የገንዘብን የመግዛት አቅም በአስራ አምስት መቶኛ የሚያወረደው አዲሱ መመሪያ በስራ ሲውል ማህበራዊ ቀውሱን ይበልጥ እንዳያግመው ስጋት አለ። በተደጋጋሚ የምንዛሬ አቅምን የማውረድ ጥያቄ ለመቀበል ሲያቅማማ የነበረው ኢህአዴግ፣ በስተመጨረሻ እጁን ሰጥቷል። ይህንኑ ተከትሎ ባንኮች ” ንፋስ አመጣሽ” ትርፍ እንደሚያጋብሱ፣ በሌላ በኩል ግን የጋለውን ድህነትና የኑሮ ችግር ወደ ወላፈንነት እንዳይቀየረው የሰጉ፣ ነገር ግን ስጋታቸውን በወጉ ያላብራሩ ” ምሁራኖች”  በፋና በኩል አስተያየት ሰጥተዋል።

Image result for devaluation of ethiopian money

የብር ዋጋ መቀነስ አዲስ ነገር እንዳልሆነ የሚጠቁሙት ክፍሎች የመንግስት ሰራተኛችና ሸማቾች ” ጌታ ይሁናችሁ” የዘለለ መፍትሄ ሲያቀርቡ አልተስተዋለም። የምንዛሬ ለውጡን ተከትሎ ከነዳጅ ጭማሪ ጋር ተያይዞ የሚከተለው የተለያዩ የአገልግሎት ጭማሪዎች ለሚያደርሱት ጫና ተከራካሪ የለም። የሰራተኞች ፣ የሙያ፣ የተለያዩ አደረጃጀት ያላቸው አክላት የታቀፉበት ነጻ ማህበራት አለመኖራቸው የህብረተሰቡን ችግር ድምጽ አልባ እንደሚያደርገው ያለፉትን አመታቶች ተሞክሮ በመጥቀስ አስተያየት የሚሰጡ አሉ።

ፋና የተለያዩ ምሁራን ያላቸውን አነጋገሮ የሚከተለውን ዘገባ በድረገጹ አቅርቧል። 

ከጥቅምት 1 ቀን 2010 ጀምሮ የብር የውጭ ምንዛሬ ዋጋ በ15 በመቶ እንዲዳከም መደረጉን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገልጿል። የብር የውጭ ምንዛሬ እንዲዳከም የተወሰነው ውሳኔ ሀገሪቱ ከወጪ ንግድ የምታገኘውን ገቢ ሊያሳድግላት እንደሚችል ነው የምጣኔ ሀብት ምሁራን ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት የተናገሩት።

ሆኖም መንግስት ይህንን ተከትሎ ሊመጣ የሚችል የዋጋ ግሽበትን በተገቢው መንገድ ሊከላከል እንደሚገባም ምሁራኑ አሳስበዋል ። የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች እንደሚሉት፥ የአንድ ሀገር ገንዘብ ከሌሎች ሀገራት አንጻር ያለው ዋጋ ሲዳከም የወጪ ንግዷ ይነቃቃል።

የብሔራዊ ባንክ መረጃ እንደሚያሳየው በኢትዮጵያ በተለይ ከ2005 እስከ 2009 ዓ.ም ባሉት ዓመታት ውስጥ የኢትዮጵያ ብር ከአሜሪካ ዶላር አንጻር ያለው ዋጋ በአንጻሩ ጠንካራ ነው።

ይህም ማለት ምርት ወደ ውጭ የሚልኩ ባለሀብቶች ያመጡት ምንዛሬ በኢትዮጵያ ብር ሲመነዘር አነስተኛ ሆኖ ይገኛል። በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ ፕሮፌሰር ጣሰው ወልደ ሀና እንደሚሉት የምንዛሬ ተመን ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ላኪዎችን የሚያበረታታ አይደለም።

ላኪዎች ተጠቃሚ የሚሆኑት ደንበኛ የሆኑበት ባንክ ምርት ወደ ውጭ ልከው ካመጡት ምንዛሬ የተወሰነው እንዲሰጣቸው በመስማማት አትራፊ የሚያደርጓቸውን ምርቶች ከሌሎች ሀገራት በማምጣት ኪሳራቸውን ስልሚያካክሱት ነው ብለዋል። ሌላኛው የኢኮኖሚክስ ባለሙያ ዶክተር ቆስጠንጢኖስ በርሄ ደግሞ ከቡና አንጻር ያለውን በምሳሌነት ያነሳሉ። ቡና አገር ውስጥ በውድ ዋጋ እንደሚሸጥ የሚያነሱት ምሁሩ፥ የብር የምንዛሪ ተመን በዚህ መልኩ መስተካከሉ ግን ቡና ወደ ውጭ ተልኮ የውጭ ምንዛሪ እንዲያመጣ ያበረታታል ነው ያሉት።

Related stories   ሰበር ዜና – ትህነግ በዲፕሎማሲ ዘመቻ ቀውስ ገጠመው፤ “ በሃሰት መረጃ አሳፈራችሁን ” የቅርብ አጋሮቻቸው

በዚህም መሰረት ዛሬ አንድ የአሜሪካ ዶላር ላመጣ ሰው 23 ብር የሚሰጠው ከሆነ በአንፃሩ በሌላ ጊዜ የብር መጠኑ ወደ 26 ቢጨምር ምርቶቹን ወደ ውጭ ሀገር የመላክ ፍላጎቱ ከፍ ይላል ማለት ነው።

በሌላ በኩል የብር የውጭ ምንዛሬ ተመኑ ከሌሎች ሀገራት ገንዘብ አንጻር እንዲዳከም ማድረጉ፥ ኢትዮጵያ ታዳጊ ሀገር በመሆኗ ለኢንቨስትመንት የሚሆኑ እቃዎችን ከውጭ ለማስገባት ፈተና አይሆንም ወይ የሚል ጥያቄ ይነሳል።

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ ምክትል ገዥና ዋና ኢኮኖሚስት ዶክተር ዮሀንስ አያሌው፥ በሀገሪቱ ከኢንቨስትመንት የሚገኝ ትርፍ ከበርካታ ሀገራት አንጻር ከፍተኛ ነው ይላሉ።

ይህ ደግም አንድ ባለሀብት የኢንቨስትመንት ጥሬ እቃ ለማስገባት የውጭ ምንዛሬ ለማግኘት የሚጠየቀው ገንዘብ ቢጨምርም፥ ከሚያገኘው ትርፍ አንጻር አሁንም አነስተኛ ስለሚሆን የብር የውጭ ምንዛሬ ተመኑ መዳከሙ ተጽእኖው ያን ያህል ነው ብለዋል።

መንግስት የሚያከናውናቸው ትልልቅ ፕሮጀክቶች ላይ ተጽእኖ አይኖረውም በሚል ለተነሳው ጥያቄ፥ እነዚህ ፕሮጀክቶች አሁንም የሚያስገኙት ጥቅም ዛሬ ካለው የምንዛሬ ለውጥ ስለማይብስ እንደሚቀጥሉ አንስተዋል።

የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች ከነገ ጀምሮ ተግባራዊ የሚሆነው የውጭ ምንዛሬ ተመን ማሻሻያ በተወሰነ መልኩ የዋጋ ግሽበትን እንደሚያስከትል ነው ያነሱት።

ይኸውም ለምሳሌ ዶላርን ለመግዛት ዋጋው ከአሁኑ ከፍ ያለ ብርን ስለሚጠይቅ ሀገር ወስጥ የሚገቡ ምርቶችን ዋጋ ሊያስወድድ እንደሚችል ጠቁመዋል።

ሆኖም መንግስት የምንዛሬ ተመን ማሻሻያውን ተከተትሎ የሚመጣ የዋጋ ግሽበትን ለመቆጣጠር መዘጋጀት እንዳለበት ምሁራኑ ተናግረዋል።

ዶክተር ቆስጠንጢኖስ ከፍተኛ ዋጋ ጭማሬን ሊያደርጉ የሚችሉ ነጋዴዎችን ከመቆጣጠር ባለፈ መጠነኛ የሆነ የዋጋ ቁጥጥር ሊያደርግ ይገባል ነው ያሉት ። ፕሮፌሰር ጣሰው ደግሞ የግብር አሰባሰቡ ላይ ከፍተኛ ክትትል ማድረግ እንደሚገባ ተናግረዋል።

በሌላ በኩል የውጭ ምንዛሬ ተመን ማስተካከያውን ተከትሎ የቀን ተቀን መጠቀሚያ ምርቶች ሊወደዱ ስለሚችሉ በተለይ በደሞዝ በሚተዳደሩ ዜጎች ላይ ጫናን ሊፈጥር እንደሚችል ተጠቁሟል።

በመሆኑም መንግስት ከዚህ ቀደም እንደሚያደርገው ምርቶችን እያቀረበ ዋጋን የማረጋጋት ስራው ላይ ጠንካራ መሆን እንዳለበት እና እንደ “አለ በጅምላ” ያሉ ተቋማት ሊጠናከሩ እንደሚገባቸው ይነሳል።

ምሁራኑ በምንዛሬ ተመን ማስተካከያው ሊፈጠር የሚችል ግሽበት የአንድ ጊዜ እንጂ፥ ያን ያህል ጠቅላላ ኢኮኖሚውን የሚጎዳ አይደለም ብለዋል፤ ይህንን ሀሳብ የብሔራዊ ባንኩ ምክትል ገዥና ዋና ኢኮኖሚስት ዶክተር ዮሀንስ ይጋራሉ።

Related stories   መከላከያ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ “ጁንታውን” ሙሉ በሙሉ መደምሰሱን አስታወቀ! በርካታ በቁጥጥር ስር ውለዋል

የውጭ ምንዛሬ ተመን ለውጡ ከረጅም ጊዜ አንጻር ከታየ ጥቅሙ ከፍተኛ መሆኑን ፕሮፈሰር ጣሰው ያነሱ ሲሆን፥ ማስተካከያው የወጪ ንግድ ገቢን እንደሚያሳድግ፣ ምርቶችን ሀገር ውስጥ ለማስገባት ምንዛሬ የማግኘት አቅምን ይጨምራል ነው ያሉት።

ይህ ካልሆነ አሁን እየተሰሩ ያሉ መሰረተ ልማቶችን እየተገነቡ የሚቀጥሉት የምንገዛውን ከምንሸጠው በጣም እያሳነስን ይሆናል፤ ይህ ደግሞ በጊዜ ሂደት ምጣኔ ሀብቱ ላይ ከፍተኛ ጉዳት እንደሚያደርስ ተናግረዋል። በሌላ በኩል ከውጭ ተገዝተው የሚገቡ ምርቶችን አስቀድሞ ለማወቅ እና ለጥንቃቄ ያግዛል ነው ያሉት ፕሮፈሰር ጣሰው። ይህም ማለት ከውጭ ከሚገቡ ሸቀጦች መካከል እጀግ አስፈላጊ የሆኑትን ብቻ እንድንመርጥ ያደርጋል ባይ ናቸው። ከዚህ ውጭ ገንዘብን ከሌሎች ሀገራት ምንዛሬ አንጻር አዳክሞ የወጪ ንግድን ማሳደግ አዲስ ነገር አይደለም ይላሉ።

በተለይ እንደ ቻይና ያሉ የሩቅ ምስራቅ ሀገራት ተመሳሳይ ነገርን በማድረግ የወጪ ንግድ ገቢያቸውንና ተወዳዳሪነቱን ማሳደጋቸውን ፕሮፈሰር ጣሰው በማሳየነት አንስተዋል። ብሔራዊ ባንክ ይፋ ያደረገው የ15 በመቶ የተመን ማስተካከያ ተመሳሳይ ውጤትን ለኢትየጵያ እንደሚያመጣ እና የጥቁር ገበያውን እንቀስቃሴ ለማዳከም ይረዳል ተብሎ ታምኖበታል።

ከነገ ጀምሮ ተግባራዊ የሚደረገው የውጭ ምንዛሬ ተመን ማሻሻያ ተጠቃሚ የሚያደርጋቸው አካላት አሉ። በዛሬ የምንዛሬ ተመን የውጭ ምንዛሬ ገዝቶ ያከማቸ ባንክ፥ ነገ ዋጋው ከፍ ስለሚል የሚያገኘው ትርፍ በንፋስ አመጣሽ ትርፍ የሚወሰድ ነው።

የገንዘብና የኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር ባወጣው የታክስ ህግ ደግሞ ከዚህ ትርፍ ላይ ግብር የመጣል ስልጣን አለው። ለምሳሌ የዛሬ ሰባት ዓመት ብር በ22 በመቶ አካባቢ እንዲዳከም ሲደረግ፥ ከዚህ ተጠቃሚ የሆኑ ባንኮች ከትርፋቸው 70 በመቶ ግብር እንዲከፍሉ የሚያደርግ መመሪያ ወጥቶ ተግባራዊ ሆኖ ነበር።

ይህ የሚደረገው ባንኮቹ ትርፉን ያገኙት መንግስት ባወጣው ህግ ስለሆነ ትርፉ ወደ መንግስት ማድላት ስላለበት ነው። አሁንም በዚህ የምንዛሬ ለወጥ ምክንያት ንፋስ አመጣሽ ትርፍ የሚያገኙ ባንኮች የትርፋቸው ሁኔታ ገቢያቸው ታይቶ ግብር እንዲከፍሉ የሚደረግ ይሆናል።

የብር የውጭ ምንዛሬ ዋጋ ከነገ ጀምሮ በ15 በመቶ ይዳከማል – ብሔራዊ ባንክ

የወጪ ንግድን ለማሳደግ ሲባል ከነገ ጀምሮ የብር የውጭ ምንዛሬ ዋጋ በ15 በመቶ እንዲዳከም እንደሚደረግ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገለፀ።

ዝቅተኛ የባንኮች የቁጠባ ሂሳብ የወለድ ተመንም ከ5 በመቶ ወደ 7 በመቶ ከፍ እንዲል እንደሚደረግ ነው ባንኩ የገለፀው።

Related stories   ብርሃኑ ነጋ አቋማቸውን ቀየሩ፤ ኢዜማ ደርግ በግፍ የዘረፈውን የግል ሃብት ለተከራይ እንደሚሸጥ ይፋ አደረገ፤ የኢዜማ የ ” ፍትህ” ሩጫ

በዚህ ጉዳይ ላይ የብሔራዊ ባንክ ምክትል ገዥ እና ዋና ኢኮኖሚስት ዶክተር ዮሀንስ አያሌው መግለጫ ሰጥተዋል።

በኢትዮጵያ የወጪ ንግድ እንቅስቃሴ ከ1996 እስከ 2004 በነበሩት 8 ዓመታት በፍጥነት ያድግ እንደነበር በመግለጫው ጠቅሰዋል።

ዓመታዊ አማካይ የእድገት ምጣኔውም 24 ነጥብ 1 በመቶ ነበር ብለዋል።

ነገርግን ከ2005 እስከ 2009 ባሉት 5 ዓመታት በዓለም ገበያ የሸቀጦች ዋጋ በከፍተኛ እና በተከታታይ ሁኔታ በመቀነሱ እና የአሜሪካ ዶላር ከሌሎች የኢትዮጵያ የንግድ ሸሪክ ሀገራት ገንዘቦች ጋር ያለው ምንዛሬ በከፍተኛ መጠን በመጠንከሩ ምክንያት የወጪ ንግድ እድገቱ ተቀዛቅዟል።

በተለይም በቡና፣ የቅባት እህል፣ ጥራጥሬ፣ ቆዳ እና የቆዳ ውጤቶች እንዲሁም ወርቅ በዚህ ምክንያት ከፍተኛ የዋጋ መቀነስ ያጋጠማቸው ምርቶች መሆናቸውን ነው የጠቀሱት።

መንግስት ባለፉት 5 ዓመታት በዓለም የሸቀጦች ዋጋ መቀነስ ምክንያት የተቀዛቀዘውን የሀገሪቱን የወጪ ንግድ ገቢ ለማካካስ ርብርብ በማድረጉ የገቢ ውድቀትን ለማስቀረት መቻሉን ባንኩ አንስቷል።

ሆኖም የ2008 እና የ2009 በጀት ዓመት የሸቀጦች የወጪ ንግድ አፈፃፀም መቀዛቀዝ ታይቶበታል።

በመሆኑም መንግስት በ2010 በጀት ዓመት የተቀመጡ ግቦችን ሳይሸራረፉ ለማሳካት ከግብርና፣ ከኢንዱስትሪ፣ ከማዕድን እና ከአገልግሎት ዘርፍ የሚገኘውን የውጭ ምንዛሬ በማሳደግ እየሰፋ የመጣውን የንግድ ሚዛን ለማጥበብ ዝግጅት አድርጎ በመንቀሳቀስ ላይ መሆኑን ዶክተር ዮሐንስ ተናግረዋል።

በማክሮ ኢኮኖሚ በኩል የወጪ ንግድ ምርቶችን ተወዳዳሪነት ለማጠናከር እና ሀገራዊ ቁጠባን ለማሳደግ የሚረዱ ፖሊሲዎችን መቅረፅ በማስፈለጉ የውጭ ምንዛሬ እና የገንዘብ ፖሊሲ ማሻሻያዎች መደረጉን ገልፀዋል።

በዚህም መሰረት ከነገ ጥቅምት 1 ቀን 2010 ዓ.ም ጀምሮ የብር የውጭ የምንዛሬ ዋጋ በ15 በመቶ እንዲቀንስ ተደርጓል ነው ያሉት።

በማስተካከያው መሰረትም ለምሳሌ ዛሬ 1 የአሜሪካ ዶላር የመግዣ ዋጋው 23 ነጥብ 4177 ብር ከሆነ፥ ነገ በምንዛሬ ተመኑ ላይ የ15 በመቶ ጭማሪ ተደርጎ 26 ነጥብ 9303 ብር የመግዣ ዋጋው ይሆናል ማለት ነው።

ዝቅተኛ የባንኮች የቁጠባ ሂሳብ የወለድ ተመንም ከነገ ጀምሮ ከ5 በመቶ ወደ 7 በመቶ ከፍ እንዲል ይደረጋል ብሏል የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ።

ከሰባት ዓመት በፊት በብር የውጭ ምንዛሬ ተመን  ላይ የ17 በመቶ ማስተካከያ ያደረገችው አገሪቱ፥ መሰል እርምጃ እንድትወስድ በዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት ስትጎተጎት ቆይታለች።

Share and Enjoy !

Shares

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *