• ጥርት – ጥንቅቅ ያለ፣ የተስተካከለና ቅጥ ያለው ሃሳብ፣ “ለመጥፋት የተቃረበ ብርቅ ቅርስ” እየሆነብን ነው።

  • በሃሳብ ውዥንብር መደናበርና ማደናበር፣ በጣም ከመለመዱ የተነሳ፣ “መደበኛ የፖለቲካ ባህርይ” እየሆነ ነው።

 

“አንድ የለስላሳ መጠጥ አምራች ኩባንያና፣ የታሸገ ውሃ የሚያመርት ሌላ ኩባንያ ለመቀላቀል ሞክረዋል” ተብለው፣ በመንግስት ቅጣት ሲወሰንባቸው አይተናል። “ሞኖፖል”ን የሚፈጥር ተግባር ፈፀሙ በሚል ውንጀላ ነው የተቀጡት። የለስላሳ መጠጥ ሞኖፖል? ይሄ የሚያሳስበን ከሆነ ያስቃል። 
በተቃራኒው ደግሞ፣ የግል ባንኮች ሳይፈልጉ እንዲዋሃዱ የሚያስገደድ ፖሊሲ ተዘጋጅቷል። ለምን? “ሞኖፖል” የሚለው ወሬ ከመቼው እንደተረሳ ባይታወቅም፣… ባለስልጣናት ሌላ ብዙ ማብራሪያና ሃተታ ከማቅረብ አይመለሱም – ኩባንያዎች በግድ እንዲዋሃዱ ማዘዝ አስፈላጊ መሆኑን ይደሰኩራሉ። በእርግጥ፣ እንዲሁ አስገዳጅ ፖሊሲ ማዘጋጀት ቢያሰኛቸውስ፣ ማን ይከለክላቸዋል? ማለቴ፣ ባለስልጣናት፣… የግል ባንኮችን በዘፈቀደ እንዲዋሃዱ ማዘዝና ማንቆራጠጥ አሰኝቷቸው ከሆነስ? ለመዋሃድ የሞከሩ ኩባንያዎችን ደግሞ መቅጣት! 
ይሄ ብቸኛው የመደናበርና የማደናበር ገጠመኝ ሊሆን ይችላል ብላችሁ ካሰባችሁ ተሳስታችኋል። 
“ፋብሪካዎች፣ በየክልሉና በየአካባቢው በተመጣጣኝ ብዛት መስፋፋት አለባቸው” የሚል የኢኮኖሚ ፖሊሲ፣ ለኢትዮጵያ እንግዳ አይደለም። በየጊዜው ስንሰማው የነበረና አሁንም የምንሰማው፣ የቅዠት አለም ፖሊሲ ነው። ፋብሪካ፣ እንደ ወፍ ዘራሽ ቁጥቋጦ፣ በየቦታ ተራርቆ እንዲከፈት መጠበቅ፣… እና ማስገደድ፣ የጤና ሊሆን አይችልማ።
በተቃራኒው ደግሞ፣… ከኢንዱስትሪ ፓርክ ውጭ፣ ለፋብሪካዎች መሬት አይዘጋጅም፣ የኤሌክትሪክ መስመር አይዘረጋም የሚሉ የመንግስት ውሳኔዎችን እያየን ነው።
ውዥንብሩ፣ ይሄ ብቻ አይደለም። 
“ኢንቨስተር እንዲበዛና የስራ እድል እንዲበራከት እንፈልጋለን” ብለው የሚናገሩ ባለስልጣናት፣ እዚያው በዚያው ዞር ብለው፣ “የሃብት ልዩነት መጥበብ እንጂ መስፋት የለበትም” ብለው ይዝታሉ። ኧረ፣ የአገራችን ውዥንብር፣ ቁጥር ስፍር አጣ። ኧረ፣ ረጋ ብሎ ማሰብ ይሻላል። እንዴት ነው ነገረ!
ብዙ ሃብት ያፈራና በሰፊ ልዩነት ከአዳሜ የሚበልጥ ሚሊዮነር፣ ቢሊዮነር ኢንቨስተር እንዲፈጠር ወይም እንዲመጣ አይፈልጉም? የስራ እድል እንዲበራከት አይፈልጉም? ሁሉም እኩል ድሃ ከሆነማ፣ ሃብት የሚያፈራና የማያፈራ ሰው ሁሉ፣ ተመጣጣኝ ሃብት እንዲኖራቸው በሚል ሰበብ፣ የአንዱን ነጥቀን ለሌላው የምንበትን ከሆነማ… ተግቶ የሚሰራና የስራ እድል የሚፈጥር ሰው ይጠፋል። እኩል ድህነት ምኑ ይፈለጋል? 
መቼም፣ ብዙ ኢትዮጵያውያን፣ አሜሪካና አውሮፓ፣… አልያም ሳዑዲ አረቢያና ደቡብ አፍሪካ ለመሄድ የሚሞክሩት፣ “በሃብት የማይበልጡኝ የድህነት እኩዮቼ ናፈቁኝ፤… ሁሉም እኩል የሆነበት የድሃ አገር አሰኘኝ” በማለት አይደለም። ብዙ ባለሃብት ወዳለበት አገር፣ ሚሊዮነር ወደበረከተበት አገር ነው የሚሰደዱት። ይሄ በየእለቱ የምናየው እውነታ ነው። በእርግጥም፣ የስራ እድል የፈለገ ሰው፣ ባለሃብት እንዲበረክት መፈለግ አለበት።
ከሁለቱ አንዱን መምረጥ ነው – እኩል ድህነት አንዱ አማራጭ ነው። ሌላው አማራጭ፣ እንደየጥረቱ የአቅሙን ያህል የማደግ እድል… ነው። መንግስትም፣ አንዱን አቅጣጫ መምረጥ አለበት – ከመደናበርና ከማደናበር ለመላቀቅ።
ወይ የስራ እድልን የሚያስፋፉ ኢንቨስተሮች ያስፈልጋሉ – በሃብት የሚበልጡን ማለት ነው። ወይም ደግሞ፣ ኢንቨስተርና የስራ እድል አያስፈልጉም – “በሃብት ላለመበላለጥ” ማለት ነው። 
ወይስ፣ መደናበርና ማደናበር… ሱስ ሆኗል?       
ይሄ፣ ከተለመደው “የአመለካከት ብዥታ” የባሰ ነው። በዘፈቀደ የማደናበር ወይም የመደናበር በሽታ፣… ልትሉት ትችላላችሁ።
ግን፣ የዘፈቀደ የውዥንብር መድረክ፣ የመንግስት ብቻ አይደለም። በርካታ ተቃዋሚዎች፣ በርካታ ምሁራንና ዜጎችም፣ የውዥንብር መድረክ መሪዎችና ተዋናዮች ናቸው። 
“እዚህ አካባቢያችን ፋብሪካ ተተከለብን፣ ይሄ ከተማ ተስፋፋብን” የሚሉ ተቃውሞዎችን በየጊዜው እንሰማለን። ከመስማትም ያልፋል እንጂ። ከባድ ውዝግብ፣ ግጭትና ጥፋትም ሲፈጠር አይተናል። ከዚሁ ጎን ለጎን ደግሞ፣ በአካባቢያችን ፋብሪካ የለም፤ ይኸኛው ከተማ ተዘንግቶ አልተስፋፋም… የሚል ሃይለኛ ተቃውሞ ይራገባል።
ለነገሩ፣ የውዥንብር ፉክክር ይመስላል።
በመንግስት የተዘጋጀ አገራቀፍ ጉባኤ ላይ፣ እንደጉድ የተግለበለበ መፈክርና ፖሊሲ፣ ሌላ የመንግስት ጉባኤ ላይ እንክትክቱ ሲወጣ ማየት ትችላላችሁ።
“ብዙ ወጣቶች ከገጠር ወደ ከተማ እየፈለሱ መሆናቸው፣ አደገኛ ነው” ተብሎ በአገርአቀፍ ጉባኤ የተደሰኮረው በቅርቡ ነው – አመት አይሞላውም። እናም፣ ከአደጋ ለመዳን፣ የገጠር ወጣቶች እዚያው ባሉበት የስራ እድል ሊፈጠርላቸው ይገባል የሚል ፖሊሲ በጉባኤው ተበስሯል። “ፋብሪካ በየቦታው”… ብሎ እንማወጅ ቁጠሩት። 
በዚህ ወር እንደሰማነው ደግሞ፣ የገጠር ወጣቶች በብዛት ወደ ከተማ ካልፈለሱ፣ የኢኮኖሚ እድገትና እመርታ ጨርሶ አይታሰብም ተብሏል። እንዴት? ያው፤ እርሻ አያድግም – መሬት ስለሚጣበብ። ኢንዱስትሪም አያድግም – በቂ አምራችና ገበያተኛ ስለማያገኝ።
በአጭሩ፣ ፍልሰት ከሌለ፣ ‘ትራንስፎርሜሽን’ እንደማይኖር ተነግሮናል። ስለዚህ፣ ፍልሰት መኖር አለበት ማለት ነው። ይሄ ደግሞ፣ “ፋብሪካ፣ በኢንዱስትሪ ፓርኮች ብቻ” ከሚለው መፈክር ጋር ይቀራረባል።
“ምንድነው እንዲህ መምታታትና ማምታታት?” አያስብልም? አያስብልም። ለምን በሉ።
በሃሳብ ውዥንብር መደናበርና ማደናበር፣ በጣም ከመለመዱ የተነሳ፣ “እንደ መደበኛ የፖለቲካ ባህርይ” መቆጠር ጀምሯል። እንደ እንስሳ መደናበር? የብዙ ሰዎች መደበኛ ባህርይ?
ጥርትና ጥንቅቅ አድርጎ ማሰብና፣ ቅጥ ያለው የተስተካከለ ሃሳብ መያዝ… ዛሬ ዛሬ፣ “የዋህነት” ሆኖ የሚታያቸው ሰዎች ጥቂት አይደሉም። ወይ አለማወቅ!

Written by  ዮሃንስ ሰ addisadmass

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *