የኬንያ ፖሊስ ኬንያ ውስጥ ሁለት የተቃዋሚ ፓርቲ ሰልፈኞች መገደላቸዉን እና ሌሎች ሦስት ደግሞ መቁሰላቸዉን አስታወቀ። ሁለቱ ሰዎች ቦዶ በተባለችዉ ከተማ የሚገኝ አንድ ፖሊስ ጣቢያ ሰብረው ለመግባት ሲሞክሩ ነው የተገደሉት ብሏል ፖሊስ። ከዚህም ሌላ ሰላማዊ ሰልፍ እንዳይካሄድ ባገደባቸው ሦስት የኬንያ ከተሞችም ዛሬ አደባባይ የወጡ ሰዎችን ፖሊስ በአስለቃሽ ጢስ በትኗል።
ፖሊስ እርምጃውን የወሰደው ዛሬ ተቃዋሚ ሰልፈኞች በተሰባሰቡበት በርዕሰ ከተማ ናይሮቢA ፍሪደም ፓርክ በተባለው ስፍራ እና በኪስሙ እንዲሁም በሞምባሳ ከተሞች ነው። በሦስተኛዋ የኬንያ ትልቅ ከተማ በኪስሙ ወጣቶች ድንጋይ ሲወረውሩ የአገር ውስጥ የቴሌቪዥን ጣቢያዎች አሳይተዋል። መንግሥት በሦስቱ ከተሞች ሰላማዊ ሰልፍ እንዳይካሄድ ያገደው ትናንት ነበር።
ሰልፎቹ የተካሄዱት የኬንያ የምርጫ ስርዓት እንዲሻሻል በመጠየቅ ነዉ። ለጥቅምት 16፣ 2010 ከታቀደው ድጋሚ ምርጫ በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ ራሳቸውን የተቃዋሚዎቹ መሪ ራይላ ኦዲንጋ ዛሬ እንዳሉት በሀገሪቱ ሕግ መሠረት ምርጫ ሊካሄድ አይችልም። ኦዲንጋ ዛሬ ለንደን ውስጥ በሰጡት መግለጫ እንዳሉት ምርጫ እንደገና እንዲጠራ የተወሰነበት የጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ብይን በዚህ ጉዳይ ላይ የሚለው ግልጽ ነው።
« በጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ውሳኔ መሠረት ከፕሬዝዳንታዊ እጩዎች አንዱ ማለትም ፕሬዝዳንቱ ወይም ይግባኝ ያሉት ራሳቸውን ከምርጫ ካገለሉ ምርጫ አይኖርም። ከዚህ በኋላ የምርጫ ኮሚሽን አዲስ የእጩዎች ምዝገባ ለማካሄድ ነው መንቀሳቀስ ያለበት። ስለዚህ በሕጉ መሠረት ጥቅምት 16፣2010 ዓም ምርጫ አይኖርም። አሁን ምርጫ ለማድረግ ነው የሚሞክሩት ይህ ግን ሊሆን አይችልም።»ኦዲንጋ የኬንያ ፖሊስ ሕገ መንግሥት የሰጠውን መብት ተጠቅሞ ሰላማዊ ሰልፍ ለወጣው ህዝብ ጥበቃ ከማድረግ ይልቅ ኃያል ተጠቅሞ መበተንኑ አግባብ አይደለም ሲሉም ተቃውመዋል።