4 eyed

የኦሪት ዘፍጥረት መጽሐፍ ሰው በእግዚአብሔር አምሳል እንደተፈጠረ ይናገራል፡፡ የነገረ ሃይማኖት መምህራን ደግሞ ሰው “አእምሮ፣ ለብዎ” (እውቀትና ማስተዋል) ካላቸው ፍጥረታት ሁለተኛው ነው ይላሉ፡፡ የመጀመሪያዎቹ እውቀትና ማስተዋል ያላቸው ፍጡራን መላእክት ናቸው፡፡ ሰው ከመላእክት የሚለየው በሥጋ መዋቲ (ሟች) ስለሆነ ነው፡፡ በነፍሱ ኅያውነት መላእክትን፣ በሥጋው መዋቲነት ደግሞ እንስሳትን ይመስላል፡፡ በመሆኑም ሰው በመላእክትና በእንስሳት መካከል ያለ ፍጡር ነው፡፡ እንስሳት እንደመላእክትና እንደሰው እውቀትም ሆነ ማስተዋል የላቸውም፡፡ ከመላእክትም ሆነ ከእንስሳት የሚለየው ግን በእግዚአብሔር አምሳል ስለተፈጠረ ነው፡፡ እግዚአብሔር መላእክትንም ሆነ እንስሳትን ሲፈጥር “ኑ፤ … በአርአያችን እንደምሳሌያችን እንፍጠር” አላለም፡፡ እንዲህ ዓይነት ክብር ያለው ሰው በተግባሩ ከክብሩ ሲወርድ ግን እንዲህ ተባለለት፡- “ሰው ክቡር ሆኖ ሳለ አላወቀም፤ እንደሚጠፉ እንስሳት መሰለ፡፡” እንስሳትን መሰለ ማለት እውቀትና ማስተዋል ተነሣው ማለት ነው፡፡

ይህ ብቻ አይደለም፡፡ ክቡር ከበደ ሚካኤል በ“ታሪክና ምሳሌ” መጽሐፋቸው
“በሰዎች መካከል ሰካራሞች ሞልተው፣
እንስሳትስ መቼም አይሰክሩ ጠጥተው፡፡” በማለት “ሰው ከእንስሳ ያንሳል” ብለው ይሞግታሉ፡፡ እውነት ይመስላል፡፡ ሰው ይሰክራል፤ እንስሳት ግን ጠጥተው አይሰክሩም፡፡ ከእንስሳት በተለየ ሰዎች ግን ሰካራሞች ነን፡፡ ሰካራምነታችንም ሆነ ጭምትነታችን የሚገለጸው ደግሞ በሥራችን ነው፡፡ በየትኛውም ቦታ ያሉ ሰዎች ከሚሠሩት ሥራ የተነሣ በአራት ይከፈላሉ፡፡

Related stories   አለቃ አጽመ ጊዮርጊስ – የተሳሳተውን የውጫሌ ውል የመረመሩ ጀግና ኢትዮጵያዊ

የመጀመሪያዎቹ ክፋትን አውቀው የሚሠሩ ናቸው፡፡ ክፋት ተፈጥሯዊ አይደለም፡፡ ይህም ማለት ሰው ከክፋት ጋር አልተፈጠረምና አንድ ሰው ክፋትን በኑሮው ይለምዳል እንጂ ይዞት አይወለድም፡፡ ለሰው ልጆች ክፋትም ሆነ ደግነት የሚማሩትና የሚለምዱት ብቻ ነው፡፡ የክፋታቸው ደረጃ ከፍ ያለ ሰዎች የክፋት አስተማሪዎች ስለሚሆኑ ክፋትን አውቀው፣ እቅድ አውጥተው፣ ስትራቴጂ ነድፈው የሚሠሩ ናቸው፡፡

ሁለተኛዎቹ ደግሞ የእነዚህ ሰዎች ተማሪዎች ናቸው፡፡ መምህሮቻቸው ክፋትን አውቀው በዓላማ ሲሠሩና ሲያስተምሩ እነርሱም ክፋትን ሳያውቁት ይማራሉ፤ ይለምዳሉ፡፡ በጎነትም ሆነ ክፋት የሚለመዱ ነገሮች ናቸውና፡፡ የክፉዎች ደቀ መዛሙርት ከመምህሮቻቸው ክፋትን እየተማሩ መሆናቸውን አይገነዘቡም፡፡ ሳያውቁት ግን ክፉዎች በዓላማ የሚያስተላልፉላቸውን የክፋት መልእክት “ላይክ” እና “ሼር” ያደርጋሉ፡፡ ቀስ እያሉ በክፋት ሲያድጉ ደግሞ ራሳቸውም የክፋት አሠልጣኞች ሆነው ያርፉታል፡፡

Related stories   እውነትን ለሥልጣን መናገር !! ሳማንታ ፖወር - ለኢትዮጵያ ዘር ፖለቲከኞች መከላከል አቁሚ!

የmiያጽናናው ነገር ግን ደግነትን አውቀውትም ባይሆን ሲሠሩት የሚገኙ ሰዎች መኖራቸው ነው፡፡ እነዚህ ሦስተኛዎቹ ምድቦች ናቸው፡፡ ከላይ ያየናቸው ሰዎች ክፋትን ሳያውቁት እንደሚሠሩት ሁሉ እነዚህ ደግሞ ደግነትን ከመምህሮቻቸው ሳያውቁት ይለምዱታል፡፡ ምሳሌ የሚሆናቸው ሰው ይፈልጋሉ፡፡

አራተኛዎቹ ሰዎች ደግነትን አውቀው፣ አቅደውና አልመው የሚሠሩ ናቸው፡፡ እነርሱ ለልጆቻቸው የሚያደርጉትን ለልጅ እንደሚደረግ ብቻ አያስቡትም፡፡ ማንኛውም የሀገር መሪ የሚገኘው ከቤተሰብ ስለሆነ ልጆቻቸውን ሲመግቡም ሆነ ሲያለብሱ፣ ሲyaስተምruም ሆነ ሲያናግሩ በዓላማ ለሀገር ግብዓት እንዲሆኑ በማድረግ ነው፡፡ ደግነትን በዓላማ የሚሠሩ ሰዎች ሀገር ማለት የቤተሰቦች ስብስብ መሆኑን ይረዳሉ፡፡ ባልና ሚስት ከልጆች ጋር ቤተሰብን፣ ቤተሰብ ማኅበረሰብን፣ ማኅበረሰብ ሀገርን እንደሚገነባ ስለሚረዱ ሁሉም ተግባራቸው ጥንቃቄን የተመላ ነው፡፡ በየደረጃው እየተመለከቷቸው የሚማሩ መኖራቸውን ስለሚረዱ ሲናገሩም ሆነ ሲሠሩ ለትውልድ አስበው ነው፡፡

Related stories   የባይደን አስተዳደር ፖሊሲ አምስተኛው ምሰሶ የኢትዮጵያ ዙፋን ላይ የሚቀመጠዉን ቡድን መወሰንና የ 2021 ምርጫን ማዋደቅ (1ኛ ክፍል 2)

በአጠቃላይ ሀገር የምትጎዳው ክፋትን አውቀው የሚሠሩም ሆነ ሳያውቁት የክፋት አስፈጻሚዎች የሆኑ ሰዎች ሲበዙ ነው፡፡ በተቃራኒው ሀገር የምትበለጽገው፣ ሕዝብ ሰላም ውሎ ሰላም የሚያdረው ደግነትን በዓላማ እየሠሩ ደጋግን የሚያበዙ ሰዎች ሲኖሩን ነው፡፡

በመሆኑም በያለንበት የሕይወት ዘርፍ ደጎች ለመሆን ደጎችንም ለማውጣት እንጣር፡፡ ደግነትም ሆነ ክፋት የሚለመዱ መሆናቸውን አንርሳ፡፡ ሳናውቀው ክፋትን ለምደን ክፉዎች ከመሆን ይሰውረን፡፡ በሀገራችን እየሆነ ያለው ነገር ሁሉ አውቀንም ሆነ ሳናውቀው ለምደን የምንሠራው ሥራ ውጤቶች ናቸው፡፡ ለመሆኑ እያንዳንዳችን ከአራቱ የትኞቹን ነን?

ደግ ደጉን ያስመልክተን፤ አሜን!

Minwagaw Temesgen    ጥቅምት 12/2010 ዓ.ም

Share and Enjoy !

Shares

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *