ዘመነ ከፍታ!! (ጌት)
ከመሬቱ ወድቀዉ በአቧራ በጭቃዉ በመቆሸሽ ፈንታ
መንግስት አበጀልን ወደ ላይ መንሳፈፍ ዘመነ ከፍታ
በቃል ይፀና ዘንድ ቃል ብቻ ተንፍሶ
ህዝቡን ከፍ አ’ረገዉ ርችት ተኩሶ
ወኔ ምን ያደርጋል ተስፋስ ወዴት አለች
በፓለቲክ ጥበብ ቅንጣት ታክል ምኞት የወደቀን ሃገር ከፍ ታደርጋለች
የጥቂቶች እድገት የብዙዎች ሆኖ ይታያል በግራፍ
ይሔን ያላመነ ከሃዲ ነዉ ተብሎ ይቀጣል በጅራፍ
አንድነቱን ትተዉ ልዩነት ዉበት ነዉ ብለዉ ይሰብኩታል
በበትረ ሙሴያቸዉ የብሔሩን ባህር መትተዉ ይከፍሉታል
ይህን ተዓምር ያየ ወንዱ ያጨበጭባል ሴቷ እልል ትላለች
ከዛ በንጋታዉ በብሔሯ ሰበብ ከሞላ ኑሮዋ ትፈናቀላለች
ኢትዮጵያዊ መሆን ስሜቱ ጠዉልጎ ከአንድ ብሔር ያንሳል
ወንድም በወንድሙ በሰበብ አስባቡ ዱላዉን ያነሳል
በልዩነት አጥር ሁሉም የኔ እያለ ቅጥሩን ከገነባ
በገዛ ሃገሩ ልክ እንደ ባቢሎን ማን ከማን ይግባባ
ሰዉ እንኳን ከሰዉ ጋ አንዳንዴ በስሜት ከራሱ ይጋጫል
የሚያስማማ ካለ ፀብ ያመጣዉ ነገር በፍቅር ይቋጫል
ሴም ካም ኩሽ እያለ አብዝቶ መራራቅ ሰዉ እንዴት ለመደዉ
አለምን ለመሙላት በፈጣሪ ሃሳብ ከአንድ አባት ተወልደዉ
አንድ ሳንሆን ሳንግባባ በመዋደድ ቋንቋ ልሳን
መቼም ከፍ አንል ከፍ ብለን ስለተነሳን
በመዋደድ ቋንቋ ልሳን አንድ ሳንሆን ሳንግባባ
ካለንበት ፈቀቅ አንልም ስለተነፋ ጥሩንባ
በችኮላ በመጣደፍ ከፈረሱ ቀድሞ ጋሪዉ
አገር እንዴት ከፍ ይላል ስላወራ ብቻ መሪዉ
የአዲስ ዘመን ጎህ ሲቀድ ለህዝቡ የተገባዉ ቃል
ፀሃይ ከምስራቅ ስትወጣ ከስሞ እንደ ጤዛ ይደርቃል
የመጣ የተመለሰ ማስታገሻዉን ሳይሰጣት
አፉን ከፍቶ የመጣ ሃገሬን ሙስና ዋጣት
ከተማዉ አሸበረቀ ፎቁም እንደዛፍ በቀለ
ሰዉ ግን እንዳልባሌ እያደር ዋጋዉ ቀለለ
ጉዑዛዊነት ገዘፈ ቁሳዊ እሳቤ መጠቀ
ሰብዓዊነት ረክሶ ተቆሮቋሪ አጥቶ ወደቀ
በተቀደደ ቦይ ፈሶ ግላዊ ኑሮ ነገሠ
አርቆ ማሰብ ባልቻሉ የእኛነት ድንበር ፈረሰ
ታዲያ እዉነቱ ሲመዘን ሁሉ ወርዶ ከዝቅታዉ
በየት በኩል ነዉ መንሳፈፍ በየት በኩል ነዉ ከፍታዉ
ኑሮ እንደ መጠጥ አስክሮት ህዝቡስ መች ይሰማሃል
በርግጥ እሱ ዝቅ ብሎ አንተን ከፍ ብለህ ያይሃል፡፡

( get) FB 

Share and Enjoy !

Shares
Related stories   እኛ የምንመርጠው አባትና አያቶቻችን የመረጡትን ነው።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *