ሼሁ፤ በችግራችን ወቅትና በዕድገታችን የጉዞ ምዕራፎች ያልተለዩን፣ ታምነው የተገኙልን፤ ወትሮም ከማይረጋውና ከሚበጸበጸው የመካከለኛው ምሥራቅ ጂኦፖሊቲካዊ ነፋስ ጋራ አብረው የማይነጉዱና የማይናወጹ የብሔራዊ ጥቅማችን ደጀን ናቸው

በፋኑኤል ክንፉ

ከክብር ዶክተር ሼህ ሙሐመድ ሁሴን ዓሊ አል-አሙዲ ጎን የምንቆመው በሁለት መሠረታዊ ምክንያቶች ነው፡፡ አንደኛው፣ ለእናት ሀገራቸው የማይናወጥ ፍቅር ስላላቸው ነው፡፡ ሁለተኛው፣ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም ጋራ ትርጉም ያለው ግንኙነት ስላላቸው ነው፡፡

ዶክተር ሼህ ሙሐመድ ሁሴን ዓሊ አል-አሙዲ፣ ከዐሥርት ዓመታት በፊት ኢትዮጵያ ለእርሳቸው ምን እንደኾነችና ኢትዮጵያ ውስጥ ኢንቨስት ማድረግ ለምን እንደፈለጉና እንደወሰኑ የተናገሩትን ማስቀመጥ፣ የአቋቋማችንን አግባብነት ያስረዳል፡፡ እንዲህ ነበር ያሉት፡-

 “Ethiopia means so much to me that even my friends wonder about my investment decision in the country. When I intent in Ethiopia, my decision to invest are based on what I feel in my heart for my motherland. All my other investment decisions in the rest of the world are based on calculated risks and benefits.

 …Ethiopia is our soul and the essence of our existence. We should not expect others to transform our motherland into a developed and a prosperous country. It is our national duty and solemn responsibility, to fully commit ourselves to develop Ethiopia and free our countrymen from shackles of abject poverty and under-development.”

(ኢትዮጵያ ለእኔ ብዙ ነገሬ ነች፡፡ ወዳጆቼ፣ በኢትዮጵያ ኢንቨስት ለማድረግ መወሰኔ ይገርማቸዋል፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ ኢንቨስት ለማድረግ ስወጥን፣ በልቤ ውስጥ ስለ እናት ሀገሬ በሚሰማኝ ስሜት ላይ ተመሥርቼ ነው፡፡ የተቀረው ዓለም የኢንቨስትመት ውሳኔዬ፣ የተሰላ ኪሳራና ትርፍን መነሻ ያደረገ ነው፡፡

ኢትዮጵያ፥ የእኛ እስትንፋስ፣ የህላዌያችን ምክንያትም መሠረትም ናት፡፡ እናት ሀገራችንን፣ ከውጭ የሚመጡ ኃይሎች በምጣኔ ሀብታዊ ሽግግር እንዲያሳድጓትና እንዲያበለጽጓት መጠበቅ የለብንም፡፡ ይህን ማድረግ የእኛ ብሔራዊ ግዴታና ሓላፊነት ነው፡፡ ለሃገራችን እድገት ቁርጠኛ በመኾን ሕዝባችንን ጠፍሮ ከያዘው ድህነትና ኋላ ቀርነት ነፃ ማውጣት አለብን፡፡)

የክብር ዶክተር ሼክ ሙሐመድ ሁሴን ዓሊ አል-አሙዲ፣ በዐደባባይ በዚህ መልኩ ለሕዝብ የተናገሩትን ቃላቸውን ተግባራዊ በማድረግ ከመንግሥት ቀጥሎ ሁለተኛው ቀጣሪና የኢኮኖሚ ሞተር ለመኾን የበቁ የሀገራዊ ልማታችን አለኝታ ናቸው፡፡  

በ2009 ዓ.ም.፣ በሚሌኒየም አዳራሽ፣ የሚድሮክ ኢትዮጵያ ዓመታዊ በዓል ሲከበር፣ ሼህ ዓሊ አል-አሙዲ በራሳቸው አንደበት እንዳስታወቁት፤ ከ110 ሺሕ በላይ ለሚኾኑ ኢትዮጵያውያን የሥራ ዕድል መፍጠር ችለዋል፤ እንዲሁም፣ በሼኹ ባለቤትነትና የቅርብ ክትትል የሚተዳደሩ ከ77 በላይ ኩባንያዎች በሀገር ውስጥ በሥራ ላይ እንደሚገኙ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡

ዶክተር ሼህ ሙሐመድ ሁሴን ዓሊ አል-አሙዲ፣ ኢትዮጵያ ካፈራቻቸው ምርጥ የቁርጥ ቀን ልጆች፣ አንዱና ተጠቃሹ ናቸው፡፡ ሁሉንም የባለሀብቱን ኢኮኖሚያዊ አስተዋፅኦ እና ሰብአዊ ረድኤት መዘርዘር ሰፊ ጊዜና ቦታ የሚፈልግ ቢኾንም፣ ሁለት የማይታለፉ አሻራቸውን ማስቀመጥ ግን ከፍ ያለ ተገቢነት ይኖረዋል፡፡

አንደኛው፤ የኢትዮጵያ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ቁመና፣ ለአንድ ዓለም አቀፍ ኢንቨስተር አስተማማኝ ባልነበረባቸው በ1980ዎቹ ፈታኝና ታሪካዊ ዓመታት፣ የመጀመሪያው ግንባር ቀደም ኢንቨስተር በመኾን በሀገራቸውና በሕዝባቸው ላይ ያላቸውን ጠንካራ እምነት ለዓለም አቀፉ ኅብረተሰብ አሳይተዋል፡፡ የእርሳቸውን ፈለግ በመከተልም፣ በርካታ ዓለም አቀፍ ኢንቨስተሮች በሀገራችን ዕድገት ላይ ተሳታፊ ለመኾን በቅተዋል፡፡

ሁለተኛው፤ ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የኤሌትሪክ ኃይል ማመንጫ፣ የአንድ ነጥብ አምስት ቢሊዮን ብር ቦንድ ግዢ መፈጸማቸው፣ ዳግም ለሀገራቸውና ለሕዝባቸው ያላቸውን ታማኝነት ያረጋገጡበት ታሪካዊ ወቅት ነው፡፡ በተለይ ይህ ርምጃቸው ከእርሳቸው ዓለም አቀፍ የኢንቨስትመንት ተደራሽነት አንጻር ብዙ ዋጋ ሊያስከፍላቸው የሚችል ቢኾንም፣ ለሀገራቸውና ለሕዝባቸው ያላቸውን የጋለ ወዳጅነት በተግባር ያሳዩበት ቋሚ ምስክርነት ነው፡፡

በማንኛውም ኹኔታ ውስጥ ቢገኙ፣ ከክቡር ዶክተር ሼህ ሙሐመድ ሁሴን ዓሊ አል-አሙዲ ጋራ ከጎናቸው እንቆማለን የምንለው፣ በእነኚህ ተጨባጭ መነሻዎች እንጅ፣ በግልብ ወይም በማይቆጠሩ እውነታዎች ላይ ቆመን አይደለም፡፡ ሼሁ፤ በችግራችን ወቅትና በዕድገታችን የጉዞ ምዕራፎች ያልተለዩን፣ ታምነው የተገኙልን፤ ወትሮም ከማይረጋውና ከሚበጸበጸው የመካከለኛው ምሥራቅ ጂኦፖሊቲካዊ ነፋስ ጋራ አብረው የማይነጉዱና የማይናወጹ የብሔራዊ ጥቅማችን ደጀን ናቸው፡፡

 የዶክተር ሼህ ሙሐመድ ሁሴን ዓሊ አል-አሙዲ ጉዳይ፣ ለእኛ የአንድ ግለሰብ ጉዳይ ሳይኾን፣ የብሔራዊ ጥቅማችንና ለማይናወጸው ኢትዮጵያዊነታቸው አጋርነታችንን የማረጋገጥ ጉዳይ ነው፡፡ ስለዚህም ሼሁ፣ በማንኛውም ኹኔታ ውስጥ ቢገኙ፣ ከጎናቸው እንቆማለን!!

ዝግጅት ክፍሉ – ይህ ጽሁፍ የሰንደቅ ጋዜጣና የጸሃፊው አቋም ብቻ ነው።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *