May 9, 2021

ZAGGOLE – ዛጎል

“Our true nationality is mankind.”H.G.

የግብፅ ቀሪ አማራጮች እና የኢትዮጵያ የቤት ሥራ

በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ በቅርቡ በካይሮ የተደረገው ድርድር ሳይቋጭ በይደር ከተላለፈ በኋላ የግብፅ መገናኛ ብዙኃንና የተወሰኑ የመንግሥት ተቋማት አፍራሽ መልዕክቶችን አስተላልፈዋል። በተያያዘ በቀጣይ ግብጽ ምን አማራጭ ልትከተል ትችላለች፣ የኢትዮጵያስ የቤት ሥራ ምን መሆን አለበት? በሚለው ጉዳይ ምሁራንም የተለያየ ሐሳብ ይሰነዝራሉ።


በመቐለ ዩኒቨርሲቲ የዓለም አቀፍ ህግ ረዳት ፕሮፌሰር አብይ ጨልቀባ እንደሚሉት፤ ሰሞኑን ከግብጽ የተንጸባረቀው ሀሳብ እ.አ.አ 1959 የተደረገው የቀኝ ገዢዎች ስምምነት መፅናት አለበት የሚል ይመስላል፡፡ በናይል ተፋሰስ አገራት ውስጥ ፊርማ ለማኖር የማትፈልገው የቅኝ ገዥዎች ውል እንዲፀና ስለምትሻ ነው፡፡ በዚህ መነሻነት የህዳሴው ግድብ የሚያደርሰው የተጽዕኖ መጠንም መለካት ያለበት 55 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ ውሃ እንደሚደርሳት በሚያስቀምጠው እና ኢትዮጵያ ከአጼ ኃይለሥላሴ መንግሥት ጀምሮ ባልተቀበለችው የቅኝ ገዥዎች ውል ሲሆን፤ ይህን ደግሞ ሌሎች የተፋሰሱ አገራትም አይቀበሉትም።

 

ሆኖም ኢትዮጵያ የጋራ ተጠቃሚነትን መርህ መሰረት በማድረግ ውሃ አሞላሉ ላይ እና ሌሎች የቴክኒክ ጉዳዮች ዙሪያ መነጋገር ይገባታል፤ ይህንንም እያደረገች ነው። ነገር ግን እ.አ.አ 1959 ከተደረገው ስምምነት ጋር በተያያዘ ምንም ዓይነት ድርድር ውስጥ መግባት የለባትም።
ግብፅ ጉዳዩን ከሚመለከታቸው አገራት አልፎ እንዲሄድ የሚጠቁም አካሄድ ሰሞኑን ማንጸባረቋን የሚያብራሩት ፕሮፌሰር አብይ፤ አገሪቱ ቀሪ አማራጮቿን ለመጠቀም መነሳሳቷን ይገልፃሉ፡፡ የአባይን ወንዝ የሚጋሩ አገራት በሙሉ የጋራ ስምምነት አላደረጉም፡፡ ወደ ዓለም አቀፍ ፍርድ ቤት ለመውሰድም ቢያንስ ሁለቱ አገራት እንዲሁም ሱዳን የተፈራረሙት የጋራ ሰነድ ያስፈልጋቸዋል፡፡ ይህ ከሆነ አስገዳጅነት ይኖረው ነበር የሚል አስተያየት አላቸው።

አቶ ብርሃኑ በላቸው በኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ የጂኦግራፊ ትምህርት ክፍል ኃላፊ እና የጂኦግራፊ መምህር ናቸው፡፡ እርሳቸው እንደሚሉት፤ የግብፆቹ እንዲሁም ዓለም አቀፍ ባለሙያዎች የተካተቱበት ጥናት ግድቡ ጉዳት እንደማያመጣ አረጋግጧል፡፡ አሁን ያለው ውይይትም እንደቀድሞ ሁሉ በባለሙያዎች ከፍ ካለ ደግሞ በውሃ ሀብት ሚኒስትሮች በኩል መፈፀም አለበት፡፡ ከዚህ በዘለለ ግን በመሪዎች ደረጃ የሚደረገው ውይይት ፍሬ አልባ ከሆነ ግብፆች ሁኔታውን ዓለም አቀፋዊ ቅርፅ እንዲኖረው ለማድረግ ይሞክራሉ። በመሆኑም ጥንቃቄ ማድረግ ይገባል ይላሉ።
በብሉ ናይል የውሃ ምርምር ተቋም ውስጥ ተማራማሪ የሆኑት ረዳት ፕሮፌሰር ውሂብእግዜር ፈረደ እንደሚያብራሩት፤ ግብፅ በመጀመሪያ ደረጃ የግደቡን ግንባታ ሙሉ ለሙሉ ማስቆም የሚል አቋም ነበራት፡፡ ሆኖም የዘርፉ አጥኚዎች በሰጡት ሙያዊ አስተያየት የተነሳ ከቀድሞ አቋሟ ሸርተት ብላለች። ይሁንና አሁንም ቢሆን በግድቡ ግንባታ ሂደት ላይ መስተጓጎል እንዲፈጠር ጥረት እያደረገች ነው፡፡

በአሁኑ ወቅትም ቀድሞ የአባይን ውሃ በበላይነት እንጠቀም የሚለው ሃሳብ ከግብፅ ዲፕሎማሲም ሆነ የፖለቲካ ልሂቃን አዕምሮ ውስጥ አልነጠፈም፡፡ በሌላ ጎኑ ደግሞ ውሃውን በጋራ መጠቀም እንችላለን የሚለው የኢትዮጵያ አስተሳሰብ ከዘመኑ ጋር የሚመጥን ነው፡፡
እንደ ተመራማሪው ገለጻ፤ ግብፃውያን ምን መሥራት እንዳለባቸው ማሰብ የጀመሩት የግድቡ መሰረት ድንጋይ ከተቀመጠ ጊዜ ጀምሮ ነው፡፡ በርካታ ውስጣዊ ችግሮች ቢኖርባቸውም የአባይን ጉዳይ ግን ቀዳሚ አጀንዳ አድርገውታል፡፡ የአሰዋን ግድብ ሲገነቡ ከፍተኛ የገንዘብ ቀውስ ገጥሟቸው ነበር፡፡ ከዚህ ጋር በማያያዝ አሁን ኢትዮጵያ ግድቡን በራሷ አቅም ስትገነባ ያላትን አቅም አሟጣ ስለምትጠቀም ሌላ መዘዝ ይዞባት ይመጣል የሚል እሳቤ አላቸው፡፡
ግብፆች መቼ ጣልቃ እንግባ? የሚለውን ሲጠባበቁ ነበር፡፡ በህብረተሰቡ ላይ የኢኮኖሚ ጫና ሲፈጠር አለመረጋጋት እና ቀውስ ይነሳል የሚል እሳቤ ይዘዋል። አገሪቱ ሙሉ ኃይሏን ወደ ግድቡ ስለምታደርግም ወታደራዊ አቅሟ ይዳከማል የሚል አመለካከትም አላቸው፡፡ በመሆኑን ግብፅ በምስራቅ አፍሪካ ቀንድ አካባቢ ከሚገኙ አገራት ጋር በሚኖራት ግንኙነት ኢትዮጵያ እንዳትረጋጋ ለማድረግ የምትከተለውን አካሄድ መረዳትና ጥንቃቄ ማድረግ ይገባል።

በግብፅ ሥነ ልቦና ውስጥ የኢትዮጵያ ዕድገት ሁሌም ለነሱ ውድቀትና ክስረት ነው የሚል አስተሳሰብ ነግሷል፡፡ ስለሆነም ኢትዮጵያን የተከፋፈለች አገር ማድረግ ዓላማቸው ነው፡፡ ኢትዮጵያ ከቀሪው የአባይ ተፋሰስ አገራት ጋር ያላትን ወዳጅነት ማሻከርም ሌላኛው አማራጭ አድርገው ሊወስዱት ይችላል የሚለው የረዳት ፕሮፌሰሩ አስተያየት ነው።
ረዳት ፕሮፌሰር ውሂብእግዜር እንደሚሉት፤ ግብፆች በኢትዮጵያ በኩል ባሉት ተደራዳሪዎች ላይም ከፍተኛ ትኩረት አድርገዋል፡፡ ተደራዳሪዎቹ የደረሱበት ቴክኒካዊ የመረዳት አቅም እና ሳይንሳዊ እውቀታቸው መጨመር ለግብፅ ስጋት ነው፡፡ በመሆኑም እነዚህን ተደራዳሪዎች አካሄድ የሚስተጓጎልበት አሊያም ተደራዳሪ የማሳጣት እንቅስቃሴ ሊጠቀሙ ይችላሉ፡፡ በዚህም የድርድሩን መንፈስ እና አጀንዳ የማይረዳ ሰው እንዲመጣ ይፈልጋሉ፡፡ ድርድሩን ከሳይንሳዊ ይልቅ ፖለቲካዊ ቅርፅ እንዲኖረው የማይፈነቅሉት ድንጋይ አይኖርም፡፡ በመሆኑም ለእነዚህ ተደራዳሪዎች ለየት ያለ ጥበቃ፣ ክትትልና እንክብካቤ ሊደረግላቸው ይገባል፡፡

ግብፅ ኢትዮጵያን ከዓለም አቀፍ የፖለቲካ አሠላለፍ ለመነጠል የምታደርገው ጥረት ሌላኛው አማራጭ ሊሆን ይችላል የሚለው የረዳት ፕሮፌሰር ውሂብእግዜር መላ ምት ነው። በተለይም ከመካከለኛው ምስራቅ ጋር ያላትን ዲፕሎማሲያዊ አካሄድን ለማክሸፍ ይጥራሉ፡፡ ከአፍሪካ አገራት ጋር የመነጣጠል ሙከራም ሌላኛው የሚጠቀሙበት ስልት ይሆናል፡፡
ምሁራኑ ኢትዮጵያ ልትከተለው በሚገባውና መፍትሄ በሚሉት ላይም ይመክራሉ፡፡ እንደ መምህር ብርሃኑ አስተያየት፤ ኢትዮጵያ ውስጣዊ ችግሯን ስታቃልል ግብፅ ልትጠቀምበት የምትችለው ቀዳዳ ይዘጋል፡፡ የውስጥ ጥንካሬ እንጂ የውጭው ተጽዕኖ ቀላል ነው፡፡
ረዳት ፕሮፌሰር ውሂብእግዜር በበኩላቸው፤ የአቶ ብርሃኑን አስተያየት በመጋራት ለውስጣዊ ችግሮች በፍጥነት መፍትሄ ማበጀት እንደሚገባ ይመክራሉ። ምሁራንና ዩኒቨርሲቲዎች የግብፅን የተዛባ አስተሳሰብ መስበር ይጠበቅባቸዋል፡፡ ከግብፃውያን ጋር የተጀመረውን የህዝብ ለህዝብ ፎረም ማጠናከር ብሎም እውነታውን እንዲያውቁ መሥራትና ሳይንሳዊ ምርምሮችን ማድረግም ይገባል፡፡

በእያንዳንዱ ስብሰባ የተደረሰበት ውሳኔዎችንና የህዝብን ንቃተህሊና የሚጨምሩ መረጃዎች ማስተላለፍ ያስፈልጋል፡፡ ግድቡ ሲጠናቀቅ የኃይል እጥረት ይፈታል ከሚለው በዘለለ በእያንዳንዱ ሰው ሕይወት ውስጥ ያለውን ትርጉም ማስረዳት ይገባል፡፡ የተለያዩ አካላትም አገራዊ አንድነትን በማጎልበት ረገድ በፅናት ሊሰሩ ይገባል የሚል አስተያየት አላቸው።
«አባይ ለእኛ ውሃ ብቻ ነበር፤ አሁን ግን ደምና ላብ ነው» የሚሉት ተመራማሪው፤ በቀጣይ በዋናነት በውሃ አሞላል እና በሌሎች ቴክኒካዊ ጉዳዮች ላይ ድርድሩ የአገርን ጥቅም በሚያስጠብቅ እንዲሁም የጋራ ተጠቃሚነትን መርህ በተከተለ አኳኋን መቀጠል እንዳለበት ለእዚህም ተደራዳሪዎቹና ፖለቲከኞቹ ትልቅ ድርሻ ስላላቸው ሚናቸውን መወጣት የኢትዮጵያ ቁልፍ አማራጭ መሆኑን ያሰምሩበታል።

እንደ ህግ ባለሙያው ረዳት ፕሮፌሰር አብይ ሃሳብ ደግሞ፤ ግብፅ እስካሁን ስትጠቀም የነበረው አካሄድ በሙሉ ውድቅ መሆኑን ተገንዝባለች፡፡ ሆኖም አሁንም ቢሆን ጥንቃቄ የሚፈልጉ ጉዳዮች አሉ፡፡ ምንም እንኳ ግድቡ ላይ ጫና ባያሳድርም ውስጣዊ ችግሮች በቅፅበት እልባት ሊያገኙ ይገባል፡፡ ግብፅም በሰፊው ልትጠቀምባቸው ከሚችሉ አማራጮች አንዱ ይህ ነው፡፡
ሁሉም ኢትዮጵያዊ በግድቡ ላይ ያለው ግንዛቤ በእጅጉ ማደግና ድጋፉን ማጠናከር አለበት፡፡ አንዳንድ አገራት የናይል ተፋሰስ ስምምነትን በፓርላማ ያለማፅደቃቸው ንፅፅራዊ ፖለቲካዊ ፋይዳ ለማግኘት በማሰብ ነው፡፡ይህ ጉዳይ የየአገራቱ ብሄራዊ ጥቅማቸው እንደሆነም ግንዛቤ በመፍጠር ረገድ ሊሠራ ይገባል፡፡ በጎረቤት አገራት ውስጥ ያለውን እንቅስቃሴም በተጠና መልኩ ክትትል ማድረግና ተገቢውን አካሄድና እርምጃ መውሰድ ያስፈልጋል፡፡ የባለሙያዎች እና የቴክኒክ ኮሚቴ አባላት ባቀረቡት ገዥ ሐሳብ መሰረት ድርድሩ መቀጠል አለበት፡፡

የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ መሰረተ ድንጋይ መጋቢት 24 ቀን 2003 ዓ.ም መጣሉ ይታወሳል። ከዚህ ወቅት ጀምሮ ግድቡ በታችኞቹ የተፋሰሱ አገራት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ይፈጥራል የሚለው ቅሬታ በመስተጋባቱ የኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብፅ ተወካዮችን ያካተተ 17 ውይይቶች ተካሂደዋል፡፡ አገራቱ መጋቢት14 ቀን 2007 ዓ.ም ካርቱም ሱዳን በደረሱት የመርሆች ስምምነት ላይ በምክንያታዊነት እና በፍትሃዊነት በአባይ ውሃ ጉልህ ጉዳት ሳያደርሱ እንደሚጠቀሙ ተስማምተዋል።
እንደ ባለሙያዎቹ አስተያየት፤ ከሰሞኑ ከግብፅ የሚንጸባረቁ አስተያየቶች አገራቱ በመርህ ደረጃ ከተስማሙበት የሚጣረስ ቢሆንም ኢትዮጵያ የግንባታ ሂደቱን ከማፋጠን ጎን ለጎን አሁንም ከግብፅ እና ሱዳን ጋር የምታደርገውን ትብብር አጠናክራ ትቀጥላለች።

(አዲስ ዘመን)

Share and Enjoy !

Shares
Related stories   የኮሚሽነር አበረ ህልፈት "በነጋዴዎች" እይታና ፤ የሃኪም ትክክለኛው መረጃ " ቸልተኛነት አይተናል"
0Shares
0
Read previous post:
ህወሃት አዜብ መስፍን አገደ፤ ሊቀመንበሩን ሻረ፤ ግምገማው ቀጥሏል

የትግራይ ነጻ አውጪ ግንባር ሕወሃት በግምገማ "መሞሻለቅ" ከጀመረ ሰነባብቷል። ይኽ "የከረረ" የተባለ ግምገማ ተከትሎ የሃሳብ...

Close