7ኛው የኦሮሞ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት (ኦህዴድ) ድርጅታዊ ኮንፍረንስ የ10 ዓመት የስራ እድል ፈጠራ ስትራቴጂ በማዘጋጀት ዛሬ ተጠናቋል።

ኮንፈረንሱ የኦህዴድ ሊቀመንበር አቶ ለማ መገርሳ፣ ምክትል ሊቀመንበር ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ እና የድርጅቱ ጽህፈት ቤት ሃላፊ ዶክተር አብይ አህመድ በተገኙበት ባለ10 ነጥብ የአቋም መግለጫ በማውጣት ዛሬ ፍፄሜውን አግኝቷል።
ከጥቅምት 19 እስከ 23 ቀን 2010 ዓ.ም ድረስ ሲካሄድ የቆየው ኮንፍረንሱ የተለያዩ ጉዳዮች ላይ ስምምነት ተደርሶበታል። በኦህዴድ ሰባተኛ ድርጅታዊ ኮንፍረንስ ለ4 ሚሊየን ስራ አጦች የስራ እድል መፍጠር የሚያስችል የ10 ዓመት ስትራቴጂ ተዘጋጅቷል።

የኮንፍረንሱ ተሳታፊዎች የጥልቅ ተሃድሶ እንቅስቃሴው ከህዝቡ ጋር መግባባት ላይ የተደረሰበትና የክልሉን ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ችግሮች በመፍታት ረገድ ውጤት የተመዘገበበት ነው ብለዋል። በኮንፍረንሱ በጥልቅ ተሃድሶ ወቅት የተሰጡ አቅጣጫዎች አተገባበር ተገምግሞ፥ ቀጣይ የስራ አቅጣጫ ተቀምጧል።
የህዝቡን አንድነት በማስቀጠል የፖለቲካ የኢኮኖሚና የማህበራዊ ተጠቃሚነቱን በዲሞክራሲያዊ መንገድ ለማረጋገጥ እንደሚሰራም ተገልጿል። የዲሞክራሲ ስርዓቱን በማጠናከር ኢትዮጵያዊ አንድነትን ለመገንባት እንደሚሰራ ነው የተነገረው። በክልሉ የሚኖሩ ብሔር ብሔረሰቦች የመዘዋወር እና የመስራት መብታቸው ተጠብቆ፥ የትግል አካል እንዲሆኑ ይሰራል ተብሏል።

opdo

የክልሉ መንግስት ከህዝብ ጋር በመሆን ለተነሱ ችግሮች መፍትሄ ለመስጠት እያደረገ ያለው ተግባር ገና የመጀመሪያ ምእራፍ ላይ ቢሆንም፥ እየተመዘገቡ ያሉ ውጤቶች ግን አመርቂ መሆናቸውን የኮንፍረንሱ ተሳታፊዎች አንስተዋል።

የኦሮሞ ህዝብ ባለው ሀብት እኩል ተጠቃሚ መሆን እንደሚገባው እና በእርሻ ስራ ብቻ ሳይሆን እሴት ጨምሮ እስከ ውጭ ሀገራት ድረስ በመላክ ተጠቀሚ እንዲሆን መስራት አለብን የሚለው ላይ መስማማታቸውም ነው የተነገረው።

ከጫት ንግድ ጋር ተያይዞ ለሚስተዋለው ችግርም አስፈላጊ መፍትሄ በመስጠት የክልሉ አርሶ አደሮች እና ነጋዴዎች ከንግዱ ማግኘት የሚገባቸውን ጥቅም እንዲያገኙ እንደሚሰራም በኮንፍረንሱ ላይ ከመግባባት ተደርሷል።

የኦህዴድ ደርጅታዊ ኮንፍረንስ ተሳታፊዎቹ ለወጣቶች የስራ እድል ፈጠራ የተጀመሩ ስራዎች ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው ነው የገለፁት።

በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች እየተከሰቱ ባሉ ሁከቶች የዜጎች ህይወት ማለፍ እና ደም መፍሰስ በአፋጣኝ መቆም አለበት የሚል አቋም ይዘዋል።

በተለይም በክልሉ እያጋጠሙ ለሚገኙ ችግሮች ዘላቂ መፍትሄ ለማስቀመጥ ውስጣዊ የድርጅቱ እና አመራሮች ችግሮች መፍታት ወሳኝ መሆኑ በኮንፍረንሱ በትኩረት ከተመከረባቸው ጉዳዮች መካከል ይገኝበታል።

በህገ መንግስቱ ላይ በተቀመጠው መሰረት የኦሮሚያ ክልል ከአዲስ አበባ ከተማ ማግኘት ያለበት ጥቅም ጉዳይም በፍጥነት ለህዝቡ ቀርቦ ውይይት እንዲደረግበት እና በሚመለከተው አካል ፀድቆ ስራ ላይ እንዲውልም የኮንፍረንሱ ተሳታፊዎች ጠይቀዋል።

ከዚህም በተጨማሪ በኮንፈረንሱ በፌዴራል ስርዓት፣ በኢኮኖሚ ተጠቃሚነት እና የክልሉን ሰላምና ፀጥታ አስተማማኝ ማድረግ ላይ ሰፊ ውይይት ተደርጎባቸው አቅጣጫ ተቀምጧል።

በኮንፍረንሱ የተቀመጡ አቅጣጫዎችን ለማሳካት አመራሩ፣ አባላት፣ ወጣትና ሴቶች፣ የመንግስት ሰራተኛ እና ህዝቡ የድርሻቸውን እንዲወጡ ጥሪ ቀርቧል። (ኤፍ.ቢ.ሲ)

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *