የኢትዮጵያ ፓስፖርት ከአፍሪካ የመጨረሻዎቹ አምስት ሀገራት ውስጥ ተመደበ

(ኢሳት ዜና–ጥቅምት 15/2010)የኢትዮጵያ ፓስፖርት ከአፍሪካ የመጨረሻዎቹ አምስት ውስጥ ሲመደብ ከአለም ደግሞ 185ኛ በመሆን ዝቅተኛ ደረጃ ላይ መገኘቱን ፓስፖርት ኢንዴክስ ይፋ ያደረገው አዲስ ሪፖርት አስታወቀ።

የሀገራትን የጉዞ ሰነድ ወይንም ፓስፖርት ጥንካሬ የሚገመግመው ፓስፖርት ኢንዴክስ ይፋ ባደረገው በዚህ አዲስ ጥናት ከአለም ሲንጋፖር ቀዳሚ ሆና ስታልፍ ከአፍሪካ ሲሸልስ የመሪነቱን ቦታ ይዛለች።

የየሀገራቱን ፓስፖርት በመያዝ ያለቪዛና አየር ማረፊያ ሲደርሱ በሚመታ ቪዛ በአለም ላይ ወደ 159 ሀገራት በነጻነት በመንቀሳቀስ የሲንጋፖር ፓስፖርት ቀዳሚ ሆኖ ተመዝግቧል። በጀርመን ፓስፖርት 158 ሀገራት በሲውዲንና ደቡብ ኮሪያ ፓስፖርት 157 ሀገራት በመጓዝ ተጠቃሾቹ ሀገራት ከአለም ግንባር ቀደም ሆነው ተገኝተዋል።

በብሪታኒያ፣ፈረንሳይ፣ጣሊያንና ጃፓን ፓስፖርቶች በ156 ሀገራት በነጻነት መንቀሳቀስ የሚቻል ሲሆን የአውስትራሊያ፣ስዊዘርላንድ፣የቤልጂየምና የኔዘርላንድ ፓስፖርት ወደ 155 ሀገራት በማስጓዝ በ5ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል፡፡ የአሜሪካና የካናዳ ፓስፖርቶች 154 ሀገራትን በነጻነት የሚያንቀሳቅሱ በመሆናቸው የ6ኛ ደረጃን ይዘዋል።

ከአፍሪካ ግንባር ቀደም በሆነችውና ከአለም በ29ኛ ደረጃ ላይ ባለችው ሲሸልስ ፓስፖርት 130 ሀገራት በነጻነት መንቀሳቀስ የሚቻል ሲሆን ከአፍሪካ 2ኛና 3ኛ በሆኑት ሞሮሺየስና ደቡብ አፍሪካ ፓስፖርት 124ና 93 ሀገራትን በነጻነት መንቀሳቀስ የሚያስችል መሆኑን ከፓስፖርት ኢንዴክስ የ2017 አዲስ ሪፖርት መረዳት ተችሏል።

ጎረቤት ሀገር ኬንያ ከአለም በ120ኛ ደረጃ ከአፍሪካ ደግሞ 8ኛ ስትሆን በኬንያ ፓስፖርት 68 ሀገራትን መጓዝ የሚቻል መሆኑንም አመልክቷል።

ኢትዮጵያ ከአፍሪካ 51ኛ ከአለም ደግሞ 185ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች።

በኢትዮጵያ ፓስፖርት 39 ሀገራት መጓዝ ሲቻል ከኢትዮጵያ አንድ ደረጃ ከፍ ብሎ በምትገኘው ኤርትራ ፓስፖርት 39 ሀገራት መጎብኘት ይቻላል።

ኤርትራ ከኢትዮጵያ በአንድ ደረጃ ከፍ ያለችው የኤርትራ ፓስፖርት በቀጥታ ያለምንም ቪዛ የሚገባባቸው ሀገራት 10 ሲሆኑ የኢትዮጵያ 9 ናቸው።

በአፍሪካ ውስጥ ከኢትዮጵያ በታች የተቀመጡት ሶስት ሀገራት ብቻ ሲሆኑ እነርሱም ሊቢያ፣ ሱዳንና ሶማሊያ ናቸው።

Related stories   ሰበር ዜና – ትህነግ በዲፕሎማሲ ዘመቻ ቀውስ ገጠመው፤ “ በሃሰት መረጃ አሳፈራችሁን ” የቅርብ አጋሮቻቸው

በሊቢያ ፓስፖርት 38 ሀገራትን፣በሱዳን 36 እንዲሁም በሶማሊያ ፓስፖርት ደግሞ 34 ሀገራትን ያለ ቪዛ መጎብኘት ይቻላል።

በአለም ላይ የመጨረሻ ሆና በተመዘገበችው አፍጋኒስታን ፓስፖርት 24 ሀገራት ያለቪዛ መጎብኘት እንደሚቻል ከፓስፖርት ኢንዴክስ አመታዊ ሪፖርት መረዳት ተችሏል።

የአል ሲሲ የፈረንሳይ ጉብኝት እና ተቃውሞው

ፈረንሳይን በመጎብኘት ላይ ያሉት የግብጽ ፕሬዝዳንት አብዱል ፈታህ አል ሲሲ አምነስቲ ኢንተርናሽናልንን እና ሂዩመን ራይትስ ዋች ከመሳሰሉ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ቡድኖች ከፍተኛ ተቃውሞ ገጥሟቸዋል። እነዚህ የመብት ተሟጋች ተቋማት የአል ሲሲ መንግሥት ጋዜጠኞችን፣የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾችን እንዲሁም ግለሰቦችን ከማሰር ባለፈ ቁም ስቅል ይፈጽምባቸዋል ሲሉ ይወቅሳሉ። የፈረንሳይ መንግሥትም ከአልሲሲ ጋር ምንም ዓይነት ኤኮኖሚያዊም ሆነ ወታደራዊ ስምምነት እንዳያደርግም ጠይቀዋል። የፈረንሳይ ፕሬዝዳንት ኤማኑዌል ማክሮም ግብጽ ለራስዋ ስትል ሰብዓዊ መብቶችን እንድትጠብቅ ጠይቀዋል። አል ሲሲ ግን ከመብት ተሟጋቾች የሚቀርቡባቸውን ክሶች አስተባብለዋል።

የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር የመንግስት ቃል አቀባይን ተቹ

(ኢሳት ዜና–ጥቅምት 15/2010)የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር የመንግስት ቃል አቀባዩን ተቹ::

ቃል አቀባዩ ነገሬ ሌንጮ በተሳሳተ መልኩ መረጃ ያቀረቡ የመገናኛ ብዙሃንን ላይ ህግን መሰረት በማድረግ እርምጃ ይወሰዳል በማለት የሰጡትንም መግለጫ የግላቸውን እንጂ የመንግስት አቋም አይደለም ሲሉ አጣጥለውታል።

ዋና ዳይሬክተሩ አቶ ዘርአይ ጨምረውም በብሮድካስት ሚዲያው ላይ የሚታይ አደገኛ አዝማማሚያ መኖሩንም ጠቁመዋል።

የህወሃት ነባር ታጋይና የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ዘርአይ አስገዶም በብሮድካስት ሚዲያው ላይ የሚታይ አደገኛ አዝማማሚያ መኖሩን ለኢትዮጵያ ቴሌቪዥን በሰጡት መግለጫ አረጋግጠዋል።

እንደ እሳቸው አባባል በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች እየታዩ ያሉትን ግጭቶች የመገናኛ ብዙሃኑ የሚዘግቡበት መንገድ ትክክል ያልሆኑና የበለጠ ግጭትን የሚፈጥሩ ናቸው። የመገናኛ ብዙሃኑ ጠንካራ አለመሆናቸውና አዘጋገባቸውም የተሳሳተ መሆኑ ለማህበራዊ ሚዲያው እንዲጋለጡ አድርጓቸዋል ሲሉም ያክላሉ። አሁን ላይ ከግሉም ሆነ ከሕዝብ መገናኛ ብዙሃን የሚታዩ ያሉ አደገኛ አዝማሚያዎች መኖራቸውንም በግልጽ አስቀምጠዋል።

Related stories   ደመቀ መኮንን በፊንላንድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ከሚመራ የአውሮፓ ህብረት ልዑክ ጋር ተወያዩ

ዶክተር ነገሬ ሌንጮ ለኢትዮጵያ ቴሌቪዥን በመገናኛ ብዙሃኑ ላይ ህግን መሰረት በማድረግ እርምጃ ይወሰዳል በማለት የሰጡትንም መግለጫ የግላቸውን እንጂ የመንግስት አቋም አይደለም ሲሉ አቶ ዘርአይ አጣጥለውታል። የሰጡት መግለጫም የግል አስተያየታቸው እንጂ የመንግስት አቋም እንዳልሆነ አረጋግጠዋል።

አቶ ዘርአይ እንደሚሉት ከሆነ የሚዲያ ተቋማት ላይ ርምጃ መውሰድ የሚችለው የብሮድካስት ባለስልጣንና ፍርድ ቤት እንጂ የመንግስት ቃል አቀባይ ጽሕፈት ቤት እንዳልሆነም ተናግረዋል። በሕወሃት ባለስልጣናት ዘንድ አንዱ የተናገረውን አንዱ የመሻርና የማጥላላት ሂደት ከበፊቱ በበለጠ መልኩ እይተባባሰ መምጣቱን በተለያየ ጊዜ የሚገልጹት ታዛቢዎች የአሁኑ የአቶ ዘርአይ አስገዶም አስተያየትም የዚሁ ነጸብራቅ ነው ብለዋል።

የኬንያ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ነገ የሚካሔደው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ይራዘም የሚል አቤቱታ እንደማያዳምጥ አስታወቀ። ፍርድ ቤቱ ጉዳዩን አልመለከትም ያለው በኮረም አለመሟላት ምክንያት መሆኑን ገልጧል።

የፍርድ ቤቱ ፕሬዝዳንት ዴቪድ ማራጋ በመጨረሻ ሰዓት የቀረበውን የምርጫ ይራዘም ጥያቄ ለመመልከት የታደሙት እርሳቸው እና አንድ ሌላ ባልደረባቸው ብቻ መሆናቸውን ተናግረዋል። ምርጫው ይራዘም የሚለውን ክርክር ለማዳመጥ ቢያንስ አምስት ዳኞች ያስፈልጉ ነበር። “የምርጫ አስፈጻሚዎች የድምፅ አሰጣጡ ነፃ፣ፍትኃዊ እና ተዓማኒ ለመሆኑ ማረጋገጥ አንችልም ብለዋል” በሚል መከራከሪያ ቀኑ እንዲገፋ የጠየቁት ሶስት ኬንያውያን ነበሩ። የምርጫው ተቃዋሚዎች እና ደጋፊዎች በየፊናቸው ድምፃቸውን እያሰሙ ሲሆን አገሪቱ ኹከት ሊቀሰቀስባት ይችላል የሚል ሥጋት አጥልቶባታል።

ከከፍተኛ ፍርድ ቤቱ ደጃፍ ሰላማዊ ሰልፍ ያደረጉ እንስቶች “ሰላም እንሻለን” ሲሉ ተደምጠዋል። “እዚህ የመጣንው ሰላምን ስለምንሻ ነው። ምርጫ እንደሌለ እንዲነገረን አንፈልግም። እስኪበቃን ተሰቃይተናል። አሁን የምንፈልገው ሰላም ነው።”የፍርድ ቤቱ ውሳኔ ከተሰማ በኋላ የራይላ ኦዲንጋ ጠንካራ ይዞታ በሆነችው ኪሱሙ ተቃዋሚዎች በአውራ ጎዳናዎች ላይ እሳት በማቀጣጠል ደስተኛ አለመሆናቸውን ገልጠዋል። የኪሱሙ አስተዳዳሪ አንያንግ ንዮንግ እንደሚሉት ምርጫው የሚካሔድ ከሆነ ዜጎች በመንግሥት ላይ ያምፃሉ። የራይላ ኦዲንጋ ደጋፊዎችም ነገ የሚካሔድ ምርጫ አይኖርም እያሉ ነው።

Related stories   አስከሬን እንዲለቀም ታዘዘ - ትህነግ የአጽም ፖለትካ ድራማ ይፋ ሆነ

“የድምፅ መስጫ ወረቀቶች እዚህ ኪሱሙ መድረሳቸውን ሰምተናል። ነገር ግን እንደ ኦዲንጋ ሁሉ በኬንያ የሚደረግ ምርጫ አይኖርም ብለን በተደጋጋሚ ተናግረናል። በየትኛውም መንገድ አንሸማቀቅም። የምርጫ ወረቀቶቹ ሥራ ላይ እንዳይውሉ እናደርጋለን። በኪሱሙ የሚደረግ ምንም አይነት ምርጫ አንቀበልም።”ራይላ ኦዲንጋ ነፃ እና ፍትኃዊ አይሆንም ባሉት የነገው ምርጫ ደጋፊዎቻቸው ድምፅ እንዳይሰጡ ጥሪ አስተላልፈዋል። “ነገ ለፍትኃዊ ምርጫ ትግል እንጀምራለን” ያሉት ኦዲንጋ በድምፅ አሰጣጡ መሳተፍ ለአምባገነን ሥርዓት እጅ መስጠት ነው ሲሉም አክለዋል።

የቻይና ኮምኒስት ፓርቲ ፕሬዝዳንት ሺ ዢንፒንግን ለሚቀጥሉት አምስት አመታት መሪው አድርጎ መረጠ። ከማዖ ዜዶንግ በኋላ ተፅዕኖ ፈጣሪ ሆነዋል የተባለላቸው ሺ ዢንፒንግ ማን እንደሚተካቸው የታወቀ ነገር የለም። ሺ ዢንፒንግ በቻይና መዲና በታላቁ የሕዝቦች የመሰብሰቢያ አዳራሽ ስድስት አባላት ያሉትን የፖሊት ቢሮ ቋሚ ኮሚቴ ይፋ አድርገዋል። ሁሉም ወንዶች ሲሆኑ እድሜያቸው በስልሳዎቹ ውስጥ የሚገኝ ናቸው። ከቀድሞው አመራር በያዙት ሥልጣን የቀጠሉት ፕሬዝዳንቱ እና ጠቅላይ ምኒስትር ሊ ኬኪያንግ ብቻ ናቸው።

አዳዲሶቹ አመራሮች የሺ አጋሮች እና የፓርቲው የቀድሞ ባለሥልጣናት ታማኞች ናቸው ሲል ሮይተርስ ዘግቧል። የኮምኒስት ፓርቲው በቻይና ማኅበረሰብ ውስጥ ያለውን ሚና ለማሳደግ የወጠኑት ፕሬዝዳንቱ ማን እንደሚተካቸው በይፋ ያሉት ነገር የለም። “የጋራ ርዕይ ያለው እና ለሁሉም የሰው ልጆች ሰላም እና ብልፅግና ታላቅ አስተዋፅዖ የሚያበረክት ዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ ለመገንባት ከአጋሮቻችን ጋር እንሰራለን።”አዲሱ የቻይና አመራር ማሻቀብ ጀምሯል ለሚባልለት ዕዳ ልጓም ማበጀት፤ ከአሜሪካ እና አውሮጳ ጋር ቻይና የገባችበትን የንግድ ውጥረት ማስተዳደር እና በሰሜን ኮሪያ የኑክሌር መሳሪያ ግንባታ መርኃ-ግብር ሳቢያ ሊቀሰቀስ የሚችል ጦርነትን የመከላከል ፈተና ይጠብቀዋል። ሺ ዢንፒንግ እንደ ማዖ ሴቱንግ ሁሉ ስማቸው እና የሚከተሉት የፖለቲካ ፍልስፍና በፓርቲው ህገ-መንግሥት ውስጥ እንዲካተት ተወስኗል።

Share and Enjoy !

Shares

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *