ከሲኖዶሳዊው የቤተ ክርስቲያን አሠራርና የውሳኔ አሰጣጥ አንጻር፣ ቅዱስ ፓትርያርኩ የማኅበረ ቅዱሳን የቴሌቪዥን ፕሮግራም እንዲታገድ በራሳቸው ደብዳቤ መጻፋቸው ትክክል አይደለም፤ በውላችን መሠረት፣ የቴሌቪዥን መርሐ ግብራችን ሥርጭቱን ቀጥሏል፤ ወደፊትም በሌሎች ቋንቋዎች ጭምር ተደራሽነታችንን በማስፋት ለመሥራት ዐቅደናል፤ አባላቱና ደጋፊዎቹ፣ ዐሥራት ለቤተ ክርስቲያን እንዲከፍሉ ያስተምራል እንጅ ማኅበሩ ለራሱ ሰብስቦ አያውቅም፤ ለወደፊትም ቢኾን የዚህ ዓላማ የለውም፤ በአባልነት አስተዋፅኦ ነው አገልግሎቱን […]

via ማኅበረ ቅዱሳን: ከፓትርያርኩ ጋራ በተያያዘ ስለሚነሡ ጉዳዮች ማብራሪያ ሰጠ፤“አጠቃላይ ጉባኤውን ለመሳተፍ እየተዘጋጀን እንገኛለን”/ዋና ጸሐፊው/ — ሐራ ዘተዋሕዶ

  • ከሲኖዶሳዊው የቤተ ክርስቲያን አሠራርና የውሳኔ አሰጣጥ አንጻር፣ ቅዱስ ፓትርያርኩ የማኅበረ ቅዱሳን የቴሌቪዥን ፕሮግራም እንዲታገድ በራሳቸው ደብዳቤ መጻፋቸው ትክክል አይደለም፤
  • በውላችን መሠረት፣ የቴሌቪዥን መርሐ ግብራችን ሥርጭቱን ቀጥሏል፤ ወደፊትም በሌሎች ቋንቋዎች ጭምር ተደራሽነታችንን በማስፋት ለመሥራት ዐቅደናል፤
  • አባላቱና ደጋፊዎቹ፣ ዐሥራት ለቤተ ክርስቲያን እንዲከፍሉ ያስተምራል እንጅ ማኅበሩ ለራሱ ሰብስቦ አያውቅም፤ ለወደፊትም ቢኾን የዚህ ዓላማ የለውም፤ በአባልነት አስተዋፅኦ ነው አገልግሎቱን የሚያከናውነው፤
  • ከመተዳደሪያ ደንባችን ባሻገር የቅዱስ ሲኖዶስን ውሳኔዎች የሥራችን አካል አድርገን እየተገበርን እንገኛለን፡፡ በቤተ ክርስቲያን የገንዘብ ደረሰኞች(ሞዴላ ሞዴል) እንድንጠቀም መወሰኑና እየተጠቀምንም መኾኑ አንዱ ማሳያ ነው፤
  • የፋይናንስ እንቅስቃሴያችን ትክክለኛ መኾኑን የውጭ ኦዲተሮች ብቻ ሳይኾኑ፣ የጠቅላይ ቤተ ክህነታችን ኦዲተሮችም ያረጋገጡት ሐቅ ነው፡፡ ያልተጨበጠ ክሥ የሚያቀርበው የቤተ ክርስቲያናችን አካል ሊኾን አይችልም፤
  • በሕገ ወጥ መንገድ ያስቀመጠው 170 ሚሊየን ዶላር በፖሊስ ተያዘበት፤” የሚለው መሠረተ ቢስ ወሬ፣ ከጥቅማቸው አንጻር ማኅበሩን የመወንጀል አባዜ የተጠናወታቸው አካላት የስም ማጥፋት ዘመቻ ነው፤
  • በማኅበሩ ላይ የሚካሔዱ የስም ማጥፋት ዘመቻዎችና አሉባልታዎች ኹሉ፣ በቀጥታም ኾነ በተዘዋዋሪ፣ ወደ መዋቅር ከገቡና ተጋልጠው ከወጡ የ‘ተሐድሶ’ መናፍቃን ጋራ የተያያዘ ነው፤
  • በ36ው አጠቃላይ የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ እንዳንሳተፍ በቅዱስ ፓትርያርኩ መታገዳችንን በወሬ ደረጃ ብንሰማም፣ ከጠቅላይ ጽ/ቤቱ 2 የግብዣ ደብዳቤዎች ደርሰውናል፡፡ በእኛ በኩል ለመሳተፍ እየተዘጋጀን እንገኛለን፤
  • ከቅዱስ ፓትርያርኩ መመሪያና ቡራኬ ለመቀበል በተደጋጋሚ ደጅ ብንጠናምልዩ ዓላማ ባላቸውግለሰቦች ምክንያትአልተሳካልንም፤ ክፍተቶቹ፣ በማንኛውም ጊዜ መነጋገር ስንጀምር በቀላሉ ሊፈቱ የሚችሉ ናቸው፤ ብለን እናምናለን፤

(ሰንደቅ፤ ረቡዕ፣ ጥቅምት ፩ ቀን ፳፻፲ ዓ.ም.)

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ማኅበረ ቅዱሳን፣ በቅዱስ ሲኖዶስ ዕውቅና አግኝቶ ከተመሠረተ 25 ዓመት ሞላው፡፡ ማኅበሩ፥ በአዲስ አበባ ከሚገኘው ዋና ማዕከሉ በተጨማሪ፣ በየአህጉረ ስብከቱ 48 ያህል ማዕከላት፣ ከ500 በላይ የወረዳ ማዕከላት እንዲሁም፣ ከ400 በላይ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የግቢ ጉባኤያት ያሉት ሲኾን፤ በሚሊየን የሚቆጠሩ አባላትና ደጋፊዎችን ማፍራት የቻለ የአገልግሎት ማኅበር ነው፡፡ በማኅበሩ ወቅታዊ እንቅስቃሴና ማኅበሩን አስመልክቶ ስለሚነሡ ሰሞናዊ ጉዳዮች፣ ከማኅበሩ ዋና ጸሐፊ አቶ ውብሸት ኦቶሮ ጋራ ባልደረባችን ፍሬው አበበ ያደረገው የቃለ ምልልስ ቆይታ ከዚህ በታች ተስተናግዷል፡፡

†††

ሰንደቅ፡- የማኅበሩ የቴሌቪዥን ፕሮግራም በተደጋጋሚ በብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ እገዳ እየተጣለበት መኾኑ ይሰማል፤ ምክንያቱ ምንድን ነው?

አቶ ውብሸት፡- እንደሚታወቀው በኢቤኤስ ቴሌቪዥን ጣቢያ በኩል ከ2005 እስከ 2008 ዓ.ም. ድረስ የቴሌቪዥን መርሐ ግብር ስናስተላልፍ ነበር፡፡ መርሐ ግብሩም፥ በርካታ ምእመናን የተማሩበት፣ ብዙዎች ለጥያቄዎቻቸው መልስ ያገኙበትና የተጠቀሙበት መርሐ ግብር ነበር፡፡ በወቅቱ በቤተ ክርስቲያን ዕውቅና የሌላቸው የተለያዩ አካላትም፣ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ስም በሕገ ወጥ መንገድ መርሐ ግብሮችን በጣቢያው ያስተላልፉ ስለነበር፤ “አግባብነት የለውም፤” በሚል ለቅዱስ ሲኖዶስ የቀረበ ጥያቄ ነበር፡፡ ቤተ ክርስቲያን የማታውቃቸው፣ ሕገ ወጥ የኾኑ፣ ነገር ግን በቤተ ክርስቲያን ስም መርሐ ግብራቸውን የሚያስተላልፉ አካላት እንዲታገዱ ከማኅበረ ምእመናንና ከወጣቶች በ2008 ዓ.ም. ጥያቄ ቀርቦ እንደነበርም የምናስታውሰው ነው፡፡

በዚህም መሠረት የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ፣ ቤተ ክርስቲያን የማታውቃቸው፣ ሕገ ወጥ የኾኑ፣ ነገር ግን በቤተ ክርስቲያን ስም መርሐ ግብራቸውን የሚያስተላልፉ አካላት እንዲታገዱ ወሰነ፡፡ ውሳኔው ሲተገበር ግን፣ ማኅበራችን ሕጋዊና በቤተ ክርስቲያን የሚታወቅ ቢኾንም፣ ለኢቢኤስ በተጻፈው ደብዳቤ የቴሌቪዥን መርሐ ግብሩ ተለይቶ ሳይገለጽ አንድ ላይ እንዲታገድ ኾነ፡፡

ከውሳኔው በኋላ ጉዳዩ እንዲታይልንና እገዳው እንዲነሣልን ለሚመለከተው የቤተ ክርስቲያናችን የበላይ አካል ጥያቄ አቅርበን ነበር፡፡ ይኹንና ጥያቄያችን ምላሽ ባለማግኘቱና በወቅቱ ቅዱስ ሲኖዶስ፣ ቤተ ክርስቲያን የራስዋ የ24 ሰዓት የቴሌቪዥን ሥርጭት እንድትጀምር ወስኖ ስለነበር አማራጩን ለመጠቀም ወሰንን፡፡ ይኸውም በቤተ ክርስቲያናችን በሚከፈተው የቴሌቪዥን ጣቢያ መጠቀም እንድንችል እንዲፈቀድልን መጠየቅ ነበር፡፡ በዚህም መሠረት ጥያቄያችንን አቀረብን፡፡ በቃል ካቀረብናቸው ጥያቄዎች በተጨማሪ ለኹለት ጊዜያት በደብዳቤም አመልክተናል፡፡

የጥያቄያችን ጭብጥ ኹለት መልኮች ነበሩት፡፡ አንደኛው፥ አቅማችንን አስተባብረን ቤተ ክርስቲያን የከፈተችውን የ24 ሰዓት የቴሌቪዥን ጣቢያ ሥርጭት እናግዝ ዘንድ እንዲፈቀድልን የሚጠይቅ ሲኾን፤ ኹለተኛው ጭብጥ ደግሞ፣ ለማኅበሩ የተወሰነ የአየር ሰዓት ተሰጥቶት መርሐ ግብሩን እንዲያስተላልፍ ይፈቀድልን የሚል ነበር፡፡ ይህን ጥያቄያችንን ያቀረብነው በ2008 ዓ.ም ነበር፤ ነገር ግን መልስ የሚሰጠን አካል አላገኘንም፡፡ በ2009 ዓ.ም. በድጋሚ ጥያቄያችንን አቀረብን፤ አኹንም መልስ አልተሰጠንም፡፡

በግንቦት 2009 ዓ.ም. የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ላይ የጠቅላይ ጽ/ቤት የብዙኃን መገናኛ አገልግሎት ድርጅት ሪፖርትበሚቀርብበት ወቅት የማኅበራችን ጥያቄም በብፁዓን አባቶች በኩል ተነሥቶ ነበር፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ ውይይት ከተደረገ በኋላ በመጨረሻ ላይ ቅዱስ አባታችን፣ ማኅበሩ የራሱን የቴሌቭዥን ጣቢያ መክፈት ይችላል፤ የሚል መልስ እንደሰጡ ተረድተናል፡፡

ቅዱስነታቸው የሰጡትን አቅጣጫ ከሰማን በኋላ ቤተ ክርስቲያናችን፥ በሚሊዮን የሚቆጠሩና ባለብዙ ቋንቋ ተናጋሮች ምእመናን ያሏት እንደመኾንዋ መጠን አንድ የቴሌቪዥን ጣቢያ ብቻ በቂ አይደለም፤ ተጨማሪ ሥራዎች ሊሠሩ ይገባል ብለን በማመን ወደ ቀጣይ ሥራ ገባን፡፡ ማኅበሩ የአየር ሰዓት አግኝቶ መርሐ ግብሩን የሚያሰራጭበትን አማራጭ መንገዶች ስናይና ስናጠና ቆየን፡፡

በዚህ መሠረት ተቀማጭነቱና ሕጋዊነቱ በአሜሪካ ከኾነው የአሌፍ ቴሌቭዥን ጣቢያ በሳምንት ለሰባት ሰዓታት የአየር ሰዓት ለመከራየት ቻልን፡፡ ከመስከረም አንድ ቀን 2010 ዓ.ም ጀምሮ በሦስት ቋንቋዎች ማለትም በአማርኛ፣ በኦሮምኛ እና በትግርኛ ቋንቋዎች እያስተላለፍን እንገኛለን፡፡ ይህ ከኾነ በኋላ ቅዱስ አባታችን ለጠቅላይ ቤተ ክህነት፣ የቴሌቪዥን ፕሮግራሙ እንዲታገድ የሚያዝዝ ደብዳቤ እንደጻፉ ሰምተናል፡፡

እንደሰማነው፣ በደብዳቤው ላይ ኹለት የቴሌቭዥን መርሐ ግብሮች እንዲታገዱ ነው የተጻፈው፡፡ አንዱ፥ በቤተ ክርስቲያን ሥር ሕጋዊነት ያለው የማኅበረ ቅዱሳን ቴሌቪዥን መርሐ ግብር ሲኾን፤ ኹለተኛው፣ በቤተ ክርስቲያን ዕውቅና የሌለውና ከቤተ ክርስቲያን ውጭ የኾነ አካል ጣቢያ እንደኾነ ሰምተናል፡፡

ይኼ ጥያቄ ለምን ቀረበ? መነሻውስ ምንድን ነው? ብለን ስናይ ሕጋዊና ተቀባይነት ያለው መነሻ አላገኘንለትም፡፡ ሕጋዊ መነሻ ስንል፣ በቤተ ክርስቲያናችን ጉዳዩ ተመርምሮ ውሳኔ የሚተላለፍበት አሠራር አለ፡፡ ይኸውም፣ ስለ ቤተ ክርስቲያን የብዙኃን መገናኛ  አጠቃቀም አጠቃላይ ሒደት ውሳኔ ያስተላለፈውና የቤተ ክርስቲያንም የመጨረሻ የሥልጣን ባለቤት የኾነው የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ነው፡፡ እንዲሁም ምልአተ ጉባኤው በተከታታይ ስለማይሰበሰብ የምልአተ ጉባኤውን ውክልና ወስዶ በቅዱስ ሲኖዶሱ የጸደቁ ሕጎችን፣ ደንቦችን፣ መመሪያዎችንና ውሳኔዎች ተፈጻሚነት የሚከታተልና የሚቆጣጠር ቋሚ ሲኖዶስ ነው፡፡ ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያናችን፣ በእነዚህ ኹለት መንገዶች የሚገለጽ ሲኖዶሳዊና ጉባኤያዊ አመራር፣ አሠራርና የውሳኔ አሰጣጥ ሒደት ነው ያላት፡፡

የቅዱስ ፓትርያርኩ የእገዳ ደብዳቤ ጉዳይ ግን፣ በዚህ መንገድ ውይይት የተደረገበትና ውሳኔ የተሰጠበት አይደለም፡፡ ስለዚህ የእገዳው ሐሳብ ሕጋዊነትና ተቀባይነት የሌለው ውሳኔ ነው፡፡ ነገር ግን፣ ጣቢያው እስከ አኹን በይፋ የደረሰው የእግድ ደብደቤ እንደሌለ ነው የገለጸልን፡፡ ስለዚህ በውላችን መሠረት የቴሌቪዥን መርሐ ግብራችን ሥርጭት ቀጥሏል፤ ወደፊትም በሌሎች ቋንቋዎች ጭምር ተደራሽነታችንን በማስፋት ለመሥራት ዐቅደናል፡፡

ሰንደቅ፡- የማኅበሩ የቴሌቪዥን ፕሮግራም አንዱና ዋናው ግቡ ትምህርተ ወንጌልን ማስፋፋት ነው ተብሎ ይታመናል፡፡ ወንጌልን ማስፋፋት፣ ለቤተ ክርስቲያኒቱ ተከታዮች የእግዚአብሔርን ቃል ማስተማር በመኾኑ እንደ ጥፋት የታየው ለምንድን ነው?

አቶ ውብሸት፡- በእውነት ለእኛም ግልጽ ካልኾኑልንና ካልገቡን ነገሮች አንዱ ይኼ ነው፡፡ ትምህርተ ወንጌልን ማስፋፋት፣ የእናት ቤተ ክርስቲያንን አገልግሎት ማገዝ ቤተ ክርስቲያናችን የምትደሰትበትና የምትደግፈው ነገር ነው፡፡ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ለማኅበሩ በፈቀደው መተዳደርያ ደንብ ላይ፥ የኤሌክትሮኒክስ ሚዲያን ጨምሮ በተለያዩ ዘመናዊ የብዙኃን መገናኛ ዘዴዎች ትምህርተ ወንጌልን ለዘመኑ ትውልድ እንድናዳርስ ነው የተፈቀደልን፡፡ ምልአተ ጉባኤው አጽድቆ የሰጠንን የቤተ ክርስቲያንን መሠረታዊ ተልእኮ የማጠናከርና የማስፋፋት ተግባር ማገድ ወይም መከልከል ማለት ቅዱስ ሲኖዶሱን መጋፋትና መቃወም ማለት ነው፡፡

እንግዲህ ይኼን ለማሰናከል የሚሠራው አካል፣ በቤተ ክርስቲያን የወንጌል መስፋፋትና ዕድገት የማይደሰት አካል ነው ብለን ነው የምናስበው፡፡ ምናልባት ለቅዱስ አባታችን በቅርብ ኾነው የተሳሳተ መረጃ የሚያቀብሉ፣ ያልኾነ ነገር የሚመክሩ አካላት እንዳሉ ነው የምንጠረጥረው፡፡ በቤተ ክርስቲያን ትምህርተ ወንጌል መስፋፋትና መጠናከር ምክንያት የሚጎዱ አካላት አሉ ማለት ነው፡፡ ሐቀኛ የቤተ ክርስቲያን ወገን የኾነ አካልም ይኹን ግለሰብ፣ የቅዱስ ሲኖዶስን ውሳኔ አይጋፋም፤ አይቃወምም፤ የአማናዊውን ቅዱስ ወንጌል መስፋፋትን አይጠላም ብለን ነው የምናምነው፡፡

ሰንደቅ፡- ቅዱስ ፓትርያርኩን አግኝታችሁ ኹኔታዎችን ለማስረዳትና ለመወያየት ያደረጋችሁት ጥረት አለ?

አቶ ውብሸት፡- ቅዱስ አባታችንን ለማግኘት የሞከርነው አሁን አይደለም፡፡ ቅዱስ አባታችን ከተሾሙበት ጊዜ ጀምሮ አግኝተናቸው መመሪያና ቡራኬ ለመቀበል ብዙ ጥረት አድርገናል፡፡ በተደጋጋሚ ደጅ ጠንተን አልሳካ ሲለን በደብዳቤ ጭምር ጥያቄዎችን አቅርበናል፡፡ ከዚህ ኹሉ ጥረት በኋላ፣ በ2008 ዓ.ም. አጋማሽ ገደማ አንድ ጊዜ ለማነጋገር ዕድል አግኝተናል፡፡ በዚያ መድረክ ስለ ማኅበሩ አገልግሎት አስረድተናል፡፡ በዚያን ወቅት ቅዱስ አባታችን ቃል የገቡልን ነገር ቢኖር፣ በተከታታይ እንደምንገናኝ፣ በውይይት ችግሮችን እንደምንፈታ፣ እንደምንመካከር፣ ቡራኬም እንደሚሰጡን፣ በራቸው ለእኛ ክፍት መኾኑን ነበር፡፡ ከዚያ ወዲህ ግን ቅዱስ አባታችንን ደግመን ለማግኘት ብንሞክርም የሚሳካልን አልኾነም፡፡ ዕድሉን ማግኘት አልቻልንም፡፡

ብፁዓን አባቶችንም በሽምግልና መልክ ልከናል፡፡ ያለው ችግር ምንድን ነው? ጥፋት ካለ እንታረም፤ ማኅበሩ፥ የኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን አገልግሎት በዕውቀታቸውና በሞያቸው ለማገዝ ለሃይማኖታቸው ቀናዒ የኾኑ ሰዎች የተሰባሰቡበት እንጂ የቅዱሳን መላእክት ስብስብ ባለመኾኑ በማወቅም ባለማወቅም ስሕተት ሊኖር፣ ሊያጋጥም ይችላል፡፡ ስሕተት ካለ እንታረም፤ ብለን ጠይቀናል፡፡ ኾኖም ግን የማነጋገሩን ዕድል በድጋሚ ማግኘት ባለመቻላችን ችግሩን መፍታት አልተቻለም፤ እናዝናለን፡፡

ሰንደቅ፡- ሌላው ማኅበረ ቅዱሳን ላይ የሚነሣው ነገር፣ ለቤተ ክርስቲያን ሊከፈል የሚገባውን ዐሥራት ይሰበስባል፤ ያለው የገንዘብና ንብረት መጠንም በትክክል አይታወቅም፤ የሚሉ ወቀሳዎችና ክሦች ናቸው፤ ይህን በተመለከተ አስተያየታችሁ ምንድን ነው?

አቶ ውብሸት፡- ማኅበረ ቅዱሳን በቤተ ክርስቲያን ሥር የተዋቀረ እንደ መኾኑ መጠን ሀብቱና ንብረቱ በሙሉ የቤተ ክርስቲያን ነው፡፡ ማኅበሩ፥ ዐሥራት በኩራትን አይሰበስብም፡፡ ይልቁንም እያንዳንዱ ምእመን፣ ለቤተ ክርስቲያን ሊከፍል የሚገባውን ዐሥራት በኩራት በአግባቡ እንዲሰጥ ነው የሚያስተምረው፡፡ ማኅበረ ቅዱሳን አገልግሎቱን የሚያከናውነው፣ አባላቱ እንደ ምእመን፥ ዐሥራታቸውን ለቤተ ክርስቲያን ከመስጠት ባሻገር ለማኅበሩ በሚያደርጉት የአባልነት መዋጮ ነው፡፡ አባላት፣ ከገቢያቸው እንደማንኛውም ምእመን ለቤተ ክርስቲያን ከሚያወጡት ዐሥራት በኩራት ተጨማሪ ኹለት በመቶ እያዋጡ የማኅበሩን አገልግሎት ይደግፋሉ፡፡ ከዚህ ውጭ ያለው የሐሰት ወሬ ስለኾነ ይህን የሚል አካል ካለ በማስረጃ ነው ማቅረብ ያለበት፡፡

ከዚያ ውጭ በአብነት ት/ቤቶችና በገዳማት የሚተገበሩ ፕሮጀክቶች አሉን፡፡ ፕሮጀክቶቹን ቀርፀን ለበጎ አድራጊ ምእመናን እንሰጣለን፡፡ ይኼን ብትሠሩ ካህናትን፣ የአብነት ተማሪዎችንና መምህራንን ከስደት፤ ቤተ ክርስቲያንን፣ አብያተ ጉባኤያትንና ቅዱሳት መካናትን ከመዘጋትና ከመፍረስ እናድናለን፤ ብለን በማስረዳት ካመኑበት ይሠሩታል፡፡ ማኅበሩም ሞያዊ አስተዋፅኦውን ያደርጋል፡፡ በዚህ መሠረት የተለያዩ ሥራዎችን አከናውነናል፤ እያከናወንም እንገኛለን፡፡

“የማኅበሩ ንብረት አይታወቅም፤” የሚል ወቀሳም እንዳለ ተጠቅሷል፡፡ የማኅበሩ ንብረት ይታወቃል፡፡ በየዓመቱ ለጠቅላይ ቤተ ክህነትና ለሚመለከታቸው አካላት ኹሉ ሪፖርት እናደርጋለን፡፡ ሪፖርቱ የሥራ ክንውንና የሒሳብ ሪፖርትን አጣምሮ የያዘ ነው፡፡ በዚህ ሪፖርት ላይ ማኅበሩ ምን ያህል ሀብት እንዳለው፣ የገንዘቡ እንቅስቃሴ ምን እንደሚመስል እናሳያለን፡፡ በሀገራችንም ኾነ በዓለም አቀፍ ሕግ ተቀባይነት ባላቸው የውጭ ኦዲተሮች ተመርምሮ የተመሰከረ የሒሳብ ሪፖርት ነው የምናቀርበው፡፡ በዚህ መሠረት ጠቅላላ ሀብቱም ኾነ የሒሳብ እንቅስቃሴው በግልጽ ይታወቃል፡፡

ማኅበረ ቅዱሳን የማይታወቅ ሀብትና የፋይናንስ እንቅስቃሴ የለውም፡፡ ይህም ብቻ አይደለም፡፡ እስከ አኹን በቅዱስ ሲኖዶስ የሚሰጠንን አቅጣጫ ተከትለንና አክብረን የምንሠራ የቤተ ክርስቲያን አካል እንደ መኾናችን መጠን፣ ከመተዳደሪያ ደንቡ ባሻገር የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ተሰብስቦ የሚወስናቸውን ውሳኔዎች የሥራችን አካል አድርገን እየተገበርን እንገኛለን፡፡ ለማሳያም ከውሳኔዎቹ አንዱ የኾነውን፣ ማኅበሩ በቤተ ክርስቲያናችን የገንዘብ ደረሰኞች(ሞዴላ ሞዴል) እንዲጠቀም ያሳለፈውን ውሳኔ መጥቀስ እንችላለን፡፡ በዚሁ መሠረት ማኅበሩ፣ ውሳኔው ከተሰጠበት ዕለት ጀምሮ የቤተ ክርስቲያናችንን የሒሳብ ሰነዶች እየተጠቀመና በየዓመቱ ከጠቅላይ ቤተ ክህነት በሚላኩ ኦዲተሮች ሒሳቡን እያስመረመረ ይገኛል፡፡

በዚህ ኹሉ ሪፖርት ላይ ማኅበሩ የማይታወቅ ንብረት እንዳለው የተገለጸበት ኹኔታ የለም፡፡ የማኅበሩ የፋይናንስ እንቅስቃሴ ትክክለኛ መኾኑን የውጭ ኦዲተሮች ብቻ ሳይኾኑ፣ የጠቅላይ ቤተ ክህነታችን ኦዲተሮችም ጭምር ያረጋገጡት ሐቅ ነው፡፡ ይህን ዓይነት ያልተጨበጠ ክሥ የሚያቀርበው የቤተ ክርስቲያናችን አካል ሊኾን አይችልም፤ የምንለው ከዚህ ተጨባጭ ኹኔታ ተነሥተን ነው፡፡

ሰንደቅ፡- ሰሞኑን በተለያዩ ማኅበራዊ ድረ ገጾች የተሠራጨ ጹሑፍ፣ ማኅበሩ በግለሰብ ሒሳብ ውስጥ በሕገ ወጥ መንገድ ያስቀመጠው 170 ሚሊየን ዶላር በፖሊስ መያዙን ይገልጻል፤ ይህ ዘገባ ምን ያህል እውነት ነው?

አቶ ውብሸት፡- ማኅበሩ ከተመሠረተበት ጊዜ ጀምሮ መሰል ውንጀላዎች ሲቀርቡበት ይህ የመጀመሪያው አይደለም፡፡ ባለፉት 25 ዓመታት ውስጥ የቅድስት ቤተ ክርስቲያንን ዕድገትና ልማት የማይፈልጉ አንዳንድ አካላት ከጥቅማቸው አንጻር የማኅበሩን ስም በተለያየ መንገድ የማጥፋት ዘመቻ በተደጋጋሚ ሲያከናውኑ ቆይተዋል፡፡ አኹንም በማኅበራዊ ድረ ገጾች ተለቋል የተባለው መሠረተ ቢስ ወሬም፣ የዚሁ ዘመቻ አካል አድርገን የምናየው ነው፡፡ በአጭሩ ማኅበረ ቅዱሳን ገንዘቡን በግለሰብ ስም ለማስቀመጥ አሠራሩ አይፈቅድለትም፡፡ በግልጽ የሚሠራ ማኅበር እንደ መኾኑ በተቆጣጣሪ አካላት በየወቅቱ የሚመረመር የሒሳብ አሠራር ያለው ማኅበር ነው፡፡ በመኾኑም ይህ ዓይነቱ ወሬ ምንም ዓይነት መሠረትና እውነት የሌለው ነው፡፡ ማኅበሩን በትክክል የሚያውቅ አካልም በዚህ ዓይነቱ ወሬ ይደናገራል ብለን አናምንም፡፡

ሰንደቅ፡- ማኅበረ ቅዱሳን፣ ቤተ ክርስቲያኒቱ የአገልግሎቷ አደጋ አድርጋ የምትገልጸውን የተሐድሶ መናፍቃንን እንቅስቃሴ ለማጋለጥ፣ የቤተ ክርስቲያኒቱን ህልውና እና ተከታዮቿን ለመጠበቅ የሚያደርጋቸውን እንቅስቃሴዎች ጨምሮ በአንዳንድ ወገኖች ዘንድ በበጎ መልኩ የማይታይበት ኹኔታ መኖሩ ይታወቃል፡፡ ይህ የኾነው ለምንድን ነው?

አቶ ውብሸት፡- ቤተ ክርስቲያን ለማኅበሩ ከሰጠችው ሓላፊነት አንዱ፣ የዘመኑን ፀረ – ቤተ ክርስቲያን እንቅስቃሴዎች መከላከልና ማጋለጥ ነው፡፡ ስለኾነም ቤተ ክርስቲያንን የሚጎዳና በተለይም በስውር የሚደረጉ ሤራዎችን እየተከታተለ ማጋለጥ አንዱ ሓላፊነቱ ነው፡፡ ባለፉት ዓመታት በድብቅና በግልጽ መናፍቃን ወደ ቤተ ክርስቲያን የሰረጉበት ኹኔታ አለ፡፡ ስማቸውን ‘ተሐድሶ’ አሉት እንጂ ያው መናፍቃን ናቸው፡፡ እነዚህ አካላት ስማቸውን ‘ተሐድሶ’ ብለው ወደ ቤተክርስቲያን ተመሳስለው ገብተዋል፡፡ ከቤተ ክርስቲያን ውጭ የምናደርገው እንቅስቃሴ ውጤት አላመጣም፤ ከአኹን በኋላ ወደ ቤተ ክርስቲያን ሰርገን ገብተን፣ ከውስጥ ኾነን ብንሠራ የተሻለ ነው፤ ብለው ስልት ነድፈው ነው ወደ ቤተ ክርስቲያን የገቡት፡፡ ባለፉት 20 ዓመታት አገልግሎቷን ውስጥ ለውስጥ ሲጎዱ የነበሩ ናቸው፡፡ ከሚጠቀሟቸው ስልቶች አንዱ በቤተ ክርስቲያን ከፍተኛ መዋቅር ጭምር የራሳቸውን ሰዎች ማስቀመጥ ነው፡፡ በውጭም ያሉት፣ በውስጥም ያሉት፣ ገና የማይታወቁትም አንድ ላይ ተባብረው የሚንቀሳቀሱበት ከመኾኑ ጋር ተያይዞ የመከላከሉን ተግባር ለቤተ ክርስቲያናችን አስቸጋሪ አድርጎታል፡፡

ማኅበረ ቅዱሳን፣ በዚህ መልክ የተደራጁ የ‘ተሐድሶ’ ኑፋቄ አራማጆች ቤተ ክርስቲያንን ለመበረዝና ለመጉዳት እያሤሩ እንደኾነ ደጋግሞ ሲናገር፣ ሲያስተምር ብዙ ሰዎች አልተረዱትም ነበር፡፡ ጉዳዩን፣ በግለሰቦች መካከል ያለ ጠብ አድርገው የሚያዩትም ነበሩ፤ ምክንያቱም የሤራው ስትራቴጂ ከባድና ምሥጢራዊ ስለነበር ነው፡፡ በሒደት ግን እየተጋለጡ ሲወጡ በቤተ ክርስቲያናችን የሚመለከታቸው አካላት በኩል ተወግዘው የሚለዩበትና የሚሰናበቱበትን ውሳኔና ርምጃ እየተመለከትን ነው፡፡

ቀደም ሲል፣ ‘ተሐድሶ’ የሚባል የለም፤ ካለ አሳዩን፤ እያሉ ለማወናበድ የሞከሩ ታይተዋል፡፡ ከእነርሱም፣ በቂ ሥራ ሠርተናል፤ ብለው ባመኑበት ጊዜ ራሳቸውን እያጋለጡ የወጡበትን አጋጣሚ ተመልክተናል፡፡ የእምነት መግለጫ እስከማውጣትም ደርሰዋል፡፡ እምነታችን ይኼ ነው፣ ብለው በሰኔ ወር 2007 ዓ.ም. ዐውጀዋል፡፡ ከዚያ በፊት እነርሱን ማግኘት፣ መለየት፣ ማጋለጥ ከባድ ሥራ ነበር፡፡ ራሳቸውን ከለዩ በኋላ ግን እየቀለለ ነው የመጣው፡፡ እንግዲህ ይህን፣ ቤተ ክርስቲያን በቅዱስ ሲኖዶስ ወስና፣ በሊቃውንት ጉባኤ አይታና መርምራ መግለጫ አውጥታለች፤ ምላሽም ሰጥታለች፡፡

ኾኖም ቀደም ሲል እንዳልሁት፣ የ‘ተሐድሶ’ ኑፋቄ አራማጆች የሚንቀሳቀሱት በውስጥም በውጪም ነው፡፡ በውስጥ፣ በቤተ ክርስቲያን ከፍተኛ የሓላፊነት ቦታዎች ጭምር ይዘው ነው፡፡ እነዚህ አካላት፣ ማኅበረ ቅዱሳን፣ የ‘ተሐድሶ’ መናፍቃንን በማጋለጥና ኑፋቄያቸውን በመከላከል ረገድ የሚሠራውን ሥራ ኹልጊዜም ይቃወማሉ፡፡ ማኅበሩን ከተቻለ ለማፍረስ አልያም ለማሸማቀቅ በሚል የሚሰነዘሩ የስም ማጥፋት ዘመቻዎችና አሉባልታዎች ኹሉ በቀጥታም ኾነ በተዘዋዋሪ ከዚህ ዓቢይ ጉዳይ ጋራ የተገናኙና የሚገናኙ ናቸው፡፡

ሰንደቅ፡- ማኅበሩ፣ ከቤተ ክርስቲያን የአስተዳደር መዋቅር ጋራ በተዋረድ ያለው ግንኙነት ምን ይመስላል? መዋቅራዊ ግንኙነቱስ ምን ያህል ጤናማ ነው ብለው ያስባሉ?

አቶ ውብሸት፡- የማኅበሩ አገልግሎት በዋናው ማዕከል ብቻ የተወሰነ አይደለም፡፡ ከእያንዳንዱ ሀገረ ስብከት ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ጋር፣ ከመምሪያዎችና ዋና ክፍሎች ጋር፣ ከሥራ አስኪያጆች ጋር ተስማምተን፣ ተናበን ነው እየሠራን የምንገኘው፡፡ ከአባቶች ቡራኬና መመሪያ እየተቀበልን ስንሠራ ነው የኖርነው፡፡ ከጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና መዋቅር ጋራም ያለን የሥራ ግንኙነት ጤናማ ነው፡፡

ማኅበሩ ተጠሪነቱ ለቤተ ክርስቲያን እንደመኾኑ መጠን ለሚመለከታቸው አካላት የሥራ ዕቅድ፣ የሥራ ክንውን ሪፖርት ከማቅረብ፣ የተለያዩ ጥያቄዎችንና እገዛዎችን ከመጠየቅ አንጻርና በሌሎችም አሠራሮች ጤናማ ግንኙነት አለን፡፡ በአንዳንድ ቦታዎች ጥቃቅን ችግሮች ሊያጋጥሙ ቢችሉም እንኳ መሠረታዊውን የሥራ ግንኙነት የሚጎዳ ነው ብለን አናስብም፡፡ አልፎ አልፎ ግን ወደ ሓላፊነት ከሚመጡ ሰዎች ጋራ የሚያያዙ የተግባቦት ችግሮች አጋጥመውናል፡፡ ሰዎቹ ለማኅበሩ ጥሩ ስሜት ሲኖራቸው ጥሩ እገዛና ድጋፍ የምናገኝበት፣ ከሌላቸው ደግሞ ዕንቅፋት የሚያጋጥምበት ኹኔታ በአገልግሎታችን ሒደት ያስተዋልነው ችግር ነው፡፡ ችግሩ፣ ተቋማዊ ነው ብለን ስለማናምን ከግለሰቦቹ ጋራ በመመካከር ለመፍታት አቅማችን የፈቀደውን ሁሉ እያደረግን ነው የምናገለግለው፡፡

ሰንደቅ፡- በሚቀጥለው ሳምንት መጀመሪያ ይካሔዳል ተብሎ በሚጠበቀው የመንበረ ፓትርያርክ አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ 36ኛ ዓመታዊ ስብሰባ ላይ እንደ ቀደሙ፣ የሥራ ሪፖርታችሁ እንዳይቀርብና እንዳትሳተፉ በቅዱስ ፓትርያርኩ እንደታገዳችሁ ይሰማል፡፡ ይህ ምን ያህል እውነት ነው? እውነት ከኾነ ጉዳዩን እንዴት ተቀበላችሁት?

አቶ ውብሸት፡- ማኅበሩ ላለፉት ኹለት ዐሥርት ዓመታት በመንበረ ፓትርያርክ አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ዓመታዊ ስብሰባዎች ላይ ሲሳተፍ ቆይቷል፤ የሥራ ክንውን ሪፖርቱም፣ በጠቅላይ ጽ/ቤቱና በአህጉረ ስብከቱ እየቀረበ ሲሰማ ቆይቷል፡፡ እገዳን በተመለከተ ለጽ/ቤታችን የደረሰን ነገር የለም፤ ነገር ግን እኛም የተባለውን ጉዳይ በወሬ ደረጃ ብንሰማም፣ በአጠቃላይ ጉባኤው እንድንሳተፍ ከጠቅላይ ቤተ ክህነት ኹለት የግብዣ ደብዳቤዎች እንደደረሱን ብቻ ነው የምናውቀው፡፡ በአኹኑ ሰዓት በእኛ በኩል አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤውን ለመሳተፍ እየተዘጋጀን እንገኛለን፡፡

ሰንደቅ፡- ማኅበሩ ከቅዱስ ፓትርያርኩ ጋራ ያለው ተቋማዊ ግንኙነት የቱን ያህል ጤናማ ነው? “ቅዱስ ፓትርያርኩ፣ ለማኅበሩ ያላቸው አመለካከት በጎ አይደለም፤ የሻከረ ግንኙነት ያለ ይመስላል፤” የሚሉ ወገኖች አሉ፡፡ ግንኙነቱን በተመለከተ ስላለው ኹኔታ ቢገልጹልኝ?

አቶ ውብሸት፡- ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርካችን፣ የቤተ ክርስቲያናችን ርእሰ መንበር ናቸው፤ ቅዱስ ሲኖዶስንና አጠቃላይ ጉባኤውን በርእሰ መንበርነት ይመራሉ፡፡ በርግጥ በመዋቅራዊ ግንኙነት፣ ከቅዱስ አባታችን ጋራ በቀጥታ የምንገናኝበት መዋቅር የለም፡፡ ማኅበራችን ተጠሪ የኾነለት አካል አለ፡፡ ቀጥተኛ ግንኙነታችን ከዚህ አካል ጋራ ነው እንዲኾን የሚጠበቀው፡፡ ከዚያ ካለፈም ከጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጅ ጋራ ነው፡፡ ኾኖም፣ እንደ ልጅና አባት ተገናኝተን ቡራኬያቸውንና አጠቃላይ መመሪያቸውን መቀበል ያስፈልገን ነበር፡፡

ነገር ግን፣ በምንፈልገው ደረጃ ከቅዱስ አባታችን ዘንድ እየቀረብን አባታዊ ቡራኬና መመሪያ እየተቀበልን ለመሥራት አልቻልንም፡፡ በዚህ ረገድ መጠነኛ ክፍተት ማጋጠሙ እውነት ነው፡፡ አንዳንድ የተለየ ዓላማ ያላቸው በቤተ ክርስቲያናችን ውስጥ ያሉ አካላት ከቅዱስ አባታችን ጋራ እንድንገናኝ አይፈልጉም፡፡ በዚህ ምክንያት ልናገኛቸው የቻልንበት ጊዜ አናሳ ነው፡፡ የቅዱስ አባታችንን ሐሳብ በቀጥታ የምንሰማበት ዕድል የለንም፡፡ ካለመነጋገር፣ ካለመገናኘት የተፈጠሩ ክፍተቶች እንዳሉ እናውቃለን፡፡ እነኝህ ክፍተቶች፣ በማንኛውም ጊዜ መነጋገር ስንጀምር በቀላሉ ሊፈቱ የሚችሉ ናቸው ብለን እናምናለን፡፡

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *