አጭር የምስል መግለጫየዚምባብዌ ጦር አባል መግለጫ ሲያነቡ
የዚምባብዌ ጦር ብሔራዊ ቴሌቪዥን ጣቢያ የሆነውን ዜድ ቢ ሲን ከተቆጣጠረ በኋላ ባወጣው መግለጫ “በወንጀለኞች ላይ ያነጣጠረ” እርምጃ በመውሰድ ላይ መሆኑን አስታውቋል።
ጦሩ “የመንግሥትን ስልጣን ለመቆጣጠር አልተንቀሳቀሰም” ሲል በመግለጫው ጠቅሶ ፕሬዝዳንት ሮበርት ሙጋቤ ደህንነታቸው እንደተጠበቀ አስታውቋል። ረቡዕ ጠዋት ላይ በዋና ከተማዋ ሃራሬ ሰሜን ክፍል ከፍተኛ የጦር መሳሪያ ተኩስ ተሰምቷል።
በደቡብ አፍሪካ የዚምባብዌ ልዑክ የሆኑት አይዛክ ሞዮ መፈንቅለ መንግሥት አለመኖሩን ጠቁመው መንግሥት በተለመደ መልኩ ሥራውን እያከናወነ ነው ብለዋል።
Image copyrightREUTERS አጭር የምስል መግለጫየዚምባብዌ ጦር አባላት በሃራሬ ጎዳና ላይ
የጦሩ መግለጫ የተነበበው በወታደሮች ሲሆን የዜድ ቢ ሲን ዋና መስሪያ ቤት ከተቆጣጠሩ ከሰዓታት በኋላ ነው። “ለህዝቡ የምናረጋግጠው ፕሬዝዳንቱ እና ቤተሰቦቻቸው በመልካም ሁኔታ ላይ ናቸው። ደህንነታቸውም ይጠበቃል” ሲል የጦሩ ባልደረባ ይፋ አድርጓል።
“ዒላማ ያደረግነው በፕሬዝዳንቱ አቅራቢያ ሆነው ወንጀል በመፈጸም ሃገሪቱን ለማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግር ያጋለጡ ወንጀለኞችን ነው። ተልኳችንን እንዳጠናቀቅን ነገሮች እንደቀድሞው ይሆናሉ” ብሏል መግለጫው።
መግለጫው ዒላማ የተደረጉ ሰዎችን ባይጠቅስም ሮይተርስ አንድ የመንግሥት ኃላፊን ጠቅሶ እንደዘገበው የገንዘብ ሚንስትሩ ኢግናቲስ ቾምቦ በቁጥጥር ስር ከዋሉት መካከል ይገኙበታል።
የጦሩን እንቅስቃሴ ማን እየመራው እንደሆነ የታወቀ ነገር የለም።
የእንግሊዝ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ለዜጎቹ “ሁኔታዎች እስኪረጋጉ ድረስ በቤቶቻቹሁ ቆዩ” በማለት ምክር ሰጥቷል።
Image copyrightAFPአጭር የምስል መግለጫጄነራል ኮነስታንቲኖ ቺዌንጋ ጦሩ ጣልቃ እንደሚገባ አስጠንቅቀው ነበር
በሃራሬ የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ “ባለው አለመረጋጋት ምክንያት” ረቡዕ ዕለት ዝግ እንደሚሆን አስታውቋል። ሌላ መግለጫ እስኪወጣ ድረስ በዚምባብዌ የሚገኙ አሜሪካዊያን “ባሉበት እንዲቆዩ” በማለት መልዕክቱን አስተላልፏል።
የአሁኑ ሁኔታ የሃገሪቱ ጦር አዛዥ በፓርቲ ክፍፍል ምክንያት ጦሩ ጣልቃ ይገባል ማለታቸውን ተከትሎ አዛዡ “የሃገር ክህደት ድርጊት” እየፈጸሙ ነው በሚል በዚምባብዌ ገዢ ፓርቲ ቅሬታ ከቀረበባቸው በኋላ የተፈጠረ ክስተት ነው።
የ93 ዓመቱ ፕሬዝዳንት ሮበርት ሙጋቤ ምክትል ፕሬዝዳንታቸውን ካባረሩ በኋላ ጉዳዩ በጄነራል ኮነስታንቲኖ ቺዌጋ ጥያቄ ቀርቦበታል።
በሙጋቤ ዛኑ ፒ ኤፍ ፓርቲ ውስጥ አባላትን ያለአግባብ የማባረር ስራን ለማስቆም ጦሩ ጣልቃ ይገባል ብለዋል ጄነራሉ። ዓላማቸው ባይታወቅም ማክሰኞ ዕለት የጦሩ የታጠቁ መኪናዎች በሃራሬ ጎዳናዎች ላይ መታየታቸው ያለውን ውጥረት ከፍ አድርገውታል። ጦሩ ዜድ ቢ ሲን ሲቆጣጠር አንዳንድ የጣቢያውን ሠራተኞች ማንገላታቱን ምንጮች ለሮይተርስ ተናግረዋል።
Image copyrightAFP አጭር የምስል መግለጫግሬስ ሙጋቤ እና ሮበርት ሙጋቤን
አካባቢውን ለመጠበቅ እንደመጡ እና “ምንም እንዳይፈሩ” ለሠራተኞች እንደተነገራቸው ምንጮቹ ጨምረው ጠቁመዋል። ፕሬዝዳንቱን ጨምሮ ብዙ የመንግሥት ኃላፊዎች መኖሪያ በሆነው ሰሜናዊ ሃራሬ ከፍተኛ የተኩስ ድምጽ መሰማቱን የቢቢሲዋ ሺንጋይ ንዮካ ዘግባለች።
አንድ የዓይን እማኝ ለኤ ኤፍ ፒ እንደገለጸው የተኩስ ድምጽ የተሰማው በፕሬዝዳንት ሙጋቤ መኖሪያ አካባቢ ነው። ማን ይተካቸዋል በሚለው ውዝግብ ምክንያት ሙጋቤ ምክትላቸው የነበሩትን ኤመርሰን ምናንጋግዋን አሰናብተዋል። በሁለቱ መካከል ያለው ልዩነት ዛኑ ፒ ኤፍ ፓርቲንም ለሁለት ከፍሎታል ተብሏል።