“ሁሉንም ፈንቅል HR 128ን አምክን” – በሶማሊያ ዕልቂት የህወሓት ሥውር እጅ? -ጎልጉል

ከሶማሊያው የቦንብ ፍንዳታ በስተጀርባ – አዲስ ዘመን

ከሶማሊያው የቦንብ ፍንዳታ በስተጀርባ

በሶማሊያ በደረሰው የፈንጂ ጥቃት 300 ሰዎች ሞተዋል፤ ፤

ሶማሊያ በታሪክዋ አይታ በማታውቀው እጅግ ዘግናኝ በሆነ የቦምብ ፍንዳታ ተመታለች፡፡ የደረሰው ጥፋትና ውድመት ዘግናኝ የተባለለት ሲሆን እንደ ቀድሞዎቹ ጥቃቶች አልሸባብ ኃላፊነቱን አልወሰደም፡፡

ፍንዳታው እንደደረሰ የሞቱትን ሰዎች ቁጥር ለመለየት አስቸጋሪ የነበረ ቢሆንም ከተገመተው በላይ እያደገ ሄዷል፡፡ በአሸባሪዎች ተሰነዘረ የተባለው ጥቃት እጅግ አውዳሚ የነበረ ሲሆን፤ የዕርዳታ ሠራተኞች በፍርስራሽ ክምሮች ውስጥም ፍለጋ እያደረጉ ነው፡፡ አሁን የሚወጡት መረጃዎች ከ300 ሰዎች በላይ መሞታቸውንና ተቀራራቢ ቁጥር ያላቸው ሰዎች መቁሰላቸውን ይጠቁማሉ።

ባለፈው ቅዳሜ የተፈጸመውን ጥቃት አስመልክቶ አንድ የዓይን ምስክር ለዘጋርድያን ጋዜጣ እንደገለፀው የቦምብ ፍንዳታው ጉዳት ያደረሰበት ሥፍራ ከሁለት የኳስ ሜዳዎች ዕኩል ይሆናል። በመኪና ላይ በተጠመደ ፈንጂ የተፈፀመው ጥቃት በሶማሊያ ዋና ከተማ በብዛት ሕዝብ በሚገኝበት ማዕከላዊ ሥፍራ ያጋጠመ ሲሆን፤ ፍንዳታው በመላ አገሪቱ መደናገጥን ፈጥሯል፡፡ የአሸባሪዎች ጥቃት እንግዳ ባልሆነባት አገር በፍንዳታው የደረሰው ጉዳት ሶማሊያ ካጋጠማት ከፍተኛው መሆኑን የሰብአዊ ጉዳዮችና የአደጋ መከላከል ሚኒስቴር ገልጿል፡፡

አገሪቱ የሞቱትን ዜጎችዋን ለማሰብ ሰኞ ዕለት የሀዘን ቀን ያወጀች ሲሆን ከ100 ሰዎች በላይ የቀብር ሥነ ሥርዓት ተካሂዷል፡፡ ባለሥልጣናት አሁንም የሟቾች ቁጥር እንደሚጨምር ይገምታሉ፡፡ በአሦስየትድ ፕሬስ ሪፖርት መሰረት እጅግ በጣም በርካታ ሰዎች ይሙቱ ይኑሩ ሳይታወቅ ጠፍተዋል፡፡ ከፍንዳታው ግዙፍነት የተነሳ የሞቱት ሰዎች ማንነታቸው ሊለይም ሆነ በጭራሽ ሊገኙ እንደማይችሉ ታውቋል፡፡

«ለመጨረሻ ከወንድሜ ጋር የተነጋገርኩት ፍንዳታው ከመድረሱ ጥቂት ደቂቃዎች በፊት ነበር» ስትል አንዲት ሴት ለሮይተርስ የዜና ወኪል ገልፃለች፡፡ «ወንድሜ ማንነታቸው ካልተለዩትና ትናንት ከተቀበሩት ውስጥ ይሆናል ብዬ እፈራለሁ፡፡ በሕይወት ወይም ሞቶም ቢሆን አስከሬኑን አገኘዋለሁ የሚል ተስፋ የለኝም» ስትል ተናግራለች፡፡

የአአሚን ከተማ የአምቡላንስ አገልግሎት መስራች የሆነው አብዱል ቃድር አደም «በርካታ የሞቱ ሰዎች አይቻለሁ፤ በስፍራው ጩኸት በርክቶ ነበር» ሲል ለኤንፒአሩ ዘጋቢ ኢይደር ፔራላታ ተናግሯል፡፡ «በየቦታው የሰዎች ቁርጥራጭ አካል አለ፤ ቤቶች ፈራርሰዋል፤ መኪናዎች ጋይተዋል። አዕምሮንም አካልንም እጅግ የሚያዛባና አሰቃቂ አስደንጋጭ ትዕይነት ነው » ብሏል በዚህ አይነት አገልግሎት ከ10 ዓመት በላይ ያለው አደም እንዲህ አይነት ነገር በፍፁም አይቶ እንደማያውቅ ተናግሯል፡፡

አንድ ሰው ደግሞ ስሜቱን ለአሦስየትድ ፕሬስ እንደገለፀው በዚህ ጥቃት በርካታ የቤተሰቡን አባላት ማጣቱን ተናግሯል፡፡ «ልቤ በጣም ተሰብሯአል፡፡ እንዲህ አይነት አስከፊ ጥቃት በፍፁም አይቼ እንደማላውቅ ነው የምመሰክረው» ብሏል፡፡

«ለእኔ ውድ የነበረውን ልጄን አጥቻለሁ፡፡ ጨቋኞች ሕይወቱን ከእኔ ነጥቀው ወስደዋል፡፡ እጠላቸዋለሁ፤ በዚህ ያልተጠበቀ ፍንዳታ ውዶቻቸውን ላጡት ቤተሰቦች ሁሉ ፈጣሪ መጽናናትን እንዲሰጣቸው እመኛለሁ። ከሀዲዎች ለፈፀሙት ሰይጣናዊ እርምጃ ፈጣሪ አንድ ቀን ፍርድ እንዲሰጥ እፀልያለሁ » ሲሉ አንድ እናት እያለቀሱ ለዘጋርድያን ተናግረዋል።

የሶማሊያ መንግሥት ግድያውን በቅርብ ዓመታት በርካታ ተመሳሳይ ማጥቃቶችን የፈፀመውንና አክራሪ እስላማዊ ቡደን የሆነውን አልሸባብን በመወንጀል ተጠያቂ አድርጓል፡፡ በ2015 በጎረቤት ኬንያ በዩኒቨርሲቲ ቅጥር ግቢ ውስጥ በፈፀመው ጥቃት ወደ150 የሚጠጉ ሰዎች ሰለባ መሆናቸውንና ከወር በፊት ቡድኑ በመቋዲሾ ሬስቶራንት ለሰዓታት የዘለቀ እገታ አድርጎ ቢያንስ 31 ሰዎች መግደሉን ዋቢ በማድረግ።

የአልሸባብ ድንበር ዘለል አሻራውና ለረጅም ጊዜ የቆየው ተፃራሪ ቅራኔ አሁን በመቋዲሾ የተፈጠረውን አይነት ማጥቃት ለመፈጸም መነሻ ሆኖታል፡፡ ዘጋርድያን ሪፖርት እንዳደረገው በርካታ ኪሎግራም ቤት ውስጥ የሚሰሩ ፈንጂዎችም በፍንዳታው ላይ ውለዋል፡፡ የአልሸባብ ወታደራዊ ክንፍ አንዳንድ ጊዜ ኃላፊነት ይወስድ የነበረ ቢሆንም ይህን ጥቃት በተመለከተ ድምፁን አላሰማም፡፡ በሶማሊያ እስር ቤት ውስጥ የሚገኘው የቀድሞው የቡድኑ መሪ ሼክ ሙክታር ሮቦው የተፈጸመውን የቦምብ ጥቃት በማውገዝ «ሃይማኖትን የሚፃረርና ልብ የለሽ ነው» ማለቱን ኦሶስየትድ ፕሬስ ገልጿል፡፡

መሀመድ ሀጂ ኢንግሪስ በመቃዲሾ ተማሪ ሲሆን ለኢይደር እንደገለጸው፤ የአገሪቱ ባለሥልጣናት ለጥቃቱ አልሸባብን ተጠያቂ ማድረጋቸው ትክክል የሆኑ ቢመስልም፤ ምናልባትም ሌላ ባልተረጋጋ መንግሥቱ ላይ ጥቅም ለማትረፍ የሚፈልግ ቡድን በዚህ ጉዳይ እጁ ሊኖርበት ይችላል ሲል ጥርጣሬውን ገልጿል፡፡

ኢይደር እንደ ገለጸው፤ አልሸባብ ራሱ ባደረሰው ጥፋት መጠንና ግዝፈት ከሕዝቡ የሚከተለውን የቁጣ ምላሽ በመፍራት ኃላፊነቱን ላለመውሰድ ጀርባውን አዙሮ ሊሆንም ይችላል፡፡ ሶማሌያውያን የደረሰውን እልቂት በመቃወም እሁድ ዕለት በአደባባይ ሰልፍ አድርገዋል፡፡ በዚህ ደረጃና መጠን አደጋ በመድረሱ ይህ ሁኔታ ሶማሌዎች ሙሉ በሙሉ ፀረ አልሸባብ አቋም እንዲይዙ ሊያደርግ ይችላል። ክስሰቱ በግጭት ውስጥ ለበርካታ ዓመታት በኖረችው አገር ወሳኝ ለውጥ ያመጣ ይሆናል።

ከፍተኛ ከሆነው የአሸባሪዎች የቦምብ ፍንዳታ ጥቃት በኋላ አልሸባብ ዝምታን መምረጡ አነጋጋሪ ሆኗል፡፡ ቡድኑ በፍጥነት ኢላማ የሚያደርጋቸው በሶማሊያ ዋና ከተማ ሕዝብ የሚበዛባቸውን አካባቢዎች ሲሆን አላማውም የማዕከላዊውን መንግሥት ዕውቅናና ሕጋዊነት ማሳጣት እንዲሁም ከአሜሪካና ከአፍሪካ አጋሮቹ ጋር ያለውን ትብብር በመቃወም ወደ ኋላ እንዲያፈገፍጉ ማድረግ ነው፡፡

አልሸባብ እ ኤ አ ከ2010 ጀምሮ አሜሪካና አጋሮቿ የእዝ ሰንሰለቱን ኢላማ ካደረጉ ወዲህ የያዘውን አካባቢ የመልቀቅ የፋይናንስና የአባላት ምልመላ ውድቀት ደርሶበታል፡፡ ይህም ሆኖ ወታደራዊ ካምፖችን ከማጥቃት በሶማሊያ ውስጥና ውጭ የቦምብ ጥቃቶችን ከማቀናበር አላገደውም ሲሉ በዋሽንግተን የሚገኘውና በፔንታጎን ፋይናንስ የሚደረገው የራንድ ኮርፖሬሽን የመከላከያ ፖሊሲ ዳይሬክተር ሴዝ ጊ ጆንስ ተናግረዋል፡፡

ጆንስ ለዋሽንግተን ፖስት አልሻባብ በአንፃራዊነት በነፃ የሚንቀሳቀስበት ቦታ አለው በማለት ገልጸዋል፡፡ ይህም በደቡብ የወንዞች ሸለቆን ያካትታል፡፡ መሬቱ ለእግረኛ ሠራዊት እንቅስቃሴ በጣም ፈታኝ ነው፡፡ ጥቅጥቅ ያለው ጫካና ቅጠላ ቅጠል ለድሮኖች (ሰው አልባ አውሮፕላኖችቅኝት አመቺ አይደለም፡፡

አሁንም ቢሆን አልሻባብ በደቡብ ገጠራማ ቦታዎችንና ወደከተሞች የሚያደርሱ መንገዶች ጭምር በቁጥጥሩ ስር ናቸው፡፡ የአልሸባብ ቡድን በሞቋዲሾ ከተማ ውስጥ በመንግሥት የተያዙበትን የባሕርዳርቻ ገቢ ለማካካስ ከነጋዴዎች ቀረጥ ይሰበስባል፡፡

የሶማሊያ ተንታኝና የጂኦግራፊ ፕሮፌሰር ሁኖ በሚኒሶታ ዩኒቨርሲቲ የሚሠራው እንዲሁም የመቋዲሾ ዩኒቨርሲቲ የቦርድ አባል ሁኖ በማገልገል ላይ የሚገኘው አብዲ ኢስማኤል ሳማታር የአሚሶም ወታደሮች በሶማሊያ አንድዋና ትልቅ ወደሆነችው የባይደዋ ከተማ ለመሄድ በደፈጣ የተሞሉ መንገዶችን በመተው አውሮፕላን እንደሚጠቀሙ ተናግሯል፡፡ አልሸባቦች በተለይ ፍፁም ተነቃናቂ በሆኑ የደፈጣ ተዋጊዎች በመጠቀም ይዋጋሉ፡፡ መንግሥት በሌለበት ሰፊ ግዛት ውስጥ ይንቀሳቀሳሉ፡፡ በሰዓቱ የፈለጉትን በራሳቸው ምርጫ ማድረግ ይችላሉ ብሏል፡፡

የአሜሪካ መንግሥት ባለሥልጣናትና ሌሎች ታዛቢዎች የቅዳሜው ጥቃት ለአልሸባብ ዳግም ማንሰራራት ምልክት አይደለም ቢሉም፤ የአሜሪካ ስቴት ዲፓርትመንት የቅዳሜው የአልሸባብ ጥቃት ቡድኑ በመላው አገሪቱ ጥቃቶችን ለማድረስ የሚችል አቅም እንዳለው ያሳየበት መሆኑን አምኗል፡፡ ቢሆንም መንግሥት ሶማሊያ በጦር አበጋዞችና በጎሳ አለቆች ከመመራት ወጥታ በመላው አገሪቱ ተደራሽ በሆነ መልኩ በፌደራል ሥርዓት እንድትተዳደር በማድረግ በኩል እርምጃ አሳይቷል ብሏል፡፡

 ወንድወሰን መኮንን

“ሁሉንም ፈንቅል HR 128ን አምክን” – በሶማሊያ ዕልቂት የህወሓት ሥውር እጅ? – ጎልጉል

ህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ /ህወሓት/ የተነሳበትን ዓላማ ለማሳካት የማይፈነቅለው ድንጋይ የለም የሚለው አስተያየት አሁን አሁን አከራካሪ ሊሆን አይችልም። በብዥታ ውስጥ የነበሩት እንኳን አሁን “ምን እየሆነ ነው” በሚል ራሳቸውን እየጠየቁ ያለአስረጂ ምላሹን እያገኙ ህወሓትን በጥርጣሬ የሚያዩበትን መነጽር አውልቀዋል። ይህ እንግዲህ በውጪውም ዓለም ጭምር እየሆነ ነው።

Related stories   ህወሃትና ኦነግ ሸኔ በሽብርተኛ ድርጅትነት እንዲሰየሙ የውሳኔ ሐሳብ ቀረበ

በአስገንጣይነትና በተገንጣይነት ሲርመጠመጥ የነበረው ህወሓት ባላሰበው መልኩ፣ በህልሙም አስቦት የማያውቀውን፤ የአገር መሪነት ያስረከቡት “ቀጣሪዎች” ሳይቀሩ አሁን አሁን ፊት ለፊት “አናምንህም” ባይሉትም፣ ዙሪያውን እየዞሩትና እያዞሩበት ይገኛል። ብዙ ምልክቶች አሉ። አንደበታቸውን የከፈቱና “ዋ” የሚሉም እየተነሱ ነው።

ከየአቅጣጫው የሚነሳውን ይህ ከላይ ጨምቀን ያቀረብነውን ጉዳይ የሚያጠናክር መረጃ ጎልጉል ስለደረሰው ነው። በአሜሪካ የህወሓት/ኢህአዴግ የፖለቲካ ግቢ /ኤምባሲ ለማለት ነው/ ውስጥ ከሚሠሩ ታማኝ ምንጮችና ለጉዳዩ ቅርብ ከሆኑ ክፍሎች የተገኘው መረጃ እንደሚያስረዳው በሶማሊያ ከደረሰው አሰቃቂ እልቂት ጋር በተያያዘ የፖለቲካ ቁማሩ ተጧጡፏል።

Related stories   የደህንነትና ፀጥታ የጋራ ግብረ ኃይል አገር ለማተራመስ በህቡዕ የተደራጁ በርካታ ግለሰቦችን ከነመዋቅራቸውና መስሪያዎቻቸው በቁጥጥር ስር አዋለ፤

እኛ ከሶማሊያ ስንወጣ የሚሆነውን ጅማሮ አያችሁ?

ጉዳዩ እንዲህ ነው። በአሜሪካ የህወሓት የፖለቲካ ጊቢ የህወሓት ሹመኛ ለአሜሪካ የእንደራሴዎች ምክርቤት የአብላጫው (ማጆሪቲ) መሪ ቢሮ ብቅ ይላል። በሶማሊያ ከ300 በላይ ንጹሃንን የቀጠፈውን ፍንዳታ ያነሳል። ከዚያም “ያልነው አልቀረም! ይኽው አያችሁት” ይላል፤ አስከትሎም “ይህ የአሁኑ አደጋ እኛ ከሶማሊያ ስንወጣ የሚሆነውን ጅማሮ የሚያሳይ ነው። አያችሁ?” ሲል አክሎ ይናገራል።

ለጎልጉል መረጃውን ያቀረቡት ሁለቱም ክፍሎች እንዳረጋገጡት “አልሸባብ እኛን ብቻ ነው የሚፈራው። እኛ ጠቅልለን ከወጣን አገሪቱ ትደበላለቃለች። ይህ አሁን የተከሰተው የወደፊቱ ማሳያ ነው …” በማለት ሹመኛው ለአብላጫው መሪ ቢሮ ተናግሯል። የመረጃው ባለቤቶች ለጎልጉል ሲያስረዱ ይህ ሁሉ ዘመቻና ሩጫ የHR 128 አናቂ ህግ እንዳይጸድቅ ለመከላከልና ለመደራደር ነው። እስካሁን ከሚደረጉት ሩጫዎች በተጨማሪ።

ጥርጣሬውና – ሰንሰለት የሆኑ ጭብጦች

አደባባይ ወጥቶ ያወጀ ክፍል ባይኖርም ህወሓት በሶማሊያ በደረሰው አሰቃቂ አደጋ እጁ አለበት የሚሉ ፍንጮች እየተሰሙ ነው። ጎልጉል ባሰባሰበው ማስረጃ ጥርጣሬው ያላቸው ክፍሎች ህወሓት የተሟላ መልስ የማይሰጥባቸው የኮለሉ ንጹህ ጭብጦችን ያነሳሉ። (ህወሓት በዓለምአቀፍ የአሸባሪዎች ቋት በአሸባሪነት ተመዝግቦ የሚገኝና የፈጸመው የሽብር ተግባር እዚያው በዝርዝር የሚገኝ መሆኑን እዚህ ላይ ልብ ይሏል)

  1. ህወሓት በአገር ውስጥ ፖለቲካ መፈናፈኛ አጥቶ መላወሻ ባጣበት በአሁኑ ወቅት አዲስ የተረቀቀው (የHR 128) ህግ የህይወትና የሞት ጥያቄ መሆኑ፣ ህጉ ተጠያቂ የሚሆኑ ባለስልጣኖችን ለይቶ አንገታቸው ላይ ሽምቀቆ የሚያስገባ መሆኑ፣ ከሁሉም በላይ አብዛኛው በግልና በድርጅት የተዘረፈ ንብረት ላይ ማተኮሩ ይህም ቤተሰቦቻቸውን ጭምር ማስጨነቁ
  2. ከዚህ ጭንቀት መውጣት አማራጭ የሌለው ግብ በመሆኑ ህጉ ከመጽደቁ በፊት ማናቸውንም ዓይነት ዋጋ መክፈል። ለሚከፈለው ዋጋና ዘመቻውን ለሚመሩት ተከፋይ ባንዳዎች ግብዓት የሚሆን ተግባራትን መፈጸም፤
  3. በዚህ መነሻ፣ ከስር በሚቀርቡ አብረቅራቂ ምክንያቶች ህወሓት በሶማሊያ በደረሰው ዘግናኝ አደጋ እጁ እንዳለበት ከግምት በላይ የዘለሉ ፍንጮች እየተሰሙ ነው።
Related stories   የኮሚሽነር አበረ ህልፈት "በነጋዴዎች" እይታና ፤ የሃኪም ትክክለኛው መረጃ " ቸልተኛነት አይተናል"

በአሜሪካ ባለው የሕግ አሠራር መሠረት የአንድ አገር የፖለቲካ ሹመኛ በቀጥታ በአሜሪካ የህግ አውጪ አካል ላይ (ህወሓት ሰሞኑን በፈጸመው መልኩ) ተጽዕኖ በማድረግ ሕግ እንዳይወጣ የማስቀልበስ ተግባር መፈጸም አይችልም በማለት አንዳንድ ወገኖች ይናገራሉ። የወትዋቾች አስፈላጊነት እየገነነ የመጣውም ከዚህ ሕግ በመነሳት እንደሆነ ያስረዳሉ። ይህ የሰሞኑ የህወሓት ተግባር አገሪቷን ወዳልተፈለገ አቅጣጫ ሊወስዳት እንደሚችል አብሮ እየተነገረ ያለ ጉዳይ ነው።

ጭብጦች

  • እልቂት ጀብድ የሆነለት አልሸባብ እስካሁን (ይህ ዘገባ እስከተዘጋጀበት) ለደረሰው አደጋ ኃላፊነት አልወሰደም፤
  • ህወሓት በሶማሊያ ምድር የድሮውን ሳይጨምር፣ እየለቀቀ መውጣቱ ብቻ ሳይሆን አልሸባብ እግር በግር እየተከተለ ከተሞቹን መቆጣጠሩ ውስጣዊ ግንኙነት እንዳለ ጠቋሚ መሆኑ በተለያዩ ጊዜያት መጠቆሙ፤
  • አሚሶም ከሚባለው የሰላም ግብረኃይል ቁጥጥር ውጪ የሆነ የህወሓት የጦር መሪዎች የሚያዙት ሠራዊት በተደራቢነት በሶማሊያ መሰማራቱ። ይህ ከአሚሶም ማዕቀፍ ውጭ የሆነውና የሕወሃት መሪዎች የሚያዙት ጦር በስትራቴጂና በወል በሚደረገው ዘመቻ ላይ እንቅፋት መሆኑ በአሚሶም አመራሮች በተደጋጋሚ በቅሬታ ደረጃ መቅረቡ፤ (በዚህ ጉዳይ ላይ ጎልጉል የዘገበውን እዚህ ላይ ይመልከቱ)
  • የህወሓት አመራሮች ሲፈልጉ የሚቆልፉት፣ ሲፈልጉ የሚከፍቱት ኮሪደር ማበጀታቸውና ከሁሉም የሶማሊያ የጎሳ መሪዎች ጋር የቆየ ትሥሥር ያላቸው መሆኑ፤ ኢትዮጵያን የማፈራረሱን ትግል በእንጭጩ ደረጃ ሲያካሂዱ ይህንኑ ስልታዊ የፖለቲካ ንግድ ለማዋቀራቸው መረጃ ያላቸው ምስክር መሆናቸው፤
  • አልሸባብ በከፍተኛ ደረጃ የስለላና የደህንነት መዋቅር ያደራጁትን ታላላቅ የሚባሉ አገሮች ሲያተራምስ ኢትዮጵያ ውስጥ ምንም ጥቃት አለመውሰዱየሽርክናቸው ማሳያ ስለመሆኑ። ይህንን የሚናገሩ ክፍሎች “ኢትዮጵያውያን ለምን አልሞቱም” ከሚል ርካሽ አስተሳሰብ በመነሳት ሳይሆን ትሥሥሩን ለማሳየት ብቻ ሲሉ መሆኑን መረዳት እዚህ ላይ ልብ ይሏል።
  • በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል እስካሁን በሰላም ይኖሩ የነበሩ ሰላማዊ ዜጎች በዘር ሳቢያ ሲፈናቀሉ ዝምታን መምረጡና ከድራማው በስተጀርባ ህወሓቶች ስለመኖራቸው መረጃ መውጣቱ፤

በጥቂቱ የሚወሱ ጭብጦች ናቸው። እነዚህንና ሌሎችንም አክለው እንዲሁም ከህወሓት አጠቃላይ የአሸባሪነት ባህርይ በመነሳት የሰሞኑን አሰቃቂ የሶማሊያ ፍንዳታና ዕልቂት ውስጥ ህወሓት እጁ ሊኖር ይችላል የሚል ግምት የሚሰጡት።

የHR 128 ጦስ በርካታ የችግር ናዳ የሚያወርድበት መሆኑን የተገነዘበው ህወሓት ከኅልውናው አንጻር ይህንን ረቂቅ ሕግ ለመቀልበስ የማይፈነቅለው የፖለቲካ ድንጋይ አይኖርም በሚለው ሃሳብ ጉዳዩን የሚከታተሉ ወገኖች በአንድ ድምጽ የሚስማሙበት ነው። ወትዋች ከመቅጠር ጀምሮ እኛ ሕጉ ከጸደቀ ከሶማሊያ እንወጣለን፤ ሲቀጥልም አልሸባብ ሶማሊያን ያፈርሳታል፤ እንዲያውም “ሠርቶ ማሳያው” ይህ ነው እስከማለት የቦንብ ፍንዳታውን ለማቀነባበር ህወሓት ቅንጣት ወደኋላ አይልም በሚለው የሚስማሙ ህወሓት ከዚህ በፊት በኢትዮጵያ ያደረገውን እንደ አስረጂ ያቀርባሉ።

መስከረም 6፤ 2009ዓም (September 16, 2006) በአዲስ አበባ በሚኒባስ የፈነዳ ቦምብ በኦነግና በኤርትራ ላይ የተሳበበ መሆኑን የሚያስታውሱ ወገኖች ህወሓት ያኔ የፈጸመውን የአሸባሪነት ተግባር ላሁኑ እንደ ግብዓት ያነሳሉ። ሆኖም ቆየት ብሎ የታተመው የዊኪሊክስ (ሹልክ ዓምድ) ዘገባ ፍንዳታውን አቀነባብሮ ያከናወነው ህወሓት ስለመሆኑ እዚህ ላይ በዝርዝር አስረድቷል። ከበረሃ ጀምሮ ማሸበር ሙያው የሆነው ህወሓት ሥልጣን ይዞም ይህንኑ በደም የተነከረ ታሪኩን ቀጥሎበታል። ታዲያ አሁን ደግሞ HR 128ን ለማምከን ሶማሊያ ቢዘምት ምን ይደንቃል? ሲሉ አስተያየት ሰጪዎች ይናገራሉ።

Share and Enjoy !

Shares

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *