በአርሲ ነጌሌ ከተማ ህዳር 14/ 2010 ምሽት ለረጅም ጊዜ በወዳጅነት ለዓመታት በኖሩ ሁለት ግለሰቦች መካከል ግጭት ተፈጥሮ ነበር። ግጭቱ የተፈጠረዉ መምህር ከማል ሀጂ ዱቤ እና አቶ ደረጀ ተክሌ በተባሉ ግለሰቦች መካከል ነዉ። መምህር ከማል እና አቶ ደረጀ ተክሌ ለአመታት የቆየ ጓደኝነት ያላቸዉ ስለሆነ መምህር ከማል ከአቶ ደረጀ ግሮሰሪ አይጠፉም። ከወዳጅነታችዉ የተነሳ አብሮ መብላት፥ አብሮ መጠጣት፥ መገባበዝ ልማድ አድርገዋል።ህዳር 14/ 2010 ምሽት እንደወትሮዉ ሁሉ መምህር ከማል ሀጂ ዱቤ በአቶ ደረጀ ተክሌ ግሮሰሪ ተገኝተዉ መጠጥ ይቀማምሳሉ። በጨዋታ መሃልም ከዚህ በፊት ያልከፈሉትን ሂሳብ ጨምሮ በግሮሰሪዉ የተጠቀሙበትን ያልከፈሉትን ሂሳብ እንዲከፍሉ በግሮሰሪዉ ባለቤት ይጠየቃሉ። በዚህ ሂደት የነበረዉ የቃላት ልዉዉጥ ወደ መዘላለፍ ያመራል። ነገሩ ተባብሶ ወደ ግጭት ከማምራቱ በፊት ሰዎች መሃል ገብተዉ ይገላግላሉ። መምህር ከማልም ወደ ቤታቸዉ ይሄዳሉ። አቶ ደረጀም ግሮሰሪያችዉን ይዘጋሉ።

በዚህ ምሽት መምህር ከማል ወደ ቤታቸዉ ተመልሰዉ አልተኙም። ወዲያዉ ወደ አቶ ተክሌ ግሮሰሪ በመመለስ ሃይለ ቃል እየተናገሩ የግሮሰሪዉን በር በመደብደብ ለግጭት ይጋበዛሉ። ይህን ሁኔታ የሰሙት በአርሲ ነጌሌ መሰናዶ ትምርት ቤት የታሪክ መምህር እና በተማሪዎቻቸዉ ዘንድ እጅግ ተወዳጅ እንደነበሩ የሚነገርላችዉ መምህር አቡ ዑመር (አቶ ደረጀ ተክሌ ጎሮቤት) ወጥተዉ መምህር ከማልን በመያዝ ከፀብ እንዲቆጠቡ ይጠይቃሉ።

በዚህ መሃል ግሮሰሪያችዉ ዉስጥ የነበሩት አቶ ደረጀ ተኩስ ይከፍታሉ። ከተኮሱት ጥይት አንዷ ችግሩን ለማብረድ ሲሞክሩ በነበሩት መምህር አቡ ላይ ታርፋለች። መምህር አቡ ክፉኛ ቆስለዉ ወደ ህክምና ተቋም እንደተወሰዱ ህይወታቸዉ ታልፋለች። አቶ ደረጀ ተክሌም እጃችዉን ለፖሊስ ይሰጣሉ።

በነጋታዉ ህዳር 15/2010 የመምህር አቡ ዑመርን ህልፈተ ህይወት የሰሙ የአርሲ ነጌሌ መሰናዶ ትምህርት ቤት ተማሪዎች እና የከተማዉ ወጣቶች ‘አቶ ደረጀ ተላልፈዉ ይሰጡን’ የሚል ተገቢ ያልሆነ ጥያቄ ያቀርባሉ። የተማሪዎቹ ጥያቄ ተቀባይነት እንደሌለዉ፥ በመምህር አቡ ግድያ የተጠረጠሩት አቶ ደረጀም ጉዳያቸዉ በህግ ብቻ እንደሚታይ በፖሊስ ይነገራቸዋል።

ተማሪዎቹም ጉዳዩ በህግ መዳኘት እንዳለበት የተሰጣችዉን ምላሽ ወደ ጎን በመተዉ ከከተማዉ ወጣቶች ጋር በመሆን ስሜታዊ በሆነ መንገድ ወደ ተቃዉሞ ሰልፍ ያመራሉ። በተቃዉሙ ሰልፉም በግለሰቦች መካከል የተፈጠረዉን ግጭት የብሄር መልክ ሊያስይዙ የሚችሉ አስነዋሪ ድርጊቶችን ይፈፅማሉ። መምህር ከማል እና መምህር አቡ በአርሲ ነጌሌ ከተማ በመምህርነት ሙያ ተቀጥረዉ የሚያገለግሉ የአርሲ ነጌሌ አካባቢ ተወላጆች ሲሆኑ አቶ ደረጀ ተክሌ ደግሞ በአርሲ ነጌሌ ከተማ ለረጅም ጊዜ የኖሩ በመጠጥ ግሮሰሪ ንግድ የሚተዳደሩ የጎንደር አካባቢ ተወላጅ ነጋዴ ናቸዉ።

ሰልፈኞቹ የአቶ አቶ ደረጀ ተክሌን ግሮሰሪ እና የሶስት ግለስቦችን ቤት ያቃጥላሉ። በተጨማሪም አንድ የግል ትምህርት ቤት ላይ ጉዳት ያደርሳሉ። የኦሮሚያ አድማ በታኝ ፖሊስ እና የፌዴራል ፖሊስም ጉዳዩ የባሰ ጉዳት ሳያደርስ ቁጥጥር ስር እንዲዉል ያደርጉታል።

በዚህ ሁኔታ ተፈጥሮ የነበረዉና ወደ ብሄር ግጭት ሊያመራ የነበረ ሁከት በፀጥታ አካላት እና በህዝቡ ጥረት ከበረደ በኋላ በዚያዉ ዕለት ህዳር 15/2010 ሰዓት በኋላ ከቀኑ 10፡00 ላይ እንደገና ያገረሻል። በዚህ ሁከት በተፈጠረ ግጭትም የአንድ ተጨማሪ ሰዉ ህይወት አልፏል። አንድ ሰዉ ላይ ደግሞ የመቁሰል አደጋ ደርሷል። ሁከቱም እንደገና የኦሮሚያ ፖሊስ እና የፌዴራል ፖሊስ ተቀናጅተዉ ተቆጣጥረዉታል።

የኦሮሚያ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት በአርሲ ነጌሌ ከተማ በተፈጠረ ሁከት ምክንያት ዉድ ህይወታችዉን ላጡ ዜጎች የተሰማዉን ጥልቅ ሀዘን እየገለፀ ለሟች ዘመድ ወዳጆች መፅናናትን ይመኛል። በሰዎች የየዕለት መስተጋብር ዉስጥ በግለሰቦች መካከል ግጭት የትም ሊከሰት ይችላል። በግለሰቦች መካከል የሚፈጠሩ ግጭቶችን የብሄር ግጭት መልክ ለማስያዝ እየታዩ ያሉ አዝማሚያዎች በፍፁም ተቀባይነት የላቸዉም። የኦሮሚያ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ግጭትን የግለሰቦችን ፀብ የብሄር መልክ ለማስያዝ የሚንቀሳቀሱ አካላትን አጥብቆ ያወግዛል። በሰዉ ህይወት፥ በአካል እና በንብረት ላይ ጉዳት ያደረሱ አካላት በህግ ተጠያቂ እንዲሆኑ ለማድረግ እየሰራ ይገኛል።

Related stories   ደመቀ መኮንን በፊንላንድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ከሚመራ የአውሮፓ ህብረት ልዑክ ጋር ተወያዩ

አቶ አዲሱ አረጋ  ፣ አርሲ ነጌሌ – ፌስቡክ 

Share and Enjoy !

Shares

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *