የምንጨነቅ ከሆነ፣ አንድንም!
• “የአለም ሙቀት ናረ” እየተባለ ፋብሪካ መዝጋትና ሚኒባስ ታክሲዎችን ማክሰር? ለምን? እርዳታ ለማግኘት?
• “የአሜሪካና የአውሮፓ እርዳታ፣… እንዲጨምር” መጠበቅም ሆነ መጠየቅ፣ ሞኝነት ነው! እነሱም እየተናጉ ነው!
• የዛሬውን ብቻ የምናይና፣ ነገና ለከርሞ የሚያስከትለውን ነገር ለማሰብ የማንፈልግ ከሆነ፣ ጉዳችን!

“የሰሜን ዋልታ በረዶ እንዳይቀልጥ፣ የካርቦን ብክለትን እቀንሳለሁ” እያለ እንደ አዲስ አበባ ባለስልጣናት ፋብሪካዎችን የሚዘጋ የአፍሪካ ባለስልጣን፣ ሚኒባስ ታክሲዎችን አዳክሜ ብስክሌትን አስፋፋለሁ የሚል የአፍሪካ ምሁርና ፖለቲከኛ… ይህንን የሚለው፣ “ከአውሮፓና ከአሜሪካ ተጨማሪ የቢሊዮን ዶላሮች እርዳታ ለማግኘት ከሆነ፤ ከእንቅልፉ መባነን አለበት።
ባለፉት አስር ዓመታት፣ “100 ቢሊዮን ዶላር ተጨማሪ እርዳታ በየአመቱ ሊመደብልን ነው” እየተባለ እልፍ ጊዜ ቢደሰኮርም፤ ጠብ ያለ ነገር የለም። ከመነሻው፣ ምፅዋትን የኑሮ አላማና መተማመኛ ማድረግ ራሱ፣ ከሰውነት በታች የወረደ ነው። በዚያ ላይ፣ ተጨማሪው እርዳታ፣ የዘመኑ ልብወለድ ተረት ከመሆን ያለፈ፣ የሚጨበጥ ነገር አላስገኘም። የውሃ ሽታ ሆኗል። ተጨማሪ ቢሊዮን ዶላሮች እንዲዘንብላቸው ሲጠብቁ ስንት ዓመታቸው። 10 ዓመት ሊሞላቸው ተቃርቧል? በእነዚህ ዓመታትስ ምን ያህል ተገኘ? ምንም! ዜሮ!
ወደፊትም አይገኝም። ለምን?
የአውሮፓ አገራት አማካይ የኢኮኖሚ እድገት፣ ድሮ ድሮ፣ ከ2.5 በታች የወረደበት ጊዜ አልነበረም። ብዙውን ጊዜ በየዓመቱ ከ3 እስከ 4 በመቶ ነበር ኢኮኖሚያቸው የሚያድገው።
ባለፉት 15 ዓመታት ግን፣ አማካይ እድገታቸው፣ ከ1% በላይ ፈቅ ማለት አቀበት ሆኖበታል። እና፣ እርዳታ እንዲጨምሩ እንጠብቃለን?
ይህም ብቻ አይደለም።
ባለፉት 10 ዓመታት፣ የአውሮፓ ዋና ዋና ፓርቲዎች፣ ዋናዎቹ ገዢ እና ተቃዋሚ ፓርቲዎች፣ ታይቶ በማይታወቅ የፖለቲካ ማዕበል እየተናጉ ናቸው።
በፈረንሳይና በኦስትሪያ፣ ዋናዎቹ ፓርቲዎች፣ በፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ተሸንፈዋል።
የጀርመን ዋናዎቹ ፓርቲዎች፣ ለወትሮው ፓርላማ ውስጥ ከ75% በላይ ወንበር ያሸንፉ ነበር። ይሄ ተረት የሆነው ከ2005 ወዲህ ነው። ዘንድሮ ደግሞ፣ በታሪካቸው ታይቶ የማይታወቅ ዝቅተኛ ድጋፍ አግኝተዋል – ገዢው ፓርቲ 32%፣ ዋናው ተቃዋሚ ፓርቲ 20%። በተቃራኒው፣ በእንግሊዝ እንደታየው፣ የአውሮፓ ሕብረትን የሚጠሉ ወይም ደግሞ በፈረንሳይ እንደታየው፣ አዲስ የበቀሉ ፓርቲዎች ያልተጠበቀ ድጋፍ በማግኘት በርካታ ወንበሮችን ለማሸነፍ ችለዋል።
የብሪታኒያ ስኮትላንድን በተመለከተ የሚብሰለሰለው ቀውስ ላይ፣ ሰሞኑን ደግሞ በስፔን የካታላን ክልልን በተመለከተ፣ አገሪቱን ለነውጥ የሚገፋፋ ቀውስ ፈንድቷል።
ሌላው ይቅርና፣ የአሜሪካ ኢኮኖሚና ፖለቲካ እንኳ፣ ምን ያህል እንደወረደ ማየት ይቻላል – ብዙ አሜሪካውያን በዋናዎቹ ፓርቲዎች ላይ በማመፅ፣ ዶናልድ ትራምፕን መምረጣቸውን ብቻ በማየት፣ ‘ነገሮች እየተናጉ’ መሆናቸውን ለመገመት ይቻላል። ግን፣ ለስልጡን ፖለቲካና ለስልጡን ጋዜጠኝነት በአርአያነት የሚጠቀሱ በርካታ ተቋማትና ሰዎች በተፈጠሩባት አገር፣ ዛሬ ወደ አፍሪካ ደረጃ እየወረደ የመጣ የፖለቲካ ውዝግብና የሚዲያ ፕሮፓጋንዳ እየተበራከተ ነው። የናዚ አድናቂ እና የ‘ብላክ ላይቭስ ማተር’ ዘረኞች፤ ሃብት ማፍራትንና የኢንዱስትሪ ምርትን የሚመቀኙ የኮሙኒዝምና የአካባቢ ጥበቃ ነውጠኞች… የገነኑበት የፖለቲካ ውዝግብኮ፣ ከአፍሪካና ከአረብ አገራት ኋላቀር ፖለቲካ ብዙም አይራራቅም። ለጥቂት ቀናት ሲኤንኤንን በማየት ወይም ዋሽንግተን ፖስትን በማንበብ ማረጋገጥ፣… ወደ ፕሮፓጋንዳ የሚያሽቆለቁል ሚዲያ ምን እንደሚመስል መታዘብ ትችላላችሁ።
ሌላውን ዓለምማ ተዉት።
በምስራቅ በኩል ኢራንና ኳታር፣ ቱርክ እና ሳዑዲ አረቢያ፣ ከሶሪያና ከኢራቅ ጀምሮ፣… በጂቡቲ ሃያላን መንግስታት “ከቅኝት” ያለፈ የረባ ውጤት ያላስገኙ የጦር ሰፈሮችን ጨምሮ፣ እስከ ደጃፋችን የመን እና ሶማሊያ ድረስ… በጦርነትና በትርምስ ትራጄዲ ተሞልቷል። ዘግናኝነቱ፣ አታካችና አሰልቺ እስከ መሆን የደረሰ ትራጄዲ!… እጅ እግር የሌለው ትርምስ! ወይም ደግሞ፣ በኤርትራ እንደምናየው፣ በብረት ቀጥቅጦ የሚገዛ የለየለት አምባገነን!
ወደ ሌላው አቅጣጫ ስንዞርም፣ ያን ያህል ተስፋ የሚሰጥ የተሻለ ሕይወት አናይም። አዎ፣ ኬንያን ጨምሮ፣ ከአገራችን ቀድመው ደህና የመራመድ ምልክት ያሳዩ አገራት አሉ። ግን፣ እነሱም እንኳ፣ ገደል አፋፍ ላይ የሚውተረተሩ ናቸው – በምርጫ ውዝግብ፣ ጎሰኝነት-ዘረኝነት በመረዘው አዘቅት፣ ኋላቀር ባሕልን በሚያሞካሽ የዘመኑ የምሁርነት ‘ፈሊጥ’፣ የሰሜን ዋልታ በረዶ ተሸረሸረ ብሎ ማላዘን እንደ አዋቂነት እየቆጠረ የሚኮፈስ ምሁርና፣ ‘የዋልታ በረዶ እንዳይቀልጥ፣ የካርቦን ብክለትን እቀንሳለሁ” እያለ እንደ አዲስ አበባ ባለስልጣናት፣ ፋብሪካዎችን የሚዘጋና ሚኒባስ ታክሲዎችን አዳክሜ ብስክሌትን አስፋፋለሁ የሚል የአፍሪካ አገራት ፖለቲከኛ… በስልጣን ሹክቻና በሙስና መንግስት በገነነበት፣ በተመፅዋችነት የድጎማ ጥገኝነት በተስፋፋበትና ብዙ ሕዝብ በሚደግፈው የመንግስት የዋጋ ቁጥጥር፣ ገበያው የሚመሳቀልበት፣ “85% ብድር እያቀረብኩ ፋብሪካ የሚከፍት ጠፋ” ብሎ ግራ የሚጋባ መንግስት… የቅይጥ ኢኮኖሚ ቀውስ፣… የሚንገዳገዱ አገራት ናቸው – እጅግ ድሃዋ ኢትዮጵያና፣ ከኢትዮጵያ በእጥፍ የተሻለ የኑሮ ደረጃ ያላቸው እንደ ኬንያ የመሳሰሉ በርካታ ደሃ የአፍሪካ አገራት። እነዚህ በጣም የተሻሉ ደህና አገራት ናቸው።  የሚንገዳገዱ፣ ሸርተት-መለስ የሚሉ ናቸው። አውሎ ነፋስንና ማዕበልን የመቋቋም ፍላጎት የራቃቸው ወይም መላ እና አቅም ያልፈጠሩ ከመሆናቸው የተነሳ፣ በትንሽ የነፋሽ ሽውታ ቁልቁል ለመውደቅ የተቃረቡ ናቸው። ከባባድ ቀውሶችንና እንደ እሳተ ጎመራ የሚንቀለቀሉ አደጋዎችን የመከላከልም ሆነ የመቋቋም ብቃትና ዘዴ ሊኖራቸው ይቅርና ሃሳቡም የለም፣… በጥቃቅን ሰበቦችና ግጭቶች፣ በቅንጣት ክብሪት የሚለኮስ እሳት ሊያተራምሳቸው ይችላል። ታዲያ፣ እነዚህ የአፍሪካና የአረብ አገራት… ከሌሎቹ ጎረቤቶቻቸው ይሻላሉ።  ሌሎቹማ፣ ለይቶላቸው፣ የምድር ሲኦል ሆነዋል – እንደ ደቡብ ሱዳን፣ ሶማሊያ፣ ሴንትራል አፍሪካ፣ ብሩንዲ፣ ሊቢያ፣ ቱኒዚያ፣ ማላዊ፣ ኮንጎ፣ ዚምባብዌ… እና ሌሎችም። እንዲህ አይነት ቀውስ (chaos)… ካሁን በፊት ነበር? ለዚያውም “መፍትሄ አለኝ” ብሎ የሚናገር እየጠፋ መምጣቱ! መፍትሄ መጥፋቱ ብቻ አይደለም። ሌሎቹ ከገደል አፋፍ ያሉ አገራትም፣… ወደዚያው ላለመግባት ሲጠነቀቁ አይታዩም። እንዲያውም፣ ሌሎቹ አገራት አይናቸው እያየ የትርምስ ሲኦል ውስጥ እስኪገቡ ድረስ ያደርጉት የነበረውን ነገር በሙሉ፣ ሌሎቹ አገራትም እያደረጉ ነው – ቀድመው ወይም ተከትለው ወደ ትርምስ የመግባት ጉዞ!
እያዩ ማለቅ… እንዳላዩ ሆነው።
ይሄ የአፍሪካና የአረብ አገራት ጉዳይ ብቻ አይደለም።
በፊት በነዳጅ ዘይት ምርት ከአለም 5ኛ የነበረችው ቬኔዝዌላ፣… ከአሜሪካና ከሳዑዲ፣ ከራሺያና ከኢራን በመቀጠል ትጠቀስ የነበረችው አገር፣ በመቶ ሺ የሚቆጠሩ ሰዎች ሸቀጣሸቀጥ ለመግዛት ቅዳሜና እሁድ ወደ ኮሎምቢያ ለመሻገር አውራጎዳናው እየጠበባቸው በወረፋ ሲራመዱ ማየት፣… በ10 ዓመታት ውስጥ እንክትክቷ ሲወጣ፣…
ከ10 ዓመታት በፊት የአገሪቱ መንግስት ሶሻሊዝምን ሲያውጅ፣ የግል ኩባንያዎችን ሲያዋክብ፣ አንዳንዶቹን ሲወርስ፣ ሌሎቹንም የግል ቢዝነሶች በዋጋ ቁጥጥር ማሳደድ ሲጀምር፣… “የድሆች አለኝታ ነኝ” እያለ፣… በአንድ በኩል አምራች ሰዎችና ቢዝነሶች ላይ የታክስ ሸክም ለመቆለል ሲዝት፣… ሌሎች ሰዎችን ደግሞ በድጎማ ለማንበሽበሽ ሲወስን… ያኔውኑ መጨረሻው እንደማያምር ማወቅ ይቻል ነበር። ግን፣ ለማወቅ የማይፈልግና ለማወቅ የማይጥር ይበዛል። ለምን? አዳሜ፣… ወዲያውኑ፣ በማግስቱና በሳምንቱ… እዚያው በዚያው መዘዙን እስካላየ ድረስ፣ የአገሪቱ ኢኮኖሚ ከመቅፅበት ካልተቃወሰ በቀር፤ እንደ ችግር አይቆጥረውም። በአንድ ወር ወይም በአንድ አመት ውስጥ ኑሮው ካልተናጋ፣… በቃ ችግር የለም! ከሁለት ከሦስት ዓመት በኋላ፣… መዘዙ አፍጥጦ አግጥጦ እስኪመጣ ድረስ፣… የእለት የእለቷን ብቻ ከማየት ያለፈ ነገር ለማሰብ አይፈልግም።
እያዩ ለማለቅ! እንዳላዩ እየሆኑ! ግን እንዳላዩ ለመምሰል መሞከርና ራስን ማታለል፣ ዋጋ የለውም።
ብዙም ሳይቆይ፣ አገሬው ሁሉ ይቃወሳል። የአዳሜ ኑሮ እየተናጋ ይጎሳቆላል። ያኸኔስ ምን ይበል? እንዳላየ ለመምሰል መመኮር ያዋጣል? አያዋጣም። እናም ያማርራል። ቀውሱና ጉስቁልናው፣ እንደ ትንግርት ማውራት ይጀምራል። “በአንዳች ተዓምር የተፈጠረ አደጋና ድንገት የመጣ ደራሽ ጎርፍ!” እያለ ራሱን ያታልላል፤ ያስመስላል። የሚወገዝ፣ የሚወነጀል አካል ይፈልጋል። “የውጭ ሃይሎች ሴራ” እያለ የራሱን ጥፋት በሌሎች ላይ ለማሳበብ ይሞክራል። “አጭበርባሪ ነጋዴዎች” ብሎ ይኮንናል። በቀውሱ ሰበብ፣ ሰዎችን በሃይማኖት ወይም በጎሳና በብሔር ብሔረሰብ ተወላጅነት ለማቧደንና ተጨማሪ የጥፋት ዘር ለመዝራት የሚሞክርም ሞልቷል። “ተው። ተው። ተጨማሪ ጥፋትና እልቂት አትደግስብን፤ በዘርና በሃይማኖት መቧደን፣ ከሰውነት በታች የወረደ ጭፍንነት ነው፤ ጥፋት ነው፤ ነውር ነው፤ ክፋት ነው” ብሎ ለመከላከል የሚሞክር ብዙ ሰው አይኖርም። ለምን? የመቧደን ቅስቀሳው፣ ወዲያውኑ እዚያው በዚያው መዘዝ አያስከትልማ። በሚቀጥለው ዓመት ወይም ከአምስት ዓመት በኋላ፣ ከአገሪቱን ለትርምስ፣ ሚሊዮኖችን ለእልቂት የሚዳርግ ጥፋት እንደሆነ ለመገንዘብና ዛሬውኑ ለመከላከል አይጥርም። ለማሰብም አይፈልግም።
እንዲህ ነው፣ እያዩ መጥፋት!
እነ ቬኔዝዌላ፣ በድጎማ እየተጥለቀለቁ ወደ ጥፋት የተጓዙት፣ ከአገሬውን የአምራቾች ሃብት በመንጠቅና በማባከን ነው።
እንደ ኢትዮጵያ የመሳሰሉ አገራት ግን፣ በድጎማ ለመንቦራጨቅ የሚሞክሩት፣ ከውጭ እየተበደሩ ነው።
በብድር ጥፋትን መደገስ!
ለከተማ ነዋሪዎች ድጎማ እሰጣለሁ በማለት፣ የኢትዮጵያ መንግስት ከአለም ባንክ 350 ሚሊዮን ዶላር ተበድሯል።
ለገጠር ነዋሪዎች ድጎማ እሰጣለሁ ብሎም፣ ከ2 ቢሊዮን ዶላር በላይ ተበድሯል።
ይሄ ይሄ… መጨረሻው እንደማያምር መገመት ያስቸግራል። ወይስ፣ ‘መዘዙን ዛሬውኑ ካላየነው በቀር’፣ ጨርሶ ማሰብ አያስፈልግም?
የታክሲ የስምሪት ቁጥጥር፣ ያኔ በተጀመረ ማግስት፣ የትራንስፖርት እጥረት ስላልተባባሰ፣… መዘዙ እያፈጠጠ የሚመጣው ከዓመት ከሁለት ዓመት በኋላ ስለሆነ ችግር የለውም?
ችግርማ አለው። ግን… ከመቅፅበት የሚታይ ካልሆነ፣ እንዳላዩ መሆን!
እስካሁን የተከማቸው ጥፋትና መዘዝ ያነሰ ይመስል፤ የከተማ ልማት ሚኒስቴር ደግሞ፣ የቤት ኪራይ ቁጥጥር እጀምራለሁ ብሎ የመኖሪያ ቤት ችግርን ለማባባስና ይበልጥ ለማቃወስ፣ እቅድ አዘጋጅቶ ሲመጣስ? ተው ያለ አለ?
የቁጥጥር መመሪያው ሁሉ አልቆ፣ ጠ/ሚ ኃይለማሪያም ደሳለኝ ጋ ሲደርስ፣ “አይሆንም” በሚል ምላሽ እንዳስቆሙት ተዘግቧል።
አንድ ጥፋት፣ አንድ ቀውስ፣ አንድ መዘዝ ተቀነሰ ማለት ነው።
ግን ምን ዋጋ አለው? እልፍ አእላፍ ተመሳሳይና ሌላ አይነት ጥፋቶች በሚፈለፈሉባት አገር፣… አንዲትዋን ጥፋት ብቻ ማስቀረት፣ ብዙ ለውጥ አያመጣም።
እያንዳንዱ ሰው፣ ባለስልጣንም ሆነ አልሆነ፣ እንደየሙያውና እንደአቅሙ፣ ጥፋቶችን ገና ከመነሻው ለመከላከል ካልጣረ፣ …በዘፈቀደና በአንዳች ተዓምር መዳን አይቻልም – የጊዜ ጉዳይ ካልሆነ በቀር፣ ከጥፋት መዳን አይቻልም። እለት በእለት እያስተዋለ፣ ዛሬን ብቻ ሳይሆን ነገ ከነገወዲያ የሚያስከትለውን መዘዝ እያመዛዘነ፣ እዚህችው አካባቢና እዚህችው ቁንፅል ጉዳይ ላይ ብቻ ሳይሆን፣ በየትኛውም አካባቢና ጉዳይ ላይ የሚኖረው ትርጉም እያገናዘበ፤… በቅንነትና በፅናት ጥፋቶችን ለመከላከል ከጣረ ግን፤… ጥፋት መዳንና ማምለጥ ብቻ ሳይሆን፣ መሻሻልና ማደግም ይቻላል። የምንፈልግና የምንጥር እስከሆነ ድረስ፣ ይቻላል!
ምርጫው የእያንዳንዳችን ነው።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *