ትናንት ማታ በቤተሰባችን ወቅታዊ ጉዳዮች እና መፃኢ እድል ላይ ለመወያየት በጠረጴዛ ዙሪያ ሰፍረናል፡፡ አብዛኞቻችን እንቅልፍ ቢያንጎላጀንም መርሃ ግብሩን ለማሟላት ከፊሎቻችን ከአልጋችን ላይ ተጎትተን ፤ የተቀረነው ከተሰካንበት ቲቪና ላፕቶፕ ወይም  ስልክ ተነቃቅለን ሳሎን ቤት ተገኘን፡፡ እምቢ ያሉትም የክፍሎቻቸውን በር ዘግተው ቀሩ፡፡ ያው እንደተለመደው አባታችን ጉሮሮውን ጠራርጎ ንግግሩን ጀመረ፡፡

“የዚህ ቤተሰብ አባላት ሁላችሁ ተፋቅራችሁና ተከባብራችሁ እንደምትኖሩ አውቃለሁ፡፡ ሌላው ቀርቶ ዘበኛችንን እንኳ ውሰዱ እንዴት እንደምትወዱት አስቡ ይህንን ፍቅር ጠብቆ ለማቆየት … ”

ወንድሜ አቋረጠው

“እኔ ግን ይሄ ሰውዬ አይመቸኝም ፋዘር እኛ እንደማንኛውም ሰው ስንወደውና ስናከብረው እሱ ግን …. ሰው ይመርጣል ያዳላል ለምሳሌ እኔ ስንት ሰዓት ሙሉ በር ላይ ቆሜ ሳንኳኳ ቶሎ አይከፍትልኝም ያ  ሃብታሙ ዳንጎቴ ማነው አጎቴ ሲመጣ የበር አከፋፈቱ ራሱ ይለያል በዛ ላይ ፍጥነቱ … እሱ ገና ለገና ብዙ መኪኖች ስላሉት ከእኔ ከልጅህ የተሻለ አቀባበል እና የበር አከፋፈት ሲደረግለት ቅር ይለኛል ፤ አንድ ቀን ግን ደንፉ ይዞኝ አንዱን መኪናውን ብሰብርለት እንዳታዝንብኝ ባለፈው ሰሞን ደሞ አጥቤ ያሰጣሁት ስኒከር ጫማ ጠፋብኝ፡፡  እሱ በሩ ላይ ተጎልቶ ሌባ  ሰረቀኝ  … ታውቃለህ ያኔ በደጉ ዘመን ሁለትሺህ ብር እንደገዛሁት አሁን ልግዛው ብዬ ብጠይቅ ሁለት ሺኅ ሶስት መቶ ብር ሆኖ ጠበቀኝ በአንድ ጀንበር 15 በመቶ ጨምሮ ኢማጅን ፋዘር ጥበቃው አልተጠናከረም ለኪሳራ እየዳረገኝ ነው ወይ ይቀየር ወይም ሰው ይጨመርና… ”

ከእኔ ሌላ በዘበኛችን ላይ የሚማረር ሰው መኖሩን ስሰማ የልብ ልብ ተሰምቶኝ እድል ሳይሰጠኝ ቀጠልኩ

“እኔ ራሱ ባለፈው አንዱ የመንደር ጎረምሳ ሲለክፈኘ እያየ መች አስጣለኝ? ሌላ ቀን  ደሞ መሽቶብኝ ስገባ አይኑ እያየ ሌቦች ሲዘርፉኝ  ቦርሳዬን ሁሉ ሲነጥቁኝ  እንኳን ሊያስጥለኝ ጭራሽ ተደርቦ … ለራሴ ለህይወቴም እፈራዋለሁና ቢቀየር ደስ ይለኛል እንደምታስበው አንወደውም…”

አስቆጣሁት መሰለኝ ”አንቺ ደሞ ዝም በይ አፍ አለኝ ብለሽ ታወሪያለሽ እንዴ?  ፌስቡክ በጣም አብዝተሻል ፡፡ እንደገባሽ ላፕቶፕላይ መተከል ነው  ፤  ለቤተሰባችን መፋቀር እና የእርስ በእርስ መልካም ግንኙነት እንቅፋት ስለሆነ ቤት ውስጥ የተከልኩትን ዋይ ፋይ አስፈላጊ ሆኖ በመሰለኝ በማንኛውም ሰኣት ላቋርጠው እንደምችል እወቂው፡፡ ለእኔም ለስራዬ ይጠቅመኛል  ፤  እሰከ መቼስ ልጆቼን አፍናለሁ ከሰው እኩል ድርጋችሁ… ከተቀረው አለም ተገናኝተሸ ስኮላርሺፕ ምናምን እንድታፈላልጊና የስራ እድልም እንድታገኚ ብዬ እንጂ ተራ አሉባልታ እና የመንደር ወሬ ነውኮ ስታወሪ የምትውይው የማላይ መሰለሽ? ግፋ ሲል ከወሌሶይንካ ፎቶ ጋር የተነሳሽውን ፎቶ ነው የለጠፍሽው ፡፡ እርምሽን ከትልቅ ሰው ፎቶ ስር ብትገኚ ትልቅ የሆንሽ አይምሰልሽ … ገና ነሽ ይቀርሻል ደሞ  ሬስቶራንት ነው ቦታው አውቀዋለሁ የበላሽውን ምግብማ መች ታሳያለሽ አዎ የኔ ልጅ ሆነሽ  ያንን የመሰለ ሬስቶራንት ገብተሸ ጣፋጭ ምግብ የመብላት አቅም እንዳለሽ የተቀረው ዓለም አይቶ እንዳያመሰግነኝ ‘ልጁ በምግብ እህል ራሷን ችላለች’ እንዳይለኝ ምግቡን ትተሽ ከሰው ፎቶ ጋር ፎቶ ትነሻለሽ ፡፡

ብሎ ወረደብኝ፡፡  መሰረተ ቢስ ቁጣ ተቆጣኝ ፡፡ይሄ ሰውዬ ምነው ጨከነብኝ? አባቴ ነው እንጀራ አባቴ ነው? ብዬ ትኩር ብዬ ሳየው… አይኑ ላይ ጥቁር ነጥብ እንደጣለበት አስተዋልኩ ::

በመሃል ለሪፍሬሽመንት ሰራተኛችን ሻይ አቀረበች በደረቁ አትጨቃጨቁ ይህቺን ፉት እያላችሁ በሚል ገፅታዋ ፡፡ ህልም ህልም በሚል የስኳር ጣዕም ሻይ መጠጣቱን ተለማምደነዋል የዛሬው  ግን ጭራሹኑ ባዶ ነው ምናምኒት ስኳር የለውም ፡፡

”ርጋፊ ስኳር አልነበረም እንዴ ጠዋት?”  የእናቴ ድምፅ አሁን ገና ተሰማ፡፡

“መንገድ ላይ አደናቅፎኝ ወድቄ ተደፋብኝ” አለች ስትፈራ ስትቸር

ለቁጣ ከተቀባበለው የእናቴ አፍ ቀድሜ መከላከል ጀመርኩ “ይውልሽ ማሚ…  እውነቷን ነው ከጓዳ  እስከ ሳሎን ያለው  ኮሊደር መሰረ ልማቱ አልተጠናከረም ደረጃው አዳጋችና አደናቃፊ ነው የተቃጠለው  አምፖል ራሱ ሳይቀየር ስንት ጊዜው  … ስትወድቅ አለመሰበሯም ተአምር ነው  አንኳን አንቺ ተረፍሽ  ልጄ”

በድንገት ከወንዶቹ መኝታ ቤት የሽብር ድምፅ  ተሰማ፡፡  ሁለቱ ወንድሞቼ በአንድ ትራስ ሳቢያ እየተደባደቡ ነው ‘የኔ ነው የኔ ነው’ በሚል መነሾ፡፡

“እነዚህ ደሞ ሃራራ ይዟቸው ነው፡፡  አልቃሙም መሰለኝ ዛሬ፡፡” ከአባቴ የማልጠብቀውን ነገር ሰማሁ በድንጋጤ ይበልጥ አተኩሬ ሳየው  የጥርሱ ፍንጭት እየሰፋ መሆኑን አስተዋልኩ፡፡

ቀጥሎም…

”በዛ ላይ የአንዱን ክፍል ቤት ኪራይ ለትንሹ ና ለስራአጡ  እንዲሰበስብ መወሰኔ ትልቁን አበሳጭቶታል በኪራይ ሰብሳቢነት ሳቢያ ነው የተጣሉት እንጂ ቤቱ ሁሉ ትራስ ነው ምን ጎደላቸው?”  ይላል፡፡ እናቴ ልጆቿን ልታገላግል ሄደች

እኔ በበኩሌ በቤት ኪራዩ ራሱ አልተስማማሁም  ጊቢ ውስጥ ያሉት ተከራዮች  ምንም ስርአት የላቸውም አንደኛው ውሃ ያባክናል ፤ ሌላኛዋ መብራት ፡፡

“የቤተሰቡን ፍቅርና አንድነት ለማጠናከር በጥልቀት መታደስ አለብን እየታደስን ለመስራት እየሰራን ለመታደስ…”

“ልክ ነህ አባቴ ከሁሉም ይልቅ የኔ መኝታ ክፍል መታደስ ያስፈልገዋል ፤ጣሪያው በስብሷል፤ ያፈሳል መስኮቱም አይዘጋልኝም  ክረምቱን እንዲሁ ነው የከረምኩት የምተማመንበት ጥበቃ በሌለበት ጊቢ በዛላይ

‘ክፈቺውና መሰኮቱን

ሰርቄሽ  ልሂድ ለሊቱን’

የሚል ሙዚቃ የሚጋብዘኝ ሰው በበዛበት በዚህ ሰሞን የመስኮቱ መላላት አሳስቦኛል  አንድ ማለዳ ጠፍቼ ባታገኙኝ እንዳታዝኑ ክፍሌይታደስልኝ፡፡ በጥልቅ፡፡” አልኩ

ችላ ብሎኝ ወደ ስኳር ችግሩ ተዘዋወረ “ስኳር መቼ ጠፋ? በጅምላ አለ አይደለም እንዴ? በጠዋት ተነስታችሁ ከሸማቾች ለምን አትገዙም?” የጥያቄዎቻችን ችላ ተብሎ መታለፍና ያለንበትን ሁናቴ ሊረዳልን ባለመቻላችን እንደ ህንድ ፓርላማ አጉረመረምን፡፡

ወዲያው ሃይለኛ የበር መንኳኳት ተሰማና በስተደቡብ የሚገኙት የጎረቤታችን ልጅ በበሩ በኩል ብቅ ብሎ

”አባዬ እንዳለ አትንጫጩ ሹሹሹ ዲሞክራሲያዊ ምርጫ ላይ ነንና አትበጥብጡን”

”እ እሺ ይቅርታ ይቅርታ” አልነውና በሹክሹክታ ከምንነጋገር ጉዳያችን በይደር ተይዞ  ወደየ ክፍላችንን ተበታተንን፡፡

ምስጋና አንድ አፍታ

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *