“Our true nationality is mankind.”H.G.

‹‹ማትስ ሊግ››

የሰባት ዓመቱ እዩ ዮሴፍ ትውልዱና ዕድገቱ በአዳማ ነው፡፡ የመዋዕለ ሕፃናት ትምህርቱን አጠናቆ ወደ መደበኛው የትምህርት ዘርፍ የተቀላቀለው ዘንድሮ ነው፡፡ እንደ ማንኛውም ሕፃን  ቅብጥብጥና አንደበቱም የሚጣፍጥ ነው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ያለ ካልኩሌተር  ለመሥራት የሚያስቸግሩ ውስብስብ የሒሳብ ሥሌቶችን በጭንቅላቱ በፍጥነት የሚሰራና የዓመታት ልምድ ያለው የሒሳብ ሊቅ ይመስላል፡፡

በነጥብ (በዴሲማል) የሚካፈሉ ቁጥሮችን ሳይቀር በፍጥነት ያሰላል፡፡ ከሌሎች ትምህርቶች በተለየ ለሒሳብ ልዩ ፍቅር አለው፡፡ ለምን ቢሉ ‹‹ጥሩ ትምህርት ስለሆነ፤›› መልሱ ነው፡፡ የሚከብደው የሒሳብ ጥያቄ ያለ አይመስልም፡፡ የሒሳብ ፈተናም አሥር ከአሥር በማምጣት በትምህርት ቤቱ የታወቀ ነው፡፡ ለነገሩ ከአንደኛ ክፍል አልፎ የስምንተኛ ክፍል የሒሳብ ሥሌቶችን መሥራት ለጀመረ ልጅ መሠረታዊ የሒሳብ ሥሌቶችን መሥራት እንዴት ሊከብደው ይችላል?

የልጃቸው የሒሳብ ችሎታ የገባቸው ወላጅ አባቱ አቶ ዮሴፍ ገብረየስ በተቻላቸው ሁሉ ይረዱታል፣ ያስጠኑታልም፡፡ በልጃቸው እንደሚተማመኑም ከሁኔታቸው መገመት አይከብድም፡፡ ‹‹59 ÷ 7 ስንት ነው›› ብለው ጠየቁት እየተኩራሩ፡፡ እንኳንስ በእሱ ዕድሜ ላለ ጥያቄው ለአዋቂም ቢሆን ጥቂት ማሰብን፣ የሥሌት ማሽን (ካልኩሌተር) ወይም ወረቀት ላይ ማሰብ የሚጠይቅ ዓይነት ነው፡፡ እዩ ግን በፍጥነት ‹‹8.428571፤›› መጠቀምን የሚጠይቅ ቢሆንም፣ በፍጥነት በማለት ከነጥብ በኋላ የሚመጡ ሽራፊ ሥሌቶችን ሳይቀር መለሰ፡፡ መልሱ ትክክል መሆን አለመሆኑንም በካልኩሌተር አስልተን አረጋገጥን፡፡ ሌሎችም ከባድና ውስብስብ የሚባሉ የሒሳብ ጥያቄዎችን አከታትለን ጠየቅነው፡፡ ሁሉንም በፍጥት ሲመልስ ምንም አይነት ስህተት አልተገኘበትም ነበር፡፡

እንደ እዩ ካሉ ለየት ያለ ስጦታ ካላቸው አንዳንድ ልጆች በስተቀር የሒሳብ ችሎታ ማዳበር ተራ ሥሌቶችን ለመሥራት ለመደመርና ለማካፈል በጭንቅላታቸው ከማሰብ ይልቅ በካልኩሌተር ማስላት የሚቀላቸው ብዙ ናቸው፡፡ የሒሳብ ትምህርት ባለመቻላቸው የኅብረተሰብ ሳይንስ ማጥናትን የሚመርጡም ብዙ ናቸው፡፡ በተቃራኒው የሒሳብ ትምህርት የሚወዱ ሲያጋጥሙ ደግሞ የተለየ ችሎታ ልዩ ተሰጥኦ ያላቸው ተደርገው ሊቆጠሩ ይችላሉ፡፡

Related stories   የዘረኝነት ጥግ “እናት ነኝ የሌሎች ህፃናት ወላጆችን ግን ገደልኩ”

‹‹ሒሳብ እንደሚፈራው ሳይሆን፣ ምክንያታዊ ሆኖ ማሰብን የሚጠይቅ መሠረታዊ የሳይንስ አካል ነው፤ የሒሳብ ዕውቀት የለኝም ማለት ማሰብ አልችልም እንደማለት ነው፤›› የሚሉት የቀድሞ የፊዚክስ መምህር አቶ ተስፋዬ ወንዴ፣ ‹‹ሒሳብ አልችልም፤›› ማለት መቀየር ያለበት አስተሳሰብ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡

የማህበረሰቡ የሒሳብ ችሎታ አሁን ካለበት አንድ እርምጃ ለማስኬድም በተማሪዎች ላይ ትልቅ ስራ መሰራት እንዳለበትና ለዚህም ሁሉም የበኩሉን ሊወጣ እንደሚገባ ያምናሉ፡፡ በግላቸውም የተለያዩ ጥረቶች ያደርጋሉ፡፡ ከጥረታቸው አንዱ በቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ኢንስቲትዩት ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ላይ የተዘጋጀው የማትስ ሊግ ዋናው ነው፡፡

ማትስ ሊግ ዓለም አቀፍ የሒሳብ ውድድር ሲሆን፣ የተጀመረውም ከ20 ዓመታት በፊት በአሜሪካ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ሲካሄድ ደግሞ የአሁኑ የመጀመርያው ነው፡፡ አቶ ተስፋዬ ውድድርን በራሳቸው ተነሳሽነት እንዲካሄድ የማስተባበር ስራ ሰርተዋል፡፡

      ‹‹የውድድሩ አላማ ተማሪዎችን ለከፍተኛ ውጤት ማነሳሳት ነው፤›› የሚሉት አቶ ተስፋዬ፣ በከተማው ከሚገኙ ከመንግሥትና ከግል ትምህርት ቤቶች የተውጣጡና የሒሳብ ችሎታ ያላቸው ከ60 የሚበልጡ ተማሪዎች የተሳተፉበት እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ በውድድሩ የተካተቱት ከአራት እስከ 12ኛ ክፍል ያሉ ተማሪዎች ናቸው፡፡

የ16 ዓመቷ ሔራን አሻግሬ በውድድሩ ከተሳተፉ ተማሪዎች መካከል ነች፡፡ በፋውንቴን ኦፍ ኖውሌጅ ትምህርት ቤት የ11ኛ ክፍል ተማሪ ስትሆን፣ ባዮሎጂ፣ ፊዚክስ፣ ኬሚስትሪና ሒሳብ ከሌሎቹ በተለየ የምትወዳቸው የትምህርት ዓይነቶች እንደሆኑ ትናገራለች፡፡ ለዚህ ፈተና የታጨችውም በሒሳብ ትምህርት የተሻለች በመሆኗ ነው፡፡

ፈተናውን ስትገልጽ ‹‹የመጀመርያዎቹ ጥያቄዎች ምንም አይሉም ነበር፡፡ ከዚያ በኋላ ያሉት ግን አስቸጋሪ ነበሩ፤›› ትላለች፡፡ ለዚህም የተሰጠው ጊዜ አነስተኛ መሆኑ፣ እንዲሁም በቂ የጥናት ጊዜ አለማግኘቷ ፈተናው እንዲከብዳት ያደረጉ ምክንያቶች ናቸው፡፡ ከተዘጋጁት ጥያቄዎች መካከል ገና ያልተማረቻቸው የሒሳብ ቀመሮችም መኖራቸው ፈተናው እንዲከብዳት ማድረጉን ትናገራለች፡፡

Related stories   ፋኦ በትግራይ ክልል ለአርሶ አደሮች የእህል ዝርያዎችን ማሰራጨትና እንስሳቶችን መከተብ ጀመረ

የስምንተኛ ክፍል ተማሪው ቅዱስ ማርዬም ፈተናውን ለመሥራት የተሰጣቸው ጊዜ አነስተኛ መሆኑ፣ ፈተናውን አስቸጋሪ እንዳደረገው ይናገራል፡፡ ‹‹ጥያቄዎቹና የተሰጣቸው ሰዓት አለመመጣጠናቸው በተሰጠው ጊዜ መጨረስ እንዳንችል አድርጎናል፤›› ይላል፡፡ በውድድሩ ጊዜ በግልና በቡድን የሚሠሩ ጥያቄዎች ተካተው ነበር፡፡ ይበልጥ የከበዳቸው ግን በግል የሚሰሩ ሁለት ጥያቄዎች ናቸው፡፡ ለእነዚህ ጥያቄዎች የተሰጣቸው ጊዜም ስድስት ደቂቃ ብቻ እንደነበር በቅሬታ ነበር የገለፁት፡፡

ውድድሩ ከፊታችን ላለው የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና እንድንዘጋጅ አድርጎናል ያለው ደግሞ የ17 ዓመቱ ሁንዳኦል ንጉሤ ነው፡፡ ለፈተናው ዝግጅት ቢያንስ የሁለት ሳምንት ጊዜ እንደሚያስፈልገው ይናገራል፡፡ በተሰጠው አጭር የመዘጋጃና ፈተናው የሚሠራበት አጭር ሰዓት ምክንያት በተገቢው መጠን እንዳልሠራ ይናገራል፡፡ ሆኖም በውድድሩ መካፈሉ ጥሩ ልምድ እንደሰጠው ያክላል፡፡

እነዚህ የሒሳብ ችሎታ አላቸው ተብለው የተመረጡ ተማሪዎች እንኳ ፈተናው ያልጠበቁት ያህል ከብዷቸዋል፡፡ ይህ በዕርግጥም ፈተናው ከባድ ሆኖ አልያም በመማር ማስተማሩ ችግር የተማሪዎቹ አቅም ውስን ሆኖ ሊሆን ይችላል፡፡ ነገር ግን በአንድም ሆነ በሌላ መንገድ ትልቅ ክፍተት መኖሩን ያሳየ አጋጣሚ ነው፡፡

አቶ ተስፋዬም በአገሪቱ የሒሳብ ትምህርት በተገቢው መጠን አለማደጉን የሚናገሩት ከራሳቸው ትዝብት በመነሳት ነው፡፡ በአንድ ወቅት የገጠማቸውንም እንዲህ አስታውሰዋል፡፡ 1.5 ÷ 0.1 ስንት ይሆናል ብለው ፊዚክስ ያስተምሯቸው የነበሩ የዘጠነኛ ክፍል ተማሪዎችን ይጠይቃሉ፡፡ ትክክለኛ መልስ የሚሰጣቸው ሰው አልነበረምና ሁሉንም የዘጠነኛ ክፍል (አራት ክፍሎች) ለመጠየቅ ተገደዱ፡፡

Related stories   የትግራይ ክልል ባቀረበው ፍላጎት መሠረት የአፈር ማዳበሪያ መቶ በመቶ እንዲቀርብ መደረጉ ተገለጸ

ነገር ግን ከዚያ ሁሉ ተማሪ ትክክለኛውን መልስ ያገኙት ሦስት ተማሪዎች ብቻ ነበሩ፡፡ ‹‹ይህንን ትምህርት አራተኛና አምስተኛ ክፍል ተምረው ያለፉት ነው፡፡ ለካ የእኔ ተማሪዎች የማይችሉት ፊዚክስ ሳይሆን ሒሳብ ነው ብዬ ሒሳብ ትምህርት ማስተማር ጀመርኩ፤›› ይላሉ፡፡ ሒሳብ ሌሎች የትምህርት ዓይነቶችን ለመማር መሠረታዊ ነው፡፡ በሌላው አገር የሚገኙ የስምንተኛ ክፍል ተማሪዎች የሚሠሩትን እዚህ የ12ኛ ክፍል ተማሪ እንደማይሠራው ይናገራሉ፡፡ በሒሳብ ችሎታቸው የተሻሉ እንደሆኑ ተመስክሮላቸው ከየትምህርት ቤቱ ተመርጠው የመጡ ተማሪዎች እንኳ ፈተናው በጣም ከብዷቸው እንደነበር፣ ይህም የችሎታ ማነስን እንደሚያሳይ ይናገራሉ፡፡

‹‹ማትስ ሊግ›› በማትስ ሊግ ተሳታፊ የነበሩ ተማሪዎች ፈተና በመሥራት ላይ ሳሉ

በአገሪቱ ያሉ የተለያዩ ትምህርት ቤቶችም ለዚህ ትኩረት አድርገው መሥራት እንደሚገባቸው ይናገራሉ፡፡ እንዲህ ባሉ ዓለም አቀፍ ውድድሮች ላይ ተሳትፈው ውጤት ማምጣት የሚችሉ ተማሪዎችን ለማፍራት እንደ እዩ ያሉ ልዩ ተሰጥኦ ያሏቸውን ልጆች ከመጠበቅ ይልቅ ያሉትን ብቁ ማድረጉ ላይ መሥራት ግድ ነው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ በተለያዩ የትምህርት ዓይነቶች ልዩ ተሰጥኦ ያላቸውን ፍጥነታቸው በሚጠይቀው መልኩ የተለየ የትምህር ሥርዓት ውስጥ እንዲገቡ ማድረግ የሚኖረው ጥቅም በግለሰብ ደረጃ ብቻ ሳይሆን እንደ አገርም ሊታይ የሚገባው ነው፡፡

‹‹ሒሳብ በ21ኛው ክፍለ ዘመን የምንደራደርበት ጉዳይ አይደለም፡፡ ድሮድሮ ሒሳብ አልችልም ማለት ምንም ማለት አልነበረም፡፡ አሁን ግን አሳፋሪ ነው፡፡ ሒሳብ አለመቻል ማሰብ አለመቻል ነው፤›› የሚሉት አቶ ተስፋዬ፣ ክሪቲካል ቲንኪንግ፣ ፕሮብሌም ሶልቪንግና ኮሙዩኒኬሽን በዚህኛው ዘመን ወሳኝ ነገር መሆናቸውን ለእነዚህ ደግሞ ሒሳብ መሠረታዊ ጉዳይ መሆኑን ይገልፃሉ፡፡

Amharic reporter

Share and Enjoy !

Shares
0Shares
0