ZAGGOLE – ዛጎል

“Our true nationality is mankind.”H.G.

ይህ ሁሉ የተደረገው አሁን ጎንደር ባሉ ሰዎችትእዛዝ ነው! -ሙሉቀን ተስፋው

ታች አርማጭሆ ኪሻ ቀበሌ በ1988 ዓም ነው። መከላከያ ሰራዊት የአቶ ጋንፋር መርሻን ቤት ላይ የተኩስ እሩምታ ይከፍታል። መከላከያ ወደ አርሶ አደሩ ቤት ያቀናበት አላማ መሳርያ ለማስፈታት ነው ቢባልም በአርማጭሆ መሳርያ ለማስፈታት፣ ሽፍታ ለመያዝ ተብሎ ንፁሃን በር ዘግተው የተቀመጡበት ቤት ላይ ሩምታ መተኮስ የተለመደ ነው። አቶ ጋንፋረ ቤት ላይም የተደረገው ይህንኑ ነው። መከላከያ የሩምታ ተኩስ በሚከፍትበት ወቅት ከአቶ ጋንፋር በተጨማሪ አባ ስመል የተባሉ መነኩሴ ቤት ውስጥ ነበሩ።

በመከላከያ የማስጠንቀቂያ ተኩስ አልነበረም የተኮሰው። ውስጥ የነበረውን አርሶ አደር ለማስፈራራት፣ ገድሎም ለመውሰድ ብቻ አልነበረም። ቤቱን በአቃጣይ (አብሪ) ጥይት እንድዶ ቤቱ ውስጥ በእሳት እንዲነዱ አድርጓል። ከአቶ ጋንፋር መርሻ በተጨማሪ አብረውት የነበሩት መነኩሴ እንዲሁም ቤት ውስጥ የነበረ ንብረት ሁሉ ወድሟል።

ዳባት ወረዳ

ሙልዬ ሹምዬ በዳባት ወረዳ የሚሊሻ ኃላፊ ነው። ይህ የሚሊሻ ኃላፊ ህወሓት የጠላውን፣ ከብአዴን ጋር አልቆምም ያለን ወይምም የጠላውን ሳይቀር “ሽፍታ ነው” እያለ የሚያስገድል ነው። ቀሪውን ደግሞ ሀብት ንብረቱን ሸጦ የገዛውን መሳርያ ይቀማል። ቤቱን አቃጥሎ፣ የቤተሰብ አባሉን ገድሎ ይመለሳል። ሙልየ ሹምየ የሚመራው ሚሊሻ ወደ ተንተሮ ቀበሌ ያቀናል። ጉዞው አዳነ አሻግሬ የሚባል አርሶ አደር ያልተመዘገበ መሳርያ ስላለው መሳርያውን ለማስወረድ ነው። ሚሊሻ አባላቱ የአቶ አዳነን ቤት ከበው መሳርያ አለህና አምጣ ይሉታል። አቶ አዳና መሳርያ እንደሌለው መልስ ይሰጣል። ቤቱን ፈትሸው ለማረጋገጥ ወይንም በጥርጣሬ ይዘው ለመመርመር አልፈለጉም። እንደተለመደው የሩምታ ተኩስ ከፈቱ። እርሱን መነኩሴ እናቱን እማሆይ አስናቁ ሙጨን በጥይት ተመቱ። መሳርያ የለኝም ያለው አርሶ አደር ባዶ እጁን ነበርና ቤት ውስጥ እንዳለ ተመትቶ ሞተ። እናቱም ቆሰሉ። ቤቱ ውስጥ ያለው ንብረት ሳይወጣ ተቃጠለ። የሟች እናት እሙሃይ አስናቁ ህክምና እንዳያገኙ ተደርገውሞቱ። እሙሃይ አስናቁ በእስር ላይ የሚገኘው አንጋው ተገኘ አክስት ናቸው።

በ1988 ዓም

ከአርማጭሆና ከጠገዴ 12 ሰዎች ይታፈናሉ። ከእነዚህም መካከል ሀብቴ አላምኔ፣ጥጋቡ አላምኔ፣ፀጋው ዘመነ፣ ደጉ ታከለ (የህክምና ባለሙያ)፣ ብርሃን ተሻገር፣ አለምሻው ውብነህ፣ ይመር እና ጀጃው የሚባሉና ሌሎች 4 ንፁሃን ታፍነው መከላከያ ካምፕ ውስጥ ይታሰራሉ። በእነዚህ አካባቢዎች ንፁሃን በመከላከያ ታፍነው እጅ እግራቸው በድብደባ መሰበሩ፣ ጉድጓድ ውስጥ ተቀብረው መሰቃየታቸው፣ ከአቅም በላይ የጉልበት ስራ መስራታቸው የተለመደ ነው። ይህን ሁሉ ስቃይ አልፎ ቤተሰብ ጋር መቀላቀል ብርቅ ነው። እነዚህ 12 ንፁሃን ላይ የደረሰውም የአካባቢው ህዝብ የሚሰጋውና የሚጠብቀው ነበር።
ችቹ አለባቸው በወቅቱ የታች አርማጭሆ አስተዳደር ነበር። አሰፋ ጫቅሌ ሌላኛው የወረዳ አመራር ነው። በእነዚህ ሁለት ግለሰቦች ትዕዛዝ ከእርሻ ቦታቸው ታፍነው የታሰሩትና ሳንጃ ከተማ ፈንድቃ የተባለ ቦታ ታስተው ከነበረበት በሌሊት አስወጥተው ተረሽነዋል። አስከሬናቸው ፀኃይ ላይ ተሰጥቶ በመከላከያ እየተጠበቀ አሞራ እንዲበላቸው ተደርጓል። ዘመድ፣ ወዳጅና የሚያውቃቸው ወይንም አልፎ ሂያጅ ቢያለቅስ፣ ከንፈር ቢመጥ እስርና ዱላ ይጠብቀዋል። እነዚህ ግለሰቦች ለመቀጣጫ በሚል ለቀናት አስከሬናቸው ፀሀይ ላይ ተሰጥቶ ዘመድና ወዳጅ እያየ አሞራ በልቷቸዋል። ከእነዚህ መካከል ሀብቴ አላምኔና ጥጋቡ አላምኔ አንድ ሰው ልጆች ናቸው። አባታቸውን አላምኔ ጫንያለውን 1985 አካባቢ ስናር ስናር ላይ በህወሓት ተገድለዋል። አለምሻው ውብነህ እና ፀጋው ዘመነ የአንድ ቤተሰብ አባላት ናቸው። ከተረሸኑት ንፁሃን አርሶ አደሮች መካከል የተዋኑት ዳንሻ ቤትና ንብረት ነበራቸው። ቤትና ንብረታቸውን ግን ለቤታባቸው አልተሰጠም። ገብረ እግዚያብሄር እና ሲሳይ ሀዲሽ የሚባሉ ግለሰቦች እንዲወርሱት ተደርጓል። በርካቶች በተመሳሳይ አድራሻቸው ጠፍቷል። መረሻቸውን ያወቁ እንኳ ለቤተሰብ ማስረዳቱን ፈርተው ወደ ሱዳንና ሌላ ሀገር እንደተሰደዱ እየነገሯቸው እስካሁን ቁርጣቸውን ያላወቁ የቤተሰብ አባላት ብዙ ናቸው።

ጥቅምት 15/ 2006 ዓም ነው። አርሶ አደር ማስረሻ ጥላሁን የመንግስትን መሬት ገፍቷል በሚል የዳባት ወረዳ ከ16 በላይ ታጣቂዎችን በሌሊት ወደ ቤታቸው ይልክባቸዋል። ” የፀረ ሽብር ግብረ ሀይል” የላካቸው ታጣቂዎች የአቶ ማስረሻ ቤት ላይ በከፈቱት የእሩምታ ተኩስ አቶ ማስረሻን ገድለው፣ ህፃን ስለእናትንም አቁስለው ተመልሰዋል። የፀረ ሽብር ግብረ ሀይል የተባለው አካል የላካቸው ባለ ጠብ መንጃዎች በረት ውስጥ የነበሩትንም እንሰሳት በእሩምታ ፈጅተው ነው የተመለሱት።

Related stories   አውሮፓ ህብረት እየተሽኮረመመ ታዛቢ ሊልክ ነው