በኢትዮጵያ የፓርቲ ፖለቲካ ህይወት ውስጥ በርካታ ስብስቦች ተከስተው አልፈዋል። ከንጉሱ መጨረሻ የህቡዕ ድርጅቶች እስከ ደርግ የታጠቁ ሀይሎች እና የህውኅት/ኢህአዴግ ተቃዋሚ ፓርቲዎች በአይነታቸውም ሆነ በይዘታቸው ብዙ አደረጃጀቶች ታይተዋል፤ እየታዩም ነው። ሁሉም አደረጃጀቶች ማለት ይቻላል ከአንድ ሰው ወይም ከጥቂት ግለሰቦች ፍላጎት ማስፈፀሚያነት ያለፈ ድርጅታዊ ቁመና ሳይኖራቸው ወደ ታሪክነት ተቀይረዋል ።

አብዛኛዎቹ ሲመሰረቱ ከመረጡት/ከሾሙት መሪያቸው ያነሰ የታሪክ ቦታ ይዘው ፣ እንዴያውም አንዳንዶቹ የግለሰቡ የታሪክ ማሟያ ሆነው ይታያሉ። እገሌ/እነገሌ የዚህ ፓርቲ አባል/አባላት ናቸው ከሚባል ይልቅ ይሄ ድርጅት ወይም ፓርቲ የገሌ/የነእገሌ ነው መባልን በተደጋጋሚ ሰምተነዋል።

የፓርቲዎች የመቆሚያ መሠረት ተስማምተው ያፀደቁት ደንብና ፕሮግራም ሳይሆን በሙያ ብቃታቸው ወይም በፖለቲካ አመለካከታቸው ከፍ ያለ ቦታ ያላቸው የግለ-ሰቦች ስም ነው። የቅርብ ጊዜ ትውስታችን የሆነው ቅንጅትም ሆነ ከሱ በኋላ የተመሰረተው አንድነት ፓርቲ የዚህ ሰለባዎች ነበሩ። ዶ/ር እገሌን ፣ፕ/ር እከሌን አይተን ነው የመጣነው ያሉ ሰዎች ያን ሰዉ ባስቀመጡበት ቦታ ሲያጡት የፓርቲ ፖለቲካ እርም ብለው የጠፉ በርካቶች ናቸው። በፖለቲካ ህይወት ውስጥ ልዩነት መኖሩ ወይም ስህተት መፈጠሩ የሚጠበቅ ነው። የድርጀቱን ጥንካሬ እና የአባላቱን ስርዓት አክባሪነት የሚያሳየው ግን የተፈጠረው ልዩነት የሚፈታበት፣ ጥፋቱ የሚታረምበት መንገድ ነው።

የገዢው ተፅዕኖ እንዳለ ሆኖ በፓርቲዎቹ ውስጥ የተፈጠሩ ልዩነቶችና የተፈጸሙ ጥፋቶች ፓርቲዎችን ለዚህ የሚያበቁ ነበሩ የሚል ግምት የለኝም። ከዚያ ይልቅ መሪዎቹ ችግሮችን ለመፍታት የሄዱበት መንገድ ከፊተኛው ጥፋት በባሰ ለውድቀት ዳርጓቸዋል። በጣም የሚደንቀው ደግሞ ድርጅቶቹ ከወደቁም በኋላ የቀድሞዎቹ አመራሮች ችግሮችን በሀቀኝነት ነቅሰው ሲያወጡና ለጠፋው ጥፋት በግልጽ ኃላፊነት በመውሰድ፣ ይቅርታ ሲጠይቁና ለቀጣዩ ትውልድ ትምህርት ሰጥተው ሲያልፉ አለመታየቱ ነው።

ሰማያዊ ፓርቲም የፓርቲዎቹ ደንብ እና ፕሮግራም ብቻ ሳይሆን የአሰራር ችግራቸውም ወራሽ ነው። ዛሬ በሰማያዊ ፓርቲ ውስጥ በአባልነትም ሆነ በአመራርነት ያለን ሰዎች አብዛኞቻችን በቅንጅት እና በአንድነት ውስጥ ያለፍን ፣ የተፈጠሩ ክፍፍሎችንም የታዘብንና ለመሸምገለም የሞከርን ነን። ከአምስት ዓመት በፊት ከአንድነት ፓርቲ በአሠራር ልዩነት ተለይተን ወጥተን ሰማያዊን ስንመሰርት ችግሮች ዳግም አይከሰቱም ባይባልም በሰለጠነ መንገድ ለመፍታት ቃል በመግባት ነበር። በ2008 በግልጽ እንደታየው ችግሮች ሲከሰቱ እነሱን ለመፍታት የሄድንበት መንገድ ታላላቆቻችን ከሄዱበት የተለየ አልነበረም። ግለሰቦች ከፓርቲው ህግ በላይ ለመሆን ሲሞክሩ ተሰተውሏል። እኔ ከሌለሁ ፓርቲው የለም ሲባል በአግራሞት ተደምጧል፣ ተስማምተን ባፀደቅናቸው ህጎች አብረን ባቋቋምናቸው ተቋማት የተሰጡ ውሳኔዎችን አልቀበልም በማለት በተለመደው መንግድ ተቀጥሎበታል።

የተቋማት ውሳኔዎች ለራስ በሚስማማ መንገድ እስካልወሰኑ አናውቃቸውም ማለት ተጀመረ። ገንዘብ ሊወጣበትና ሊሰበሰብበት የተበጀው መንገድ ተገድፎ፣ ገንዘብ ሊውልበት ከታሰበው ዓላማ ወጥቶ የተሄደበት መንገድ ፣ ፓርቲው የግለሰቦች ሱቅ እስኪመስል ድረስ፣ የጠፋው የገንዘብ መጠን ተጠቅሶ የተጣራበት ሁኔታ በግልፅ የተቀመጠ ቢሆንም የአገዛዙ ሰዎች እንደሚሉት ያወጣነው መመሪያ የታችኛውን እንጂ እኛ አንመራበትም ተባለ።
ይህ ደግሞ ለፓርቲው ተቋማትና በስራቸው ላሉ አባላት ፈፅሞ ተቀባይነት የለውም። በፓርቲው መተዳደሪያ ደንብ መሠረት አመራሩንም ሆነ አባሉን የመዳኘት ስልጣን የተሰጠው አካል ያሳለፋቸውን ውሳኔዎች ለማስፈፀም ከአባላቱ የሞራል ግዴታ በስተቀር ምንም የማስገደጃ ሀይል እንደሌለው ይታወቃል። የቀድሞ የፓርቲው አመራር ግልጽ የሆነው ጥፋት የገንዘብ ምዝበራ ነው። አሁንም በግልፅ በቁጥር የተቀመጠ እዳ አለ። ከዚህ የተረፈው ተጨማማሪ ጥፋት ተከትሎ የመጣ በመሆኑ እንደዋና ለመቁጠር በእኔ ግምት እቸገራለሁ። በእኔ እምነት የፓርቲው ተቋማት ለዚህ ያቅማቸውን ታግለዋል፣ ተገቢውን ውሳኔ እንዳሳለፉም አምናለሁ።

እኔ ከእስር ተፈትቼ ወደ ፓርቲው በሄድኩበት ወቅት የነበረው ሁኔታ ይህን ቅጣትን የማስፈፀም እና ያለመቀበል ግብግብ ነበር። ግራቀኙን ሰምቼ ባገኘሁት መረጃ ተምረንበት እንለፍ የሚል አቋም ላይ ደርሼ አስማምቼ ለማለፍ የምችለውን ያህል ጥሬያለሁ። አልሆንም። የመጨረሻ ውሳኔ ሰጪ አካል ጉባኤ በመሆኑ ጉዳዩን ወደዚያ መውሰድ ግድ ሆነ። ሂደቱም ግልጽና ህጋዊ ነበር። ያም ሆኖ ሁሉም አማራጭ ሲሟጠጥ የሄድንበት እንጂ ሌላ መንገድ ቢኖር በዚህ በኩል አናልፍም ነበር።

ይሄንን ግልፅ መንገድ እንዳላወቁ በመሆን ጥላሸት ለመቀባት የሚደረገው መንፈራገጥ ትዝብት ላይ ይጥላል እንጂ ሌላ ትርፍ የለውም። ለመቀባት የተሞከረውን ጥላሸትም በላባችን ግፋ ቢል በደማችን እንደምናጥበው የሚሳት አይመስለኝም፤ ምክንያቱም የእናንተ እንቅፋት መሆን ተጠንቅቀን እንድንራመድ ያደርገናል እንጅ ከትግል ጉዟችን እንደማያቆመን እንተዋወቃለን፤ ማንነትም በሥራ ይገለጣል።

የአሁኑ ነጥቤ ከዚህ ከፍ ይላል። ይሄ ፓርቲ ከተመሰረተ አምስት አመታትን ብቻ ያስቆጥር እንጂ አመራሩና አባላቱ በሌሎች ፓርቲዎች ውስጥ የቆዩ ናቸዉ። በጊዜ፣ በገንዘብ፣ በእውቀት፣ በጉልበት፣ ለኢትዮጵያችን እና ለህዝባችን ነፃነት የታገሉ ናቸው። ስለሆነም ከፓርቲው ባላፈ ስለ-ትግሉና ስለ-ሀገር ማሰብ ግድ ይላቸዋል። ለትግሉና ለሀገር የተከፈለውን መሰዋዕትነት መገንዘብ ይገባቸዋል። ከዚህ በመነሳት የጠፋው ጠፍቷል፣ ከዚህ በኋላ እንዳይደገም ብለን የማለፍ የሞራል ብቃት ሊኖረን ያስፈልጋል። በፓርቲው በኩል ስርዓት ከማስያዝ ያለፈ ዓላማ የለም። በሌላው በኩል ግን እንደምናየው ለጥፋቱ ሌላ ጥፋት ከመጨመር ውጭ የፀፀት ስሜት አለመታየቱ ይቅር ለማለት እድሉን ጠባብ እንዳደረገው ቀጥሏል።

በእኔ በኩል የጠፋው ገንዘብ እንደማይመለስ ለመገመት ብዙም አልቸገርም። የመኢአድም፣ የቅንጅትም፣ የአንድነትም ገንዘብ እንዳልተመለሰ ሁሉ የሰማያዊም ይመለሳል ብዬ አልገምትም። ገንዘቡ የማይመለስ ከሆነ ደግሞ ገንዘቡንም ሰውንም ማጣት ኪሳራ ይመስለኛል።
በእኔ በኩል (የፓርቲው ውሳኔ እንደተጠበቀ ሆኖ) እንኳን ለቀድሞ የትግል አጋሮቼ፣ ሀገሬን ለሚጨቆነውና ህይወቴን ላመሰቃቀለው፣ ጤናዬን ላወከው ወያኔ/ኢህአዴግም ከዚህ በኋላ የምንገላገለው ከሆነ ይቅር የማለት የሞራል ብቃት አለኝ ብዬ አስባለሁ። እዚህ ላይ የህጋዊነት ነገር ሊነሳ ይችላል፣ ሆኖም ግን ሞራል ህግን ያግዛል እንጂ አይቃረንም። የሞራል ብቃቱ ካለ ብዙ ገደል መሻገር ይቻላል።

ዛሬ ሀገራችን እና እኛ ዜጎቿ ከገባንበት ቀውስ የሚያወጣ የሞራል ግዴታና የዜግነት ኃላፊነት አለብን። በማንኛውም ጊዜ ይህ ኃላፊነትና ግዴታ እንደሚኖር ብናውቅም የአሁኑ የተለየ እንደሆነ ለሁላችንም ግልፅ ይመስለኛል። ያንን ለማድረግ ይቅር ማለት ቀዳሚ ተግባር መሆን እንዳለበት ይሰማኛል። የፓርቲው አመራርና ተቋማትም ይህ የታሪካችን አካል እንደሚሆን በማሰብ የይቅርታ እጃችንን እስከሚቻለው ርቀት እንድንዘረጋ አደራ እላለሁ። እግዚአብሔር ረድቶን ከተሳካ ለአገራዊው ህልማችን መማሪያ ይሆነናል፤ ካልሆንም በሁለት ሁነቶች ርግጠኛ ነኝ – ትግሉም ይቀጥላል ፓርቲውም ድርጅት ይሆናል-ድርጅት ለመመስረት የሚያስፈልገውን መስዋዕትነት ከፍለንበታናልና።

ርግጥ ነው የምን ተቆጢታ እንደሚባለው ተሽቀዳድማችሁ ወደ ስድብና ፍረጃ በመሮጥ፤ የገባችሁበት ቅርቃርና የከሠከሳችሁት እሾህ የመመለሻ መንገዳችሁን እንዳጠረው መረዳት ይቻላል። ነገር ግን ለሀገር ሲባል መራራዋን እውነት ውጦ ከመመለስ ውጭ ምን አማራጭ አለ? ቀደም ሲል እንደገለፅንላችሁ ሂሳቡን ማወራረድና እዳችሁን መዝጋት ከቻላችሁ እድሜ ልካችሁን ሲከተላችሁ ከሚኖር ጥያቄ ትድናላችሁ።

የፓርቲውን ደንብ ማክበር እንደተጠበቀ ሆኖ በእኔ በኩል ግን ውድ ጊዜአቸውን ሰውተው እየጣሩ ስላሉ ሽማግሌዎች፣ በዚህ ፓርቲና በትግሉ ስም የሞቱትን እንደ ወጣት ሳሙኤል አወቀ አይነቱን ወንድም በማስታወስ ፤ ስለተንገላቱ፣ ስለተሰደዱ እና ስለታሰሩት ከሁሉ በላይ ስለ ሀገር ሲባል ሁሉን ለመተው ልቤ ትሁት ነው። እናተም እንዲህ ታስቡ እንደሆነ በመጀመሪያ ለሽማግሌዎች ክብር ስጡ፣ ከአፍራሽ እንቅስቃሴዎችና የፓርቲውን ሥም ለማጠልሸት በየቦታው ከምትጭሩት ነገር በመቆጠብ ይቅር ለማለት እድል ስጡን።

ደግ-ደጉን ያሳስበን፣ ሰላም።  Yeshiwas Assefa

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *