“ኢትዮጵያዊነት ረቂቅ ጉዳይ ነው፣ ኢትዮጵያዊነት ረቂቅ ነው… “ይህንን ያለው ቴዎድሮስ ካሳሁን ነው። ቴዲ አፍሮ ስለ ኢትዮጵያዊነት ብዙ ተናግሯል። አቀንቅኗል። መስክሯል። አገር ወዳድነቱን ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያዊነትን ፍንትው አድርጎ ለማሳየት ሌት ተቀን ባዝኗል። ስራዎቹና አንደበቱ ተጋምደው ይህንኑ መስክረውለታል። እናም ሁሉንም ነገር ቢያደርግም ” ኢትዮጵያዬ” ብሎ ቢያዜምም ኢትዮጵያዊነትን መግለጽ ባለመቻሉ ” ኢትዮጵያዊነት ረቂቅ ነው” ለማለት ተገዷል። አዎ ረቂቅ ነው። አቶ ካሌብ ግርማ የሚከተለውን ጽፈዋል። 

በካሌብ ግርማ

“ኢትዮጵያን የሚያከብር ሁሉ ይከብራል፣ ኢትዮጵያን ያኮሰሰ ሁሉ ይኮስሳል”
ፕሮፌሰር ፍቅሬ ቶሎሳ
“ኢትዮጵያዊነት ሱስ ነው፣ በልብና በደም ውስጥ የሚገኝና የሚያሰክር ዕፅ ነው”
አቶ ለማ መገርሳ

 

እነዚህ ሁለት የአንድነት፣ የኢትዮጵያዊነትና የፍቅር ሰባኪዎች የኢትዮጵያን ፓለቲካ 360 ዲግሪ አዙረውታል። ፍቅርን ሰላምን፣ አንድነትንና ኢትዮጵያዊነትን በማጉላት በቋንቋና በዘር ላይ የተገነባውን የጎሰኝነት አጥር በማፈራረስ በደም፣ በተዋልዶና አብሮ በመኖር ላይ የተመሰረተ ኢትዮጵያዊነትን ለአገራችንና ለህዝባችን ሰብከዋል። ፕሮፌሰር ፍቅሬ ቶሎሳ “የኦሮሞና የአማራ የዘር ግንድ ” በተሰኘው መፅሐፋቸው ስለ ሁለቱ ህዝቦች ያለውን ዘላለማዊ እውነት ከታሪክና ከድርሳናት በመጥቀስ አስደምመውናል። በተመሳሳይ ሁኔታ አቶ ለማ መገርሳ የኦሮሞና የአማራ ህዝቦች ወንድማማችነትን በመመስከር ለኢትዮጵያ አንድነትና ክብር በጋራ እንዲቆሙ ኢትዮጵያዊነትን ከወደቀበት አንስተው ሰማይ ምድሩን አስደምመዋል።
የሁለቱ ትልልቅ ህዝቦች፣ ማለትም የኦሮሞና የአማራ በሰላምና በፍቅር መኖር ለሁሉም ኢትዮጵያዊያን ዋስትና ከመሆኑም በላይ የጥላቻንና የዘረኝነትን ግድግዳ ያፈራረስ ክስተትም ነው። የኢትዮጵያዊነትን ብሔራዊ ስሜት እንደገና በማቀጣጠል ለአዲሱ ትውልድ መፃኢ ዘመን ብሩህ ተስፋን የፈነጠቁ እንቁ የኦሮሞ ልጆች ፕሮፌሰር ፍቅሬ ቶሎሳና አቶ ለማ መገርሳ ታሪክ ለዘላለም በኢትዮጵያዊነት የክብር መዝገብ ሲዘክራቸው ይኖራል። ባለፊት 3000 ዓመታት ተዘርቶ የበቀለውና ስር የሰደደው የኢትዮጵያ ህዝቦች ፍቅር በሰላሳ ዓመት የጥላቻ ወንጌል ሊተን ፈፅሞ እንደማይችልም አሳይተዋል።

በመሆኑም እኒህ ሁለት ታላላቅ ሰዎች ለአሁኑና ለመጪው ትውልድ ያስተላለፉት መልዕክት ሲጠቃለል ይህን ይመስላል:-

√ ኢትዮጵያዊነት ማለት የህይወት ምንጭነት፣ የስብዕና መገኛ ስፍራ ማለት ነው
√ ኢትዮጵያዊነት ማለት የስነ መለኮት ከፍታ፣ የስልጣኔ መጀመሪያ፣ የሰው ዘር አርአያ፣ የስነ ምግባር ልዕልና ማለት ነው
√ ኢትዮጵያዊነት ማለት የርህራሄነት፣ የጀግንነትና የፍትሃዊነት ተምሳሌትነት ነው
√ ኢትዮጵያዊነት ማለት የእኩልነትና የሰው ልጅ ክቡርነት አርማ ነው
√ ኢትዮጵያዊነት ማለት የታማኝነትና የተአማኒነት እንዲሁም የመለኮት ማህደርነት ነው
√ ኢትዮጵያዊነት ማለት የፅናት፣ የብርታት፣ የትዕግስትና የዘላቂነት ምልክት ነው
√ ኢትዮጵያዊነት ማለት የሀቀኝነትና የእውነተኛነት ምሳሌ ነው
√ ኢትዮጵያዊነት ማለት የርህራሄና የቸርነት ናሙናነት ነው
√ ኢትዮጵያዊነት ማለት ሰው አክባሪነት፣ እንግዳ ተቀባይነት፣ ይሉኝተኝነትና፣ አዙሮ ተመልካችነት ነው
√ ኢትዮጵያዊነት የጥበበኝነት ቁንጮ፣ የብልህነት እራስ ማለት ነው
√ ኢትዮጵያዊነት ማለት የቅድስና እና የብጹዕነት ጫፍ ማለት ነው
√ ኢትዮጵያዊነት ማለት የወንድማማችነትና የእህትማማችነት የመተዛዘን ማማነት ነው።
____________________________________

ኢትዮጵያን የሚጠሉ፣ የሚያንቋሽሹ በመጪው ዘመን በግንባራቸው ተደፍተው ይቅርታ ይጠይቃሉ!!
በኢትዮጵያዊነትና በኢትዮጵያዊያን ላይ ወንጀል የሰሩ ሁሉ ይዋረዳሉ!!
ኢትዮጵያ በልጆቿ ፍቅር፣ አንድነትና መተሳሰብ ተከብራ ትኖራለች!!
ኢትዮጵያ በክብር ለዘላለም ትኖራለች!”

Share and Enjoy !

Shares
Related stories   የምዕራባውያን በኢትዮጵያ ላይ አቅል ያጣ ፍላጎት ግን ምንድን ነው!?

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *