የኦሮሞ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት (ኦህዴድ) ማዕከላዊ ኮሚቴ ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ባካሄደው ስብሰባው በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል በጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ እንዲማሩ የተመደቡ የኦሮሚያ ክልል ተወላጆችን በተመለከተ ውሳኔ አስተላልፏል። ኦህዴድ ተማሪዎቹ «ለደህንነታቸዉ» ሲባል በሌሎች የሀገሪቱ ዩኒቨርሲቲዎች እንዲመደቡ መወሰኑን ገልጿል። 

የኦሮሞ ተማሪዎች ከጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ እንዲዛወሩ ተወስኗል

ኦህዴድ ዓርብ ጥቅምት 18 ቀን 2010 ዓ.ም በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል በሚገኘዉ በጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ ትምህርት ላይ የሚገኙ የኦሮሞ ተወላጆች ደህንነታቸዉ «በአሳሳቢ ሁኔታ» ስለሚገኝ «ለደህንነታቸዉ» ሲባል ወደ ሌሎች የሀገሪቱ ዩኒቨርሲቲዎች እንዲመደቡ መወሰኑን የክልሉ የኮሙዩኒኬሼን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አዲሱ አረጋ በፌስቡክ ገጻቸዉ ላይ ባሰፈሩት መልዕክት ገልጸዋል። ምደባቸዉንም ትምህርት ሚኒስቴር እያጠናቀቀ እንደሚገኝም አቶ አዲሱ አሳዉቀዋል። ምደባቸዉ እስከሚታወቅ ድረስም ተማሪዎቹ ከዩኒቨርሲቲዉ ግቢ እንዳይወጡና በትዕግስት እንዲጠባበቁም አሳስበዋል።

ማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎችን ጨምሮ ሌሎች በአገሪቱ ያሉ የብዙሃን መገናኛዎች እንዲህ አይነቱ ርምጃና ዉሳኔ የፌዴራል መንግሥት እንጂ የአንድ ክልል ፓርቲ ወይም መንግሥት ርምጃ መሆን የለበትም በማለት ሲከራከሩ ታይቷል። በዚህም ፓርቲዉ የወሰደዉ ርምጃ «ጤነኛ» እንዳልሆነ፣ ሕጋዊ ማዕቀፍ እንደሌለዉ፣ የፌዴራል መንግሥቱ ኃላፊነቱን እየተወጣ አይደለም የሚሉ እና ሌሎች ነጥቦችንም በማንሳት ሲተቹ ይደመጣል።

ሌሎች ደግሞ የክልሉ ገዥ ፓርቲም ሆነ መንግሥት ለተማሪዎቹ ደህንነት ሲባል ይህን ዉሳኔ መወሰናቸዉን በመደገፍ ይሞግታሉ። የአዳማ ከተማ ነዋሪ የሆኑት ስማቸዉ እንዳይጠቅስ የፈለጉ ግለሰብ ፓርቲዉም ሆነ የክልል መንግሥት «ርምጃዉን ለመዉሰድ ዘገይተዋል »ይላሉ። ዩኒቨርሲቲዎች በፌደራል መንግሥት ሥር ቢተዳደሩም በዩኒቨርሲቲዉ የተከሰተዉን የደህንነት ችግር ግን ማስቆም አልቻለም በማለትም ይተቻሉ። ጉዳዩ የፌደራል ስልጣን ተነካ አልተነካ ሳይሆን ፓርቲዉ የወሰደዉ ርምጃ የተማሪዎቹን ደህንነት ለመጠበቅ ነዉም ይላሉ።

የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት ትምህርት ተቋሞች አገልግሎታቸዉ ከሃይማኖታዊ፣ ፖለቲካዊና ባህላዊ መድሎዎች ነፃ መሆን እንዳለበት ይደነግጋል። ይሁን እንጂ ተግባራዊዉ እዉነታ ተፃራሪዉ በመሆኑ አንቀፁን «የወረቀት ነብር» ሲሉም የሚተቹ አሉ። በጉዳዩ ላይ ከፌደራልም ሆነ ከክልሎቹ ማብራሪያ ለማገኘት ያደረግነዉ ሙከራ አልተሳካም።

መርጋ ዮናስ  ሸዋዬ ለገሠ 

Share and Enjoy !

Shares
Related stories   ኢትዮጵያን የምታለቅሰው በ"መሪዎቿና በውድ ልጆቿ" ነውና !! ጆሮ ያለው ይስማ!!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *