ZAGGOLE – ዛጎል

“Our true nationality is mankind.”H.G.

የሕወሃትና ሻዕቢያ ሽምግልና – ካርዲናል ብርሃነየሱስ ኤርትራ እንዳለገባ ተከለከልኩ አሉ፤ ቀሪዎቹ ሽምግልናውን አያካሄዱ ነው

Related stories   “የአውሮፓ ህብረት የምርጫ ታዛቢዎች አለመምጣት የሚያጎለው አንዳችም ነገር የለም፤ እኛም አንጠብቃቸውም” ፕሮፌሰር በየነ

ኢትዮጵያና ኤርትራን ለማደራደር የተነሳው የምሥራቅ አፍሪካ የካቶሊክ ጳጳሳት ጉባዔዎች ማኅበር (አሜሰያ) /Association of Member Episcopal Conferences in Eastern Africa (AMECEA)/፣ ፕሬዚዳንትና የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ሊቀ ጳጳሳት ብፁዕ ካርዲናል ብርሃነየሱስ ሱራፌል ኤርትራ እንዳይገቡ ታገዱ፡፡

የካርዲናሉ የቅርብ ሰዎች ባለፈው ሳምንት ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ እሳቸው የሚመሩትና የምሥራቅ አፍሪካ አገሮች ጳጳሳትና የማኅበሩ አባላት ወደ ኤርትራ በማቅናት በሁለቱ አገሮች መካከል ዕርቅ ለማውረድ ጥያቄ ቢያቀርቡም፣ ኤርትራ ኢትዮጵያዊውን ሊቀ ጳጳሱ ወደ አገሯ እንዳይገቡ ከልክላለች፡፡ የአሥራ አንድ አገሮች ጳጳሳትና ተወካዮች ወደ አገሪቱ እንዲገቡ ግን ፈቅዳለች፡፡

ካርዲናሉ የተከለከሉበት ምክንያት የኢትዮጵያ ዜግነት ስላላቸው ብቻ እንደሆነ ታውቋል፡፡ ቀሪዎቹ ጳጳሳትና የማኅበሩ አባላት ኤርትራ መሄዳቸውንና የማሸማገል ሥራቸውን መጀመራቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡

የማኅበሩ ዋና መቀመጫ ኬንያ ውስጥ ሲሆን፣ ኤርትራ ምንም እንኳ ኢትዮጵያዊውን ካርዲናል እንዳይገቡ ብትከለክልም፣ የክፍለ አህጉራዊው የአሜሲያ ፕሬዚዳንት እንደ መሆናቸውና በሁለቱ አገሮች መካከል ዕርቅ እንዲፈጠር ካላቸው ጉጉት የተነሳ ጥረታቸውን አያቆሙም በማለት የካርዲናሉ የቅርብ ሰዎች ተናግረዋል፡፡

ዘጠኙ የማኅበሩ አባል አገሮች ኢትዮጵያ፣ ኤርትራ፣ ኬንያ፣ ማላዊ፣ ደቡብ ሱዳን፣ ሱዳን፣ ታንዛኒያ፣ ኡጋንዳና ዛምቢያ ሲሆኑ ጂቡቲና ሶማሊያ የኅብረቱ ተባባሪ አባላት ናቸው፡፡

የማኅበሩ ዋና ዓላማ ከቤተ ክርስቲያን ሐዋርያዊና ማኅበራዊ አገልግሎት በተጨማሪ በአፍሪካ በተለይም በምሥራቅ አፍሪካ አገሮች መካከል ዘላቂ ሰላም እንዲኖርና አገሮች እርስ በርስ በመረዳዳትና በመደጋገፍ፣ በሰላም የሚኖሩበትን መንገድ ማመቻቸት እንደሆነ ታውቋል፡፡ ማኅበሩ በኢትዮጵያና ኤርትራ መንግሥታት መካከል ለረዥም ዓመታት የቆየውን ልዩነት ለመፍታት ጥረት እያደረገ ቢሆንም፣ በአሁኑ ወቅት ግን ዓላማውን ሰፋ በማድረግ ትኩረቱን በምሥራቅ አፍሪካ አገሮች ሰላም ላይ ያተኮረ ሥራ እንደሚያከናውን ተጠቁሟል፡፡

የማኅበሩ አባላትም በሁለቱ አገሮች መካከል ያለውን ችግር ለመፍታት ከዚህ በፊት አንድ ጊዜ ወደ ኤርትራ እንደሄዱና ተስፋ ሰጪ ነገሮች እንደተገኙ ምንጮች ጠቁመዋል፡፡

ኤርትራ ሄደው የነበሩ የማኅበሩ አባላትም ከመንግሥት ኃላፊዎችና ከሃይማኖት አባቶች ጋር ሰፊ ውይይት በማድረግ መመለሳቸውን መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ በቅርቡ በኬንያ በሚካሄደው የክፍለ አህጉሩ የጳጳሳት ጉባዔ ላይ ከኤርትራና ከኢትዮጵያ መንግሥት የተወከሉ ኃላፊዎች እንዲሳተፉ ጥሪ እንደሚደረግ ታውቋል፡፡

‹‹የኢትዮጵያ መንግሥት በዚህ የሰላም ድርድር ሁሌም በሩ ክፍት እንደሆነ አረጋግጧል፤›› ያሉት አንድ የካርዲናሉ የቅርብ ሰው፣ በኤርትራ በኩል ያለው ጉዳይም ተስፋ የሚሰጥ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ ወደፊት በሚደረገው ጉዞም የኤርትራ መንግሥት ካርዲናሉን እንዳይከለክል ሌሎች የማኅበሩ አባላትና ጳጳሳት የማግባባት ሥራዎችን እያከናወኑ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡

የኤርትራ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ከኢትዮጵያ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ተለይታ ራሷን ከቻለችበት ከጥር 2007 ዓ.ም. በፊት ለ24 ዓመታት ትመራ የነበረው በኢትዮጵያና ኤርትራ ጳጳሳት ጉባዔ ፕሬዚዳንት ካርዲናል ብርሃነየሱስ ሱራፌል እንደነበር ይታወሳል፡፡  

ኢትዮጵያና ኤርትራ በ1990 ዓ.ም. በድንበር ይገባኛል ጥያቄ ወደ ጦርነት ከገቡ በኋላ ሰላምም ሆነ ጦርነት በሌለበት ሁኔታ ውስጥ እንደሚኖሩ ይታወቃል፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥት ከኤርትራ ጋር ለመደራደር ዝግጁ መሆኑን በተደጋጋሚ ጊዜ ሲገልጽ ቢሰማም፣ በኤርትራ በኩል እስካሁን ምላሽ እንደሌለ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡

Share and Enjoy !

Shares
0Shares
0
Read previous post:
“እንግልቱና ድካሙ ስለበዛብኝና …. አፋጣኝ ውሳኔ እንጂ ፍትሐዊ ፍርድ አልጠብቅም “አቶ መላኩ ፈንታ

‹‹እንግልቱና ድካሙ ስለበዛብኝና አቅሜም እየተሟጠጠ ስለመጣ፣ የተከበረውን ፍርድ ቤት የምጠይቀው የተፋጠነ ውሳኔ እንዲሰጠኝ ብቻ ነው፤›› ‹‹እንግልቱና...

Close