Skip to content

በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴና በንጉሥ ኦላቭ ሃኮን የተጠነሰሰው ወዳጅነት

የታሪክ ድርሳናት እንደሚያሳዩት፣ ግጭቱን የቀሰቀሱት የጣሊያን ወታደሮች ነበሩ፡፡ ነገር ግን የጣሊያን መሪ የነበረው ቤኒቶ ሞሶሎኒ ራስን ለመከላከል የተወሰደ ዕርምጃ እንደሆነ በመግለጽ፣ ድርጊቱ በየትኛውም በዓለም አቀፍ ስምምነት ለዳኝነት የሚቀርብ አለመሆኑን ተከራከረ፡፡ እንዲያውም በግጭቱ ለጠፋው የወታደሮች ሕይወት ካሳ፣ አካባቢውም የጣሊያን ቅኝ ግዛት ሆኖ እንዲታወቅ የሚል የይገባኛል ጥያቄ አነሳ፡፡

በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴና በንጉሥ ኦላቭ ሃኮን የተጠነሰሰው ወዳጅነት

ነገሩ ‹‹ጅራፍ ራሱ ገርፎ ራሱ ይጮሀል›› ዓይነት የሆነባቸው አፄ ኃይለ ሥላሴም የፋሺስትን ጥያቄ ባለመቀበል ነገሩን ለሊግ ኦፍ ኔሽን (ለዓለም መንግሥታት ማኅበር) አቤት አሉ፡፡ ሊግ ኦፍ ኔሽንም ሁለቱን አገሮች የሚያስማሙ የተለያዩ የመፍትሔ ሀሳቦች አቀረበ፡፡ የሚነሱት የመፍትሔ ሐሳቦች ያልተዋጡለት ቤኒቶ ሞሶሎኒ ኢትዮጵያን ለመውረር ሠራዊቱን ያደራጅ ጀመር፡፡

መስከረም 23 ቀን 1928 ዓ.ም. የጣሊያን ጦር የኢትዮጵያን የተወሰኑ ክፍሎች ወረረ፡፡ በመንፈቁም አዲስ አበባን መቆጣጠር ቻለ፡፡ አፄ ኃይለ ሥላሴም ጉዳዩን በጄኔቫ ተገኝተው የጣሊያን ጦር አገራቸውን በግፍ እንደወረረው ድርጊቱን በማውገዝ ሊጉ ምላሽ እንዲሰጣቸው ታሪካዊ ንግግር አደረጉ፡፡ ነገር ግን ከሊጉ የጠበቁትን ምላሽ አላገኙም ነበር፡፡ ሊግ ኦፍ ኔሽን በግፍ የተወረረችውን አገር ነፃ እንድትሆን ግፊት በማድረግ ፈንታ የጣሊያን ግዛት ሆና እንድትኖር እውቅና ሰጠ፡፡ አፄውም አገሪቱ ነፃ እስክትወጣ በስደት በእንግሊዝ አገር ለመቆየት ተገደዱ፡፡

በዚህ አጋጣሚ ነበር እንደ እሳቸው እንግሊዝ አገር በስደት ይኖሩ ከነበሩት ከኖርዌው ንጉሥ ኦላቭ ሃኮን ጋር የተገናኙት፡፡ ንጉሡ አገራቸውን ለቀው ወደ እንግሊዝ የተሰደዱበት አጋጣሚም ከአፄ ኃይለ ሥላሴ ጋር ተመሳሳይ ነበር፡፡ የጣሊያን አጋር የነበረውና በሒትለር የሚመራው የጀርመን መንግሥት ኖርዌይን በመውረሩ ነበር ንጉሡ ወደ እንግሊዝ የተሰደዱት፡፡ በተመሳሳይ የታሪክ አጋጣሚ ለስደት የተዳረጉት ነገሥታቱ ወዳጅነት መሠረቱ፡፡ በዚህ አጋጣሚ የተመሠረተው የሁለቱ ወዳጅነት ነገሮች ተረጋግተው ወደየመንበራቸው ከተመለሱ በኋላ ተጠናክሮ ቀጠለ፡፡

 

በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴና በንጉሥ ኦላቭ ሃኮን የተጠነሰሰው ወዳጅነት

ለልዑል አልጋ ወራሽ ሃኮን ማግነስና ለልዕልት ሜቲ ሜሪት ፕሬዚዳንት ሙላቱ ተሾመ በብሔራዊ ቤተ መንግሥት አቀባበል ባደረጉላቸው ወቅት

አፄ ኃይለ ሥላሴ  በ1958 ዓ.ም. ወደ ኖርዌይ ተጉዘው የጓዳቸውን አገር ጎበኙ፡፡ የኖርዌዩ ጓዳቸው ንጉሥ ሃኮንም በ1959 ዓ.ም. ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት አጸፋውን መለሱ፡፡ በዚህ የተጀመረው የሁለቱ አገሮች ግንኙነት በ1987 ዓ.ም. በተፈረመው የሁለትዮሽ ስምምነት ተጠናክሮ ቀጠለ፡፡ ስምምነቱን ተከትሎም ኖርዌይ በአፍሪካ ትልቁ የሆነውን ኤምባሲዋን በአዲስ አበባ ከፈተች፡፡ ኖርዌይ በተለያዩ የልማት ጉዳዮች ድጋፍ ከምታደርግላቸው 12 አገሮች መካከልም ኢትዮጵያ አንዷ ነች፡፡

በዚያች ቀውጢ ወቅት የተፈጠረው የእነዚህ መሪዎች ጉድኝት ከነሱ አልፎ በአገሮቹ መካከል መሆኑ ያስደሰተ ነበር፡፡ ይህንን ታሪካዊ ግንኙነት ይበልጥ እንደሚያጠናክር የታመነበት አጋጣሚ በዚህ ሳምንት ተደግሟል፡፡ የኖርዌይ ንጉሠ ነገሥት መንግሥት አልጋ ወራሽ ልዑል ሃኮን ማግኑስ ከባለቤታቸው ከልዕልት ሜቴ ሜሪት ጋር ኢትዮጵያን ለመጎብኘት አዲስ አበባ ጥቅምት 28 ቀን 2010 ዓ.ም. ተገኝተው ነበር፡፡

በአሁኑ ወቅት ያለው የኖርዌይ ንጉሥ ሀራልድ አምስተኛ ይባላሉ። በኢትዮጵያ የሦስት ቀናት ጉብኝት ያደረጉት ልዑል አልጋ ወራሽ ማግኑስ ወራሻቸው ናቸው፡፡ ጉብኝታቸው ዘመን ተሻጋሪ የሆነውን የሁለቱን አገሮች ግንኙነት ይበልጥ እንዲጠናከር የሚያደርገው እንደሆነ ተነግሯል፡፡

በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴና በንጉሥ ኦላቭ ሃኮን የተጠነሰሰው ወዳጅነት

በቤተ መንግሥት በነበራቸው ቆይታ ፕሬዚዳንቱና ልዑል አልጋ ወራሹ ሰባት አሠርታት ያስቆጠረው የሁለቱ አገሮች ግንኙነት ወደ አዲስ ምዕራፍ ለማሸጋገር በሚቻልባቸውጉዳዮች ላይ መክረዋል፡፡ የጉብኝቱ ዋነኛ ትኩረት ሁለቱ አገሮች ተባብረው በሚሰሩባቸው ጤና፣ ትምህርት፣ አየር ንብረት ለውጥና ዘላቂ የመሬት ሃብት ልማት አጠቃቀም፣ የግሉዘርፍ ዕድገትና ልማት፣ ስደትና ፍልሰት ጉዳዮች ላይ ያለውን ግንኙነት የበለጠ ለማጠናከር ሲሆን፤ ግንኙነቱ ወደ ተሻለ ስትራቴጂካዊ ትብብር በሚያድግበት ሁኔታ ላይምተነጋግረዋል፡፡

ኢትዮጵያ ከኖርዌይ ጋር ያላትን ታሪካዊ ግንኙነት በሁሉም ዘርፎች ለማሳደግ ዝግጁ መሆኗን ፕሬዚዳንት ሙላቱ ተናግረዋል። ኢትዮጵያ በገነባቻቸውና በግንባታ ላይ ባሉ ሰፋፊናምቹ የኢንዱስትሪ ዞኖች፥ የኖርዌይ ባለሃብቶች መጥተው በተለያዩ የኢንቨስትመንት መስኮች ቢሰማሩ ውጤታማ እንደሚሆኑም አብራርተዋል፡፡ ልዑል ሃኮን በበኩላቸው፣ ከ51 ዓመት በኋላ በንጉሣዊ ቤተሰብ ደረጃ የተደረገው ጉብኝታቸው አገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር ላላት ግንኙነት የላቀ ግምት ማሳያ ነው ብለዋል።

አልጋ ወራሹ ባለቤታቸውን ልዕልት ሜቲ ማሪትን አስከትለው ነበር የመጡት፡፡ ልዕልቷ በአዲስ አበባ ሒልተን ተዘጋጅቶ በነበረው የንግድ ዐውደ ጥናት ላይ ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር ‹‹ይህ ለኛ በጣም የተለየ ነገር ነው፡፡ ሁለታችንም ይህንን በጉጉት ስንጠባበቀው የነበረ አጋጣሚ ነው፡፡ የሁለቱም አገሮች ግንኙነት በጠንካራ መሰረት ላይ ያረፈ፣ በእውነተኛ ጓደኝነት የተጀመረ ነው፤›› በማለት ለመጀመሪያ ጊዜ ኢትዮጵያን በመጎብኘታቸው ደስተኛ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

አልጋ ወራሹ አያታቸው ንጉሥ ኦላቭ ሃኮን በ1959 ዓ.ም. ኢትዮጵያን በጎበኙበት ወቅት ያጋጠሟቸውንና ያዩዋውን ነገሮች በጽሑፍ አስፍረው ነበርና ስለአገሪቱ የተወሰነ ነገር ቀደም ብለው ለማወቅ ችለዋል፡፡ ወደ ኢትዮጵያ ሲመጡ ይህ የመጀመሪያቸው ቢሆንም፣ ለአገሪቱ የእንግድነት ስሜት እንዳያድርባቸው ማድረጉን ተናግረዋል፡፡ በሕዝቡ የእንግዳ አቀባበል ደስተኛ መሆናቸውን፣ ይህም ቀደም ብለው በአያታቸው ማስታወሻ ውስጥ ያነበቡትና አይተው ያረጋገጡት መሆኑንም ልዕልቷ ገልፀዋል፡፡

 ‹‹የአየር ንብረት ለውጥ በአሁኑ ወቅት አንገብጋቢ የዓለም ጉዳይ ነው፡፡ የኢትዮጵያና የኖርዌይ የሁለትዮሽ ትብብርም በቀጥታ ከዚህ ጉዳይ ጋር የተገናኘ ነው፡፡ ትብብራችን በደን ጥበቃ፣ ቀጣይነት ባለው የአስተራረስ ዘዴ እንዲሁም በታዳሽ ኃይሎች ልማት ላይ ትኩረቱን ያደረገ ነው፤›› ብለዋል፡፡ የአገሮቹ የሁለትዮሽ ግንኙነት በንግድና በኢንቨስትመንት ረገድም መንፀባረቅ መጀመሩን፣ የኖርዌይ ባለሀብቶችም በኢትዮጵያ ኢንቨስት የማድረግ ፍላጎታቸው እያደገ መምጣቱን ልዕልቷ ገልፀዋል፡፡

‹‹ለንግድ ዕድገት ዋነኛው ነገር በቂ የመሠረተ ልማት አቅርቦት መኖር ነው፡፡ ምርትና አገልግሎትን ለገበያ ለማቅረብ ጥሩ የመንገድ ዝርጋታ መኖር ወሳኝ ነው፡፡ በዚህ ረገድ ኢትዮጵያ ጥሩ ሠርታለች፡፡ ይህም አገሪቱን ለንግድ፣ ለገበያና ለኢንቨስትመንት ምቹና ሳቢ ያደርጋታል፤›› ብለዋል፡፡

የሁለቱ አገሮች ትብብር ከፀጥታና ደኅንነት ጀምሮ የአየር ንብረት ለውጥ፣ የፆታ እኩልነት፣ ትምህርት፣ የግሉ ዘርፍ ዕድገት ላይ ያተኮረ ነው፡፡ በእነዚህ ጉዳዮች ላይ የሚደረጉ የድጋፍና የትብብር ስራዎችን በቀጥታና በተዘዋዋሪ መንገድ የሚያከናውኑ ሲሆን፣ ከ1962 ዓ.ም. ጀምሮ በኢትዮጵያ በተለያዩ ማኅበራዊ ጉዳዮች ላይ በመሥራት ላይ የሚገኘው የኖርዌጅያን ሚሺን ማኅበረሰብ በዚህ ረገድ በግንባር ቀደምትነት ሊጠቀስ ይችላል፡፡ በኢትዮጵያ ከሚሠሩ ዓለም አቀፍ ተቋማት መካከል ዩኤንዲፒ፣ ዩኒሴፍ፣ አይኤልኦ፣ አይኦኤም ከኖርዌይ ድጋፍ የሚደረግላቸው ዋና ዋናዎቹ ናቸው፡፡

በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ (ዕትዕ) የያዛቸው ልዩ ልዩ እቅዶችን ለማሳካት በሚደረገው ርብርብም ኖርዌይ የተለያዩ ድጋፎች ታደርጋለች፡፡ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን በመከላከል፣ የፆታ ዕኩልነት እንዲሰፍን ጥረት በማድረግ፣ በኢኮኖሚ ደካማ የሆኑ ሴቶችን በማብቃት፣ ፆታዊ ጥቃቶችን በመከላከል፣ በሥነ ተዋልዶ ጤና እና መብት እንዲሁም በኤችአይቪ ላይ የተለያዩ ተግባራትን ታከናውናለች፡፡  እ.ኤ.አ ከ2012 እስከ 2016 ድረስ የፆታ እኩልነትን፣ ሴቶችን ከጥቃት መከላከልን፣ ሴቶችን ማብቃትን፣ የትምህርት ተደራሽነትን፣ የአመራር ብቃትን በመሳሰሉት ማኅበራዊ ጉዳዮች ላይ 16.6 ሚሊዮን የኖርዌይ ክሮነር (1 ክሮነር 0.12 የአሜሪካ ዶላር ነው) በጀት መድባ ስትሠራ ቆይታለች፡፡ ፕሮግራሙ እ.ኤ.አ እስከ 2018 እንዲቀጥል የማድረግ ሐሳብም አላት፡፡

ከማኅበረሰቡ የተገለሉ የኅብረተሰቡ ክፍሎችን በኢኮኖሚ ራሳቸውን እንዲችሉ የተለያዩ የክህሎት ሥልጠናና ሌሎችም ኑሯቸውን ለመቀየር በሚችሉ ድጋፎች ላይም ድጋፍ ታደርጋለች፡፡ በእነዚህ የማኅበረሰቡ ክፍሎች ላይ የሚከናወኑ ሥራዎችን እ.ኤ.አ ከ2007 ጀምሮ ድጋፍ ስታደርግ መቆየቷን፣ እስካሁን በዚህ ረገድ ለተሰሩትም 200 ሚሊዮን ክሮነር ወጪ ማድረጓን በኢትዮጵያ ከሚገኘው የኖርዌይ ኤምባሲ የተገኘው መረጃ ያሳያል፡፡

አገሪቱ ስደትን በተመለከተ በኢትዮጵያ የሚገኙ ስደተኖችን ኑሮ ለማሻሻልና ስደትን እንደ አንድ አማራጭ እንዳይጠቀሙ ለማድረግ ሽሬ በሚገኘው የስደተኞች ካምፕ እየሠራች ትገኛለች፡፡ በካምፑ ለሚገኙ ስደተኛ ወጣቶችና ሴቶች ተምረው  ራሳቸውን እንዲችሉ፣ ሴቶችና ወጣቶች ትምህርት እንዲያገኙ ለማስቻልም ትምህርት ቤት ተገንብቶ አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል፡፡ ትምህርት ቤቱ አገልግሎት መስጠት ከጀመረ ወዲህ እስካሁን 3033 የሚሆኑ ስደተኞች ትምህርት አግኝተዋል፡፡ ልዑሉም ይህንን የስደተኞች ካምፕ ሳይጎበኙ አልተመለሱም፡፡

በአሁኑ ወቅት በዓለም ላይ በሕገ መንግሥታዊ የዘውድ ሥርአት የሚመሩ ኖርዌይን ጨምሮ 50 አገሮች ይገኛሉ፡፡ ከእነዚህም መካከል ታይላንድ፣ ስፔን፣ ስዊድን፣ ካታር፣ ካምቦዲያ፣ ባህሬን፣ ኒውዚላንድ፣ ኔዘርላንድ፣ ሞሮኮ፣ ሞናኮ፣ ማሌዥያ፣ ዮርዳኖስ፣ ጃፓን፣ እንግሊዝ፣ ካናዳና ሉክሰምበርግ ይጠቀሳሉ፡፡ እነዚህ ነገሥታት የፖለቲካ ተሳትፏቸው የተገደበ ቢሆንም በተለያዩ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ትልቅ ተሳትፎ አላቸው፡፡ ለየአገራቸው የዴሞክራሲ እድገትም እንደ ምልክት ናቸው፡፡

ምስልና ዜና ሪፖርተር አማርኛ    ሻሂዳ ሁሴን  ሪፖርተር

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Copyright - zaggolenews. All rights reserved.

Read previous post:
ከአይኤስ ጋር ግንኙነት አላቸው የተባሉ 26 ተጠርጣሪዎች ተከሰሱ፤ “የጅሐድ ጦርነት ለማወጅ ነበር”

Via Reporter Amharic በኢትዮጵያ የጅሐድ ጦርነት ለማወጅ ዝግጅት እያደረጉ ነበር ተብሏል አይኤስ ከሚባለው የሽብር ቡድን ጋር ግንኙነት አላቸው የተባሉና በአዲስ...

Close