ዛጎል ሪፖርት- መለስ በህወሃት ውስጥ እምነት ነበሩ። ሄኖክ የሺ ጥላ እንደሚለው ” የፖለቲካው ሞንስተር፣ ባለካራማ” !! መለስን “አዋቂ” በሚለው መድብ ላይ አስቀምጠው የመሪዎች ቁንጮ ያደረጉት ክፍሎች፣ሄኖክ እንደሚለው ሳይሆን መለስ አምላካዊ ባህሪ ያላቸው ፖለቲከኛ ነበሩ። እነዚህ ክፍሎች ተረደተውት ይሁን በሞቅታ ” የመለስ ኢትዮጵያ ” በሚል የሚስሏት አገርም አለች። መለስ ሊገጣጥሟት የፈለጓትን ኢትይጵያ በአርክቴክት ደረጃ እንዳጠናቀቁ የሚናገሩት ክፍሎች እስካሁን ቅዠት ውስጥ መሆናቸውን ከማሳወቅ በስተቀር መከራከር እንደማይቻል ለእነዚሁ ” ቅዠታሞች” ምላሽ የሚሰጡ አሉ።

ጠለቅ ብሎ ሲገባ ደግሞ ሄኖክ ” መለስ የዛኛው ዓለም ሰው ነው። ጉዳዩ ጸሎት የሚያስፈልገው ነው” በሚል የሚያቀርበውን ማብራሪያ የሚጋሩ፣ መለስ ክፋታቸው ተዘርዝሮ የማያልቅ፣ በትምህርት ቤት ወጥ ከመጨልፍ ጀምሮ የዘረኝነት በሽታ ያጠቃቸው፣ በበረሃ ባልደረቦቻቸውን ቆራርጠው አናት ላይ ጉብ ያሉ። ኢትዮጵያን መምራት ከጀመሩበት ጊዜ አንስቶ አንድን ብሄር ላይተው የደበደቡና ያጠቁ፣ አገሪቱን ቁልፍ የፖለቲካ ምድር እንዳትሆን የባህር በሯን ያስረከቡ፣ በባድመ ጦርነት ወቅት በተከፈለው መዋዕትና ድል ላይ ሽፍጥ የሰሩ፣ ታሪካቸውና መዳፋቸው በደም የቀላ፣ መሰሪ፣ አድፍጠው የሚያጠቁ፣ አምባ ገነን፣ መመለክ የሚወዱ… ሲሉ ይዘረዝሩና ይህ ሁሉ የጤና እንዳልሆነ ይስማማሉ። እውነትም ” የዛኛው ዓለም ሰው” ሲሉ ከሄኖክ ድምዳሜ ዘንድ ይደርሳሉ። የዚሁ መንፈስ ጉዳይ ” መመለክን” እንዳስከተለ ያስባሉ።

ኢትዮጵያ በታሪኳ አይታ የማታውቀውን እድገት እንደታሳይ ያደረጉ፣ ባለራዕይ፣ አስተዋይ፣ አርቆ አሳቢ፣ የማይተኩ፣ ኢንሳይክሎፒድያ፣ ቅርስ፣ አባት፣ ደግ፣ ሩህሩህ፣ ከሙስና የጸዱ፣ አገሪቱን በባለ ሁለት አሃዝ የኢኮኖሚ እድገት ያስጋለቡ፣ ወዘተ በሚል ለአድናቆታቸው ወደር የሌላቸው ምርቃት ያዘንቡላቸዋል። መለስ ተፈለገም አልተፈለገም በስልጣን ዘመናቸው በዙሪያቸው ታቦት ነበሩ። ለዚህም ይመስላል ህልፈታቸውን የዓለም መጨረሻና የሞት መጀመሪያ ተደርጎ አልፏል። 

“የመለስን ሌጋሲ ሳንበርዝ እናስቀጥላለን፣ ራዕዩ ላይ ተተክለን እንመራለን፣ መለስ አልሞተም፣ መለስ አለ፣ መለስ ይኖራል…” በሚሉ መፈክሮች የታጀበው አዲሱ፣ ግን አሮጌው አስተዳደር፣ አፍታም ሳይቆይ አገሪቱን በቡድን እንደሚመሩት አበሰሩ፣ አቶ ስብሃት ነጋ የመለስ ሌጋሲ ብሎ ነገር የለም በማለት አካሄዱን ተቹ። አገሪቱ በቡድን የምትመራው ስልጣንን አንድ ሰው ጠቅልሎ እንዳይዝ ነው በሚል ማብራሪያ ተሰጠ። አሁን ግራ የገባቸው ሌጋሲውና በተግባር የሚሆነው አምታታቸው።

ወ/ሮ አዜብ በሄዱበት ባገደሙበት ሁሉ የመለስ ሌጋሲ እንዳይሸራረፍ መመሪያና ተማጽኖ ማሰማታቸው ተያያዙ። ቀደም ሲል ጀመሮ በጫት ንግድ፣ በእንጀራ ንግድ፣ በመሬት ንግድ፣ በመሳሰሉት ስማቸው ቢነሳም ” ቀዳማይ እመቤት” የሚለው ስማቸው ከወየበ በሁዋላ በርካታ ጉዳዮች ዙሪያቸውን ይዞሩዋቸው ጀመር። ከለላው እና ትዕግስቱ ለመለስ ስም ሲባል እንደሆነም ቅርብ የሆኑ ያናፍሱ ጀመር። 

በድንገት በዛሚ ሬዲዮ ብቅ ብለው የኑዛዜ ዓይነት ቃለ ምልልስ ያካሄዱት አዜብ መስፍን ከጣያቄና መልሱ በላይ ” አሁን መናዘዝ ለምን ፈለጉ” የሚለው ጉዳይ የፖለቲካ በላቾችን ቀልብ ሳበ። በግልብ በየማህበራዊ ገጹ ከሚራገበው ወፈፌ መረጃ በዘለለ መልኩ ጉዳዩን ያበጠሩ ” አዜብ አለቀላቸው” ሲሉ ተሰሙ። 

የአዜብ መስፍንን ቃለ ምልልስ እያላገጡ ያደመጡ ” አዜብ በፖለቲካ መቃተት ውስጥ መውደቃቸውን ለባለቤታቸው ወዳጆች ለማሳየት” ያደረጉት መሆኑንን አፍታም ሳይቆዩ ተናገሩ። ቃለ ምልልሱ ከጀርባው ባዘለው የመራድ ስሜት ሳቢያ መነጋገሪያ ሆነ። እጅግ ነጻና በራሳቸው የሚተማመኑ፣ እንዲሁም ኢህአዴግ የለቀቃቸው እለት ሃብታም እንደሚሆኑ ያስታወቁት አዜብ እንዳሉት ይህንን ባሉ በወራት እድሜ ውስጥ ታገዱ።

ጎልጉል ምንጮች ነገሩኝ ሲል እንዳስነበበው ” ታግደው እንዲቀመጡ” የሚለው ውሳኔ ውስጥ ከአገር የመውጣት ማዕቀብ የተካተተበት ነው። በሌላ አነጋገር የኡም እስር ነው። ይህ የሆነው ደግሞ ከላይ በተገለጸው መሰረት እሳቸውን የመለስ ካራማ ሳይቆጣ ለማስወገድ ነው።

የመለስ አምልኮም ተቀበረ ሲል የአዜብ መስፍንን እግድ ያወጀው ጎልጉል የድረ ገጽ ጋዜጣ ስብሃት ነጋ ቀን ቆጥረው አዜብን እዳሽቀነጠሯት፣ አያይዞም አሁን ወደ ህወሃት ወንበር የሚገሰግሱት እንስት የወንድማቸው ልጅ በመሆናቸው የስብሃት ሌጋሲ መጣ ማለት እንደሆነ ገልጿል።

አዜብን ቀስ ብሎ የማስለል ስራ የሚሰራው ለሟቹ ” ታላቁ መሪ” ሲባል እንደሆነ እየተነገረ ባለበት በአሁኑ ሰዓት ሪፖርተር ምንጮቹን ሳይጠቅስ የወ/ሮ አዜብ መስፍን እግድ ገና የጠቅላላ ጉባኤውን ውሳኔ እንደሚጠብቅ ገልጿል። ምንጮች ባይናገሩም ጉዳዩ የህግ በመሆኑ በድርጅቱ አሰራር መሰረት ወሳኔዎች ሁሉ በድርጀቱ ጉባኤ የሚጸድቁ መሆናቸውን ለአሰራሩ የሚያውቁ አመልክተዋል።

ስለግምገማው ጭላንጭል መረጃ ያላቸው እንደሚሉት በጠቅላላ ጉባኤ ወቅት አዜብ ደፍረው ሌላ ሙገት ውስጥ እንደማይገቡና ሌጋሲ እያሉ የሚንጠላጠሉበት መሰላል መሰበሩን የተረዱበት ደረጃ ላይ መድረሳቸው ታውቋል። ምን አለባትም ለልጆቻቸው ሲባል ሃዘኔታ ካልተደረገላቸው ጎልጉለ እንዳለው መጨረሻቸው ሌላ ሊሆን እንደሚችል ግምቱ ሰፊ ነው። 

ስብሃት ነጋ በመሪነት የሚጫወቱት ሚና አይሎ ከመውጣቱ ጋር አዜብ የማንሰራርት እድላቸው የማይታሰብ እንደሆነ የሚጠቁሙ፣ ምን አልባትም ክፉውን ነገር ከያዘላቸው የባለቤታቸውን ላይብረሪና ሙዚየም የማስተዳደሩ ስራ ላይ እንዲያተኩሩ ሊደረጉ እንደሚችሉ ነው። ለሁሉም አዜብን አስመልክቶ የህወሃት ምጥ እዚህ ላይ የተገላገለ ይመስላል። የራሱ የተፈጠረበት ችግር ሲቀር!! እንዲሁም የመለስ ካራማ እስካልተቆጣ ደረስ፤ በሄኖክ የሺ ጥላ ” የዛኛው ዓለም መንፈስ” በወዳጆቻቸው አባባል ” የመለስ አምልኮ ይግዛን” እንደሚሉት አምልኳቸውን እስካላነካ ደረስ!!

 

Related stories   The National Movement of Amhara(NaMA) Denounces International Violations of the Sovereignty of Ethiopia

 

 

Share and Enjoy !

Shares

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *