“Our true nationality is mankind.”H.G.

ከኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ የተሰጠ መግለጫ

የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር ኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ከጥቅምት 18-19/2010 ዓ.ም ድረስ በጥልቀት የመታደስ ንቅናቄ የደረሰበት ደረጃ እና ወቅታዊ አገራዊ ሁኔታን በዝርዝር የገመገመበትን ስብሰባ አካሂዷል፡፡
ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴው ባለፈው ጳጉሜ የተሰበሰበው የኢህአዴግ ምክር ቤት የገመገማቸውንና የወሰናቸውን ውሳኔዎችም በመፈተሽ የተጀመረው የጥልቅ ተሃድሶ እንቅስቃሴ አበረታች ነበር ተጠናክሮ መቀጠል ይገባዋል ያለው የምክር ቤቱ ውሳኔ የደረሰትን ደረጃ ገምግሟል፡፡ በዚህ መሰረት በሁሉም ብሄራዊ ድርጅቶች የምክር ቤቱን ውሳኔ ተከትለው እየፈፀሙት ያሉት ተግባራት በትክክለኛ አቅጣጫ እየተፈፀሙ ያሉ ቢሆንም የተለየ ትኩረት የሚሹ በአሁኑ ወቅት በተወሰኑ የአገሪቱ አካባቢ የተከሰቱ ችግሮችና ግጭቶች ባህሪያቸውና ምክንያታቸው ምን እንደሆነም በዝርዝር ተመልክቷል፡፡
በዚህ መሰረት በመስከረም ወር መጀመሪያ በምስራቁ የሀገራችን አካባቢ በኦሮሚያና በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች የተከሰቱት ግጭቶች በዜጎች ህይወት እና በንብረት ላይ እጅግ ከፍተኛ ጉዳት ከማስከተላቸውም አልፎ በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ከቤት ንብረታቸውና ከኑሮአቸው ተፈናቅለው ከባድ ጉዳት የደረሰባቸው መሆኑን ተመልክቷል፡፡ ይህ ድርጊት በምንም መልኩ መከሰት ያልነበረበት የኪራይ ሰብሳቢነትን ችግሮች መድፈቅ ባለመቻላችን የተፈጠረ እንደሆነም የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴው አስምሮበታል፡፡
ይህንን ችግር ተከትሎ በኦሮሚያ ክልል አንዳንድ አካባቢዎች የተከሰቱት ግጭቶች በተመሳሳይ መንገድ በዜጎች ህይወት መጥፋትና ንብረት መውደም መንስኤ መሆናችውንም የተመለከተው የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴው ግጭቶቹ በተከሰቱባቸው ሁሉም አካባቢዎች መላው የአካባቢው ህዝብ፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ አባ ገዳዎች፣ የሃይማኖት አባቶች ግጭቱን ለማስቆም የጥፋቱን መጠን ለመቀነስ ያደረጉት እጅግ የሚያስመካ ስራ ህዝቦቻችን እርስ በርሳቸው ያላቸው ትስስር እና ጠንካራ መስተጋብር ውጤት መሆኑን ያረጋገጠ እንደሆነ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴው በአዎንታ ተመልክቶታል፡፡
በመሆኑም ለሀገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ ለመምህራን፣ ለሴቶችና ወጣቶች እንዲሁም ችግሩ በተከሰተባቸው ቦታዎች በመሰለፍ የዜጎችን ህይወት ለመታደግ ለተንቀሳቀሰው የፀጥታ መዋቅር በሙሉ ከፍተኛ ምስጋና አቅርቧል፡፡
ለጋው ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ስርዓታችን የአገራችን ህዝቦች፣ መብቶች ነፃነቶችና ጥቅሞችን በተሟላ መንገድ ለማስከበር ያስቻሉ ህጋዊና ህገ መንግስታዊ መሰረቶች የጣለ ነው ያለው የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴው ይህንን በተዛባ መንገድ እንዲተረጎም ነባር የጋራ ጠንካራ መስተጋብሮች እንዲሸረሸሩ የሚሹ የውስጥ ጥገኛ ሀይሎችና የውጪ ጠላቶቻችን በመረባረብ ላይ ይገኛሉ ብሏል፡፡ ይህንን መርዘኛ ምኞታቸውን ከንቱ ለማድረግ በፌዴራሉ ስርዓት ውስጥ የበለጠ መተማመንንና መቀራረብን የሚፈጥሩ ስራዎች በሁሉም ደረጃዎች በፍጥነት እንዲሰሩ በኢህአዴግ እህት ድርጅቶች የጋራ አላማ ዙሪያ በትግል ላይ የተመሰረተ ጓዳዊ ትስስር ይበልጥ እንዲዳብር ማድረግ በተለየ ሁኔታ ማከናወን እንደሚገባ አስምሮበታል፡፡
ኢህአዴግና አጋር ድርጅቶች በጋራ በምንገነባው አገር የህዝቦቻችንን ተሳታፊነትና ባለቤትነት የጋራ መዳረሻችን የሆነው የኢትዮጵያ ህዳሴ እውን ለማድረግ በየጊዜው እየተከሰቱ የሚፈታተኑን ችግሮች በፍጥነት በመፍታት መተማመናችንን ማጠናከር ይገባልም ብሏል፡፡
ከዚህ በተጨማሪ የተፈናቀሉትን ወገኖች ለማቋቋምና ወደ ቤት ንብረታቸው እንዲመለሱ ለማድረግ ህዝቡ እያደረገ ያለውን ጥረት በአድናቆት የተመለከተው ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴው መንግስት ተፈናቃዮችን ወደ ነበሩበት እንዲመለሱ ለማድረግና ወደ መደበኛ ኑሮአቸው ተመልሰው እንዲቋቋሙ ማድረግ እንደሚገባው አቅጣጫ ተቀምጧል፡፡
ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ ለግጭቶቹ መፈጠር ምክንያት የሆኑ የኪራይ ሰብሳቢነት፣ የሙስናና የብልሹ አሰራሮች ከዚህ ጋር ተያይዞ ህገ ወጥነት እንዲስፋፋ እያደረጉ ያሉ የኮንትሮባንድ ትስስሮች በዝርዝር ተፈትሸው በአፋጣኝ እንዲቀረፍ የፀረ ሙስና ትግሉ የኢህአዴግ ምክር ቤት በወሰነው መሰረት ተጠናክሮ እንዲቀጥል ከእነዚህ ችግሮች ጋር በተያያዘ የሚከሰቱ ህገ ወጥነቶች በምንም መልኩ እንዲቀጥሉ እንደማይፈቅድላቸው እና የህግ የበላይነት መረጋገጥ እንደሚገባ በአፅንኦት አስምሮበታል፡፡
በምስራቁ የአገሪቱ አካባቢዎችም ይሁን ለሌሎች አካባቢዎች በተከሰቱት ግጭቶች ለዜጎች ህይወት መጥፋትና ንብረት መውደም የሰላም መናጋት አስተዋፅኦ ያደረጉ አካላት እስከ አሁን ድረስ በፖሊስ ተይዘው በምርመራ ሂደት ያሉም ሆነ በህግ ቁጥጥር ስራ ያልዋሉትን በሙሉ በህግ ቁጥጥር ስር በማድረግ በተሳትፏቸው ልክ ተጠያቂ የሚሆኑበት ሁኔታ ከተጀመረው በላይ እንዲጠናከርና በቂና አስተማሪ የሆነ እርምጃ መውሰድ እንደሚገባም አቅጣጫ አስቀምጧል፡፡ እነዚህን ተጠርጣሪ ወንጀለኞች ለህግ ለማቅረብ በሚደረገው ርብርብ ውስጥ ህዝቡ እስካሁን ያሳየውን የሰላም አለኝታነቱን አጠናክሮ እንዲቀጥልም የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴው ጥሪውን አቅርቧል፡፡
በሌላ በኩል የኢኮኖሚውን አፈፃፀም የገመገመው የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴው የኢህአዴግ ምክር ቤት የአመቱ እቅድ አፈፃፀም ሲገመግም የኢኮኖሚ አፈፃፀማችን ከወጪ ንግድ ገቢ ግኝት በስተቀር በሁሉም መመዘኛዎች ጤናማና ውጤታማ መሆኑን መገምገሙ ትክክለኝነቱን አስታውሶ በአሁኑ ወቅት የውጭ ምንዛሬ ተመን ለውጥ መደረጉ ወቅታዊና ተገቢ መሆኑን በመገምገም ከዚህ ጋር ተያይዞ እየተፈጠሩ ያሉ የኑሮ ውድነትን የሚያስከትሉ ጉዳዮችንም በዝርዝር ፈትሿል፡፡
በዚህ መሰረት መንግስት የህብረተሰቡን ኑሮ በቀጥታ ሊያቃውሱ የሚችሉ ሸቀጦች ዋጋ ማለትም የነዳጅ፣ የስኳር፣ የስንዴና የዘይት ዋጋዎች በነበሩበት እንዲቀጥሉ መወሰኑ ትክክለኛ ነውም ብሏል፡፡ ይሁንና የማይቀረው ከውጭ የሚገቡ ምርቶች ላይ ሊኖር የሚችለው የዋጋ ጭማሪ እንደተጠበቀ ሆኖ ምክንያታዊ ባልሆነ መንገድ በአገር ውስጥ ምርቶችና ምንም ለዋጋ ጭማሪ ተያያዥነት በሌላቸው ምርቶች ላይ የሚደረገው ጭማሪ ተቀባይነት ስለማይኖረው ከላይ እስከ ታች ያለው የመንግስት አካላት በቅንጅት መመከት እንደሚገባም አቅጣጫ አስቀምጧል፡፡
ባጠቃላይ የጥልቅ ተሃድሷችን እንቅስቃሴ ማምጣት የሚገባውን ለውጥ በተሟላ ሁኔታ ባለማምጣቱ እየተከሰቱ ያሉ ግጭቶች ምክንያት የሚሆኑ የወሰን መካለል በወቅቱ ያለመፍታት፣ የወጣቶች የስራ እድል ፈጠራ አለመጠናከር፣ የመልካም አስተዳደር እጦትና የስልጣን እይታ ብልሽቶች ችግሮች በዚህ መልኩ እየተንከባለሉ መቀጠል በፍፁም መፈቀድ የሌለበት በመሆኑ መላው የድርጅታችን አባላትና አመራሮች የሀገራችን ህዝቦች ችግሮቹን ለመፍታት በሚደረገው ርብርብር ውስጥ በንቃት በመሳተፍ ባለቤትነታችሁን እንድታረጋግጡ የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴው ጥሪውን ያቀርብላችኋል፡፡
ባለፉት ሁለት ወራት በተከሰቱት ችግሮች እርስ በርሳቸው በመተጋገዝ ለሰላማቸው፣ ለልማታቸውና ለአብሮነታቸው አለኝታነትን ያረጋገጡትን የኦሮሚያ ክልል ህዝቦችና የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ህዝቦች እንዲሁም በተከሰተው መፈናቀል የደረሰውን ጉዳት ለመቀነስ ከፍተኛ ወገናዊነታቸውን ላሳዩት የሀረሪ ክልልና የድሬደዋ አስተዳደር ነዋሪዎችና አመራሮች ምስጋና ያቀረበላቸው የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴው በሌሎችም ግጭቶች በተከሰቱባቸው የኦሮሚያ ክልል አካባቢዎች ህዝቦች የተከሰቱትን ግጭቶች ለማብረድ ላሳዩት ህዝባዊ ቁርጠኝነትና ኢትዮጵያዊ ጨዋነት የላቀ ምስጋና እያቀረበ አሁንም ችግሮችን በተሟላ ሁኔታ ለማስወገድ በሚደረገው ርብርብ ውስጥ ዛሬም እንደትናንቱ ድጋፋችሁንና ባለቤትነታችሁ መተኪያ የሌለው በመሆኑ አጠናክራችሁ እንድትቀጥሉበት ማሳሰብ ይወዳል፡፡
መላ የአገራች ህዝቦች በአንዳንድ አካባቢዎች በሚከሰቱ ግጭቶች ምክንያት ስለሰላማችንና ስለአገራችን ደህንነት እንዳሳሰባችሁ በአፅንኦት ተመልክተናል ያለው የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴው እነዚህ ችግሮች እንዳይደጋገሙ የችግሮቹ ምንጭ የሆኑ ጉዳዮች ደረጃ በደረጃና በፍጥነት እንዲፈቱ ሰላማችንን አስተማማኝ ለማድረግ ልማታችንን ለማፋጠንና ዴሞክራሲያችንን ለማስፋት ያለንን ቁርጠኝነት በድጋሚ እያረጋገጠላችሁ እንደተለመደው ከድርጅታችንንና ከመንግስታችን ጎን እንድትቆሙ ጥሪውን እናቀርብላችኋለን፡፡

0Shares
0