ZAGGOLE – ዛጎል

“Our true nationality is mankind.”H.G.

የትውልዳችን ድምጽ፤ ድምጻዊት ሀኒሻ ሰለሞን!

ጥሎብኝ ለሚወዷት አገራቸው የወደቁና የደከሙ የኢትዮጵያ ጀግኖችን የሚያስታውሱ ቁም ነገረኛ ልጆችን ስራ ከልቤ እወዳለሁ። አርብ እለት በኢንተርኔት አማካኝነት የተለቀቀ የሀኒሻ ሰሌሞን «ከፍ በይ ሃገሬ» የሚለው ዜማ ነፍስ ያለውና ከቀኝ ጌታ ዮፍታሔ ንጉሴ በኋላ ታላቁን የኢትዮጵያ ጀግና የራስ ጎበና ዳጨን ውለታ ያወሳ ነበር።

ታላቁ ባለውኔ ቀኝ ጌታ ዮፍታሔ ንጉሴ በስራዎቻቸው በቁማቸው ከበደኑ ከንቱዎች ይልቅ በሕይወቱ ከተለዩት ሙታን መካከል ሕያዋንን የሚፈልጉ ይመስሉኛል። ኢትዮጵያ በፋሽስት ጥሊያን በግፍ በተወረረች ዘመን ኢትዮጵያውያን በፋሽስት ሊሬና በጊዜያዊ ጥቅማጥቅም እየተደለሉ በሎሌነት አድረው ሰልፋቸውን በማስተካከል የባንዶችን ሰፈር ሞልቱ እንዲፈስ በማድረግ እልቆ መሳፍርት ሆነው ጀግኖቻችንን እየወጉ አገራቸውን ማድማታቸውን በመታዘቡ ጊዜ በቁም ከበደኑ ከንቱዎች ይልቅ በሕይወት ከሌሉት ሙታን መካከል ሕያዋን ፍለጋ በሕሊናቸው እያማተሩ፤

Image may contain: one or more people and closeup


አጥንቱን ልልቀመው መቃብር ቆፍሬ፣
ጎበናን ከሸዋ አሉላን ከትግሬ፣
ስመኝ አድሬያለሁ ትናንትና ዛሬ፤
አሉላን ለጥይት ጎበናን ለጭሬ፤
ተሰባሰቡና ተማማሉ ማላ፣
ጎበና ከሸዋ ከትግሬም አሉላ፣
ጎበና ሴት ልጁን ሲያስተምር ፈረስ፣
አሉላ ሴት ልጁን ጥይት ሲያስተኩስ፤
አገሬ ተባብራ ካልረገጠች እርካብ፣
ነገራችን ሁሉ የዕንቧይ ካብ የዕንቧይ ካብ።


 

 

ሲሉ የሚጣላ ሕሊና ያላቸውን ሰዎች አስደምመው ነበር።

ይህንን የቀኝ ጌታ ዮፍታሔን መንፈስ የተላበሰችው ልጅ እግሯ ሀኒሻ ሰለሞን የዮፍታሔን ሁለት ጉባኤ ወደ አራት ከፍ አድርጋ፤

አሉላ፣ መኮንን፣ ደረሰ፣ ጎበና፣
አራቱ ጉባኤ፣ይነሱልንና፣
ዳግም ይመርብን፣ ኅብረታችን ይጽና፤

ስትል ራስ አሉላን፣ ራስ መኮነንን፣ ራስ “ደረሰን” ና ራስ ጎበናን በጉባኤ በመመሰል በመረዋ ድምጿ ነፍስ የሆነ ዜማ ታሰማናለች። ሀኒሻ «አራቱ ጉባኤ» ያለቻቸውን ታላላቅ ኢትዮጵያውያን እኔ የ19ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የኢትዮጵያ Founding Fathers እላቸዋለሁ። አዎ እነራስ ጎበና፣ ራስ መኮነን፣ ራስ ደረሶና ራስ አሉላ የዘመናዊቷ ኢትዮጵያ Founding Fathers ናቸው። ይህ በታሪክም የተረጋገጠ ነው። በዚያ ዘመን በመላ አገሪቱ ስማቸው በጀግንነት ከሚጠሩት አራቱ ስመ ጥር ራሶች መካከል ራስ ጎበና ዳጨ [አባ ጥጉ] ከሸዋ፣ ራስ ደረሶ [አባ ጠቦ] ከጎጃም፣ ራስ መኮነን ወልደ ሚካኤል [አባ ቃኘው] ከሸዋ/ ሐረር እና አራተኛው ስመጥሩ ጀግና ራስ አሉላ እንግዳ [አባ ነጋ] ከትግሬ እንደሆኑ ያ ትውልድ ዋጋውን ከትቢያ እኩል ያደረገው በደምና ባጥንት የተገነባው ታሪካችን ይነግረናል።

ሀኒሻ ዘፈን ላይ ግን አንድ የስም እርማት ማድረግ አስፈላጊ ነው። ሀኒሻ በዘፈኗ «ደረሰ» ያለችው የጎጃሙን ራስ ደረሶን ይመስለኛል። የውጭ አገር ሰዎችና በምዕራባውያን ቋንቋ የኢትዮጵያን ታሪክ የሚጽፉ የኛ ምሁራንም ሳይቀር የራስ ደረሶን ስም በላቲን ፊደል በእንግሊዝኛ ሲጽፉ «ደርሶ»፣ «ደረሰ» ወይንም «ደራሶ» እያሉ ጽፈውት ስለሚገኝና ይህንን ስያሜ በግዕዝ ፊደል የኛ ሰው ሲጽፍ ደራሶ፣ ደረሰ ወይንም ደርሶ ብሎ ስለሚጽፈው የጎጃሙን የጦር መሪ ትክክለኛ ስም ብዙ ሰው ባግባቡ አይጠራውም። የሆነው ሆኖ የሰውየው ትክክለኛ ስም ደረሶ ነው። ራስ ደረሶ የጎጃም አገው ምድርና የዳሞት ተወላጅና የንጉስ ተክለ ሃይማኖት ዘጎጃም ወከፋ የጦር መሪና አፍ የሚያስከፍት ቅኔ የሚያወርዱ ጀግና ነበሩ። ራስ ደረሶ የቅኔ እውቀቱን በየዘመቻው አብረዋቸው ይዘምቱ ከነበሩት ከአለቃ ወልደ ጊዮርጊስ [ ኋላ እጨጌ] እንደተማሩ ይነገራል።

ርዕሰ መኳንንት ደጃዝማች በዝብዝ ካሳ ሐምሌ ፮ ቀን ፲፰፻፷፫ ዓ.ም ዓፄ ተክለ ጊዮርጊስን አድዋ አካባቢ አሳም የሚባል ሥፍራ ላይ ወግተው ድል ካደረጉ በኋላ ጥር ፲፫ ቀን፲፰፻፷፬ ዓ.ም አክሱም ላይ ሥርዓተ ንግሣቸው ተፈጽሞ «መልእክተ ዘሥዩመ እግዚአብሔር ዮሐንስ ንጉሠ ጽዮን፤ ንጉሠ ነገሥት ዘኢትዮጵያ» ተብለው ከነገሱ በኋላ የጎጃሙን ራስ አዳል ተሰማን በጥምቀት ዕለት ሾመው «ንጉሥ፡ተክለ: ሃይማኖት፡ ንጉሠ፡ ጎጃም፡ ሠያሚሁ፡ ዮሐንስ ንጉሠ ጽዮን፤ ንጉሠ ነገሥት» አሰኟቸው። ከዚያም በአዋጅ «ንጉሥ ተክለ ሃይማኖት ዘጎጃም ወከፋ» በማለት የከፋም ንጉሥ አድርገው ስለሾሟቸው ንጉሥ ምኒልክ ማቅናት የጀመሩትን ከፋን ለማቅናት የጦር አዛዣቸውን ራስ ደረሶን ወደ ከፋ ምድር ላኩ። ንጉሥ ምኒልክ ይህንን «የራስ አዳልን» ድርጊት በሰሙ ጊዜ ዋናውን የጦር አዛዣቸውን ራስ ጎበና ዳጨን ወደ ከፋ ላኩ።

Image may contain: 1 person, smiling, closeup

ዐፄ ዮሐንስ ንጉሥ ተክለ ሃይማኖትን ከፋን ደርበው እንዲገዙ የሾሟቸው ሁለቱ ንጉሦች በተጋጩ ቁጥር እሳቸው እየገላገሉ፣ እያስታረቁና ጥፋተኛውን እየቀጡ፤ በበላይነት ለመቆየት ይረዳቸው ዘንድ ነበር። ከዚህ በተጨማሪ ዐፄ ዮሐንስ ምኒልክንና ተክለ ሃይማኖትን ፉክክር ውስጥ እንዲገቡ የሚያደርጉበት ምክንያት ለስልጣናቸው የሚያሰጓቸው ንጉሥ ምኒልክ ከሳቸው ጋር ሳይሆን በማዕረግ አቻቸው ከሆኑት ከንጉሥ ተክለሃይማኖት ጋር ሲፎካከሩ እንዲኖሩ ነበር።

የራስ ደረሶን ወደ ከፋ መዝመት ተከትሎ ራስ ጎበና ዳጨ ድምጻቸውን አጥፍተው ሊሙ በመከሰት ቀድመዋቸው ከፋ የከረሙት ራስ ደረሶ ከተለያዩ የአካባቢው ገዢዎች ያስገበሩትን ዝባድና የዝሆን ጥርስ ሳይዘጋጁ አደጋ ጥለው በመውጋት አንድ ሳይቀር አራገፈው ወረሱባቸው። ባገራችን ባህል ዘመቻ ሲኖር አዝማሪም አብሮ ይከተላልና ከራስ ደረሶ ጋር ወደ ከፋ አብረው ከዘመቱት የጎጃም አዝማሪዎች መካከል አንዷ ራስ ደረሶ ያስገበሩት የዝሆን ጥርስና ዝባድ በሸዋው በራስ ጎበና መወረሱን በሰማች ጊዜ፤

 

 

እኚህ ጎጃሜዎች በምን ይስቃሉ፣
ጥርሳቸውን ሊሙ ጥለውት ሔዱ አሉ። ብላ ተቀኘች።

የራስ ጎበናን ድርጊት የሰሙት ንጉሥ ተክለ ሃይማኖት ወደ ከፋ ከጉድሩ ተጨማሪ ጦር ልከው ራስ ደረሶን አጠናከሩ። ባገኙት ተጨማሪ ጦር የልብ ልብ የተሰማቸው ጦረኛው ራስ ደረሶ እሳት ጎርሰው እሳት ለብሰው ጥቃት በፈጸሙባቸው ራስ ጎበና ላይ አጸፋ ከመሰንዘራቸው በፊት «አገሬን ለቀህ ውጣ» የሚል ጉልበት የተሰማው የጦር መሪ መልዕክት ወደራስ ጎበና ላኩ።

ከወደ ራስ ጎበና መልስ በመጥፋቱ ራስ ደረሶ ሠራዊታቸውን አስከትለው ወደ ራስ ጎበና ገሰገሱ። ራስ ደረሶ ተጨማሪ ጦር አሰልፎ ወደሳቸው መዝመቱን የሰሙት ብልሁ ራስ ጎበና ውጊያ ቢገጥሙ ስለማሸነፋቸው እርግጠኛ ስላልሆኑ ሰራዊታቸውን ለውጊያ እያዘጋጁ፤ የምኒልክም፣ የተክለ ሃይማኖትም ጌታ በሆኑት በዐፄ ዮሐንስ ስም «በዮሐንስ አምላክ! ተዳኝ!» ብለው ሊሙ የነበሩ የትግሬ ነጋዴዎችን ዋቢ አድርገው ወደ ደራሶ መልክት ላኩ። መልዕክተኞችም በበኩላቸው ጦርነት እንዳይጀመር ሁለቱንም ወገን አንተም ተው፤ አንተም ተው እያዩ የሁለቱ ወንድማማቾች ደም እንዳይፈስ የተቻላቸውን ያህል ጣሩ።

ጉልበቱ ያየለው ራስ ደረሶም «በዮሐንስ አምላክ» ከተባለ በኋላ ቢዋጉ መዘዙ ብዙ መሆኑን ስላወቁ ቂማቸውን ለመወጣት ቢጓጉም ፍላጎታቸውን ገትተው ነገሩን ለአለቃቸው ለንጉሥ ተክለሃይማኖት ለመንገር ወደ ዋና ከተማቸው ወደ ደብረ ማርቆስ ተመለሱ። ራስ ጎበናም በበኩላቸው ለንጉሥ ምኒልክ ደብዳቤ ጻፉ። ራስ ጎበና «በዮሐንስ አምላክ» በማለት ወደ ራስ ደረሶ መልዕክት መላካቸውን የሰማችው የጎጃም አዝምሪ፤

እገዛለሁ ብሎ ከእንጦጦ ገስግሶ፣
በዮሐንስ አምላክ አሰኘው ደረሶ! ብላ ራስ ጎበናን ነቆረቻቸው።

ንጉሥ ምኒልክ አፄ ዮሐንስ ከእሳቸው ይልቅ ለማይቀናቀኗቸው ለንጉሥ ተክለሃይማኖት እንደሚወግኑ ስለሚገምቱ በቅድሚያ ለንጉሠ ነገሥቱ መበደላቸውን በደብዳቤ ጽፈው ላኩ። ተክለሃይማኖትም በበኩላቸው ደብዳቤ ለአፄ ዮሐንስ ልከው ለሠራዊታቸው እንዲከት አዘዙ። ዐፄ ዮሐንስም የሁለቱን ደብዳቤ ባገኙ ጊዜ ምንም እንኳ ተክለ ሃይማኖትን እየረዱ ምኒልክን እንዲወጋላቸውና የዙፋናቸው ተፎካካሪ እንዲዳከሙ ለተክለ ሃይማኖት በሚስጥር ጦር ቢልኩም፤ ለሁለቱም በግልጽ መልስ ሲጽፉ ግን «እንዳትጣሉ» የሚል መልዕክት ይልኩ ነበር።

Image may contain: 1 person

የዮሐንስ ደብዳቤ ምኒልክ እጅ ሲገባ፤ለተክለ ሃይማኖት የተላከው «እንዳትጣሉ» የሚለው ደብዳቤ ግን ራስ ደረሶ በቅድሚያ አንብቦ «እንዳትጣሉ» ስለሚልና ንጉሱም ይህንን ቢያዩ አይዘምቱም ብለው በማሰባቸው ራስ ጎበና እንዳልወጋ ያደርገኛል ያሉትን ዮሐንስ ለተክለ ሃይማኖት የላኩትን ደብዳቤ ቀዳደው ጥለው ለጦርነት ይዘጋጁ ጀመር። በምኒልክ በኩል የዘመቻው እንቅስቃሴ በስፋት ተጀምሯል። የምኒልክ ቤት ሸብረብ ራስ አዳልን ለመውጋት እንደሆነ በጭምጭምታ የሰሙት የምኒልክ ሥራ ቤቶች፤

ሴቶች ተሰብሰቡ እንውቀጥ ዳሂራ፣
ክርክር አይቀርም ከራስ አዳል ጋራ፤
ይታመሳል አሉ ከፋና ቦረና፣
አማን አይደሉም ወይ እነ ራስ ጎበና፤ በማለት ዘፈኑ።

በተክለ ሃይማኖት በኩልም ዝጅግቱ ተጠናቆ የፍልሚያ ሸማ ተልኮ ቀን ተቆርጦ እምባቦ ሜዳ ላይ ጦርነት ሆነ። ሁለቱም ንጉሦች ሠራዊታቸውን አስከትተው ተዋጉ። አንድ ሰዓት ያህል ፍልሚያ ሆኖ ከቆየ በኋላ ተክለ ሃይማኖት ተመተው ወደቁ። የምኒልክ ጦር መሪ ከሆኑት መካከል የጎጃሙ ራስ መንገሻ አቲከም [የጠቅላይ ሚንስትር ልጅ እንዳልካቸው መኮነን አያት]ተመተው የወደቁትን ንጉሥ ተክለ ሃይማኖትን በመያዝ ማርከው ለምኒልክ አስረከቧቸው።

ንጉሥ ተክለሃይማኖት ተመተው መማረካቸውን ምኒልክ እንዳዩዋቸው «ወንድሜ እንኳን ክርስቶስ በሕይወት አገናኘን!» ብለው አቅፈው ሳሟቸውና «እኔ ራሴ ነኝ የማክመው!» በማለት ደማቸውን በእጃቸው እየጠራረጉ ቁስላቸውን ማጠብ ጀመሩ። ጦርነቱትም ያበቃ ዘንድ ምኒልክ «በል ያለፈው አልፏል። አሁን ሠራዊትህን አስተወኝ!” ሲሉ ተክለ ሃይማኖትን ጠየቋቸው። ምርኮኛው ንጉሥ ተክለሃይማኖትም ሠራዊታቸው ውጊያ እንዲያቆም አዘዙ። እነ ራስ ደረሶ ግን «በሕይወት ሳለ የተማረከ ንጉሥ ንጉሤ አይደለም አቁም የሚለኝን ትዕዛት አልቀበልም» በማለት ጦርነቱ ለተጨማሪ አራት ሰዓት እንዲዘልቅ አደረጉ።

Image may contain: 1 person

በመጨረሻው እነ ራስ ጎበና ድል አድርገው ታሪካዊው የእምባቦ ፍጻሜ ሆነ። እነ ራስ ደርሶ ከጎጃም ለፍልሚያ ሲነሱ በነራስ ጎበና ከፋ ላይ የተወረሰባቸውን ዝባድና የዝሆን ጥርስ፤ ከሸዋ ወደ እምባቦ ይዘውት የዘመቱትን ሰንጋም ለምልክት ጀሮውን እየተለተሉ በድል አድራጊነት ወደጎጃም ሲመለሱ እየባረኩ ለድል አድራጊው ሰራዊታቸው እናበላነን በማለት መዛታቸውን የሰማች የሆሮ ጉድሩ ባለ ቅኔ መንገድ ተሳስተው ብዙ የጎጃም ጦር ጮመን በሚባለው ረግረግ እየሰረገ ስለቀረና በመጨረሻም ስለተሸነፈ፤

አመጣለሁ ብሎ ጆሮ ትልትል በሬ፣
ጮመን ገብቶ ሞተ የጎዣም ገበሬ፤ ስትል ተቀኘች።

ብዙ የልተነገረላቸው ራስ ደርሶ ራስ ጎበና ሌቃ ቄለምና ሌቃ ለቀምትን ሳይረግጡ አባይ ተሻግረው ከዴዴሳ ወዲያ ማዶ ያለውን ምዕራብ ወለጋና ከወዴዴሳ ወዲህ ማዶ ያለውን ምስራቅ ወለጋን በዲፕሎማሲና በጦር በማስገበር ከፋ ድረስ ይገዙና ቤተ ክርስቲያን ይተክሉ ነበር። የምስራቅ ወለጋዎቹን ሞቲ ሞሮዳ በከሬንና ወንድሙን፤ እንዲሁም የምዕራብ ወለጋውን ሞቲ ጆቴ ቱሉ በማስስማማት በተክለ ሃይማኖት ስር አድርገው የደጃዝማችነት ማዕረግ የሰጧቸው ራስ ደረሶ ነበሩ።

Image may contain: 1 person, smiling

ከኢምባቦ ጦርነት በኋላ የሞተው ተቀብሮ፤ የቆሰለው ታክሞ እርቅ ወርዶ ሕይወት ወደነበረችበት ተመለሰች። አንድ ምሽት በምርኮኛው ተክለሃይማኖት ማረፊያ ቤት እነ ራስ ደረሶና ሌሎችም የተማረኩት የጎጃም መኳንንት በተገኙበት ምኒልክ ግብር ጥለው እየተበላና እየተጠጣ፤ ደስታና ጨዋታው በደራበት ጊዜ፤ ስለ እምባቦ ጦርነት ተነስቶ፤ ንጉሥ ምኒልክ ጎጃሞች በጦርነቱ ላይ የፈፀሙትን ጀግንነት በአድናቆት ተናግረው፤ ስለ ጀግንነታቸው አመሠገኑዋቸውና አንድ ጥያቄ ጠየቋቸው። ጥያቄ እንዲህ የሚል ነበር፤
«እንደው ያለፈው አልፏል፤ እስቲ እውነቱን ንገሩኝ ለመሆኑ እናንተ አሸንፋችሁ እኔ ተማርኬ ቢሆን ኖሮ፤ ምን ታደርጉኝ ነበር?” አሉና ጠየቁ።

የነራስ ደረሶ መልስም. . . «ጌቶች የእውነት ተናገሩ ካሉንማ፤ እኛ ድል አድርገን አርስዎን ማርከን ቢሆን ኖሮ፤ ቆራርጠን የአሞራ ራት ነበር የምናደርግዎት» የሚል ነበር። ንጉሥ ምኒልክ ጥያቄያቸውን ቀጠል አድርገው፤ «ታድያ ከእናንተ ጭካኔ እና ከእኔ ርህራሄ የትኛው ይሻላል?» ሲሏቸው እነራስ ደርሶም «ሲዋጉ ጭካኔ፤ ድል ካደረጉ በኋላ ግን ርህራሄ መልካም ነው» ብለው መለሱላቸው። ምኒልክ መልሳቸውን ሰምተው፤ እውነቱን በመናገራቸውም ተደስተው «ከአሁን በኋላ የጎጃሜ እስረኛ የለኝም። ቤቴ ቤቱ፣ አገሬም አገሩ ነው» ብለው አዋጅ አስነገሩ።

እንዲህ አይነቱን አብሮ የመኖር ጥበብ ነው እንግዲህ ሀኒሻ ሰለሞን «ብል እየበላው ነው፤ ወገኔ ተነስ» የምትለው። አንዳንዴም በስምምነት፤ አልሆን ሲል ደግሞ በጦር አንድ አይነት ራዕይ የነበራቸው ታላላቆቹ አያቶቻችን ፈርሳ የነበረችውን ታሪካዊ አገር እንደገና አንድ ካደረጉ በኋላ ፊታቸውን የጋራ ተቋማትን ወደመፍጠር አዞሩ። ከደቡብም ሆነ ከሰሜን የተነሱቱ አያቶቻችን የነበራቸው ራዕይ አንድ ታላቅና ጠንካራ አገር መገንባት ስነበረር አንዱ አንደኛውን አስገብሮ ከጠቀለለ በኋላ ሕይወት ወደነበረበት ተመልሶ በጋራ ራዕያቸው አገር ገምደው፤ ወራሪ በተነሳ ቁጥርም ቀፎው እንደተነካ ንብ ባንድ ላይ ሆ ብለው እየተነሱ ተዋደውና ተስማማተው አንድ ሆነው በፍቅር ኖረዋል።

አያቶቻችን ለፍልሚያ የሚዘምቱት በጥላቻ አልነበረም፤ ሁሉም የነበራቸውን ትልቅ አገር የመገንባት የጋራ ራዕይ ይዘው አንዱ አንዱን ለመጠቅለል እንጂ። አንዱ አንዱን ከጠቀለለ በኋላ የጋራ ሕይወትና አብሮነት በፈሪሃ እግዚያብሔርና በሕሊና ዳኝነት ይቀጥል ነበር። ዛሬ እውቀት ከንቱ ሆነ፤ በደምና ባጥንት የተሰራው ያያቶቻችን ታሪክ ተደምስሶ በጥላቻ ባበዱ ጥራዝ ነጠቆች የፈጠራ ታሪክ ተተካ፤ በተመረዘ ጭንቅላት፣ በደነዘዘ አእምሮ፣ በመሳይ ውሸትና በመከነ ርዕዮተ አለም እውር ድንብራችንን እየሄድን በጎሳ አጥር እየተተራመስን በመከሳከስ ሞትንና ስደትን እያነገስን፤ ለገዢዎቻችን ሕይወት እየገበርን እንገኛለን።

ዛሬ ላይ ሀኒሻ ሰለሞን «አራቱ ጉባኤ» ስትል የጠራቻቸው የዘመናዊቷ ኢትዮጵያ Founding Fathers አይነት ሰፊ አስተሳሰብ ያለው ልጅ ስለጠፋ ችግር ገጠመን። ብልሆቹ አያቶቻችን ወደፊት እያዩ የፈጠሯት ሰፊ አገር በክብር እንዳላስረከቡን የልጅ ልጆቻቸው በምስራቃውያን የባዕድ አስተምህሮ ተጠምቀው አፍ ነጠቅ በመሆን ወደኋላ እያዩ በጎሳና በመንደር ከፋፈሉን።

የተለፋባት አገራችን በባዕዳን አስተሳሰብ ስትፈርስ ዝም ብለን እንዳናይ ገና ጥንት የሚጣላ ሕሊያ ያላቸው አርቆ አሳቢዎች፤
መሬት እግር አለው ይሄዳል እንደሰው ፣
ጀግና ልጅ ተወልዶ እዚያው ካልመለሰው፤ ያሉት ደርሶ በታሪካችን አይተናል።

አንድ ሆነን በሕብረት ለጋራ አላማ አለመቆማችን እንቅልፍ የነሳት የዘመናችን ድምጽ ሀኒሻ ሰለሞንም በዚያ ዘመን «ጀግና ልጅ ተወልዶ እዚያው ካልመለሰው» የተባለውን፤

ትሄዳለች እንደሰው ሃገር እግር አላት፣
ባንድነት በመሆን ሳትርቅ እንመልሳት፤ ስትል ሁላችንንም ትጠይቃለች።

እኔም እንደ አንድ የትውልድ አካል ምትክ የማይገኝላቸው አያቶቻችን የለፋባት ኢትዮጵያ ዳግም ትነሳ ዘንድና ያምርብንና ሕብረታችን ይጸና ዘንድ በምኞትና በተስፋ ከሀንሻ ሰለሞን ጋር እቆማለሁ። እኔም ልክ እንደ እንደ ሀኒሻ ሰለሞን፤

ዳግም ይመርብን፣ ኅብረታችን ይጽና፣
ለእማማ ኢትዮጵያ፣ምትክ የለምና፤
አንድ ሆነን በሕብረት፣ ካልቆምን በጋራ፣
እናት አገራችን፣ አትታይም አምራ፣
የተፈጠርንብሽ ማተብ፣ውል፣ክራችን፣
ዘላለም ኑሪልን፣ እናት ሀገራችን፣
ዘላለም ኑሪልን ውቢቷ አገራችን፤ በማለት ድምጼን ከፍ አድርጌ እዘምራለሁ።

Image may contain: 1 person

ትልቅ አገር ለመስራት ጥቂቶችም ቢሆኑ ጠንካሮች እስከሆኑ ድረስ ካምዕሯቸው ጥንካሬ የሚፈልቀው አስተሳሰባቸው የትውልድ ሁሉ ብርሃን ሊሆን እንደሚችል እናት አይዋጁ የምትባል የቡልጋ አዝማሪ፤

ጎበና ጎበና ጎበና ፈረሱን አማን ቢያስነሳው፣
ዓባይ ላይ ገታው፤
ጎበና ፈረሱን ፋሌ ላይ ቢያስነሳው፣
አረብ አገር ገታው፣
ጎበና ፈረሱን ቼቼ ቢለው፣
ሱዳን ላይ ገታው፤
የመዳኒት ጥቂት ይበቃል እያለች፣
እጅጋየሁ ኃይሉ አንድ ወልዳ መከነች፤ ስትል ስለሆነ እውነት ተቀኝታ ነበር። እናት አይዋጁ እውነት አላት። ሀኒሻ «አራቱ ጎባኤ» ያለቻቸውና እነ ዳግማዊ ምኒልክ ጥቂቶቹ የሰሩት ታሪክ ከኛ አልፎ ለጥቁሩ አለም ሁሉ መነቃነቂያ ርዕዮት ወልዷል። እነራስ ደረሶ፣ ራስ መኮነንና ራስ አሉላ አድዋ የዘመተው የኢትዮጵያ ጦር አዝማቾች ነበሩ። ኢንባቦ ላይ ከነራስ መኮነን ጋር እስከመጨረሻው ሰዓት ድረስ ላለመጠቅለል የተዋጉት ራስ ደረሶ ከተጠቀለሉ በኋላ አድዋ ላይ ከራስ መኮነን ጋር ለኢትዮጵያ ባንድነት ተሰልፈው አሸንፈዋል። ታላላቆቹ ኢትዮጵያውያን እንዲህ ነበሩ። [በነገራችን ላይ ከፍ ሲል ስማቸው የተጠሰሱት እጅጋየሁ ኃይሉ የዳግማዊ ምኒልክ እናት ናቸው።]

ስለዚህ ጥቂቶችም ቢሆኑ እውነተኞችና ላላማቸው ሟች እስከሆኑ ድረስ የክፋት ሁሉ ምንጭ የሆነውን የፋሽስት ወያኔና ያጋሮቹን አስተሳሰብ መብለጥና ማሸነፍ ይቻላቸዋል። የሀኒሻ ሰለሞን አይነት ታላላቅ ሀሳብ የሚያቀነቅኑ ኢትዮጵያውያትንና ኢትዮጵያውያንን ያብዛልን! ረጅም እድሜና ጤና ለውዷ እህታችን ለሀኒሻ ሰለሞን ይሁን!

– አቻምየለህ ታምሩ

Share and Enjoy !

0Shares
0
0Shares
0
Read previous post:
የሀገራችን አራት ዓይነት ሰዎች

የኦሪት ዘፍጥረት መጽሐፍ ሰው በእግዚአብሔር አምሳል እንደተፈጠረ ይናገራል፡፡ የነገረ ሃይማኖት መምህራን ደግሞ ሰው “አእምሮ፣ ለብዎ”...

Close