በግምገማ ተወጥሮ የከረመው የትግራይ ሕዝብ ነጻ አውጪ ግንባር / ህወሃት/  ዶክተር ደብረጽዮን ገብረ ሚካኤልን ሊቀመንበር አደረገ። በስፋት በማህበራዊ ሚዲያዎችና በውጪ አገር ባሉ መገናናዎች ለመሪነት መታጨታቸው ሲነገርላቸው የነበሩት ወ/ሮ ፈትለወርቅ ገብረእግዚአበሔር ምክትል ሆነዋል። 

ስርነቀል ግምገማ፣ የሰላ ሂስና ገለሂስ ሲያካሂድ መሰንበቱን ያስታወቀው ህወሃት ዘጠኝ ስራ አስፈጻሚዎችን ከሰየመ በሁዋላ ድልድሉን ይፋ ሲያደርግ ሂደቱን ” በድል ተጠናቀቀ” በማለት ነው። “ስር ነቀል” የተባለው ለውጥ “አዲስ” ከተባለው ሹመት አንጻር ” ስር ነቀል ” ስለመሆኑ አድሮ አስተያየት የሚሰጥበት ሲሆን፣ ድርጅቱ በቀጣይ አጠቃላይ ጉባኤውን እንደሚያካሂድ ታውቋል። 

ከተለያዩ የሃይል እርምጃዎች በተጨማሪ ” በጥልቅ መታደስ” በሚል መፈክር በአብዛኛው የአገሪቱ ክፍል የተቀጣጠለውን ህዝባዊ ተቃውሞ ለማስታገስ እላይ ታቸ ሲል የቆየው ኢህአዴግ፣ በአባል ድርጅቶቹ መካከል እያካሄደ ያለው ጥገናዊ ለውጥ ምን ያህል ለህዝብ መላሽ ይሆን? የሚለው ጥያቄ አሁንም እንደቀጠለ ነው።

“በአገሪቱ ያለው ችግር ፖለቲካዊ እና ዴሞክራሲያዊ ለውጦችን የሚሹ ሆነው ሳለ ህወሃት አዲስ ስራ አስፈጻሚ መደበ አልመደበ ለማንም ቁቡ አይደለም” በሚል በድርጀቱ የተደረገው ለውጥ ከህዝብ ጥያቄ አንጻር ምንም ሊባል እንደማይችል አስተያየት እየተሰጠ ነው። በእርግጥ ለድርጅቱ ህልውና የሚመለከታቸው አካላት አስፈላጊ ነው ያሉትን የመፍትሄ እርምጃ መውሰዳቸው ለትችት የሚያበቃ ባይሆንም፣ በአገር ደረጃ ለውጥ ያመጣል የሚል ግምት እንደሌላቸው በውጪ አገር የሚገኙ ፖለቲከኞች እየገለጹ ነው።

አሁን ህወሃትን የሚመሩት ደብረጽዮንም ሆኑ የሌሎች አቻ ድርጅት አመራሮች በአገሪቱ የተፈጠረው የዴሞክራሲ ጥያቄዎች፣ የስብአዊ መብቶች አለመከበር ጉዳይ እስር፣ ግድያና አፈና ወዘተ ሲፈጸም፣ አሁንም እየተፈጸመ ባለበት ሁኔታ ዋና ተዋነያን በመሆናቸው ጥገናዊ ለውጡ በአገር ደረጃ ምንም ለውጥ ሊያመጣ እንደማይችል ተቃዋሚዎች በርግጠኛነት ተናገረዋል።

አገሪቱ አሁን ባለችበት ሁኔታ አንዱን አባሮ ሌላውን ጉልበተኛ መሰየም ችግሩን ይበልጥ የሚያባብሰው እንደሆነ በፍርሃቻ የሚናገሩ ክፍሎች ” በኢትዮጵያ ስር ነቀል የፖለቲካ ለውጥ ግድ መሆኑንን አለመረዳት አድሮ ዋጋ ያስከፍላል” ባይ ናቸው። በቅርቡ ከሰንደቅ ጋዜጣ ጋር ቃለ ምልልስ ያደረጉት የህወሓት ታጋይና በኋላም የአየር ኃይል አዛዥ የነበሩት ሜጀር ጄኔራል አበበ ተ/ሃይማኖት ” ኢህአዴግ ወደደም ጠላም ሕዝብ አልገዛም ማለቱን መረዳት አለበት” ማለታቸው ይታወሳል።

በመቀሌ ዩኒቨርስቲ የፖለቲካ ሳይንስ መምህር ረዳት ፕሮፌሰር አቶ የማነ ዘርዓይ ቆራጥነት ካለ መንግስትና ፓርቲ እንዲለያዩ ከመግባባት ላይ መደረስ አለበት። ሕወሐት ዘመኑ የሚጠይቀዉን አመራር መስጠትና መፍጠር አልቻለም ሲሉ ጉባኤው ከመጠናቀቁ በፊት አስተያየታቸውን መስጠታቸውም አይዘነጋም። አብዛኞች ከጉባኤው ምንም እንደማይጠብቁና ትግሉ የእርስ በእርስ ፍትጊያ በመሆን አንዱ ሌላውን አሸንፎ የሚወጣበት ነውና ድብረጽዮን አሁን ጠቀለሉ ሲሉ ተደምጠዋል።

ፋና እንዳለው የህወሓት ማእከላዊ ኮሚቴ ከአንድ ወር በላይ ሲያካሂድ የነበረውን ስር ነቀል ግምገማ፣ ሂስና ግለ ሂስ ህዳር 20 ቀን 2010 በድል ተጠናቋል።  ከግምገማው በኋላ በሂስና ግለ ሂስ የማጥራት እርምጃ በመውሰድ፥ ዘጠኝ አባላት ያሉት የድርጅቱን ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት ምርጫን በዴሞክራሲያዊ አግባብ አካሂዷል።

በዚህም መሰረት፦

ዶክተር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል

ወይዘሮ ፈትለወርቅ ገብረእግዚአብሄር

አቶ ጌታቸው አሰፋ

አቶ አለም ገብረዋህድ 

ዶክተር አዲስአለም ባሌማ 

አቶ አስመላሽ ወልደስላሴ

አቶ ጌታቸው ረዳ

ወይዘሮ ኬሪያ ኢብራሂም እና

ዶክተር አብርሃም ተከስተ

የህወሓት ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት ተደርገው ተመርጠዋል።

 

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *