የኢትዮጵያ አገራዊ ንቅናቄ የተወካዮች ምክር ቤት ከኦክቶበር 20 እስከ ፟22 በአሜሪካን አገር በሚገኘው ሰፕሪንግፊልድ ቬርጂኒያ ግዛት ውስጥ ተገናኝቶ በኢትዮጵያ የወቅቱን ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ሁኔታዎች እንዲሁም አገራችን አሁን የገጠማትን የፀጥታ ጉዳዮች በሚመለከት ሰፋ ያለ ውይይት አካሂዶአል። ከዚህም በተጨማሪ አገራዊ ንቅናቄው ከተመሠረተበት ጊዜ ጀምሮ ላለፈው አንድ ዓመት የተጓዘበትን የሥራ አፈጻጸም በዝርዝር ገመግሟል።

በግምገማውም መሠረት አሁን አገራችን ኢትዮጵያ ያለችበት ጠቅላላ የፖለቲካ፡ የኢኮኖሚ፡ ማህበራዊና የፀጥታ ሁኔታ እጅግ አስጊና አሳሳቢ ደረጃ ላይ የደረሰ መሆኑን ተገንዝቧል። በዚህም መሠረት ይህ አስጊ ሁኔታ ከቁጥጥር ውጪ ከመውጣቱ በፊት ንቅናቄያችን ያለውን ኃይል፣ ዕውቀቱትና ጉልበት ሙሉ በሙሉ በማንቀሳቀስ አገራችን የተደቀነባትን አደጋ የመቀልበስ ሥራ በአስቸኳይ መስራት እንዳለበት ግንዛቤ ላይ ተደርሷል።

ባለፈው የአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ የኢትዮጵያ አገራዊ ንቅናቄ ትግሉ የሚጠይቀውን ድርጅታዊ ብቃት በማጠናከር ላይ ትኩረት ስጥቶ ሲሠራ የቆየ ሲሆን ይህን የአቅም ግንባታንና ድርጅታዊ ብቃትን ባገር ውስጥና በውጭ መዋቅራዊ አሠራርን የመገንባት ሥራውን አሁን በሚገባ አጠናቋል። በመሆኑም በኦሮሚያ በአማራና በሌሎችም ክልሎች ውስጥ እየተፋፋመና ከዕለት ዕለት የሕወሐትን ሥርዓት መውጫ መግቢያ በማሳጣት የሚያስጨንቀው ህዝባዊ አመጽ ከተነሳለት ግብ እንዲደርስና የኢትዮጵያ ህዝብ ለዘመናት የታገለለት ፍትህ የሰፈነባት ዲሞክራሲያዊት አገር የመገንባት አላማ ባጭር ጊዜ ውስጥ እንዲሳካ በትግሉ ውስጥ በቀጥታ ለመሳተፍ፣ ለማስተባበርና ለመምራት ዝግጁነቱን ያረጋግጣል።

የኢትዮጵያ አገራዊ ንቅናቄ በዚህ የሶስት ቀናት ስብሰባዉ የተለያዩ ዋናና መሠረታዊ የሆኑ ጉዳዮችን አንስቶ በዝርዝር የተነጋገረ ሲሆን እስከ ዛሬ ድረስ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ውይይት ውስጥ እንደከፋፋይና ከስምምነት ላይ ለመድረስ አስቸጋሪ ናቸው የተባሉትን የተለያዩ ጉዳዮችን ሣይቀሩ አንስቶ በግልፅነትና ምንም መደባበቅና መፈራራት በሌለበት መንፈስ በመወያየት ከስምምነት ላይ መድረስ ችሏል። ይህ በአገራችን የፖለቲካ ዕውነታ ውስጥ ለረዥም ዓመታት ጠፍሮ ያሠረን በቁልፍ ጉዳዮች ላይ በግልፅነትና ተነጋግሮ ከስምምነት ላይ መድረስ ያለመቻል መሰናክል የንቅናቄው አባል ድርጅቶች አገሪቱን ከተጋረጠባት አደጋ ለማዳን ካላቸው የፀና እምነት የመነጨና በሂደትም ሁሉን ዜጎች በእኩልነት የምታይ አገር መገንባት ይቻላል ከሚል ቀና አመለካከትና ሃላፊነትን ከመቀበል ስሜት የመነጨ ነው። ስለሆነም በገዛ አገሩ ላይ ነፃነት፣ ሰላም፣ ዕድገት፣ ፣ የተሟላ የዲሞክራሲ መብት፣ ፍትህና እኩልነት እንዲኖረዉ በመታገል ላይ ለሚገኘዉ የኢትዮጵያ ሕዝብ የአትዮጵያ አገራዊ ንቅናቄ በሚቻለዉ መንገድ ሁሉ ከጎኑ ለመቆም መወሰኑን ልናረጋግጥለት እንወዳለን፡፡

Related stories   ዝሆን ላይ የሚጮህ እብድ ውሻ ብቻ ነው

በሕወሐት የግፍና የጭቆና ሥርዓት ውስጥ ያላችሁ የአገር መከላከያ፣ የፖሊስና የደህንነት አባላትም አስተምራና ባለ አቅሟ ተንከባክባ ያሳደገቻችሁ አገራችሁ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ እንደምትፈልጋችሁ ትገነዘባላችሁ ብለን እናምናለን፡፡ በየተሰማራችሁበት መስክ የተቀበላችሁት ኃላፊነትም የተወለዳችሁበትንና ያደጋችሁበትን ማህበረሰብ የመጠበቅና መብታቸውም እንዲከበር የማድረግ መሆኑን እንደምትገነዘቡ አንጠራጠርም፡፡ በመሆኑም ይህ የግፍ ሥርዓት ከሥር መሠረቱ እንዲገረሰስ ለማድረግ ይቻል ዘንድ በህዝብ ደምና ሃብት የሰከሩ ጥቂት መሪ ነን ባዮች የሚሰጡዋችሁን የግድያና የአፈና ትዕዛዝ ወደ ጎን ትታችሁ ከተጨቆነውና ለነፃነቱ እየታገለ ከሚገኘዉ ወገናችሁ ጋር እንድትቆሙ፤ ይህን ከሕዝብ ጎን የመሰለፍ ታሪካዊ እርምጃ በመዉሰድም ሕወሐት መራሹ የመከራ ዘመን ያበቃ ዘንድ የድርሻችሁን እንድታበረክቱ የኢትዮጵያ አገራዊ ንቅናቄ አበክሮ ያስገነዘባችኋል፡፡

ከዚህ በመነሣት ሕወሐት ላለፉት 26 ዓመታት አገራችን ውስጥ ያሰፈነው አፈና፡ ጭቆናና የሕዝብ ሃብት ብዝበዛ ያስመረረው ህዝባችን ምድር ላይ እያካሄደ ያለው የተናጠል ትግል በቂ አመራር እንዲያገኝ እና የጭቆና አገዛዝ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እንዲያበቃ ለማድረግ የኢትዮጵያ አገራዊ ንቅናቄ ያለዉን ዕውቀት፡ ገንዘብና የሰው ኃይል በማቀናጀት በአስቸኳይ ለመንቀሳቀስ መወሰኑን ደግመን እያረጋገጥን የኢትዮጵያ ጉዳይ ያገባናል የሚሉ የዲሞክራሲ ኃይሎች ሁሉ ከንቅናቄያችን ጎን ተሰልፈው ለትግላችን በድል መጠናቀቅ አቅማቸው የፈቀደውን አስተዋፅኦ እንዲያበረክቱ እና ይህን ከውስጡ መፈረካከስ የጀመረ ሥርዓት ከሥር መሠረቱ ለመገርሰስ ተባብረው እንዲሠሩ የኢትዮጵያ አገራዊ ንቅናቄ ወገናዊ ጥሪውን ያቀርባል።
ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *