Image result for abadula

ዘግይቶ እንደተሰማው አባዱላ በቃኝ ማለታቸው እንደተሰማ ይኖሩበት ከነበረው ቤት እንዲወጡ ተደርጓል። በተለያዩ ማህበራዊ ገጾችና ሚዲያዎች እንደተነገረው አባ ዱላ ባልደረቦቻቸው ቤት አርፈው በበነጋታው የሚከራይ ቤት አግኝተዋል።

ከኦሮሚያ ባለስልጣኖች መካከል ተሰሚነትና ተቀባይነት ያላቸው አባ ዱላ ያስገቡት የስራ መልቀቂያ በኦህዴድ በኩል መናጋት መኖሩን የሚያመላክት እንደሆነ እየተነገረ ነው። የሶማሊ ክልል ባለስልጣኖች የኦህዴድ ባለስልጣኖችን “ኦነግ፣ አሸባሪና፣ ከውጭ አክራሪ ድርጅቶች ጋር የሚሰሩ፡ ሲሉ በከሰሱበት ወቅት፣ ከኦሮሚያ ሃላፊዎች ዘንድ የተሰጠው መልስ ያለተለመደ መሆኑንን ያስታውሳሉ።

ለቀረባቸው ክስ የኦሮሚያ ሃላፊዎች ” ፋሽኑ ያለፈበት፣ የድሮ ቀልድ፣ የድሮ ፖለቲካ” ሲሉ የሶማሊ ክልል ሃላፊዎችን ክስ ማጣጣላቸውን የጠቆሙት ክፍሎች ” ዛሬ ኦህዴድን የሚመሩትን ካቢኔዎችና የመካከለኛ ደረጃ አመራሮች እንደ ፈጣን ሎተሪ ሲፍቋችሁ ኦነጎች ናቹህ ብሎ መዛበትና አፍ መክፈት የሚቻልበት ጊዜ አይደለም” ሲሉ ይናገራሉ። በዚሁ መነሻ የአባ ዱላን ጉዳይ ከዚህ እንደማይለይ ያስረዳሉ።

ለአባ ዱላ ቅርብ የሆኑ ሌሎች እንደሚሉት የተባሉት ጉዳዮች ሁሉ እንዳሉ ሆነው ፣  አባዱላ አሁን አሁን የኢየሱስ ፍቅር ጸንቶባቸዋል። አስቀድመው እንደሚሉት ወደ መንፈሳዊ ህይወት የመግባት ዝንባሌያቸው እንቅልፍ ነስቷቸዋል። ቀደም ሲል እሳቸውም ሆኑ ፓርቲያቸው ያከናወኑት፣ ዛሬ በየቦታው እየተከናወነ ያለው ሁሉ ህሊናቸውን እርፍት የነሳው በመሆኑ ቀሪ ህይወታቸውን ከፈጣሪያቸው ጋር ለመኖር ወሰነዋል። ይህ ውሳኔ ለጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማሪያም የማንቂያ ደወል እንደሚሆንም አስተያየት እየተሰጠ ነው። አቶ ሃይለማሪያም ” ለንስሃ እንኳን የማልበቃ ነኝ” በማለት በአስር ሺህ በሚቆጠር ህዝብ ፊት ማንባታቸውን፣ በቤተክርስቲያን ደረጃ እሳቸው ለሚመሩት የምሁራኖች ህብረት ” ወደ ፖለቲካ አትግቡ፣ ፖለቲካ ክርስትናን ይበላል” ይሉ እንደነበር ያስታወሱ የቤተክርስቲይን ወንደሞቻቸው፣ አቶ አባ ዱላ ያስገቡት የበቃኝ ጥያቄ አቶ ሃይለማሪያምን ሊያነቃ እንደሚገባ ይጠቁማሉ። ከነሙሉቤተሰቦቻቸው!!  ቀደም ባሉት ቀናት የዘገብነውን ይመለከቱ

ዛጎል ዜና -በኦህዴድ አባላት  ዘንድ “ጃርሳው” የሚል መጠሪያ ያላቸው አባ ዱላ ገመዳ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ከሰለቻቸው ከፍተኛ አመራሮች መካከል በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀሱ ናቸው። ” ንፍሮ እየበላሁ ከተራው ህዝብ ጋር መኖር ናፈቀኝ፤ ወደ ቤተ ክርስቲያን በነጻነት የምሄድበት ቀን መቼ ነው?” በማለት ለሚቀርቧቸው ሲናገሩ መቆየታቸውን በቅርብ የሚያውቋቸው ምስክርነት ይሰጣሉ።

የጦር ሰራዊት መለዮ አውልቀው መከላከያ ሚኒስትር፣ ከዛም የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት ሆነው የተሰየሙት አባዱላ፣ በኢህአዴግ አመራሮች የማይደፈሩ ቦታዎች ድረስ ዘልቀው በመግባት ከህዝብ ጋር በተደጋጋሚ የመከሩ፣ ኢህአዴግ ወደ ስልታን ከመጣ ጀምሮ ኦሮሚያ ላይየተሻለ ተቀባይነት ያገኙ ናቸው።
በአቶ ደራራ ሞት እጃቸው አለበት በሚል የሚከሷቸው ያሉትን ያህል፣ በባህሪያቸው ሩህሩህ እንደሆኑ በቅርብ የሚያውቋቸው ይናገራሉ። አርሲና ባሌን ማዕከል አድርጎ የተዋቀረውን የአቶ ጁነዲንን ካቢኔ ያፈራረሱትና በወጣቶች የተሞላ አዲስ ካቢኔ ያቋቋሙ አባዱላ፣ በአንድ ታሪካዊ ንግግር ይታወቃሉ።
አዲሱን ካቢኒያቸውን ሲያዋቅሩ ” በአመላካከት የፈለጋችሁትን ሁኑ፤ ለክልሉ የሚበጀተውን በጀት ተመላሽ አታድርጉ፣ የልማት ስራ መስራት፣ ለክልላችሁ የምትችሉትን ማድረገን ግን አትርሱ፣ ስራችሁን ስሩ ” ብለው ነበረ። በወቅቱ የኦፌኮን የወጣት ክንፍ አባላትና የኦነግ ደጋፊ የነበሩትን አካተው ኦህዴድን ካዋቀሩ በሁዋላ እያደር ኦህዴድ ቀለሙ ተቀየረ።
ለአቶ መለስ ቅርብ የነበሩና የሚታመኑ እንዲሁም በህወሃት የህንፍሽፍሽ ዘመን እነ አቶ ኩማ ደመቅሳ ” በህወሃት የውስጥ ጉዳይ አያገባንም” ሲሉ አባ ዱላ ከመለስ ጊን በቆመ የማይረሳ ውለታ በማስቀመጣቸው ኦሮሚያ ላይ ለሚወስኑት ውሳኔ ፍርሃት የለባቸውም ነበር። በሼህ መሐመድ ሁሴን አላሙዲን ጉዳይ የወረዳና የዞን አመራሮች፣ የገቢ ሰብሳቢ አካላቶች፣ የህግ ዘርፎች አግባብ ያለው ወሳኔ እንዲሰጡ በድፍረት ያዘዙ፣ በተደጋጋሚ እንዲለሳለሱ ቢጠየቁ አሻፈረኝ ማለታቸው በተለያዩ ሚዲያዎች ምስክርነት የተሰጠበት ጉዳይ ነው።
ከብዙ ፍትጊያና ዘመቻ በሁዋላ አባዱላ በኦሮሚያ ክልል ምርጫ እንዳይወዳደሩ ሲወሰን / ውሳኔው ሆን ተብሎ ከክልል ለማንሳት ነበር/ ድፍን ካድሬው ” አሻፈረኝ ” በማለት አቶ በረከት ስምዖንን ሳይቀር አልተቀበለም ነበር። የኦህዴድ ካድሬ ከላይ እስከታች ለአባ ዱላ ልዩ ፍቅር ያለው ሲሆን፣ በዋናነት የሚቃወሙዋቸው አቶ ሙክታር እና አቶ ጁነዲን ብቻ ነበሩ።
በቅርቡ ወ/ሮ አዜብ ” መኖሪያ ቤቱን ለቀቀልኝ” ሲሉ ያሞካሹዋቸው አቶ ሙክታር አባ ዱላን ከሚቃወሙና ከኦሮሚያ እንዲነሱ ሲደቡ ከነበሩት ባለሃብቶች ጋር ወዳጅ እንደነበሩ ስለ ግንኙነት መስመሩ የሚያውቁ በተለያዩ ወቅቶች መስክረዋል።
በራሳቸው ተማጽኖ፣ ካድሬውን ለምነው ያሳመኑት አባ ዱላ ” ጃርሳ” የሚላቸውን ካድሬና የፐሬዚዳንትነት ወንበር ትተው አፈ ጉባኤ ቢሆኑም ኦሮሚያ ላይ አሁንም ከፈተኛ አሻራ እንዳላቸው ይነገራል። በውቅቱ አባ ዱላ ቦሌ በተለያየ መለኩ ተገነባላቸው የተባለውን ትልቅ ቪላ ” ይህንን ቤት ይዤ ለመታገል አይመቸኝም” በሚል ለኦህዴድ ማስረከባቸው፣ ከተቀነባበረባቸው ወጥመድ እንዲያመልጡ እንዳደረጋቸው በወቅቱ በስፋት የተወሳ ነበር።
አባ ዱላ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ከፖለቲካው የመውጣትና ተራ የቀበሌ ነዋሪ ሆኖ መኖር እንደናፈቃቸው በተደጋጋሚ ለቤተሰቦቻቸውና ለርሳቸው ቅርብ የሆኑ ሲናገሩ ነበር። የሆኖ ሆኖ በሃላፊነታቸው እስካሁን ቆይተዋል። በትክክል መረጃ ባይሰጥም አቶ አባ ዱላ በተለያዩ ምክንያቶች ለማረፍ ያላቸው ፍላጎት ግን እንዳልተቀየረ መርጃዎች ነበሩ።
በጓሮ ሲሰማ የነበረውን ጉዳይ አዲስ ስታንዳርድ ሁለት ከፈተኛ ሃላፊዎች እንደነገሩት ጠቅሶ አባ ዱላ የስራ መልቀቂያ ማስገባታቸውን ይፋ አድርጓል። እንደ ዘገባው ከሆነ አባ ዱላ ከሃላፊነታቸው ለመነሳት የወሰኑት በሶማሊ ክልልና በኦሮሚያ ክልል መካከል በተፈጠረው ቀውስ የተነሳ የፌደራል ሃይል ኦሮሚያ ላይ ጣልቃ በመግባቱ የተነሳ ነው።
የኦሮሚያ ሚዲያ ኔት ዎርክ በበኩሉ አባ ዱላ ለኦህዴድ አመራሮች በቢሯቸው መግለጫ እንደሰጡም ምንጮቹን ዋቢ አድርጎ አመልክቷል። ዘጋብው አክሎም አባ ዱላ በመጪው መስከረም 29 ለሚከፈተው የኢህአዴግ ፓርላማ መልቀቂያቸው እንደሚቅርብ አመልክቷል። አባ ዱላ ውሳኔያቸውን እንዲቀይሩ ቢጎተጎቱም እንዳልተቀበሉት ተናግሯል።
በኢትዮጵያ ባለው የፖለቲካ ግለት አባዱላን የሚያክል ነባር የፖለቲካ አመራር በበቃኝ ለመገላገል መወሰኑ ፖለቲካዊ ቀውሱ ትኩሳቱ መጨመሩን አመላካች እንደሆነ አስተያየት እየተሰጠ ነው። አባ ዱላ በጤና ችግር ማርፍ እንዳለባቸው አጉልቶ በማሳየት የስንብት ጥያቄያቸውን እንደሚያጸድቅላቸው የሚናገሩ ክፍሎች ” ዜናው ሰበር አይባልም፣ አስቀድመው በውስጥ ሳይጨርሱት መልቀቂያ እስከማስገባት አይደርሱም፤ አባ ዱላ ህወሃትን በመቃወም የስራ መልቀቂያ ሊያስገቡ አይችሉም፤ ካደረጉትም ከመሬት ጋር አያይዘው ወደ ማረፊያ ያስገቧቸዋል” ሲል የዘወትር የዛጎል አስተያየት ሰጪ ተናግሯል። በዴን ማርክ ትምህርት ላይ የሚገኘው አስተያየት ሰጪ ” በቅርብ እንደማውቀው እንዳለው አባ ዱላ እንዲህ አይነት ድፍረት ሊሳዩ አይችሉም። ይልቁኑም ከአቶ ለማ መገርሳ ጀርባ ሆነው ኦሮሚያን እንዲያረጋጉና የሚወዳቸውን ካድሬ ወደ ቀድሞ ቀልቡ እንዲመልሱ ታስቦ ሊሆን ይችላል”
ዘናውን አስመልክቶ ከኢህአዴግም ሆነ ከኦህዴድ ወገን የተባለ ነገር የለም።

Related stories   "ኢትዮጵያን የውስጥና የውጭ ጠላቶች ግንባር ፈጥረው ሊያጠፏት የተነሱበት ወቅት ላይ እንገኛለን፤ ሁሉም አንድ መሆን ይገባዋል – የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም

በመጨረሻ በተገኘ ዜና የኢትዮጵያ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ አቶ አባዱላ ገመዳ የሥልጣን መልቀቂያ ደብዳቤ ማቅረባቸውን በይፋ አረጋግጠዋል። አፈ-ጉባኤው በመንግስት ሚዲያ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ “አሁን በደረስኩበት ደረጃ በዚህ ኃላፊነት ለመቀጠል የማያስችሉኝ ምክንያቶች በመኖራቸው እና ፍላጎቱም ስለሌለኝ ለመልቀቅ ድርጅቴን እና የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትን ጠይቄያለሁ” ሲሉ ተናግረዋል።

አቶ አባዱላ ከዚህ ውሳኔ ላይ የደረሱት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከወከሉት እና የኢሕአዴግ አባል ከሆነው ፓርቲያቸው ጋር ተማክረው ስለመሆኑ ያሉት ነገር የለም። አቶ አባዱላ ከአፈ-ጉባኤነት ኃላፊነታቸው ለመልቀቅ የወሰኑባቸውን ምክንያቶች በግልፅ አልተናገሩም። “ድርጅቴ እና የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሁኔታውን አይተው ሕጋዊ መስመሩን ተከትለው ጥያቄዬ ተገቢውን ምላሽ ያገኛል” ያሉት አቶ አባዱላ “ጥያቄዬ ተገቢውን ምላሽ ሲያገኝ የምክር ቤት አፈ-ጉባኤነቴን ለመልቀቅ የፈለኩባቸውን ምክንያቶች በዝርዝር ለሕዝብ አስረዳለሁ” ሲሉም አክለዋል። አያይዘውም ከአፈ ጉባኤ ሃላፊነታቸው ሲወርዱ በምክር ቤት አባልነታቸው እንደሚቀጥሉ አስታውቀዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *