Via BBC Amharic “ችግርን ከመፍታት ይልቅ ጩኸት ማፈን ነው የሚቀናቸው”

የአፄ ፋሲል ቤተ-መንግሥት

ጎንደር ፖለቲካዊና ምጣኔ ሃብታዊ ምሬቶች የሾፈሯቸው ናቸው የተባሉ ከፍተኛ ሕዝባዊ ተቃውሞዎችን ካስተናገደች ከአንድ ዓመት በላይ ጊዜ ቢያልፍም፤ ነዋሪዎቿ የሻቱትን ለውጥ አለማግኘታቸውን ይናገራሉ።

በከተማዋ አሁንም የብሔር ተኮር ውጥረት ምልክቶች የሚስተዋሉ ሲሆን፤ በመዝናኛ ስፍራዎች ፖለቲካዊ ይዘት እንዳላቸው የሚታመኑ ዘፈኖችን ማድመጥ እንግዳ አይደለም።

ከዚህም ባሻገር ስፖርታዊ ትዕይንቶችን እና ሃይማኖታዊ ክብረ በዓላት የሚፈጥሯቸውን አጋጣሚዎች ቅሬታዎቻቸውን ለማንፀባረቅ እንደሚጠቀሙባቸው ቢቢሲ ያነጋገራቸው ወጣቶች ይገልፃሉ።

የመልዕክቶቹ ፖለቲካዊ አንድምታ ብዙም የተደበቀ እንዳልሆነ የሚያወሳው የከተማዋ ነዋሪ ወንድወሰን አለባቸው*፤ ከሳምንታት በፊት የተከበረው የመስቀል በዓል ላይ ይታዩ ከነበሩ አልባሳት ላይ ከታተሙ ጥቅሶች መካከል “የፈራ ይመለስ” እና “የወጋ ቢረሳ የተወጋ አይረሳም” የመሳሰሉትን እንደሚያስታውስ ይናገራል።

የፀጥታ ኃይሎች አልባሳትን ለማስወለቅ ሲጥሩ መመልከቱንም ጨምሮ ይገልጻል።

“ችግርን ከመፍታት ይልቅ ጩኸት ማፈን ነው የሚቀናቸው” ይላል ወንድወሰን ከቢቢሲ ጋር በነበረው ቆይታ።

በ2008 ዓ.ም የክረምት ወራት በጎንደር ተቃውሞ መቀስቀስ ሲጀምር ከሰሜናዊው አዋሳኝ የትግራይ ክልል ጋር የድንበር ጥያቄ በማንሳት እንደነበር ይታወሳል።

በሐምሌ ወር መባቻ አዋሳኙ የወልቃይት አካባቢ በአማራ ክልል ስር እንዲጠቃለል ጥያቄ ለማቅረብ የተዋቀረውን ኮሚቴ አባላት በቁጥጥር ስር ለማዋል ሙከራ ተደርጎ በከሸፈበት ወቅት በተደረገ የተኩስ ልውውጥ ከአስር በላይ ሰዎች ህይወት መጥፋቱ ተዘግቦ የነበር ሲሆን፤ የኮሚቴው ሊቀ መንበር ኮሎኔል ደመቀ ዘውዱ ክስ ተመስርቶባቸው እስር ላይ ይገኛሉ።

ኮሎኔሉን ከመያዝ ለመታደግ ሲጥር በተኩስ ልውውጡ ወቅት ሕይወቱን ያጣ ጠባቂያቸውን በማስታወስ ወደ መቃብር ስፍራው ሲያቀኑ ከፖሊስ ጋር ግጭት ውስጥ የገቡና እንዲመለሱ የተደረጉ ሰዎችን እንደሚያውቅ ሌላኛው የከተማዋ ኗሪ አንዋር አብዱልቃድር ይናገራል።

Related stories   ሀገሪቷን ከጥፋት ለመከላከል ፣ ህግን ለማስከበር ፌዴራል ፖሊስ ተግባሩን ያጠናክራል
ባህረ ሰላም ሆቴል
አጭር የምስል መግለጫባህረ ሰላም ሆቴል

ያልተወራረደ ሒሳብ

ተቃውሞውን ተከትሎ በተፈጠረው ያለመረጋጋት ጥቃት ከደረሰባቸው የንግድ ተቋማት መካከል ባሕረ ሰላም ሆቴል አሁንም እንደተሰባበረ ተዘግቶ ይገኛል።

ሆቴሉ የጥቃት ሰለባ የሆነው የኮሚቴው አባላትን በቁጥጥር ስር ለማዋል የመጡ የደህንነት አባላት ስላረፉበት መሆኑን የስፍራው ኗሪዎች ይናገራሉ።

በሆቴሉ አካባቢ በአነስተኛ የችርቻሮ ንግድ ላይ የተሰማራች ወጣት የሆቴሉ ባለቤቶች ከጥቃቱ በኋላ ተመልሰው መምጣታቸውን እንደማታውቅ ትናገራለች።

ተቃውሞው በከረረበት ወቅት ከጥቃት ለመሸሽ በርካታ ቁጥር ያላቸው የትግራይ ተወላጆች ሐብትና ንብረታቸውን ጥለው ወደ ትግራይ ክልል መግባታቸው የተዘገበ ሲሆን ከመካከላቸው ጥቂቶቹ ብቻ መመለሳቸውን እንደሚያውቅ አንዋር ይናገራል።

በበርበሬ ንግድ ሥራ ላይ የተሰማራችው ሰናይት መኮንን* እንደምትለው በጎንደር እና በትግራይ ክልል መካከል ያለው የንግድ እንቅስቃሴ መዳከሙ ሥራዋን ክፉኛ ከማወኩም ባሻገር “ግርግሩ ብዙ ገንዘብ አሳጥቶኛል” ትላለች።

ሰናይት በርበሬን ከምዕራብ ጎጃም ከገዛች በኋላ የተለያዩ እሴቶችን ጨምራ በሽሬ እና ሑመራ ለሚገኙ ቸርቻሪ ነጋዴዎች ትልክ እንደነበር ትገልፃለች።

“ሁሌም በንፁህ መተማመን ነበር የምንሰራው። ስልክ ደውለው የሚፈልጉትን ያህል መጠን ይነግሩኛል፤ አስጭኜ እልክላቸዋለሁ። እርሱን ሸጠው በሳምንትም በወርም ገንዘቡን ይልኩልኛል” ስትል ለቢቢሲ ታስረዳለች።

በዚህም መሰረት ያለመረጋጋቱ ሲከሰት 280 ሺህ ብር የሚገመት በርበሬ ለደንበኞቿ ልካ እንደነበርና ከአንድ ዓመት የሚልቅ ጊዜ ቢያልፍም ገንዘቡን ማግኘት መቸገሯን ትናገራች።

“እነርሱም ወደዚህ አይመጡ፤ እኔም ወደዚያ አልሄድ፤ በስልክ ብቻ እየወተወተኩ ነው” ትላለች።

ደንበኞቿ በጎንደርና በአካባቢው ሌሎች ከተሞችም ጭምር ልዩ ልዩ የንግድ ሥራዎችን ያከናውኑ የነበረ ሲሆን፤ ያለመረጋጋቱን ተከትሎ ሥራቸውን እንደቀደመው ማከናወን ባለመቻላቸው ለኪሳራ ተዳርገው ገንዘቧን ሊልኩላት እንዳልቻሉ ገልፀውላታል።

በዚህ መልኩ ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብን ያጡ በተለይ በሕንፃ ሥራዎች ንግድ ላይ የተሰማሩ የሙያ አጋሮቿን እንደምታውቅ የምታስረዳው ሰናይት “እንግዲህ ከእነርሱም ወገን እንዲሁ ገንዘብም ዕቃም የቀረበት ይኖር ይሆናል” ትላለች።

Related stories   “ጣልያኖችም ሆኑ እንግሊዞች ቅኝ ግዛትን ለማስቀጠል ህዝቡን በዘር መከፋፈልን እንደ አንድ ስልት ይጠቀሙ ነበር” -አቶ ታቦር ገረሱ ዱኪ

“ከዚህ በኋላማ መተማመኑ ጨርሶ ጠፍቷል” የምትለው ሰናይት የወትሮ የንግድ አሰራሯ እንዳከተመለት ትናገራለች።

በመምህርነት ሙያ ለተሰማራው ሞገስ አብርሃ* የመተማመን መሸርሸር እጅጉን የሚያሳስብ ጠባሳ ነው።

“ፖለቲካው በማኅበራዊ ሕይወት ውስጥ ሰርጎ ጥርጣሬን የዘራ ይመስለኛል” ይላል የትግራይ ተወላጁ ሞገስ።

ከተማዋ በተቃውሞና በግጭት በምትናጥበት ወቅት በቤተሰባዊ ጉዳይ ትግራይ ውስጥ የነበረው ሞገስ፤ ወደጎንደር እንዳይመለስ ከዘመዶቹ ግፊት እንደነበረበት ያስታውሳል።

“ስጋታቸው ገብቶኛል፤ ነገር ግን ትዳርና ልጆች ካፈራሁበት ቦታ እንዲሁ ብድግ ብዬ አዲስ ህይወት ልመሰርት አልችልም” ሲል ለቢቢሲ ይናገራል።

ያለመረጋጋቱን መስከን ተከትሎ ወደሥራው ከተመለሰ በኋላ የገጠመው የተለየ ነገር እንደሌለ የሚናገረው ሞገስ ሄደው የቀሩ የሥራ ባልደረቦች እንዳሉት ይጠቅሳል።

“የትግራይ ክልል ለተፈናቃዮቹ ድጋፍ አድርጌያለሁ ቢልም [በግለሰብ] ከጥቂት ሺህ ብር በላይ የሰጠ አይመስለኝም።”

ጎንደር

ከአንድ ዓመት በኋላ

የጎንደር ከተማው የባህል፣ ቱሪዝም እና ወጣቶች ጽህፈት ቤት ኃላፊ የሆኑት አቶ አስቻለው ወርቁ ወደ ከተማዋ ዘላቂ ሰላምን እንዲሁም ተጠቃሚነትን እንዲመለስ ለማድረግ ብዙ ሥራዎች ተከናውነዋል ይላሉ።

ለወጣቶች የሥራ ዕድልን ለመፍጠርና ለከተማዋ እና ለአካባቢው ምጣኔ ሃብት የጎላ ሚና የሚጫወተውብን የቱሪዝም ዘርፍ ዳግመኛ ለማነቃቃት መሰራቱን ይገልፃሉ።

“በ2009 የውጭ አገር ጎብኝዎች ቁጥር በጣም ቀንሶ የነበረ ሲሆን፤ ይህንን በማካካስ በዘርፉ ላይ የተሰማሩት የኅብረተሰብ ክፍሎች የማይጎዱበትን ሁኔታ ለመፍጠር ሞክረናል” ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

በዚህም መሰረት ከ45 ሺህ በላይ የሃገር ውስጥ ጎብኝዎች ለመዝናናት፣ ለስብሰባ፣ ስፖርታዊ ትዕይንቶችን ለመታደም እንዲሁም በክብረ በዓላት ላይ ለመሳተፍ ወደ ከተማዋ አቅንተዋል።

Related stories   በቡድን ተደራጅተው የውንብድና ወንጀል የፈጸሙት ተከሳሾች ከ18 እስከ 20 ዓመት በሚደርስ እስራት ተቀጡ፡፡

“በያዝነው ዓመት ግን ከውጭ አገር የሚመጡ ጎብኝዎች ቁጥር ከፍ ያለ ሆኗል” የሚሉት አቶ አስቻለው ከተማዋ በነሐሴና መስከረም ወራት ብቻ ከ3000 በላይ የውጭ አገር ጎብኝዎችን ማስተናገዷን ይገልፃሉ።

ቁጥሩ ከዚህ እየተሻሻለ እንደሚሄድም ይጠብቃሉ።

በዚህ አባባል የሆቴል ባለቤትና አስተዳዳሪው አቶ ስዩም ይግዛውም ይስማማሉ።

“በአሁኑ ሰዓት ካሉን ክፍሎች መካከል ሰባ አምስት በመቶው ያህል ተይዘዋል” ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የጎብኝዎች ቁጥር እና ተያይዞ ያለው ኢንዱስትሪ በወቅት ላይ የተመሰረተ መሆኑን የሚያስረዱት አቶ ስዩም፤ በሥራ ላይ ከቆዩባቸው ስድስት ዓመታት መካከል ያለፈውን ዓመት እጅግ ዝቅ ባለ የሥራ እንቅስቃሴ በተለየ እንደሚያስታውሱት ያወሳሉ።

ለዚህም የአካባቢው የፀጥታ ሁኔታ ጉልህ ሚና እንዳለው ይገምታሉ።

በተለይም በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች በርካታ ስፍራዎች ተቃውሞዎች እና ግጭቶች መቀጣጠላቸውን ተከትሎ፤ ባለፈው ዓመት ጥቅምት ወር ላይ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መደንገጉ የጎብኝዎች ቁጥር ለማሽቆልቆሉ በምክንያትነት ይወሳል።

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በመደንገጉ የተለያዩ አገራት ዜጎቻቸውን ወደ ስፍራው እንዳይሄዱ መምከራቸው አልቀረም።

ከዚህም ባሻገር ባለፈው ዓመት አጋማሽ በተከታታይ ያጋጠሙት የእጅ ቦንብ ፍንዳታዎች፤ የተለያዩ ሃገራት ወደ ጎንደር ለማቅናት ላሰቡ ዜጎቻቸው የጉዞ ማስጠንቀቂያ እንዲያወጡ አስገድዷቸዋል።

“የጉዞ ማስጠንቀቂያዎቹ ሥራችንን በከፍተኛ ሁኔታ ጎድተውታል፤ ከየሃገራቸው ለጎብኚዎች ጉዞዎችን የሚያሰናዱ አካላት ስለአካባቢው ያለውን ሁኔታ ከኤምባሲያቸው ማጥናታቸው አይቀርም” ይላሉ አቶ ስዩም።

አዋጁ ያለመረጋጋቱን ቢያሰክነውም ለጥያቄዎች መልስ በመስጠት ረገድ ግን መንግሥት በቂ እርምጃዎችን እንዳልወሰደ ተንታኞች ሲያስረዱ ይደመጣሉ።

ወንድወሰን ባለፈው የአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ “ምንም የተቀየረ ነገር የለም” ባይ ነው።

የከተማዋ ነዋሪ አንዋር እንደሚለው፤ ተቃውሞዎቹ ኅብረተሰቡ ያለውን ስሜት እንዲያሳይ እድል ፈጥረውለታል፤ ይሁን እንጅ “ጥያቄያችን ሳይመለስ ችግሩ ተቀርፏል ማለት ራስን ማታለል ነው።”

ጎንደር

*ስም የተቀየረ

Share and Enjoy !

Shares

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *