ሰው መርጦና ፈቅዶ ከሾመ፣ መልሶ ስለሚያወርድ ቅኑን ጠብቆ እንደሚቀጣ ያውቃልና ወደ አመጽና ግርግር አይሄድም። እኛ አገር ግን “እኔ ካልመራውህ ትፈርሳለህ፣ ትበተናለህ፣ ከእኔ ውጪ ሊመራህ የሚችል የለም። በስብሼም ቢሆን አማራጭህ እኔ ነኝ፤ በበሰበስኩ ቁጥር እስክታደስ ጠብቀኝ፤ እጣፈንታህ እኔ ነኝ …” የሚለው እሳቤ የትም አያደርስምና ቢታሰብበት ደግ ነው። ኢሳት ከዚህ የሚከተለውን ዘግቧል። 

በባህርዳር ከተማ በሚገኘው የዳግማዊ ዮሃንስ ጋርደን ሆቴል አቅራቢያ ይሁን ውስጥ በግልጽ ባይነገርም ቦንብ ፈንድቷል መባሉን ተከትሎ ” ለምን?” የሚል ጥያቄ ይነሳል። ጥያቄውን የሚያጎላው ፍንዳታው ደረሰ የተባለው የትግራይ ክልል ወኪል የሆነው የአክሱም ከነማ እግር ኳስ ቡድን ከአቻው ባህር ዳር ከነማ ጋር ለመጫወት ባህርዳር ከተማ መግባቱና በተጠቀሰው ሆቴል መስተንግዶ መደረጉን ተከትሎ ነው።

ከኢትዮጵያ እግር ኩስ ፌዴሬሽንም ሆነ ከክልሉ አካላት በይፋ ስለፍንዳታው የተባለ ነገር የለም። ድርጊቱ የተፈጸመው የትግራይና የአማራን ሕዝብ ለማቀራረብ በሚል የሚካሄደው ጉባኤ ዝግጅት በሚካሄደበት ወቅት አፍላው ላይ መሆኑ የሁለቱን ክልል ሕዝቦች ጉዞ ወዴት? የሚል መላሹ አካል ያልለየበት ጥያቄ ያስነሳል። ጥያቄው የቆየ ቢሆንም አሁን ላይ የሚታዩት ጉዳዮች አጠቃላይ አገሪቱ ውስጥ ካለው የዘር ችግር ጋር ተዳምሮ ስጋቱን ከፍ ያደርገዋል።

“ስፖርት የሰላማዊ መድረክ ነው” የሚለው የንግድ ቋንቋ ሃሰት መሆኑንን የሚያረጋግጡ በርካታ ሁነቶች በኢትዮጵያ ካለፉት ስርዓቶች ጀምሮ የሚስተዋል ነው። በቀደሞው ስርዓት የአስመራ ቡድኖች ከሸዋ ጋር ሲጫወቱ ጦርነት ነበር የሚመስለው። ውስጡ የፖለቲካው እሳት ስላለ ግጥሚያው የጦርነቱ ነጸብራቅ የሚታይበት ነበር። በተመሳሳይ የኤርትራ ቡድኖች ከሌሎች ጠቅላይ ግዛት ጋር ሲጫወቱ ያ ስሜት እንደማይታይ በወቅቱ ውድድሮቹን ሲመለከቱ የነበሩ የሚናገሩት ሃቅ ነው።

ራቅ ባሉት ዓመታት እምባይሶራ፣ ቴሌ፣ ሃማሴን … የሚባሉት ከዛም እንደ አዱሊስ፣ ቀይባህር፣ ሰላም የመሳሰሉት ቡድኖች ከአዲስ አበባ ክለቦች ጋር ሲጫወቱ ተመሳሳይ ስሜት ይታይ ነበር። የአሁኑንን ለየት የሚያደርገው ከጨዋታው ሜዳ ፍትጊያና ጸያፍ የቃላት ጦርነት፣ እንዲሁም በደጋፊዎች መካከል የሚታየው መናረት ሳያንስ ወደ ቦንብ ፍንዳታ መሸጋገሩ ነው።

Related stories   የትህነግ "ውሮ ወሸባዬ" - የመንግስት ሩጫ - የሃላኑ የኢትዮጵያን ቋንጃ የመበጠስ የእባብ አካሄድና ባንዳዎች!

በአዲስ አበባና በተለያዩ የኳስ ሜዳዎች መንግስትን፣ ገዢን፣ አስተዳደርን ጥርጎ መሳደብና ስሜትን ገሃድ ማውጣት የተለመደ ነው። አዲስ አበባ ስታዲየም ይህንኑ ለመስማትና የተጎዳ ስሜታቸውን በስላቅ ለመግለጽ የሚታደሙ መኖራቸውም ይታወቃል። እንኳን ፖለቲከኞች ስፖርቱ አካባቢ ድጎማ በማድረግ ስም ለክለባቸው አድልዎ እንዲሰራ ያደረጉ ” ሃብታሞች” ድራሻቸው እስኪጠፋ በክበረ ነክ ስድብ መሳለቂያ ሆነዋል። ዜማ ተደርሶ የቅሌት እንጉርጉሮ ወርዶባቸዋል። በሰውነት ቅርጻቸውና በምግባራቸው ” ማሪዮ ፑዞ” ተብለው የጭቃ ያህል ተላቁጠዋል። እኒህ ሰዎች ስድብና ውርደት ቀለባቸው እስኪመስል ድረስ እንደ ውርጋጥ ለጆሮ የሚቀፍ ድምጽ ሲወረወርባቸው እርም አለማለታቸው ” ምን ቢያተርፉ ነው?” በሚል የሚገረሙ ሰዎች ይጠየቁም ነበር። አንዳንዴ ስድቡን ለማመጣጠን በጀትም እየመደቡ ተሳዳቢ፣ ደብዳቢ፣ ሲቀጥሩም ነበር።

ከላይ የተባለውን ለማስታወስ የተሞከረው ሰዎች ስሜታቸውን ባደባባይ መግለጽ ሲያቅታቸው በስፖርት ሜዳዎች፣ በሩጫ ስፍራዎች፣ አንዳንዴም በሃይማኖት ስብሰባዎችና በሚወዱዋቸው ሙዚቃዎች  ተሸሽገው መናገራቸው የተለመደ መሆኑንን ለማመላከት ነው። አሁን የሚታየውና መልኩ ከቀደመው የተለየ ነው። ባህር ዳር የተወረወረው ቦንብ የሕዝብን ስሜት ይግለጽ አይግለጽ ማስረጃ መጥቀስ ባይቻልም፤ በሌሎች ክልል ከተማ ክለቦች ላይ ባልታየ መልኩ የአክሱም እግርኳስ ክለብን  ተከትሎ ፍንዳታ መሰማቱ በብዙ መልኩ አሳዛኝ፣ አስደንጋጭ እንዲሁም ጉዞ ወዴት? የሚያሰኝና መጪውን በሃዘን እንድናስብ የሚያደረግ ነው።

አብዛኞች እንደሚሉት አገሪቱ በህግ፣ በህገ መንግስት፣ በአዋጅ፣ ይህንን ሁሉ ሲያስፈጽም ለኖረ መንፈስ በመማልና ግብር በማስገባት ጭምር ሕዝብ በጎሳና በዘር፣ እንዲሁም በቋንቋ እንዲለያይ በተፈቀደው መሰረት አሁን የመጨረሻው መቃረቡን የሚያሳይ ነው። የአንድ አገር ብሄራዊ ሚዲያ ሲረጨው የነበረውና እየረጨ ያለው የመጠላላት ፖለቲካ እንደ ትልቅ ስራና ስትራቴጂክ ድል ተቆጥሮ ለሙት የክፉ መንፈስ የሚገብሩ ዛሬም ይህንኑ ” ቅርስ ፣ ሌጋሲ… አርቆ አስተዋዩ” በሚል ሲያሞካሹት መስማት ከስህተት ለመማር አለመሞከር ነው።

Related stories   አስከሬን እንዲለቀም ታዘዘ - ትህነግ የአጽም ፖለትካ ድራማ ይፋ ሆነ

በተራና በተለመዱ የግምገማ ቃላት ጋጋታ ተደናብሮ ከመደናበር፣ አገሪቱን ወደ ሰላማዊ ጎዳና የሚያመሩ ውሳኔዎች፤ ሁሉንም ያካተተ እርቅ፣ ሁሉንም ያካተተ መፍትሄ ካልተወሰደ ተመሳሳይ ድርጊቶች ላለመፈጸማቸው ዋስትና አይኖርም። ሕዝብ በመረጠው አካል እንዳይተዳደር ከተከለከል ችግሩ ሊበርድ የምይችልበት ደረጃ ደርሷልና ይህንኑ ተረድቶ መላ መፈለግ ግድ ነው። ምንም ይሁን ምን በተጨዋቾች ላይ ወይም እነሱን ተከትሎ ተፈጸመ የተባለው ድርጊት ፍጹም ተቀባይነት ባይኖረውም፣ ለመፍትሄው በምትጋት ቀጣይ ችግሮችን መቅረፍ ግድ ነው።

ሰው መርጦና ፈቅዶ ከሾመ፣ መልሶ ስለሚያወርድ ቅኑን ጠብቆ እንደሚቀጣ ያውቃልና ወደ አመጽና ግርግር አይሄድም። እኛ አገር ግን “እኔ ካልመራውህ ትፈርሳለህ፣ ትበተናለህ፣ ከእኔ ውጪ ሊመራህ የሚችል የለም። በስብሼም ቢሆን አማራጭህ እኔ ነኝ፤ በበሰበስኩ ቁጥር እስክታደስ ጠብቀኝ፤ እጣፈንታህ እኔ ነኝ …” የሚለው እሳቤ የትም አያደርስምና ቢታሰብበት ደግ ነው። ኢሳት ከዚህ የሚከተለውን ዘግቧል።

ከባህርዳር ከነማ ጋር ውድድሩን ሊያካሂድ ባህርዳር የገባው የአክሱም ከነማ እግር ኳስ ቡድን ያረፈበት ሆቴል ላይ የቦምብ ጥቃት መፈጸሙን ተከትሎ ውጥረት መንገሱ ተሰማ ማምሻውን የልዩ ሀይል ፖሊሶች ተጫዋቾቹን ከሆቴሉ ለማስወጣት እየሞከሩ መሆናቸው ታውቋል።

በሁለቱ ቡድኖች መካከል ነገ ይካሄዳል ተብሎ ስለሚጠበቀው ጨዋታ ግን የተባለ ነገር የለም። ነገር ግን ቡዳኑ ወደ ከተማዋ ከገባ በኋላ ንብረትነቱ የህወሃት የደህነነት ሰው እንደሆነ በሚታወቀውና ቀበሌ 02 በሚገኘው ዳግማዊ ዮሃንስ ጋርደን ሆቴል ማረፉ የታወቀው በሆቴሉ ላይ የቦምብ ፍንዳታ ከተከሰተ በኋላ ነው። በተፈጸመው ጥቃትም እስካሁን ሁለት ሰዎች መጎዳታቸውናን ወደሆስፒታል መወሰዳቸውን የኢሳት ምንጮች ገልጸዋል።

Related stories   Egypt-Sudan alliance shifting in row with Ethiopia over Nile dam

ማምሻውን የልዩ ሀይል ፖሊሶች ተጫዋቾቹን ለማስወጣት እየሞከሩ መሆኑን ከመረጃው ለማወቅ ተችሏል። እስካሁን ጥቃቱን ማን ፈጸመው ለሚለው ግን ምላሽ አለተገኘለትም።

ከተፈጸመው የቦንብ ጥቃት ጋር ተያይዞ ነገ ይካሄዳል የተባለው ጨዋታ በመርሃ ግብሩ መሰረት ይካሄድ አይካሄድ የታወቀ ነገር የለም። የከተማው ህዝብ ጨዋታውን ለመመልከት ወደስፈራው የመሄዱ ጉዳይም አጠራጣሪ ሆኗል። እንደ ኢሳት ምንጮች ከሆን ከቦምብ ጥቃቱ ጋር ተያይዞ በከተማዋ ውጥረት ነግሷል።

ከባህርዳር ከነማ ጋር የአክሱም ከነማ እግር ኳስ ቡድን ጨዋታውን በባህርዳር ብሔራዊ ስታዲየም እንዲያካሂድ መርሃ ግብር ወጥቶለታል። ነገር ግን ከዚህ በፊት በከተማዋ ይካሄዱ የነበሩ የሊግ ጨዋታዎች ሲካሄዱ የነበሩት በአጠቃላይ በባህርዳር ዩንቨርስቲ ፔዳ ሜዳ ሲሆን አሁን ይህ ጨዋታ በባህርዳር ብሄራዊ ስታዲየሙ እንዲካሄድ መወሰኑ ጥያቄ አስነስቷል።

በሌላ በኩል በኦሮሚያ ክልል ዝዋይ /ባቱ/ ከተማ በግለሰቦች መካከል ተቀስቅሷል የተባለ ጸብ ወደ ሌሎች ተሸጋግሮ ከ10 በላይ ለሚሆኑ ሰዎች ሞትና ለበርካቶች መቁሰል ብሎም መፈናቀል ምክንያት መሆኑ ታውቋል። በቡድን የተደራጁ ወጣቶች ወደ ከተማዋ የተለያዩ አካባቢዎች በመዘዋወር ነዋሪዎችን ሲደበድቡና ሲያዋክቡ መዋላቸው ተነግሯዋል።

ችግሩ በተከሰተበት ሰዓት የከተማው ፖሊስ በፍጥነት ባለመድረሱና በቂ ሃይል ይዞ ባለመምጣቱ አስቸኳይ መፍትሄ መስጠት እንዳልተቻለ ምንጮቻችን ገልጸዋል።

በዚህም ምክንያት በግጭቱ 11 ሰዎች ሕይወታቸውን ማጣታቸውን የአካባቢው ምንጮች አስታውቀዋል። በግጭቱ ጉዳት የደረሰባቸውና የተፈናቀሉ ነዋሪዎች በከተማዋ አስተዳደር እርዳታ እየተደረጋላቸው መሆኑ ሲጠቀስ ነዋሪዎቹ አሁንም ስጋት ወስጥ መሆናቸውን የደረሰን መረጃ ያመለክታል።

 

Share and Enjoy !

Shares

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *