1. ፖለቲከኛ አንዱዓለም አራጌ የታሰረው ከህግ አግባብ ውጭ መሆኑን በመጥቀስ ከእስር እንዲፈታ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጥሪ ማድረጉ የተዘገበው በመስከረም 2010 ዓ.ም ነው፡፡

ከህግ አግባብ ውጭ ስለሚፈጸሙ እስራትን የሚመለከተው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ቡድን (United Nations Working Group on Arbitrary Detention) እንዳመለከተው የፖለቲከኛ አንዱዓለም አራጌ እስር ዓለማቀፍ ህግጋትን የተላለፈና መሰረታዊ መብቶቹን የጣሰ ነው፡፡ Freedom Now በተባለ ተቋም የአንዱዓለምን እስር የተመለከተ አቤቱታ ቀርቦለት ሲመረምር እንደቆየ የገለጸው UN Working Group የኢትዮጵያ መንግስት አንዱዓለምን ለእስር መዳረጉ ዓለማቀፍ ህግን የጣሰ ነው፣ ስለዚህም ያለምንም ቅድመሁኔታ ከእስር ሊለቀቅ ይገባል ሲል አሳስቧል፡፡
በተጨማሪም የአንዱዓለም አራጌ እስር የኢትዮጵያ መንግስት የጸረ-ሽብርተኝነት ህጉን ተቃውሞ የሚያሰሙ ዜጎችን ለማፈን እየተጠቀመበት ስለመሆኑ በተደጋጋሚ ስለመስተዋሉ ተጠቅሷል፡፡ ፖለቲከኛ አንዱዓለም አራጌ በተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ውስጥ እስከ ከፍተኛ አመራርነት ተሳትፊ ሲሆን፣ የእድሜ ልክ እስር ተፈርዶበት ከስድስት አመት በፊት ጀምሮ በእስር ላይ ይገኛል፡፡

2. የኢትዮጵያ መንግስት ለ10 አመታት ያህል በእስር ያቆያቸውን ሁለት ኤርትራዊያን ጋዜጠኞችን መልቀቁ ታውቋል፡፡
ከአስር አመት በፊት በኬንያና ሱማሊያ ድንበር ተይዘው በኢትዮጵያ መንግስት በእስር የከረሙት ሁለት ኤርትራውያን ጋዜጠኞች ተስፋልደት ኪዳኔና ሳልህ ጋማ ከእስር መፈታታቸው የታወቀው በመስከረም 2010 አጋማሽ ነው፡፡ መረጃውን ያወጣው የአሜሪካ ድምጽ ራዲዮ የአማርኛ ቋንቋ ዝግጅት ክፍል፣ ጋዜጠኞቹ ከእስር ስለመለቀቃቸው የጋዜጠኛ ተስፋ ልደት ኪዳኔ የቤተሰብ አባልንና የሰብዓዊ መብት ተከራካሪ ተቋማትን በዋቢነት ጠቅሷል፡፡

Related stories   ኦፌኮ ራሱን ከምርጫው ማግለሉን አረጋግጧል

3. ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ሊፈታ ነው፡፡

የሦስት አመታት የእስር ቅጣት ተወስኖበት በእስር የከረመው ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ የተወሰነበትን ቅጣት ጨርሶ በጥቅምት ወር 2010 ዓ.ም መጀመሪያ ቀናት ከእስር እንደሚፈታ ይጠበቃል፡፡ ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ በአመክሮ መፈታት የነበረበት የዛሬ አመት ገደማ የነበር ቢሆንም አመክሮ በመከልከሉ ሙሉ ቅጣቱን በእስር አሳልፏል፡፡

4. የእነ ዶ/ር መረራ ጉዲና እና የእነ ጉርሜሳ አያኖ የክስ መዝገቦች ከጥቅምት ወር ጀምሮ መታየት ይቀጥላሉ፡፡
የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 19ኛ እና 4ኛ ወንጀል ችሎቶች ካለፈው አመት ወደዚህ አመት ተላልፈው ቀጠሮ የተሰጠባቸውን የኦፌኮ አመራሮችን ያካተቱ የክስ መዝገቦችን መመልከት እንደሚጀምሩ የተያዘላቸው ቀጠሮ ያመለክታል፡፡ የኦፌኮ ሊቀመንበር ዶ/ር መረራ ጉዲና የአቃቤ ህግ ምስክሮች ዝርዝር ሊደርሳቸው እንደሚገባ የጠየቁበት የክስ መቃወሚያ ለህገ-መንግስት ትርጉም ለፌደሬሽን ም/ቤት መላኩ የሚታወስ ሆን፣ ፌደሬሽኑ ትርጉሙን ሰርቶ መላኩን ለመጠባበቅ በተያዘው ቀጠሮ መሰረት ጥቅምት 6/2010 ዓ.ም ችሎት ይቀርባሉ፡፡

Related stories   አለቃ አጽመ ጊዮርጊስ – የተሳሳተውን የውጫሌ ውል የመረመሩ ጀግና ኢትዮጵያዊ

እነ ጉርሜሳ አያኖ ደግሞ ቀሪ የመከላከያ ምስክሮቻቸውን ለማሰማት ከጥቅምት 27-29/2010 ዓ.ም ቀጠሮ 4ኛ ወንጀል ችሎት እንደሚቀርቡ የተያዘው ቀጠሮ ያሳያል፡፡

አክቲቪስት ንግስት ይርጋ የተካተተችበት የክስ መዝገብም ጥቅምት 21/2010 ዓ.ም መታየት ይቀጥላል፡፡

Share and Enjoy !

Shares

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *