የህወሃት ማዕከላዊ ኮሚቴ አልቋጭ ባለው ግምገማ በቅላት ሲሞሻለቅ መከረሙ፣ የሃሳብና የአቋም ጉዳይ የመለያየቱ ዋና መነሻ ሆኖ ፖለቲካዊ ፋይዳቸው ሊመዘን የማይችለው ወ/ሮ አዜብና አንድ ባልደረባቸው ስብሰባ ረግጠው እስከመውጣት መድረሳቸው መዘገቡ ይታወሳል። ዛሬ ህወሃት ተጠቅሶ የተሰራጨ ዜና እንዳስረዳው ” ግምገማው በድል ተጠናቋል” የሚል ነው። ” ገምተናል” ሲል ራሱን የሰደበው ህወሃት ዛሬ በራሱ ሚዲያዎች የድል ብስራት አሰምቷል። ግን አዲስ አመራሮች እነድሚመጡ ፍንጭ ሰጥቷል።

ከመግማት ወደ ማብረቅረቅ ለመቀየር ተስፋ የሰነቀው ህወሃት፤ ታድሶ አገራዊና ክልላዊ ሃላፊነቱን እንደሚወጣ አመልክቷል። በግምገማው የተለመዱት “ጠባቦችና ትምክህተኞች ” የሚባሉት የህብረተሰብ ክፍሎች በእነሱ ችግር ምክንያት ቀዳዳ እንዳገኙም ተወስቷል። ዜናው ህወሃት በፓርቲ ደረጃም ሆነ በግለሰብ ደረጃ በሙስና ስለመበስበሱ ብዙ ቢባልም አሁን በግምገማው ላይ ምን እንደተወሰነና ምን ዓይነት እርምጃ እንደተወሰደ አልተጥቆመመ። የፋና ዜና እንዲህ ይነበባል።

የህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ /ህወሓት/ ማዕከላዊ ኮሚቴ የአመራር ዳግም ማደራጀትና ማስተካከያ እንደሚያደርግ ገለፀ። ማዕከላዊ ኮሚቴው ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት በላከው መግለጫ ከመድረኩ ተልእኮ አንፃር ያለውን ጥንካሬና መሰረታዊ ድክመቶችን ለመለየት የጀመረው ጥልቅ ግምገማ በድል በመፈፀም የሂስና ግለ ሂስ መጀመሩን አስታውቋል።

ላለፉት ተከተታይ ሶስት ሳምንታት ባካሄደው ጥልቅ ግምገማ፥ በአመራር ስትራቴጂካዊ ፖለቲካዊ ሁነቶች፣ ሁለንተናዊ የልማታዊ ትራንስፎርሜሽን ማረጋገጥ እና በዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ዙርያ በጥልቅ በመገምገም ያሉትን መሰረታዊ ክፍተቶችን በዝርዝር ማየቱን ያመላክታል።

በዚህ መሰረት በስትራተጂካዊ አመራር የታቀፈው ማእከላዊ ኮሚቴ በትግልና በመርህ የተመሰረተ አንድነት አለመኖር፣ በመጠቃቃትና መከላከል ዝምድና ላይ መመስረት፣ የፀረ ዴሞክራሲ ጥልቅ አስተሳሰብና ተግባራት እንዳሉ መገምግሙን ነው ያስታወቀው። በተጨማሪም የወጣቱን ትውልድ እና የምሁሩን አቅም በመገንባት፣ በማሰለፍና ተጠቃሚ በማድረግ ረገድ መሰረታዊ ጉድለቶች መኖራቸውን ገምግሟል።

ከእህት ድርጅቶች ጋር የግንኙነት ችግር እንደነበረ በጥልቀት የገመገመው ኮሚቴው፥ በዚህም በትምክህትና ጥበት ሃይሎች ምክንያት በአገራችን የተፈጠረው ሕገ-መንግስታዊ ስርዓት ለአደጋ የሚዳርጉ አዝማማያዎችና ተግባራት ለመታየታቸው በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የአመራሩ የራሱ አሉታዊ አስተዋፅኦ እንደነበረው መግባባት ላይ መደረሱን ገልጿል።

በሌላ በኩል በትግራይ ክልል ትራንስፎርሜሽን ከማረጋገጥ አኳያ መሰረታዊ ስትራቴጂካዊ የአመራር ችግር እንደነበረበት በመገምገም፥ ባለፉት አመታት በተደረገው እንቅስቃሴ በገጠርና ከተማ የተመዘገቡ የልማት ድሎች መኖራቸውን ያረጋገጠ ቢሆንም ከዕድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ማሳካት አኳያ የህዝቡ ተጠቃሚነት ከፍላጎቱ ጋር ሲመዘን ግን መሰረታዊ ችግሮች እንደነበሩበት በመገምግም ማረጋጋጥ ችያለሁ ነው ያለው በመግለጫው።

ከአመራሩ የሚጠበቅ ብቃት ያለው ስትራተጂካዊ አመራር በመስጠት ፈንታ በተደማሪ ድሎች ብቻ መርካት እንዳለ መግባባት ላይ መደረሱንም መግለጫው ያመለክታል።

ማእከላዊ ኮሚቴው የጀመረውን ግምገማ በመቀጠል የድርጅቱ ነባር ስትራቲጅካዊ አመራርን ጨምሮ የሁሉንም የማእከላዊ ኮሚቴ አባላት ሂስና ግለ ሂስ ግምገማ በሚቀጥለው ሳምንት እንደሚያጠቃልል ይጠበቃል።

ግምገማው የአመራር ዳግም አደረጃጀትና ማስተካከያ በማድረግ ለተገመገሙት ችግሮች መሰረታዊ ለውጥ የሚያስገኙ የፕሮግራም አቅጣጫ በማስቀመጥ ክልላዊና አገራዊ ተልእኮን በብቃት ማስፈፀም የሚችል አቅም ለመፍጠር የሚያስችል መሆኑን ማእከላዊ ኮሚቴው አረጋግጧል።

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *