“Our true nationality is mankind.”H.G.

“የቀረችኝን ነገር ለቃቅሜ ሕይወቴን ይዤ ከዚህ ቦታ መውጣት ነው የምፈልገው”

Via- BBC Amharic በቤኒሻንጉል ጥቃትን በመፍራት ሰለባዎች ወደመኖሪያቸው መመለስን ፈርተዋል

ባለፈው ሐሙስ ጥቅምት 16 ቀን በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ካማሽ ዞን ሃሮ ዴዴሳ ቀበሌ የተቀሰቀሰውና ለሕይወት መጥፋት እንዲሁም ለንብረት መውደም ምክንያት የሆነው ግጭት ግላዊ ጠብ የጫረው ነው ቢባልም ቢቢሲ ያነጋገራቸው የጥቃቱ ሰለባዎች ግን ማንነታቸው ላይ ያነጣጠረ መሆኑን ይናገራሉ።

በተለያዩ ጊዜያት ከምዕራብ ጎጃም ዞን ለስራ ወደአካባቢው አቅንተው ኑሯቸውን በመሰረቱ የአማራ ተወላጆች እና በጉሙዝ ብሔረሰብ አባላት ውጥረቶች እና ግጭቶች አዲስ ያለመሆናቸውን የሚያስረዱት የጥቃቱ ሰለባዎች ከሁለቱም ወገን ሰዎች መሞታቸውን ይገልፃሉ፤ ከሟቾቹ መካከል የኦሮሞ ተወላጆችም ይገኙበታል ተብሏል።

በግጭቱ ማግስት የአማራ ክልል የብዙኃን መገናኛ ድርጅት የቤኒሻንጉል ክልል የኮሚኒኬሽን ጽሕፈት ቤት ኃላፊ የሆኑትን አቶ መንግስቱ ቴሶን ጠቅሶ ባቀረበው ዘገባ ክስተቱን ወደግል ጠብ ዝቅ አድርጎት እንደነበር ይታወሳል።

በ1997 ዓ.ም ከከሰላ አካባቢ ስራ ፍለጋ ወደስፍራው ካቀና በኋላ ኑሮውን በቀበሌው ደናባ ጎጥ የመሰረተው የ36 ዓመቱ ባይህ ታፈረ በግጭቱ የተገደሉ ሰባት ሰዎችን አስከሬን መመልከቱን ይናገራል፤ ሟቾቹ ስድስቱ የአማራ አንዱ ደግሞ የጉሙዝ ተወላጆች ናቸው ይላል።

ባይህ በደረሰባቸው ድብደባ ከፍተኛ የመቁሰል አደጋ የገጠማቸውን የስምንት እና የአስራ አንድ ዓመት ልጆቹን በነቀምት አጠቃላይ ሆስፒታል በማስታመም ላይ የሚገኝ ሲሆን በተለይ ባለፉት ሁለት ዓመታት “ወደአገራችሁ እንመልሳችኋለን” የሚል ዛቻ ከአገሬው ሰው ጎልቶ ይሰማ ነበር ይላል።

Related stories   የመ/ሰራዊትን መለያ ለብሶ ከሱዳን ወደ ወልቃይት ሊገባ የነበረ የትህነግ የሽብር ሃይል ተደመሰሰ፤

ይህ መንፈስም ከሌሎች ቦታዎች የመጡ ናቸው የተባሉ ሰዎች ላይ ጥቃት እንዲነጣጠር ምክንያት ሆኗል ሲል ያምናል።

“በየጠላ ቤቱ፣ በየአረቄ ቤቱ ብናባርራችሁ መንግስት መለሳችሁ፤ አሁንም ግን ዋጋችሁን እንሰጣችኋለን ይሉናል” ሲል ለቢቢሲ ተናግሯል፤ “መንግስት መሳሪያችን ቢነጥቀንም ቀስትና ጩቤ አለን ሁሉ እንባላለን።” ይላል ባይህ

የቤኒሻንጉል ክልል በሕገ መንግስቱ መሰረት “ነባር ሕዝቦች” ናቸው በሚል ዕውቅና የሰጣቸው ለበርታ፣ ጉሙዝ፣ሽናሻ፣ ማዖ እና ኮሞ ብሔሮች ሲሆን “መጤ” ናቸው ከሚባሉ የሌላ ብሔር ተወላጅ ሕዝቦች ጋር ግጭቶች ሲፈጠሩ አሁን የመጀመሪያው አይደለም።

በ2006 ዓ.ም በሺዎች የሚቆጠሩ የአማራ ብሔር ተወላጆች ጥቃትን በመሸሽ ከአካባቢው ተፈናቅለው በምዕራብ ጎጃም ዞን ፍኖተ ሰላም አካባቢ ሰፍረው የቆዩ ሲሆን፤ ቆይቶም ወደክልሉ እንዲመለሱ መደረጋቸው ይታወሳል።

የቤኒሻንጉል ክልል የኮሚኒኬሽን ጽሐፈት ቤት ኃላፊው አቶ መንግስቱ የተከሰተው ግጭት የብሔር መልክ የለውም ይበሉ እንጅ፤ የሃሮ ደዴሳ ገብርዔል ቤተክርስትያን አስተዳዳሪ የሆኑት ቄስ እንኳሆነ ቸሬ “ምንም በማናውቀው ጉዳይ መደብደባችን ወገን ናችሁ ቢባል ነው እንጅ” በማለት

ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ካማሺ ዞንImage copyright Google MAPS

ቄስ እንኳሆነ ከልጃቸው ጋር ወደስራ በሚሄዱበት ሰዓት በድንገት ጥቃት እንደደረሰባቸው ነው የሚናገሩት። ከባድ ድብደባ ለሕይወቱ የሚያሰጋ ሁኔታ የዳረገው ልጃቸው ሆስፒታል ውስጥ ይገኛል።

Related stories   “የግድቡ ግንባታ ውሃ ይቀንስብኛል የሚለው የግብጽ ጩኸት የማጭበርበሪያና የተለመደ የሃሰት ክስ ነው››

ባይህ ጥቃት አድራሾቹ በሕፃናት ላይ እንደሚበረቱ ይናገራል፤ “ልጆቻችን እዚሁ ተወልደው ስላደጉ ጉምዝኛ ቋንቋ ችለዋል። እነርሱ ይሄንን አልወደዱትም፤ ቋንቋችንን ሰረቃችሁን ይላሉ” ብሏል።

እርሱና መሰል የአማራና የኦሮሞ ተወላጆች መሬት በመከራየትና እርሱን አርሰው የመሬት ባለቤት ከሆኑ የአካባቢው ተወላጆች ጋር ምርቱን በመካፈል እንደሚተዳደሩ ሲያስረዳ “ውል እንገባለን። በውሉ መሰረት ተስማምተን፤ ሽማግሌ አስቀምጠን ነው የምንሰራው። ውሉን ከፈፀምን በኋላ

የእነርሱን ድርሻ እንሰጣለን። የራሳችንንም እንወስዳለን። ይህ ሲሆን ግን ጎጃሜ እኛ አገር መጥቶ ለምን ይደሰታል ነው የሚሉት” ይላል።

በስራ መካከል ግጭቶች በሚፈጠሩበት ጊዜ በሽማግሌዎች የማይፈታ ከሆነ በጎጥና በቀበሌ የአስተዳደር አካላት ፍትህን ማግኘት አዳጋች ነው ይላል።

ቄስ እንኳሆነ የቀጣይ ቀናት እርምጃቸውን ማሰብ አይፈልጉም፤ ትኩረታቸው ሁሉ የልጃቸው ጤና መመለስ ላይ ነው። “ከዚያ ወዲያ ያለውን እግዚያብሄር ነው የሚያውቀው ። ደውለን ስንጠይቅ አሁንም ብዙ ሰዎች ጫካ እንዳሉ ናቸው። ያለዕህል ውሃ መመለስ ፈርተዋል” በማለት ይናገራሉ።

ባይህ ደግሞ ወደነቀምት ከመጣ በኋላ የቅርብ ጎረቤቱን ጨምሮ አራት ሰዎች -ሁለት የአማራ ተወላጆች እና ሁለት ከእነርሱ ጋር አብረው የሚሰሩ የኦሮሞ ብሔር አባላት- በቢላዋ ተወግተው ተገድለው እንደተገኙ በስልክ ከወዳጆቹ መስማቱን ያብራራል።

Related stories   እስራኤል አልጃዚራ ቴሊቪዥን፣ አሶሲየትድ ፕሬስና ሌሎች ሚዲያዎች የሚጠቀሙበትን ህንጻ አወደመች

ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት ያፈራውን ንብረት ሙሉ ለሙሉ እንደተዘረፈ የሚናገረው ባይህ ፤ ወደ ቤኒሻንጉል ክልል የመመለስና ሕይወቱን ዳግም የመገንባት ፍላጎት የለውም።

“የቀረችኝን ነገር ለቃቅሜ ሕይወቴን ይዤ ከዚህ ቦታ መውጣት ነው የምፈልገው” ይላል።

ይህንንም ተከትሎ የአማራ ክልል ኮሚኒኬሽን ኃላፊ አቶ ንጉሱ ጥላሁን ዛሬ በፌስቡክ ድረ-ገፃቸው የፃፉት መረጃ እንደሚያሳየው የስምንት ሰዎች ህይወት የጠፋ ሲሆን ቁጥራቸው ያልተገለፁ ቤቶችም ተቃጥለዋል።

ከዚህም ጥቃት ጋር ተያይዞ የመከላከያ ሰራዊት እና ፖሊስ ሁኔታውን ለማረጋጋት እየሰሩ መሆናቸውን የአቶ ንጉሱ ጥላሁን ፅሁፍ ጠቅሶ 11 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ዉለዋል።

ምንም እንኳን የቤኒሻንጉል ጉሙዝም ሆነ የአማራ ክልል አመራሮች ጉዳዩን ወደ ግለሰባዊ ፀብ አውርደውት የነበረ ቢሆንም ጉዳዩን በጥልቀት እያጤኑት እንደሆነ አቶ ንጉሱ ጠቅሰዋል።

የሁለቱም ክልል ሀላፊዎች በቦታው ላይ የማረጋጋት ስራ እየሰሩ እንደሆነ አቶ ንጉሱ ጠቅሰው የክልሉ አመራሮች እና የብአዴን አስተባባሪዎች ህዝብ የማወያየት ስራ እንደጀመሩ ጨምረው ጠቅሰዋል።

ከዚህም በተጨማሪ ስለደረሰው ጉዳት ዝርዝር መረጃ በቦታው የተሰማራው ቡድን እያሰባሰበ እንደሆነ አቶ ንጉሱ ጠቅሰዋል።

Share and Enjoy !

Shares
0Shares
0