ቀዝቃዛው አየር የፀሐዩዋን መውጣት ተከትሎ ሞቅ እያለ ቢመጣም ሙቀቱ ቆዳን አልፎ ውስጥን ሊሰማ አልቻለም። በአካባቢው በፀሐይ መውጣት ከመተማመን ይልቅ ቀኑን ሙሉ ልብስ ደራርቦ መልበስ ተመራጭ ነው። ምክንያቱም አካባቢው በዓመት ከሰባት ወራት በላይ ዝናብ የማያጣው ነውና።

በከተማዋ የትኛውም አካበቢ ሲዘዋወሩ ከርቀት የሚታዩት ተራራዎች አረንጓዴ ብርድ ልብስ የለበሱ ይመስላሉ። ጥቅጥቅ ባለ ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ ደን መልበሳቸው የተራራነት ግርማ ሞገሳቸው ከፍ እንዲል አድርጎታል። በከተማዋና በአካባቢዋ ነዋሪዎች ኮፍያ ወይም ፎጣ፣ ኮት፣ ካፖርትና ጋቢ፣ ሱሪና ቦት ጫማ ማድረግ የተለመደ ነው። እኛም በእንግድነት ወደአካባቢው የመጣነው የሌሊቱ ቅዝቃዜ ቆዳችንን አልፎ ውስጣችን ቢገባ በጧቷ ደማቅ ፀሐይ ሊመለስ እንደማይችል በመገመት አለባበሳችን ከአካባቢው ማህበረሰብ ጋር አመሳስለናል።

ካለፉት አራት ዓመታት ወዲህ መስፋፋት የጀመሩት የከተማዋ ሕንጻዎች አዲስ እንደተተከለ ዛፍ እዚህም እዛም ብቅ ብቅ ማለት ጀምረዋል። በተወሰኑ ዓመታት የሕንጻዎቹ ቁጥር እየጨመረ መምጣት በዙሪያዋ የከበቧትን ተራሮች ለመወዳደር የሚፎካከሩ ይመስላል።ከ26 ዓመት ያልዘለለ ታሪክ ያላት ከተማዋ እደጊ፣ ተመንደጊ… ተብላ የአባቶች ምርቃት የተቸራት ስለመሆኑ በእዚህ አጭር ጊዜ ውስጥ ረጅም ዘመን ያስቆጠሩ የዞን ከተሞችን መወዳደሯ ማሳያ ነው።

በቅርቡ በአማራ ክልል የሚከበረውን የዓለም የቱሪዝም ቀን በዓል ምክንያት በማድረግ በፍኖተ ሰላም የተጀመረው ጉብኝት በአባይ ወንዝ መነሻ በሆነችው “ሰከላ” አድርጎ የአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን ዋና ከተማ የሆነችው እንጅባራ ከተማ ድረስ ዘልቆ ነበር። ለጉብኝቱ ተሳታፊዎች የተያዘልን ሆቴል ዘመናዊ ቢሆንም ካለው ቀዝቃዛ የአየር ንብረት ጋር ተያይዞ ሙቀት የሚሰጥ ቴክኖሎጂ ባለመገጠሙ የሌሊቱን ቅዝቃዜና ውርጭ መቋቋም ያቅት ነበር።

ጧት ገና መንጋቱ ሳይታወቅ ሰዓቱ 2፡15 ይላል። ለበዓሉ የተዘጋጀው የፓናል ውይይት ሰዓቱ በመቃረቡ ሁሉም ታዳሚ አራተኛ ፎቅ በሚገኘው መሰብሰቢያ አዳራሽ ገብቶ ቦታ ቦታውን ይዟል። የአዊ የባህል ቡድን “ከስከሲንባኦ” በሚባለውና በሌሎች የብሔረሰቡ ባህላዊ ዘፈኖችና ውዝዋዜዎች አዳራሹን አድምቀውታል። ታዳሚውንም ቁጭ ብድግ፣ ወዝ ወዝ፣ ትካሻ ነቅነቅ… በማድረግ ያቁነጠንጡታል። መክፈቻ ንግግር ተካሂዶ ውይይት እንደተጀመረ ኳኳ…ኳኳ… የሚል ተከታታይነት ያለው ድምጽ ጆሯችን ድረስ መጥቶ ይሰማን ጀመረ።

በተመሳሳይ ሰልት ኳኳ ኳኳ… የሚል ድምጽ ምን ሊሆን ይችላል? በውስጤ ራሴን ጠየኩ። በመስኮት አንገቴን አውጥቼ ቁልቁል ወደመሬት ተመለከትኩ። የአስፓልት መንገዱ ሙሉ በሙሉ በአጌጡ ፈረሶችና ጋላቢዎች ተሞልቷል። አንድ ሺህ የሚሆኑ ፈረሶች በእዚች ጠባብ አስፓልት ላይ አንገታቸውን እንደ ጤፍ ዛላ ከወዲያ ወዲህ ሲያዘናብሉ ላየ ሰው የተለየ ስሜት ይሰጣል። ፈረሶቹ በልጓም የተሰነገውን አገጫቸውን ወደ ብብቻቸው ቀብረው ወደ ላይና ወደ ታች ሲሉ ልቀቁኝ… ልቀቁኝ…ልሂድ…ልጋልብ… የሚሉ ይመስለሉ። ፈረሶቹ ሲያሰግሩ የሚያሳዩት እንቅስቃሴና ድምጽ ከፈረሰኞቹ “አሃው ጃሌ… አሃው ጃሌ…“ ከሚለው የሆታ ድምጽ ጋር ተዋህዶ በውስጥ አንዳች ስሜት ይፈጥራል።

የፈረስ ኮቴ አራተኛ ፎቅ ድረስ ዘልቆ መሰማቱ እያስደነቀኝ ከአዳራሹ ወጥቼ ወደፈረሰኞቹ አመራሁ። ከታች ወርጄ የፈረሰኞችን ትርኢትን መመልከት ጀመርኩ፤ ፈረሶቹ በቆሙበት ወደ ሰማይ እየዘለሉ  መልሰው ወደ መሬት ይወርዳሉ። ሁሉም የሚያሳዩት ትርኢት ተመሳሳይ ነው።

እንስሳንም በአግባቡ ካሰለጠኑት የማይሰራው ነገር እንደሌለ ትልቅ ማሳያ ነው አልኩ በልቤ። ፈረሶቹ በቆሙበት ቦታ  የፊት እግሮቻቸውን ወደ ላይ አንስተው ወደ ታች ሲመለስ በእዚያው ቅጽበት የኋላ እግሮች ደግሞ መልሰው ወደ ላይ መዝለል ይጀምራሉ። አዳራሹ ድረስ ዘልቆ የተሰማው የኳኳታ ድምጽ የእዚህ ትርኢታቸው ውጤት ነው።

ፈረሶቹ የሚያሳዩት ትርኢት ሁለት ህጻናትን በዥዋዥዌ ላይ ጫፍና ጫፍ ሆነው አንዱ ወደ ላይ ሲወጣ ሌላው በተቃራኒው ወደ መሬት እንደሚወርድበት የዘመኑ ጨዋታ ጋር ይመሳሰላል። የአንድ ሺህ ፈረስ ትርኢት በጠባብ አስፓልት ላይ በአንድ ላይ ሲታይ ደግሞ ከሚፈጥረው አንዳች ውስጣዊ ስሜት በተጨማሪ ለአይንም ግርምትን ይፈጥራል። ጋላቢው ፈረሰኛም ዥዋ ዥዌ እንደሚጫወት ህጻን ብቅ ጥልም የሚል ትዕይን ያሳያል።

የፈረስ ትርኢት ጉዞው የእንጅባራን ከተማ ከሰሜን ወደ ደቡብ መሀል ለመሀል አቋርጦ ወደ “ዘንገና ሐይቅ” አድርጓል። የዘንገና ሐይቅ ከከተማዋ በግምት ከሁለት እስከ ሦስት ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ይገኛል። መንገዱ ከሱዳን በጎንደር፣ ወረታ፣ እንጅባራ፣ ቡሬ፣ ፍኖተሰላምና መሰል ከተሞችን አቋርጦ አዲስ አበባ የሚገባ ዋና መስመር ነው።

ዘንገና ሐይቅ ከርቀት ሲታይ በገበታ ላይ የታቆረ ውሃ መስሎ ይታያል። ጥልቀቱ ከ100 ሜትር በላይ እንደሚገመት የአካባቢው ነዋሪዎች ነግረውኛል። ከቲሊሊ ታጥፎ የሚገኝ የጥርባ ሐይቅ በተመሳሳይ መልኩ ይታያል።ጥልቀቱ ከ150 ሜትር በላይ እንደሆነ ነው የሚነገረው። በቮልካኖ መፈንዳት ምክንያት እንደተፈጠሩ የሚገመቱት ሐይቆችን ተጠግቶ ለማየት ስቦ የሚያስገባ የሚመስል አስፈሪ ገጽታ አላቸው። ዘንገና ሐይቅ እንደደረስን በአቅራቢያው በሚገኙ ረጃጅምና እድሜ ጠገብ በሆኑ ዛፎች ውስጥ ፈረሰኛው ገብቶ ትርኢት ማሳየት ጀመረ። በአካባቢው በየዓመቱ የሚከበረውን የመስቀል በዓል ለመዘከርም የደመራ መለኮስ ስነ ስርዓት በዘንገና ሐይቅ ዳርቻ ተካሂደ።

የፈረስ ትርኢቱን የሚያሳዩን በዞኑ ከሚገኘው ባንጃና ሌሎች ቅርብ ወረዳዎች የመጡ የሰባት ቤት አገው የፈረሰኞች ማህበር አባላት ናቸው። ማህበሩ ምናልባት በአገራችን ከተቋቋሙ ማህበራት ግንባር ቀደም ተጠቃሽ ስለመሆኑ ይነገርለታል። በ1932 ዓ.ም እስከ 25 ፈረሰኛ አባላትን ይዞ እንደተቋቋመ የሚነገርለት ማህበር አሁን ላይ ከ48 ሺህ በላይ ፈረሰኞችን አቅፎ ይዟል። ቁጥራቸው የተጠቀሰውም በአባልነት የተመዘገቡና መታወቂያ የተሰጣቸው መሆኑን የማህበሩ ሊቀ መንበር አቶ ጥላዬ አየነው ገልጸዋል። ማህበሩ በመጭው ዓመትም አባላቱን ከ70ሺህ በላይ ለማድረስ ግብ ይዞ እየሰራ ይግኛል።

ማህበሩ የሰባት ቤት አገው የሚለውን ስያሜ ያገኘው በአንድ ወቅት  “አንክሺ፣ ባንጂ፣ ዘጋሚ፣ አዚኒ፣ ኳኩሪ፣ ቻሪና ሚቲክሊ” የተባሉ ሰባት ወንድማማቾች ከዋግ ህምራ አካባቢ መጥተው መልክዓ ምድራዊ አቀማመጡና ለአደን ምቹ መሆኑን ስለተገነዘቡ በአካባቢው መስፈራቸውንና የዘር ግንድ አመጣጡን ለመዘከር ሲባል ነው። አንድ ፈረሰኛ ለመባል ፈረስ ፣ ኮርቻ፣ ፋርኒስ፣ ለኮ፣ ወዴላ፣ ምቹና ግላስ ለፈረሱ ያስፈልገዋል። ለራሱ ደግሞ አለንጋ፣ ዘንግ፣ ገንባሌ፣ ሳርያን ኮት፣ ጀበርና ያስፈልገዋል። ጦር፣ ጋሻና ሌሎች የአባቶቻችን የዘመቻ ቁሳቁሶች ካሉት ደግሞ ተመራጭ ነው እንደማህበሩ ሊቀመንበር ገለጻ።

አገውና ፈረስ ተለያይተው አያውቁም፤ ለወደፊትም አይለያዩም። በአገዎች ዘንድ ፈረስ የታመመን ወደክምና ያደርሳል፣ የተጋቡ ጉብሎችን ያንሸራሽራል፣ በዓልና ሃዘንን በማድመቅም ትዝታው እንዲታወስ ያደርጋል። ፈረስ መሬቱን አርሶ ጎተራ ሙሉ እንዲሆን ያደርጋል። በዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ ማጓጓዣ ሆኖም ያገለግላል። ለእነሱ ፈረስ ሁሉም ነገራቸው ነው ማለት ይቻላል።

የፈረሰኞች ማህበር በመጭው ጥር ወር ከተመሰረተ 78 ዓመት ይሞላዋል። የአማራ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ሂሩት ካሳው እንደሚሉት የዘንድሮውን በዓል (በፈረስ ግልቢያና ጉግስ ትርኢት የሚከበረውን በዓል) በአገርና በዓለም አቀፍ ደረጃ በማስተዋወቅ ለቱሪስት መስህብነት ለማዋል ይሰራል። የማስተዋወቅ ሥራውን በተደራጀና በተቀናጀ አግባብ ለመስራትም “ቢሲአር በጀት” የተበላ አስጎብኚ ድርጅት፣ ማህበሩና ቢሮው የሦስትዮሽ ፕሮጀክት ተፈራርመዋል። ማህበረሰቡ የእኔና የራሴ ብሎ የያዘው ጉዳይ ዘላቂነቱ አጠራጣሪ እንደማይሆን ይህ ማህበር ማሳያ ነው።

ማህበሩ በ1932 ዓ.ም መመስረቱን ስንሰማ የተመሰረተበትን ምክንያት፣ እንዴት፣ ለምን የሚሉ ጥያቄዎች ቶሎ ፊታችን ድቅን ማለቱ አይቀርም። ነገሩ እንዲህ ነው፣ በ1888 ዓ.ም የጣሊያን ወራሪ ጦር መረብ ወንዝን ተሻግሮ የመጣበት ጊዜ ነበር። በእዚህ ወረራ ወቅት አቅም ያለው ሁሉ የአጼ ሚኒሊክን ጥሪ ተቀብሎ ባለበት እየተሰባሰበ ዘምቷል። በእዚህ ወቅት የአገው ፈረሰኞችም ጦርና ጋሻቸውን ሰብቀው ዘምተዋል። ወጣቱ በጉልበቱ፣ ነፍጥ ያለው በነፍጡ  በስለትና…ሌሎች የአካባቢ ቁሳቁሶችን በመያዝ የጠላትን ቅስም ሊሰብር ቀፎው እንደ ተነካበት ንብ ሆ ብሎ መዝመቱን የታሪክ ድርሳናት ዛሬ ድረስ ይመሰክራሉ።

በአዊ ብሔረሰብ ዞን የሰባት ቤት አገው ፈረሰኞች ማህበር ታሪክ እንደሚያስረዳው በየአካባቢው የቀሩት ሴቶች፣ ህጻናትና አቅመ ደካሞች ደግሞ በየአብያተ ክርስትያናቱ ምህላና ጸሎት ይዘው ነበር።ድሉም በስተመጨረሻ የኢትዮጵያ ሆኗል።

ይህን ታላቅ ታሪክ ለመዘከር ሲባል የሰባት ቤት አገው ፈረሰኞች ማህበር በ1932 በጦርነቱ በተሳተፉ ፈረሰኞችና በአካባቢው አባቶች ተመስርቶ እስካሁን በየዓመቱ እየተከበረ ዛሬ ላይ ደርሷል። ከድሉ በኋላ በዓሉ አንድም ቀን ሳይቋረጥ እየተከበረ ዛሬ ላይ ደርሷል። ይህም በአሁኑ ወቅት በአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን የሚኖሩ አገዎች ለሃይማኖታቸው፣ ለባህላቸው፣ ለማህበራዊ ትስስራቸው የማህበሩ መመስረት አስተዋጽኦ ማበርከቱ ይነገራል።

ማህበሩ አገርን ከጣሊያን ወረራ በመከላከል፣ የተጣላን በማስታረቅ በፍቅር እንዲኖር በማድረግ፣ ችግር የደረሰበትን በመደገፍ፣ የታመመን በመርዳትና የሞተን የማህበሩ አባል በፈረስ ትርኢት አጅቦ በመሸኘት ቤተሰቦቹን የማጽናናት ስራዎች ሲያከናውን ቆይቷል። በተለይ የማህበሩ አባል በሞት ሲለይ ሁሉም አባላት ፈረሳቸውን ይዘው፣ አልባሳትና ጌጣቸውን ለብሰው በለቅሶው ስነ ስርዓት ይታደማሉ። ፈረስ የሌለው ከሞተ ደግሞ አንድም ፈረስ አይመጣም። ልቅሶውም አይደምቀም።

ማህበሩ በዓሉ በየዓመቱ ጥር 23 ቀን በዞኑ በሚገኙ በእያንዳንዱ ወረዳ በዙር የሚከበር ሲሆን በዓሉም የሚከበረው በፈረስ ግልቢያና ጉግስ ትርኢት ነው። ከእዚህ በተጨማሪ ባህላዊ ጭፍራና ቀረርቶዎችን በማሳየት እንዲሁም በባህላዊ ምግቦችንና መጠጦችን በጋራ በመገባበዝ መሆኑን አቶ ጥላዬ አስታውቀዋል። ግብዣው ከባህላዊ ጨዋታው ጋር ተዳምሮ በብዙዎች ዘንድ የበዓሉን መምጣት ተናፋቂ ያደርገዋል።

በዞኑ ከጓጉሳ ሽኩዳድ ወረዳ የመጡት ፈረሰኛ አቶ አያና ምትኩ እንዳሉት በወረዳቸው እድሜው የደረሰ የብሄሩ አባልና ፈረስ የገዛ ሁሉ የማህበሩ አባል መሆን ይችላል ይላሉ። በቀጠናቸው ከ10ሺህ በላይ ፈረሰኞች በአባልነት ታቅፈው ከአባቶቻቸው የወረሱትን ዓመታዊ በዓል በፈረስ ጉግስና ሽምጥ ግልቢያ በመወዳደር ከማክበር ባሻገር ማህበሩ ያስቀመጣቸውን ዓላማዎች ለማሳካት እየሰሩ እንደሚገኙ ተናግረዋል።

የባንጃ ወረዳ የፈረሰኞች ማህበር አባል አቶ ወርቁ ኃይሌ ከአባቶቻቸው የወረሱትን በዓል በየዓመቱ ማክበራቸው በተለያዩ አካባቢዎች የሚኖሩ የማህበሩ አባላት ግንኙነትና ትስስር ተጠናክሮ እንዲቀጥል ማስቻሉን ይገልጻሉ። ከፍተኛ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ያለውን የፈረሰኞች ማህበር እሴት ለልጆቻቸውና ለመጭው ትውልድ ለማስተላለፍ እየሰሩ መሆናቸውንም ተናግረዋል።

በዞኑ ከሚገኙ የተፈጥሮና የሰው ሰራሽ ቅርሶች ጋር ተዳምሮ ከዋና ዋና የቱሪዝም መዳረሻዎች ጋር በማስተሳሰር በርካታ ጎብኚዎች ወደ አካባቢው እንዲመጡና የቆይታ ጊዜያቸውን እንዲያራዝሙ መስራት እንደሚገባም ጠቁመዋል።

የብሔረሰቡ የፈረሰኞች ማህበር አባላት ከአባቶቻቸው የወረሱትን በዓል በተለያዩ ዝግጅቶች ላለፉት 78 ዓመታት ሳይቋረጥ እያከበሩ መዝለቃቸው በራሱ ታሪካዊና በቅርስነት ለማስመዝገብ መሰረት እንደሚሆን አስረድተዋል።

በመጭው ጥር 23 ቀን 2010 ዓ.ም በዓሉን በድምቀት በማክበር በሀገር አቀፍና በዓለም ደረጃ ለማስተዋወቅና በዓለም ቅርስነት እንዲመዘገብ ለማድረግ ማህበሩ ከቢሲአር በጀት አስጎብኚ ድርጅትና ከክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ጋር ያደረገው የሦስትዮሽ ስምምነት ወደተግባር ተቀይሮ ውጤት እንዲያመጣ ማህበሩ የጀመረውን ጥረት ሊያጠናክር ይገባል።

በእንግዳው ከፍያለው (ኢዜአ)

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *