“Our true nationality is mankind.”H.G.

የተዘነጉ ወይስ የተጠሉ መፍትሄዎች? – የግለሰብ መብት፣ ነፃ ገበያ እና የህግ የበላይነት!

• ትክክለኛም ሆነ የተሳሳተ መርህ፣… ስልጡን ሃሳብም ሆነ ኋላቀር የዘረኝነት ሃሳብ…
•“በተመጠነ ኮታ፣ በተመረጠ ቦታና ጊዜ፣… በልዩ ጉዳይና ሁኔታ ላይ ብቻ!” የሚል ማስጠንቀቂያ ተለጥፎለት በጠርሙስ ታሽጎ፣… የተቆለፈ ሳጥን ውስጥ ሊቀመጥ አይችልም።
• በተመጠነ ሁኔታ የሰውን ንብረት አለማክበር፣ በተመጠነ ሁኔታ ዘረኝነትን መስበክ፣ በተመጠነ ሁኔታ ፍትህን መጥላት ብሎ ነገር የለም። ተመጥኖ አይዘልቅምና።

የዋጋ ቁጥጥር ቢሮክራቶች፣ የምርትና የንግድ ተቋማትን ለማሸግ ይዘምታሉ። ውጤቱስ? የገበያ ግርግጥና የሸቀጥ እጥረትን ማባባስ፣… የንብረት ባለቤትነት መብትን ይበልጥ መሸርሸር፣… የደበዘዘውን የፍትህ ትርጉም ጨርሶ ለማጥፋት መቃረብ፣… ሰውን ይበልጥ እያዋረደ ወደ መስዋዕት እንስሳነት የሚያስጠጋ የዘፈቀደ ህግ የለሽ ስልጣንን ወይም የሰፈር ጉልበኞችን እንደአሸኝ የሚፈለፈሉበት ትርምስና ስርዓት አልበኝነት ማስፋፋት!… ከዚህ ከዚህ ጥፋት በስተቀር፣ ሌላ ጠብ የሚል ቅንጣት ጥቅም የለውም – የዋጋ ቁጥጥር ዘመቻ።
አለማወቅ ነው? እንዴት አለማወቅ ሊሆን ይችላል? የዋጋ ቁጥጥር አጥፊነትኮ፣ በተደጋጋሚ በየቦታው በግል የታየ እውነት ነው።
ቢያንስ ቢያንስ፣ የዋጋ ቁጥጥር፣… በተፈጥሮው የነፃ ገበያ ስርዓት በእንጭጩ ተቀጭቶ እንዲቀርና እንዳይስፋፋ የሚገታ መሆኑ… አይታወቅም? ይታወቃል። እና ታዲያ ምንድነው ሚስጥሩ?
እንዲያው፤ ሌላው ቢቀር፣ “ዋነኛ የኑሮና የኢኮኖሚ መግባቢያ” ሊሆን የሚችለውን የነፃ ገበያ ስርዓትን፣ ገና ከጅምሩ መልሶ ለመቅበር ዘመቻዎችን እየፈጠሩ መረባረብ ምን ይባላል?
እንዴ?… ያለ ነፃ ገበያኮ፣ ሌላ ምንም የኢኮኖሚ መግባቢያ ነገር የለም። ነፃ ገበያን ከማስፋፋት ይልቅ፣ ጨርሶ ለምልክት እንኳ እስኪጠፋ ወይም ትርጉም እስኪያጣ ድረስ ለመሸርሸር መሯሯጥ… መዘዙ ብዙ እንደሆነ ከምር ለመገንዘብ፣ እስካሁን ያየናቸው ቀውሶችና ጥፋቶች አይበቁም? ሙሉ ለሙሉ መንኮታኮት ወይም መተራመስ ያስፈልጋል?
ለነገሩማ፣ አሁን አሁን እየተረሳ፣ እየተተወ፣ ወይም እየተጠላ መጣ እንጂ፣… ገዢው እና ተቃዋሚ ፓርቲዎች፣… ፖለቲከኞችና ምሁራን፣… አዘውትረው ባይሆንም አልፎአልፎ፣ በብዛት ባይሆንም አንዳንዶቹ፣… “የግለሰብ ነፃነት”፣ “የንብረት ባለቤትነት የተከበረበት ነፃ ገበያ”፣ “በህግ የበላይነት የሰፈነበት ፍትህ”… የሚሉ ሃሳቦችን የሚሰነዝሩበት ጊዜ ነበር። ይህም በኢህአዴግ ላይ ደህና ተፅእኖ የነበረው ይመስላል። በ1993 እና በ1994 ዓ.ም ያሳተማቸውን ሰነዶች ማየት ይቻላል።
በኢህአዴግ ሰነዶች ውስጥ፣ “የህልውና ጥያቄ” ናቸው በማለት የተጠቀሱ ሶስት መሰረታዊ ጉዳዮች፣ “የግለሰብ ነፃነት”፣ “ነፃ ገበያ”፣ እና “የህግ የበላይነት” የሚሉ ናቸው። ቃል በቃል ነው የተዘረዘሩት – በያኔዎቹ የኢህአዴግ ህትመቶች ውስጥ። በእነዚህ ስረመሰረት ላይ ነው፣ ተጨማሪ ነገር የምናስገባው በማለትም ማብራሪያ ሰጥተው ነበር። “የአገራችንን ተጨባጭ ሁኔታ ግንዛቤ ውስጥ በማስገባት”… ብሄር ብሄረሰብ፣ የቡድን መብት… ምናምን የሚሉ ሃሳቦችን መጨመር ግዴታ ነው በማለት ገለፃ አቅርበዋል ነበር – የኢህአዴግ ፅሁፎች። (የተቀየጠ ሃሳብ፤ ከጊዜ በኋላ… ወይ እየጠራ አልያም ይበልጥ እየደፈረሰና እየተበከለ ይሄዳል። በእርግጥም፣ የተቀየጠ ሃሳብ፣… እንደዚያው እንደተቀየጠ ረግቶ እንደማይቀጥል፣ ይሄው ከአመታት በኋላ እያየነው ነው)።

Image result for democracy

እንዲያም ሆኖ፣ “የግለሰብ ነፃነት”፣ “ነፃ ገበያ”፣ እና የህግ የበላይነት” የሚሉ ሃሳቦችን ካልያዝን፣… መያዣ መጨበጫ ወደሌለው የብዥታና የውዥንብር፣ የድህነትና የቅርምት፣ የዘረኝነትና የመጠፋፋት የትርምስ ውስጥ እንገባለን… የሚል ማሳሰቢያ፣ በኢህአዴግ የያኔ መፃህፍት ውስጥ፣ በተደጋጋሚና በግልፅ ተፅፏል። ጉዳዩ የአገር ህልውና ጉዳይ እንደሆነ ጭምር ተጠቅሷል። ለምሳሌ ያለ ነፃ ገበያ መርህ፣ አገሪቱ፣… በብሄር ብሄረሰብ ፖለቲካ እንደምትበታተን ተገልጿል። (በኢህአዴግ የተለመዱ ቃላት ሲገለፅ፣… “ጠባቦች፣ ኪራይ ሰብሳቢዎች፣ ጥገኞች፣… የሚያራምዱት ነፃ ገበያን የሚቃረን አቋም፣ አገርን የሚያደኸይና የሚበታትን ነው” የሚል ሃሳብ ማለት ነው)።
ዛሬ፣ እነዚያ መርሆች…፣ “የግለሰብ ነፃነት”፣ “ነፃ ገበያ”፣ እና የህግ የበላይነት” የሚሉ መሰረታዊ የፖለቲካ ሃሳቦች ተዘንግተዋል፤ ወይም ተጠልተዋል።
በተቃራኒው፣ እነዚህን መርሆች የሚጥሱ የተሳሳቱ ሃሳቦችና አጥፊ ዘመቻዎች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተበራከቱ መጥተዋል – በተለይ ደግሞ ከ2000 ዓ.ም ወዲህ።
ከመበራከታቸው የተነሳም፣… በጣም ተላምደናቸዋል። ይሄውና ሰሞኑን፣ የዋጋ ቁጥጥር ሱስ የያዛቸው የሚመስሉ ቢሮክራቶች፣ የምርትና የንግድ ተቋማትን ለማሸግ ሲዘምቱ እያየን አይደል? እንደ ጉድ አልታየም። በጣም እየተለመደ የመጣ ነገር ነዋ። ግን፣ የእንዲህ አይነት ሱስና ዘመቻ፣ የእንዲህ አይነት የጥፋት ሃሳብ ትርጉም ምን እንደሆነ፣… ያው መያዣ መጨበጫ ወደ ሌለው ትርምስ እንደመንደርደር መሆኑና ከዚህ የተለየ ትርጉም እንደሌለው ያውቃሉ? እናውቃለን?
ለነገሩ፣ ዛሬ ዛሬ፣ “ማወቅ” እና “አለማወቅ” የምንላቸው ነገሮችም ትርጉም እያጡ ናቸው። ትክክለኛ ሃሳብና የተሳሳተ ሃሳብ… እንደ ምናባዊ ፈጠራ፣ እንደ መጫወቻ የቁማር ካርድ እየታዩ ስለሆነ፣… ማሰብ ራሱ አስቸጋሪ እየሆነ ነው – ለብዙ ሰው።
ግን፣ ለማሰብ መሞከር አለብን።
አሁን አሁን አፍጥጠው የመጡትን አስፈሪ የጥፋት ቀውሶች፣ በየጊዜውና በየአካባቢው እያየን፣ እንዴት ዝም እንላለን? ለአፍታም ቢሆን፣ ከምር ለማሰብ መሞከር አለብን። በዘር የመቧደን ቀውሶችና ጥፋቶች፣… ከምር ከታዩ፣… ሰሞኑን ከምናየው የዋጋ ቁጥጥር ዘመቻ ጋር፣… ከመንግስት የዘፈቀደ ስልጣን ጋር፣… ምንም ግንኙነት የላቸውምን? ስረመሰረታቸው አንድ አይደለምን? እስቲ ትርጉማቸውን በደንብ ለማሰብ እንሞክር።
ሃሳብ፣… ትክክልም ሆነ ስህተት፣… ማብሪያ ማጥፊያ የለውም!
የመንግስት ቢሮክራቶች፣ እንዳሻቸው በዘፈቀደ በሰው ኑሮና ንብረት ላይ፣ በሰው ምርት ወይም ሸቀጥ ላይ የሚዘምቱ ከሆነ፣… እንዳሰኛቸው ማዘዝ፣ ዋጋ መተመንና ማሸግ የሚችሉ ከሆነ፤… ምን ማለት ነው?
መንግስት እንዲህ እንደምናየው… “ህግ በማይገድበው የዘፈቀደ ስልጣን” ያሻውን ነገር መፈፀም፣ “አስፈላጊውን ሁሉ እርምጃ መውሰድ” የሚችል ከሆነ፣… ይህንንም እንደ ገድል፣ እንደ ጀብድ የሚሰብክ ከሆነ፣…
“የሕዝቡን ፍላጎት ለማርካት፣ የሕዝቡን ጥያቄ ለመመለስ አስቤ ነው”፣ “ድሃውን ህብረተሰብ ከጉዳት ለማዳን ብዬ ነው”፣ “አገራዊ ጥቅምን ለማስቀደም አስቤ ነው”… በማለት የሰበብና የማመካኛ መዓት እየደረደረ ፕሮፓጋንዳ በመንዛት፣ በማንኛውም ሰው ንብረትና ሸቀጥ ላይ ያሰኘውን ድርጊት መፈፀም የሚችል ከሆነ፣…
ግን ጉዳዩ፣ መች የመንግስት ብቻ ሆነ?
የአብዛኛው ሰው የተሳሳተ የአስተሳሰብ ቅኝትም፣ ከመንግስት ስብከት ጋር የሚስማማ በመሆኑ… “የመንግስት ቁርጠኛ አቋም አንሷል፤ እርምጃ ዘግይቷል”… ከሚሉ ማጋጋያ ቅሬታዎች በስተቀር፣ በዋጋ ቁጥጥር ላይ ብዙም ተቃውሞ የለውም። ታዲያ፣ አብዛኛው ሰው፣ በየእለቱ የሚዥጎደጎዱ ሰበቦችንና ማመካኛዎችን ሰምቶ ሲስማማ፣… የመንግስት የዘፈቀደ እርምጃዎችንም አይቶ በይሁንታ ሲቀበል፣ ከዚያም አልፎ ሲደግፍ፣ ይባስ ብሎም… “አነሰ-ዘገየ” እያለ በእሪታ ወይም በሆይሆይታ ሲያጋግል… የዚህ ሁሉ ትርጉም ምንድነው?
ሰበብ አስባብ መደርደር እስከተቻለ ድረስ፣… የሰውን ንብረት መድፈር ይቻላል ማለት ነው? ማጯጯህና ማግለብለብ እስከተቻለ ድረስ፣… የንብረት ባለቤትነትን መጣስ ይቻላል። “ጭፍን እምነትን”፣ “መስዋዕትነትን” እና “ዘረኝነትን” ተገን ያደረጉ ማመካኛዎችን ማስተጋባት እስከተቻለ ድረስ፣…
በሌላ አነጋገር፣… የተለመዱትን ማደንዘዣ አባባሎችን በማነብነብ፣… “የህዝቡ ጥያቄና ፍላጎት፣… ባህልና እምነት፣… የአገርና የድሃው ህዝብ ጥቅም፣… የብሄር ብሄረሰብ ምናምን…” የሚሉ… ማመካኛ አባባሎችን በማነብነብ፣ የግለሰብን መብት መድፈር፣ ኑሮውንና ንብረቱን መስዋዕት ማድረግ፣… ምርታማ ሰው የስራ ፍሬውን እንዲያጣ፣ ያላመረተ ሰው ደግሞ የሚሸለምበት ተግባር መፈፀም፣…  ህግ ዘለልና ፍትህ አልባ አሰራር መዘርጋት ይፈቀዳል?
እሺ ተፈቀደ!… ታዲያ መቼ መቼ ነው የነፃ ገበያ መርህ የሚተገበረው?… ማለትም፣ የንብረት ባለቤትነት መብት እንዲከበር የሚፈለገው፣ መቼ መቼ ነው? በየት በየት ቦታ? በምን በምን ጉዳይ ላይ?…
እንደየወቅቱ፣ እንደየአካባቢው፣ እንደየሁኔታው፣ እንደየጉዳዩ፣ እንደየአስፈላጊነቱ ነው፣… የሰው ንብረት የሚከበረው? የነፃ ገበያ ሥርዓት የሚሰራው? እያንዳንዱ ሰው እንደየስራው የሚመዘንበትና ዳኝነት የሚያገኝበት የፍትህ መርህ፣… እንዲሁም ማንም አካል፣… ማንም ሰውም ሆነ ማንም ባለስልጣን፣ ሚሊዮን ሰዎችም ሆኑ የሚሊዮን ሰዎች ማህበር፣ የመንግስት ተቋማትም ሆኑ የመንግስት ካቢኔ፣… የማንንም ሰው መብት መጣስ የማይችሉበት፣ ለህግ ተገዢ የሚሆኑበት… የፍትህ አሰራር፣… የህግ የበላይነት መርህ፣… ተግባራዊ የሚሆነውስ መቼና የት ይሆን?
“ተግባራዊ ይሆናል” የሚል መልስ ይሰጣል መንግስት፤ የብዙ ሰው ምላሽም ተመሳሳይ ነው። ግን ሁልጊዜ፣ በሁሉም ቦታና ጉዳይ ላይ ተግባራዊ ይሆናል ማለታቸው አይደለም። ተግባራዊ የሚሆንበት ጊዜ፣ ቦታና ጉዳይ ይኖራል። አዎ፤… የሰው ንብረት፣ የባለቤትነት መብት፣ ነፃ ገበያ፣ ፍትህ፣ ህጋዊ አሰራር (የህግ የበላይነት) ይከበራል። “አይኑር” ብዬ እስካልተናገርኩ ድረስ፣ “እንዳይተገበር” እስካልፈለግኩ ድረስ፣ እንዳይከበር እስካላዘዝኩ ድረስ… ይኖራል፣ ይተገበራል፣ ይከበራል።… ማለታቸው ነው።
ሌላ ሌላ ጊዜስ?
በሌላ ጊዜስ፣ የሰው ንብረትን መድፈር ይቻላል? በሌላ በሌላ ቦታስ፣ የንብረት ባለቤትነት መብትን መጣስ ይቻላል? በሌላ በሌላ ጉዳይስ፣… ከባለንብረት ነጥቆ መውረስ፣ መስረቅና መዝረፍ ይቻላል? ማሸግና ማፍረስ፣ መንገድ መዝጋትና ማቃጠል… ይቻላል?
እንዲከበርም እንዲደፈርም ነው የሚፈልጉት። ባሰኘኝ ጊዜ፣ ባማረኝ ቦታ፣ በመሰለኝ ጉዳይ ላይ… ይከበራል፣ ይደፈራል! የሰውን ንብረት ለመድፈር፣ የባለቤትነት መብትን ለመጣስ፣… ከመፈለግም አልፈው፣ ቀላል እንዲሆንም ይፈልጋሉ። “የሕዝብ ጥያቄና ፍላጎት፣ የአገርና የብዙሃኑ ህብረተሰብ ጥቅም፣ የብሔር ብሔረሰብ… ምናምን”… የሚሉ ሰበቦችን መደርደር፣ ማጯጯህ፣ የጥፋት ማላከከያ ምናባዊ ‘ጠላት’ መፍጠር፣ እና ጉልበት መጠቀም ብቻ ነው የሚያስፈልገው። …
ግን፣ የዚህን ትርጉምና መዘዝ ለማስተዋልና ለማገናዘብ አይፈልጉም።
ይሄ… ሰውን እንደባርያ ለማዘዝ፣ ለመግዛትና ለማዋረድ የሚያስችል ህግየለሽ ገናና ስልጣን፣… ይሄ፣ ከእውነታ ጋር የተጣላ ጭፍን ስልጣን፣… ይሄ የሰውን ኑሮ እንዳሰኘው የሚያናጋ፣ የስራ ፍሬውንም የሚነጥቅ ወይም ንብረቱን የሚቃጥል የጥፋት ስልጣን፣… ሰውን እንደ መስዋዕት በግ እየቆጠረ የውርደት ህይወትን የሚያሸክም የክፋት ስልጣን፣… ጠርሙስ ውስጥ ታሽጎ፣… “በተመጠነና በተመረጠ ሁኔታ” የሚንቆረቆር አይደለም። የጊዜ ሰሌዳ የሚዘጋጅለት፣ በራሽን የሚሰፈር፣ በኮታ ተለክቶ የሚከፋፈል ነገር አይደለም።
ሃሳብ ነው፤ መርህ ነው። ሰውን እንደ እርድ በግ የሚቆጥር የተሳሳተ፣ አጥፊና ክፉ የአስተሳሰብ ቅኝት ነው ስረመሰረቱ።
በሰበብ አስባቡ፣ “የሰውን ንብረት መድፈር ይቻላል፤ የንብረት ባለቤትነትን መጣስ ይቻላል” የሚል ነው መርሁ፣… ይሄው ነው። በአገራችን ለምዕተዓመታት በስፋት ሰፍኖ የቆየ፣ ብዙ ሰዎች በይሁንታ አልያም በድጋፍ ስሜት የሚቀበሉት፣ በመንግስት ተዘውትሮ የሚሰበክ ሃሳብ… ይሄው ነው።
ይህንን መርህ፣… “በተመጠነ ኮታ፣ በተመረጠ ቦታና ጊዜ፣… በልዩ ጉዳይና ሁኔታ ላይ ብቻ!” የሚል ማስጠንቀቂያ ተለጥፎለት በጠርሙስ ታሽጎ፣… በተቆለፈ ሳጥን ውስጥ ሊቀመጥ አይችልም።
የአስተሳሰብ ቅኝት፣… ሃሳብ፣… መርህ፣… በባህርያቸው፣… እንደእቃ አይደሉም።
አሃ! እውቀትን በትምህርት መጨበጥ የምንችለውኮ፣… እውነተኛ መረጃዎች፣ ትክክለኛ ሃሳቦችና መርሆች፣ ሳይንሳዊ የአስተሳሰብ ቅኝት… በኮታ የሚከፋፈሉ ስላልሆኑ ነው። አንድ ሰው በምርምር የጨበጠውን እውቀት፣… ሌሎች ሰዎችም በትምህርት መጨበጥ የሚችሉት፣ እውቀትን ከሰውዬው ቀንሰው በመውሰድ አይደለም። ወይም፣ እሱ ስላሰኘው፣ ስላማረው… “ለዚህ ለዚህ ጊዜ ብቻ፣… ለዚህ ለዚህ ቦታ ብቻ፣… ለዚህ ለዚህ ጉዳይ ብቻ፣…” ብሎ ባዘዛቸው መጠን አይደለም፣ ሌሎች ሰዎች እውቀትን የሚጨብጡት። “የተመጣጠነ ምግብ መብላት ለጤንነት ጠቃሚ ነው”… ይሄ እውቀት ግን፣ “ከፆም ውጭ ላሉ ቀናት ብቻ ነው”! ብሎ ማስጠንቀቂያ ተለጥፎለት የሚታሸግ እውቀት የለም።
የተሳሳተ፣ ጎጂና መጥፎ ሃሳቦችም እንደዚያው ናቸው። በተመጠነ ሁኔታ የሰውን ንብረት አለማክበር፣ በተመጠነ ሁኔታ ዘረኝነትን መስበክ፣ በተመጠነ ሁኔታ ፍትህን መጥላት ብሎ ነገር የለም።
“አልፎአልፎ፣ በአንዳንድ ቦታዎች፣ ለተወሰኑ ጉዳዮች ብቻ፣… እና ደግሞ መንግስት ብቻ፣… የሰዎችን ንብረት መድፈር፣ ማሸግ፣ መውረስ፣ ማፍረስ ይችላል” የሚል ሃሳብ ብንሰብክ፣ ዋናው መልእክት፣…
“ባሰኘው ጊዜ፣ በየትኛውም ቦታ፣ ባሻው ጉዳይ ላይ፣… መንግስትም ሆነ ሌላ ቡድን፣ ፓርቲ፣ ተቃዋሚ… የተለያዩ ሰበቦችን የሚደረድር ማንኛውም ጉልበተኛ፣ የሰውን ንብረት መድፈር፣ ማሸግ ወይም መንገድ መዝጋት፣ መውረስ ወይም መዝረፍ፣ ማፍረስ ወይም ማቃጠል ይችላል” የሚል ይሆናል።
ለተቃውሞ ሲሆንስ?
ያው ነው። “አልፎአልፎ፣ በአንዳንድ ቦታዎች፣ ለተወሰኑ ጉዳዮች ብቻ፣… እና ደግሞ “በጎ አላማ” የሚል ሰበብ የያዘ ይሄኛው ወይም ያኛው ተቃውሞ ላይ ብቻ፣… ጉልበትን በመጠቀም፣ የሰዎችን ንብረት መድፈር፣ መንገድ መዝጋት፣ መዝረፍ፣ ማቃጠል ይችላል” የሚል ሃሳብ ከተቀበልን፤… ትርጉሙ ግልፅ ነው። “ብዙ ብዙ ጉልበት ያለው መንግስትማ፣ ምን ይሳነዋል? ምን ይከለከላል?” የሚል ሃሳብም ተቀብለናል ማለት ነው።

ዮሃንስ ሰ. addisadmassnews

Share and Enjoy !

Shares
Related stories   ሕዝብን ማን ይሰራዋል?
0Shares
0